Thursday, June 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹ፓሎማ›› የሰላሟ ርግብ

በምትኩ በቀለ

ዓይኔን በዓይኔ ካየሁ አንድ ዓመት ሞላኝ፡፡ እጅግ ንቁ፣ ደስተኛ፣ ጤነኛና ውብ ሴት ልጅ ወልጃለሁ፡፡ ታድያ ይህችን መሳይ ልጅ እንዲሁ በቀላሉ ያገኘሁ አይምሰላችሁ፡፡ ከፈጣሪ በጎ ቸርነነት ጋር የእኔና የባለቤቴ ማስተዋል፣ ተግባብቶና ፍቅር ታክሎበት ነው፡፡

ከባለቤቴ ጋር በተጋባን ከዓመት በኋላ ነበር ልጅ ለመውለድ ውሳኔ ላይ የደረስነው፡፡ በውሳኔያችን መሠረት ከወራት በኋላ መፀነሷን የሚያሳዩ ምልክቶችን በማስተዋላችን እጅ ለእጅ ተያይዘን አቅራቢያችን ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ አደረግን፡፡ በዚህም መሠረት በማህፀንዋ ፅንስ መኖሩን የምርመራ ውጤቱ አበሰረን እጅግም ተደሰትን፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ እኔ በግሌ ለልጅ ብዙ ጉጉ አልነበርኩም ‹‹በዚህች አሜኬላ በወረሳት ምድር ዘር አይዘራም›› የሚል አጉል ፍልስፍና ነበረኝ፡፡ ሆኖም ትዳር ባልና ሚስት (ሴትና ወንድ) በጋራ የሚመሠርቱት ትልቅ ተቋም በመሆኑና የግል አመለካከትና ፍልስፍና የሚራመድበት ቤተ ሙከራ ባለመሆኑ፣ እንዲሁም የባለቤቴ ለልጆች ያላት ብርቱ ፍቅርና ፍላጎት የግል እምነትና ፍልስፍናዬን አሽሮብኝ ዛሬ የቆንጅዬ ሴት ልጅ አባት ሆኛለሁ፡፡

ከእኔ ቀድመው በልጅ ለተባረኩ አንዳንድ የልብ ወዳጆቼ ምሥጋና ይግባቸውና  የባለቤቴን መፅነስ በነገርኳቸው ጊዜ በእጅጉ ተደሰቱ፣ ከደስታም ባሻገር እነሱ ያለፉበትን መንገድ በማስታወስና ተሞክሯቸውን በማጋራት ከአንድ የሕክምና ባለሙያ ባልተናነሰ ምክር ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለብኝ በፅኑ አስገነዘቡኝ፡፡ በእርግዝና ወቅት በአንዲት እርጉዝ ላይ የሚፈጠርባት ማንኛውም ዓይነት ጫና በተዘዋዋሪ በሚወለደው ልጅ ባህሪ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥርበት፣ ይህም ማለት እናት በእርግዝናዋ ወቅት ደስተኛ ካልሆነች የሚወለደውም ልጅ ነጭናጫ፣ አልቃሻና ሐዘንተኛ እንደሚሆን ሁሉ በተለያየ ጊዜ ካገኘኋቸውና የሕክምናም ሆነ የሥነ ልቦና ትምህርት ከሌላቸው የተለያዩ ወዳጆቼ ከተሰጡኝ ምክሮች አንዱና ዋነኛው ነበር፡፡

እኔም በተሰጠኝ ምክር መሠረት የራሴ የምላቸው ጉዳዮቼን ወደ ጎን በመተው አቅሜ በፈቀደው መጠን ከባለቤቴ አጠገብ ባለመራቅ ባለቤቴንና በሆዷ የሚገኘውን ፅንስ መንከባከብን ዓብይ ጉዳዬ አደረግሁት፡፡ በዚህም መሠረት ባለቤቴ ወደ ሥራ በምትሄድባቸው እያንዳንዷ ዕለት በጠዋት ተነስቼ ቁርስ በማዘጋጀት፣ ቡና በማፍላትና በንቃትና በቅልጥፍና የሥራ ገበታዋ ላይ እንድትገኝ አበረታትቼ በመሸኘት፣ እቤት በምውልባቸው ጊዜያት በቤት ውስጥ የሚሠሩ ማናቸውንም ሥራዎች ጎንበስ ቀና ብዬ በመሥራት (ዕቃ በማጠብ፣ ቤት በመወልወል፣ አልጋ በማንጠፍ፣ ምግብ በማብሰል ወዘተ)፣ ከሥራ መልስ መንገድ ላይ ጠብቄ አብሬያት በመጓዝና አብሮነቴን በተግባር በማሳየት፣ ኪሴ በፈቀደው መጠን አንዲት እርጉዝ ሴት እንድትመገባቸው የሚመከሩትን የፍራፍሬና የአትክልት ዓይነቶች በማቅረብ፣ እንደ ልብስ ማጠብ ያሉና በጋራ የሚሠሩ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በማገዝ ብሎም ከወዳጆቼ በተለገሰኝ ምክር መሠረት ነብሰ ጡር ሴትን ሊያስከፏት ይችላሉ የሚባሉ ቅንጣት ታክል ስህተቶችን ላለመሥራት በመጣር እንደ ባል፣ እንደ ወንድም በተለይም እንደ ጠባቂ መልዓክ ከአጠገቧ ባለመራቅ ለልጄ ጎበዝ አባት ለሚስቴ ጠንካራ ባልነቴን በተግባር አሳየሁ፡፡

በዚህም መሠረት እኔና ባለቤቴ እንደኔና እንደሷ ብሎም እንደ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ሳንፈለግ በድንገት ይህችን ዓለም እንደተቀላቀልነው ሳይሆን፣ ከፈጣሪ በረከት ጋር ይሁነን ብለን አስበንበት አምሳያችንን ለመተካት በመሻት ባደረግነው ጥረትና ምርመራ የልባችንን መሻት ጤና ተቋም ሄደን ካረጋገጥን በኋላ ጎተራ አካባቢ የሚገኘውና በተመጣጣኝ የገንዘብ ክፍያ አገልግሎት እንደሚሰጥ የሚነገርለት፣ የሕክምና ባለሙያዎቹ እናቶች በቀዶ ሕክምና ከመውለድ ይልቅ ተፈጥሯዊ በሆነው የአወላለድ ሥርዓት (ምጥ) እንዲወልዱ የሚያበረታቱ ከመሆናቸውም ባሻገር፣ ሥራቸውን በአግባቡና በጥንቃቄ የሚያከናውኑ ብቁ ባለሙያዎች እንደሆኑ፣ በከተማዋ በእጅጉ በሚነገርለት እንዲሁም ከዚህ ቀደም ጓደኞቿ በዚህ ማዕከል በሰላም መገላገላቸውን ከግንዛቤ በማስገባት ባለቤቴ ለቅድመ ምርመራ፣ ለውልጃና ለድኅረ ውልጃ አገልግሎት ይኼንኑ ማዕከል ምርጫዋ አደረገች፡፡

በመሆኑም በማዕከሉ እስከ ስምንት ወራት የሚደረጉትን ወርኃዊ ምርመራዎች በመቀጠልም ከስምንት ወራት በኋላ የሚደረጉትን የዘጠነኛ ወር ሳምንታዊ ምርመራዎች በተቀጠርንባቸው ቀናትና ሰዓታት አንድም ቀን ሳናስተጓጎል በአንድ ላይ በመሄድ የተከታተልነው፡፡

እስከ ስምንተኛው ወር ከሰባተኛው ቀን ድረስ የፅንሱም ሆነ የባለቤቴ የጤንነት ሁኔታ ጥሩ እንደሆነ ተነግሮን የነበረ ሲሆን፣ በቀጣዩ የስምንት ወር ከአሥራ አምስት ቀን ሳምንታዊ ቀጠሯችን ግን የገጠመን ነገር በሕክምና ማዕከሉ ላይ የነበረን እምነት እንዲሸረሸር ብሎም የማዕከሉን ሠራተኞች ትዝብት ውስጥ የሚከት ነበር፡፡

ቀኑ አርብ ነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ነው፡፡ በዛሬው ቀጠሯችን ፅንሱ ስምንት ወር ከአሥራ አምስት ቀኑ ነው፡፡ እንደተለመደው ከባለቤቴ ጋር ከምንኖርበት ቃሊቲ አካባቢ ተነስተን ደጃችን ላይ ከሚተላለፉት መኪናዎች ለአንዱ ትብብር እንዲያደርግልን በእጃችን ምልክት ሰጠነው፡፡ ወዲያው መኪናውን አቁሞልን ደጉ ሰው ጎተራ አካባቢ እንደሚሄድና ግጥምጥሞሹ እየደነቀው ዕድለኛ መሆናችንን ገልጾልን እዛው የሕክምና ማዕከሉ ድረስ አደረሰን፡፡ ደጋግ ሰዎች ይጨመርላችሁ፡፡

እንደተለመደው ካርድ አውጥተን የተለመዱትን የሽንትና ‹‹የአልትራሳውንድ›› ምርመራዎችን በማድረግ ነው በስተመጨረሻ ፅንሱ የሚገኝበትን ሁኔታ ወደሚገልጸው ዶክተር ክፍል በአንድነት የገባነው፡፡

ወጣቱ ዶክተር ከላይ እስከ ታች አንዴ እኔን አንዴ እሷን እየተመለከተ ከተለያዩ ክፍሎች በውስጥ ለውስጥ የኮምፒዩተር ግንኙነቶች የደረሱትን ውጤቶች በመመልከት ለጊዜው ዱብ ዕዳ የሆነብኝን ነገር የነገረን፡፡

ይኼውም ምንም እንኳን ፅንሱ ለመወለድ የደረሰ በእነሱ አገላለጽ (Machured) ቢሆንም ነገር ግን የባለቤቴ የእንሽርት ውኃ መጠን በመቀነሱና ይኼም ፅንሱ እንደልቡ እንዳይንቀሳቀስ ብሎም በአግባቡ እንዳይተነፍስና እንዲታፈን በማድረግ የከፋ ችግር ከመግጠሙ በፊት የማዋለጃ አልጋዎች በመኖራቸው ዝግጁዎች ከሆንን ዛሬውኑ አሊያም ነገ (ቅዳሜ) ተመልሰን በመምጣት በአስቸኳይ መወለድ እንደሚኖርበት ገለጸልን፡፡

ደነገጥን፣ ምን ማድረግ እንዳለብን ባለማወቃችን ሁለታችንም ግራ ተጋባን፡፡ ከቤታችን የወጣነው መደበኛ ሳምንታዊ የሕክምና ክትትል ለማድረግ ነው፡፡ የተነገረን ውጤት እውነት ስለመሆኑ እርግጠኞች ባንሆንም በእኛ ቤት ገና የሚቀሩ ሁለት ሳምንታቶች በመኖራቸው ከምርመራው በኋላ የማስታወሻ ፎቶ ለመነሳት እንጂ እንደዚህ ያለ ሁኔታ ይገጥመናል ብለን አልነበረም፡፡

ይሁንና እውነት ከሆነ የዶክተሩ አባባል ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ በተለይ ‹‹መታፈን›› የሚለው ቃል በጭንቅላታችን እያቃጨለ መዋል ማደር ብዙ የደከምንበትንና የጓጓንለትን ፍሬያችንን ማንቀዝ፣ ሲከፋም የባለቤቴን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል መስሎ ስለተሰማኝ የመጀመርያውን አማራጭ በመቀበል ዶክተሩ አቀባብሎ ወደላከን የማዋለጃ ክፍል በመሄድ ስለሁኔታው ተነጋገርን፡፡

በዚህም መሠረት የዕለቱ ወጣት ሴት ተረኛ ባለሙያዎች ባለቤቴ በማህፀን ማለስለሻ መድኃኒት በቀላሉ የምትወልድ ከሆነ እስከ ስድስት ሺሕ ብር፣ በምጥ መርፌ የምትወልድ ከሆነ እስከ ስምንት ሺሕ ብር ካልሆነም ከእነዚህ ሁሉ ሙከራዎች በኋላ ባለቤቴ በቀዶ ሕክምና የምትወልድ ከሆነ እስከ አሥራ ሁለት ሺሕ ብር መክፈል እንደሚጠበቅብን በማሳሰባቸውና የምንስማማ ከሆነ ምሽት አሥራ ሁለት ሰዓት ላይ ባለቤቴ እራቷን ጠግባ በመብላት እንድትመጣ አዘዙን፡፡

እኛም የገጠመንን ሁኔታ ለቤተሰቦቻችንና ለወዳጆቻችን ደውለን በማሳወቅ የቀጠሯችን ሰዓት እስኪደርስ ድረስ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ጸሎት ካደርስን በኋላ ይዘናቸው እንድንመጣ በተነገረን መሠረት የሕፃን መታቀፊያ ካናቴራና ጡጦ በመግዛት መጀመርያ ከቤታችን ስንነሳ አስበነው የነበረውን የማስታወሻ ፎቶዎች ለመነሳት አንዱ ፎቶ ቤት ገብተን ድንገተኛ የሆነብንን የዕለቱን የእርግዝናዋ የመጨረሻ ቀን ማስታወሻ ፎቶግራፎች ተነሳን፡፡

ባሳወቅናቸው መሠረት አፍታም ሳይቆዩ ከጎናችሁ ነን በማለት ከተፍ ያሉት ከተፎ ጓደኞቻችን እንድንበረታ በማፅናናትና መልካሙን በመመኘት ባለቤቴን ዘና የሚያደርጋትን ጨዋታዎች ከጥሩ እራት ጋር ጋብዘውን የቀጠሮ ሰዓታችን ስለደረሰ ተያይዘን ወደ ማዕከሉ አመራን፡፡

የዕለቱ የምሽት ተረኛ ዶክተሮች ገብተው አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ባለቤቴ አልጋ እንድትይዝ ተደርጎ እንደተባለው የማህፀን ማለስለሻውን ከማዕከሉ መድኃኒት ቤት እንዳመጣ በመታዘዝ የመጀመርያው ሙከራ ተደረገ፡፡ ይሁንና ማለስለሻው እስከ ምሽቱ ስድስት ሰዓት ድረስ ምንም ዓይነት ምልክት ባለማሳየቱ በድጋሚ ለሁለተኛ ግዜ ማለስለሻው ተደርጎላት እስከ ንጋቱ ሁለት ሰዓት ተጠበቀች፡፡ ይሁንና የማህፀን ማለስለሻው ሁለተኛ ሙከራም ከሸፈ፡፡ የሌሊቱ ተረኛ ሐኪሞች ለዕለቱ የቀን የሕክምና ባለሙያዎች ተራቸውን አስረከቡ፡፡ የሚቀጥለው የምጥ የተባለው መርፌ ነው፡፡ ተረኛው ነርስ በስሪንጅ የያዘውንና በጉሉኮስ መልክ የሚሰጠውን የማማጫ መርፌ በተንጠልጣዩና በጠብ ጠብ የባለቤቴ ሰውነት ውስጥ የሚገባው ፈሳሽ ላይ ጨመረው፡፡

ይሁንና ሙሉቀን ቢጠበቅም የምጥ መርፌ የተባለው ፈሳሽ በባለቤቴ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ማሳየት አልቻለም፡፡ ባለቤቴ ማማጥ ቀርቶ አንዳችም የሕመም ስሜት ሳይሰማት እንደ ደህናው ቀን እየተጨዋወትን የሚሆነውን መጠባበቅ ግድ ሆነብን፡፡

በዚህ ግዜ በማዕከሉ በሚደረጉት የሕክምና ሒደቶች ላይ የነበረኝ ጥርጣሬ ይበልጥ ጨመረ፡፡ ብዙዎቻችን በማናስተውለው መንገድ በልጅ ሰበብ በምክንያት እያቀባበሉ የሰውን ኪስ የሚያራቁቱ ዘመናዊ ዘራፊዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ልብ አድርጉ ዘጠኝ ወር ባልሞላት ነብሰ ጡር ላይ እንሽርት ውኃ ቀንሷል በሚል ሰበብ አስገዳጅነት ያለ ወቅቱ ማህፀን ቢለሰልስ እንዴት ሆኖ ነው ፅንሱ ለመወለድ ዝግጁ የሚሆነው? ምጥስ ቢሆን ምን በማስማጫ መርፌ ቢታገዝ አለ ጊዜው ይሆናልን? ፍርዱን ለዘርፉ ባለሙያዎች ትቼዋለሁ፡፡ በነገራችን ላይ በእነዚህ ሁሉ ሙከራዎች ውስጥ ደረጃ በደረጃ የማዕከሉ ክፍያ እየጨመረ የሚሄድ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

ሰዓቱ ወደ አስራ አንድ ሰዓት እየጠጠጋ ነው ቅዳሜ በመሆኑ ተረኛ ሐኪሞች ቀደም ብለው ነው የተቀያየሩት፡፡ ተረኛው ዶክተር ባለቤቴን ጨምሮ በክፍሉ ውስጥ የሚገኙትን ተገልጋዮች ጎበኘ፡፡ ተረኛዋ የእኔ ባለቤት ነች የቀረው ሙከራ ደግሞ አንድ ብቻ ነው ቀዶ ሕክምና (Operation)፡፡

በሰሚ ሰሚ በምጥ መውለድን በከፍተኛ ሁኔታ ያበረታታል የሚባልለት ይህ ማዕከል በዚሁ ዕለት ብቻ ዓይኔ እያየ እንደእኔው በሰበብ አስባቡ ወጥመድ ውስጥ የገቡላቸውን ከአሥራ አምስት የማያንሱ እናቶች ማህፀን በመቅደድ የማዋለድ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡

የልብ ምቴ ጨመረ፣ ግራ ተጋባሁ በኮሪደሩ ላይ ወዲህ ወዲያ መቁነጥነጥ ጀመርኩ ‹‹ከፈጣሪ ቀጥሎ በእነሱ እጅ ነው ያለነው ምን ማድረግ ይቻላል›› እያልኩ ብቻዬን ሳወጣና ሳወርድ የባለቤቴ ስም ተጠርቶ ለቀዶ ሕክምናው ኃላፊነት የመውሰጃ ፎርሙን በመሙላት እንድፈርም ተጠየቅኩ፡፡ ፈረምኩ ባለቤቴን በመሳም በስስት ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍሉ ሸኘኋት፡፡ አብረውኝ ያሉ ወዳጆቼን ጨምሮ ሁላችንም በጭንቀት ተዋጥን፡፡

ሃያ ደቂቃ እንኳን በወጉ በማይሞላ ቅጽበት ባለቤቴ ለቀዶ ሕክምናው ከገባችበት ክፍል ውስጥ በእሪታ የምታቃጭል ቀጭን የሕፃን ልጅ ድምፅ ተሰማ፡፡ በሰማሁት የሚያቃጭል ቀጭን ድምፅ የወለድኩት ሴት ልጅ እንደሆነች ታውቆኛል፡፡ ባለቤቴም በሰላም ተገላግላ ከሚያስፈራው ክፍል ውስጥ ወጣች፣ አሁን ደግሞ በተቃራኒው ሁላችንም ተደሰትን፡፡

በማዕከሉ ተገቢው ክትትልና ምክር ከተሰጠን በኋላ ወደ ቤታችን ለመሄድ የአገልግሎት ክፍያ መክፈል እንዳለብን ተነገረን፡፡ በዚህም መሠረት ወደ ሒሳብ ክፍል በመሄድ ቀደም ሲል ከተነገረን ከፍተኛ ሒሳብ አሥራ ሁለት ሺሕ ብር ላይ ሁለት መቶ ብር ተመለሰልኝ፡፡ ዋናው ጤነኛ ልጅ በሰላም ማግኘት ነው በማለት ከማዕከሉ በሰላም ወጣን፡፡

በወቅቱ ይህ የገንዘብ መጠን በከተማችን ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ የማዋለጃ የግል ሆስፒታሎች በ ‹‹ቪአይፒ›› ደረጃ (በአንድ ክፍል ውስጥ አንድ ተገልጋይ ከልዩ እንክብካቤ፣ መስተንግዶና ምርመራ ጋር) የሚሰጥበት የገንዘብ መጠን ሲሆን ግፋ ቢል በተጠቀሰው ገንዘብ ላይ ሁለት ሺሕ ብር ቢያስጨምር ነው፡፡ በዚህ ተቋም ግን በአንድ ክፍል ውስጥ ከስምንት እስከ አሥራ ሁለት አልጋዎች እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡

በከተማችን ላይ በርካታ ቅርንጫፍ ማዕከሎች ያሉትና በአብዛኞቹ የከተማችን ነዋሪዎች እምነት የሚጣልበት ይህ የእናቶችና የሕፃናት ሕክምና ማዕከል በዓለም አቀፍ የልግስና ድርጅት ስም ምናልባትም ‹‹ከቀረጥ ነፃ ከውጭ አገሮች በሚያስገባቸው የሕክምና መሣሪያዎች›› እየሰጠ የሚገኘው አገልግሎት የማኅበረሰባችንን አቅም ያላገናዘበና ለአገልግሎቱ የሚያስከፍለው ክፍያ እምብዛም ከተማዋ ላይ ከሚገኙት የግል የማዋለጃ ማዕከላት የማይተናነስ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን ከእኔ በተሻለ ዕይታ ተመልክተው ሃይ ቢሉት ይበጃል፡፡ ተገልጋዮችም በስመ ዶክተር የተባልነውን ከማድረግ ተቆጥበን እንደ እኔ ከመሆን ይልቅ በተረጋጋ መንፈስ ጊዜ ወስደን የተነገረንን ውጤት በሌላ ተቋማት በድጋሚ በማረጋገጥ ውሳኔ ላይ ብንደርስና በአሁኑ ወቅት መንግሥት በየአካባቢያችን በከፍተኛ ወጪ የገነባልንን፣ በሦስት ብር ክፍያ ልጅ እያዋለዱ የሚሸኙ የጤና ጣቢያዎች እየሰጡ ያለውን ጥራት ያለው አገልግሎት ለኅብረተሰባችን በማስተዋወቅና ችግር ያለባቸውን በመፈተሽ ተገቢውን የማስተካከያ ዕርምጃ በመውሰድ ተገልጋዩ በቀላል ወጪ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ምቹ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ምንም እንኳን በማዕከሉ ያለ አግባብ ተጎጂ እንደሆንኩ ቢሰማኝም፣ ባገኘኋት ዕፁብ ድንቅ ልጅ የተካስኩ በመሆኑ ነገር ከስሩ እንዲሉ በእንደዚህ ዓይነቱ የአገራችን ብሎም የዓለማችን ስንክሳሮች ውስጥ በማለፍ፣ ያፈራናቸው ልጆቻችንን በመጪው አዲስ ዘመን ብሩህ ተስፋ የሞላባትንንና ከእንደዚህ ዓይነት ብልሹ አሰራር የፀዳችና ሰላሟ የበዛ የነገ ዓለማችንን የሚያበጁ ተስፋ ያላቸው ተስፋዎቻችን በመሆናቸው የልጄን ስም ‹‹ፓሎማ›› የሰላም ርግብ ብዬ ሰይሜያለሁ፡፡

እርግጥ ነው በመጀመርያ ለልጄ ያወጣሁላት ስም የዓለም ሕዝቦች የዘወትር ረሃባችን የሆነውንና አገራችን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በመመልከት ለምድራችን ሰላምን በመሻት ከኖህ ዘመን አንስቶ እስካሁን በምድራችን ላይ በሰላም ተምሳሌትነቷ መላው ዓለም የሚስማማባት የዋህ ፍጥረት ላይ ነጭ የሚል ቅፅል በማከል ‹‹ነጭ ርግብ›› የሚል ነበር፡፡

ይሁንና ‹ስም አይመስልም፣ አልረዘመም?፣ አልተለመደም፣ ርግብ ብትላት አይሻልም?› የሚሉት የተለያዩ ሰዎች አስተያየት የስያሜውን አገርኛ መጠሪያ በማሸፈት ዓለም አቀፍ ቅርፅ አስያዙት፡፡

ስያሜው የተገኘው በትውልድ ስፓኒሻዊ (ስፓኒያርድ) በዜግነት ደግሞ ፈረንሣዊ ከሆነውና ዓለማችን ካፈራቻቸው ድንቅ ሠዓሊያን አንዱ የነበረው ፓውሎ ፒካሶ የፈጠራ ሥራዎቹ መካከል አንዱ ከሆነችውና በዓለማችን ላይ የሰላም ዓርማ ተደርጋ በመወሰዷ የዘንባባ ዝንጣፊ በአፏ ይዛ ስትበር ከምናያት ነጭ ርግብ ነው፡፡

ፒካሶ ሥዕሏን ባስተዋወቀበት ዕለት ለወለዳት ሴት ልጁ ስያሜውን የተጠቀመበት ሲሆን  በሙያቸው የላቀ ደረጃ ላይ የደረሱና በተለይም በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ለዓለማችን አለ የተባለ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ጥቂት ግለሰቦችም ‹‹ፓሎማ›› የሚለውን መጠሪያ ተጠቅመውበታል፡፡

የልጄ የተመጣጠነ ሰውነት፣ አንድ ዓመት ሳይሞላት የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶችን በእጇ ይዛ ቆማ መሄድ መቻሏ፣ የምትሰማቸውን ሙዚቃዎች ሥልተ ምት (Rithm) እየተከተለች ለመደነስ የምታደርጋቸው ጥረቶች፣ ከእኛ ከወላጆቿ ጋር ያላት የመግባባት ክህሎት፣ ከእንቅልፏ ስትነቃ እንደ አብዛኛዎቹ ሕፃናት ከማልቀስ ይልቅ ተረጋግታ አካባቢዋን የመቃኘት ችሎታዋ ሁሉ በእሷ ላይ ያለኝ እምነት በአገር ደረጃ ብቻ የተገደበ ሳይሆን እንደ ስመ አምሳያዎቿ ሁሉ እሷም ነገ ዓለማችንን ከሚቀይሩ መልካም ፍሬዎች መካከል አንዷ እንደምትሆን ሙሉ ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ 

በእርግጥም ሰላም ርቋት፣ በየጊዜው በልዩ ልዩ ጉዳዮች እየተተራመሰች ለምትገኘው አገራችን አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም የሰላም ሚኒስቴር የተባለ ተቋምና የአዲስ አበባ ከተማ የሰላም ምክር ቤት ማቋቋም ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዳችን የሰው ልጆች የሰላምን ዋጋ ጠንቅቀን በመረዳት ልጆቻችን ከስም ስያሜያቸው ጀምሮ ነገ የዓለማችን የሰላም አምባሳደሮች መሆን የሚያስችላቸውን ኃላፊነት በማሸከም መቅረፁ የወል ኃላፊነታችን ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህም ነው ከኦሮሞ አባቷና ከአማራ እናቷ አብራክ የተከፈለችውን ልጄን በጠባቦቹ ዘራዊ፣ ክልላዊ፣ ብሔረሰባዊ፣ ጎሳዊ፣ ነገዳዊ ወዘተ. መስፈሪያዎች ሳይሆን፣ በሰው ልጆች ተፈጥሯዊ የነፃነት መሥፈርት መሠረት ታዳጊዋ ልጄ በአገሯ ብሎም በመላው ዓለም እንደ ሰላሟ ርግብ በነፃነት በመብረር ለክፍለ ዘመናት የራቀንን ሰላም ቀን ከሌት እንድትዘምር በመሻት የልጄ ስም ‹‹ፓሎማ›› (የሰላሟ ርግብ)  የፍቅርና የሰላም ቅዱሳዊ ተምሳሌት የተሰኘው፡፡ ሻሎም፡፡ 

 ከአዘጋጁ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles