Monday, May 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በቋንቋ አጠቃቀም ላይ እንድንጠነቀቅ ለማሳሰብ

በዛወርቅ ሺመላሽ

እኔ የሕግ ተማሪ ነኝ፡፡ የቋንቋ ተማሪ አይደለሁም፡፡ ከሰው ጋር ለመግባባትና አሳብንም ለሌላው በአግባቡ ለማስተላለፍ ቋንቋ ወሳኝ ነው ብዬ ስለማምን በጥንቃቄ መያዝ ወይም መስተናገድ ይገባዋል የሚል አቋም አለኝ፡፡ አንዳንድ ሰዎች በተለይ ጋዜጠኞች (ገጣሚ ነን የሚሉትም ጭምር) ለሚጠቀሙባቸው ቃላት ምንም ደንታ ሳይሰጡ እንዳፈተታቸው ስለሚጽፉና  ስለሚናገሩ ሃይ የሚላቸው የለም ወይ? እላለሁ፡፡ የቋንቋ ሊቃውንት እነ ፕሮፌሰር ባዬ ይማም ነቅተው ትክክለኛውን መንገድ እስከሚያሳዩን ድረስ ዝም ማለት አይገባኝምና ያለኝን ልወርውር፡፡

የእንግሊዝኛ ቃላትን አማርኛ አስመስለው ወይም አደባልቀው ስለሚጠቀሙ ሰዎች በሌላ ጊዜ አነሳለሁ፡፡ አሁን ለጊዜው ለመነሻ፣ ለመተዋወቂያ ያህል በስህተት የሚነገሩ አንዳንድ የአማርኛ ቃላትን ላንሳ፡፡

  1. ሚኒስቴር፣ ሚኒስትር

ሉ የውጭ አገር ቢሆንም ዛሬ እንደ አማርኛ ነው የምንጠቀምበት፡፡ ሆኖም ሰዎች (አንዳንድ ጋዜጠኞች) ልዩነቱን ካለማወቅ መሥሪያ ቤቱን ሚኒስትር፣ የሚመራውን ሰው ደግሞ ሚኒስቴር በማለት ሲጠቀሙ ይሰማል፡፡ ይኼ ስህተት ነው፡፡ መሥሪያ ቤቱ ሚኒስቴር ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ ሚኒስቴሩን በበላይነት የሚመራው ሰው ደግሞ ሚኒስትር ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ “ሜሪት” መዝገበ ቃላትን በማየት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ትርፍ ነገርንም ማስወገድ ይገባል፡፡ ለምሳሌ ክቡር አቶ ከተማ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሎ መጥራት በቂ ነው፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ብሎ መጥራት ግን አስፈላጊ አይደለም፣ ትርፉ ድካም ነው፡፡

  1. ተግዳሮት፣ ተገደረ

እንደ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ትርጓሜ ከሆነ ተግዳሮት ትቢት፣ ኩራት፣ ጡር፣ ሽሙጥ ማለት ነው፡፡ ዘርጋውም እንደዚሁ ነው የሚተረጉመው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ተግዳሮት “Challenge” ለተሰኘው የእንግሊዝኛ ቃል ትክክለኛ ትርጓሜ እየመሰላቸው “አዎ በሥራችን ብዙ ተግዳሮቶች አሉብን” በማለት ሲጠቀሙ ይሰማል፡፡

 ተገደረ የሚለውን ቃል ዘርጋው በኩራት ተወጠረ፣ ታበየ በማለት ተርጉሞታል፡፡ አጣ፣ ተቸገረ በሚል ሁለተኛ ትርጉምም ሰጥቶት ይገኛል፡፡ እንግዲህ አንድ ሰው (ጋዜጠኛ ሊሆን ይችላል ወይም ብዙ ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርብ ሹም ሊሆን ይችላል) አጣ፣ ተቸገረ የሚለውን ትርጓሜ ሰምቶ ገንዘብ በማጣት መቸገርና ከባድ ሥራ በማጋጠሙ መቸገር በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት ሳያገናዝብ ተገደረ ተቸገረ ተግዳሮት ችግር ብሎ የሄደበት ይመስላል፡፡ ስለዚህ ሰው ተግዳሮት የሚለውን ቃል አለቦታው እየተጠቀመበት ስለሆነ ቢታረም መልካም ነው እላለሁ፡፡

  1. አንድምታ፣ አንደምታ

የሜሪት መዝገበ ቃላት “Imply” ለተሰኘው የእንግሊዝኛ ቃል አመለከተ፣ በተዘዋዋሪ ጠቀሰ የሚል ፍቺ ሲሰጥ “Implication” ለሚባለው ቃል ደግሞ “አንደምታ” የሚል ፍቺ ሰጥቶት ይገኛል፡፡ ሆኖም “አንደምታ” በየትኛውም የአማርኛ መዝገበ ቃለት ውስጥ አይገኝም፡፡

ትክክለኛው ቃል “አንድምታ” ነው፡፡ አመጣጡ አንድም ከሚለው ቃል ሲሆን አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ “የልዩ ልዩ ትርጓሜ ምስጢር መነሻ” በሚል ተርጉመውታል፡፡ ልክ እንደ ትዝታ፣ ውልታ፣ ይቅርታ ወዘተ ለቃሉ ስም (“ናውን”) ፍለጋ አንድምታ ሊባል እንደቻለ መገንዘብ አያዳግትም፡፡

የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ባዘጋጀው “ኣማርኛ መዝገበ ቃላት፡  አንድ መጽሐፍ ሲተረጎም አባባሉን በተለያየ መንገድ አጉልቶና ዘርዝሮ ምስጢሩን የመተርጎሚያ ስልት በማለት ለአንድምታ ፍቺ ሰጥቶት እናገኛለን፡፡

ስለዚህ አንድምታ ለሚለው ቃል እላይ ከተሰጠው ፍቺ አንጻር “Imply” ወይም (Implication) ለሚለው ቃል ማገልገሉን መጠራጠሬ እንደተጠበቀ ሆኖ ከአንድምታ ጋር  በአጉል መንገድ ተመሳሳይነት ያላቸው ቃላት ማለትም፡-

  • አንደምታ
  • እንድምታ
  • እንደምታ

ትክክለኛ ስላልሆኑ አውቀን እንታረም እላለሁ፡፡

  1. አበባዬ ሆይ፣ አበባየሆሽ

በአዲስ ዓመት ለእንቁጣጣሽ ወጣት ሴቶች በቡድን ሆነው ከበሮ እየመቱ “አበባዬ ሆይ ለምለም፣ አበባዬ ሆይ ለምለም አበባዬ ርግፍ በሸማዬ” እያሉ ነበር የሚዘፍኑት፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ካለማወቅ ይህ ተቀይሮ “አበባየሆሽ” በሚል ተለውጦ ይገኛል፡፡ ማን እንደቀየረው፣ እንዴትስ እንደተቀየረ አይታወቅም፡፡ ቅዳሜ ዕለት በመስከረም 2 ቀን 2013 ዓ.ም. በሸገር ሬዲዮ ጋዜጠኛው ይኼንኑ አንስቶ “አባባየሆሽ” እያለ ሲያወራ ነበር፡፡ ትክክለኛው መጠሪያ “አበባዬ ሆይ፣ አበባዬ ሆይ” ነው፡፡ ይህን ማረጋገጥ ከተፈለገ የአለቃ ደስታ ተክለ ወልድን ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላትን አገላብጦ ማየት ይችላል፡፡

  1. አስረሽ ምቺው፣ አስረሽ ምቺው

መስፍን በቀለ በሚዘፍነው አንድ ቪዲዮ ውስጥ አንዲት ወጣት መቀነቷን በወገቧ ላይ አጠንጥና እያጠበቀች እየፈታች ትታያለች፡፡ መስፍን “አስረሽ ምቺው” እያለ ሲዘፍን መቀነቷን እያጠበቀች እስክስታዋን ታሳያለች፡፡ ለመስፍን ግጥሙን የሰጠው ሰው “አስረሽ  ምቺው” የሚለው ሐረግ ትርጉሙ መቀነትሽን አጥብቂና እስክስታሽን አሳዪ ማለት መስሎታል፡፡ ግን አይደለም፡፡

“አስረሽ” ጠብቆ ነው የሚነበበው፡፡ አምሳሉ አክሊሉና ዳኛቸው ወርቁ “የአማርኛ ፈሊጦች” በተሰኘው መጽሐፋቸው አስረሽ ምቺው ፈንጠዚያ ማለት እንደሆነ ጽፈዋል፡፡ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ደግሞ፣ አስረሽ ማለት ከፍ አድርገሽ ማለት እንደሆነ ይጠቅስና አስረሽ ምቺው ሰብአ ትካት የኖኅ ዘመን አመንዝሮች ሁሉ አታሞ በደረታቸው እየያዙ የዘፈኑበት ጊዜ የጥፋት ውኃ እየበዛ ስለሄደ ከበሮውን ከምድር ወደ ጉልበት፣ ከጉልበት ወደ ደረት ከደረት ወደ ራስ ከፍ አድርገሽ ምቺው ማለት ነው በማለት አብራርቶ ጽፏል፡፡

በአጭሩ፣ አስረሽ ምቺው መቀነት ማሰርና እስክስታ መደለቅ አይደለም ለማለት ነው፡፡

  1. አጎራ፣ አጎና

አዲስ አበባ ውስጥ ጎተራ አካባቢ ሲኒማ ቤት አለ፡፡ እነ ሠራዊት አጎና ብለው ስም ስላወጡለት የሰፈሩ ሰው፣ ባለታክሲው የታክሲ ረዳቱ ሁሉ አጎና አጎና እያለ ነው የሚጠራው፡፡ ቃሉ አማርኛ እስከሚመስል ድረስ ማለት ነው፡፡ ስም አውጭዎቹ አጎና ምን ማለት እንደሆነ ቢጠየቁ በቂ ምላሽ የሚኖራቸው አይመስለኝም፡፡ እንደሚታወቀው ሲኒማ ቤት እንደመሆኑ ብዙ ሰው የሚገባበትና የሚወጣበት ነው፡፡ አደባባይ ነው፣ መሰብሰቢያ ነው፡፡ ለእንደዚህ ዓይነቱ ሥፍራ ትክክለኛው መጠሪያ አጎራ ነው እንጂ አጎና አይደለም፡፡ በጥንታዊት ግሪክ የሕዝብ መሰብሰቢያ ሥፍራዎች አጎራ ይባሉ እንደነበር ፕሉታርክ “ሴሌክትድ ላይቭስ ኤንድ ኤሴይስ” በተሰኘው መጽሐፉ አስፍሮት ይገኛል፡፡ ኮሊንስ መዝገበ ቃላትም ይኼንኑ ነው የሚያረጋግጠው፡፡

ስለዚህ ለሲኒማ ቤቱ ስም የሰጡ ሰዎች ይኼንኑ ተገንዝበው ስሙን ወደ አጎራ (ቃሉ አማርኛም ሳይሆን) እንዲለውጡ እመክራለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles