ትምህርት ቤቶችን ዳግም መክፈት በሚቻልበት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት ውይይት እየተካሄደ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እየተካሄደ ባለው ውይይት የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ሚኒስትሮችም ተገኝተዋል።
ውይይቱ ትምህርት ቤቶችን ዳግም ለመክፈት ለውሳኔ የቀረበ ምክረ ሃሳብ፣ የ8ኛ እና 12ኛ ከፍል ብሄራዊ ፈተናና የግል ትምህርት ቤቶችን የትምህርት አሰጣጥ ሂደት የተመለከተ ነው።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ትምህርት ቤቶችን ዳግም ለመክፈት ስለቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ገለፃ አድርገዋል።
ባለፉት ሁለት ቀናት ከሁሉም ክልሎች የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ውይይት መካሄዱንና የውሳኔ ሃሳብም መቅረቡን አንስተዋል።
በዚሁ መሰረት የትምህርት ቤት አከፋፈት ሂደቱ በሶስት ዙር እንደሚከናወን አስታውቀዋል
በመጀመሪያው ዙር ማለትም ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ የውሳኔ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።
በ2ኛ ዙር ጥቅምት 16 ቀን 2013 ደግሞ በሁሉም የዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ ነው ምክረ ሃሳብ የቀረበው።
በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት እንዲጀምሩ የውሳኔ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።
የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን አስመልክቶም ሁሉም ተፈታኞች ለፈተና እንዲቀመጡ የሚል የውሳኔ ምክረ ሃሳብ መቅረቡ ተገልጿል።
የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሕዳር 22 እና 23 ቀን 2013 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን ፈተና ላይ መቀመጥ የሚችሉት 7ኛ ክፍልን ተምረው ያጠናቀቁና የ8ኛ ክፍልን የአንደኛ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው።
በተመሳሳይ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መውሰድ የሚችሉት የ11ኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀቁና የ12ኛ ክፍልን የመጀመሪያ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው ተብሏል።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሕዳር 28 እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚሰጥም በምክረ ሀሳቡ ላይ ተጠቅሷል።
የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን በተመለከተ ለመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚወጣው መመዘኛ በግል ትምህርት ቤቶችም ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።
የግል ትምህርት ቤቶች የምዝገባ ክፍያ በ2012 ዓ.ም በነበረው መጠንና የክፍያ ስርዓት መሆን እንዳለበትም ተገልጿል።
የትምህርት ቤቶች የክፍያ ስርዓት በባንክ በኩል ብቻ መፈጸም እንዳለበትም ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።
በቀረበው ምክረ ሃሳብ ላይ የሚደረገው ውይይት አሁንም እንደቀጠለ ነው።