Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለጥቂቶች የተራዘመው የኩላሊት እጥበት ነፃ ሕክምና ሌሎችን የሚረዳ እንዲጠፋ ማድረጉ ተገለጸ

ለጥቂቶች የተራዘመው የኩላሊት እጥበት ነፃ ሕክምና ሌሎችን የሚረዳ እንዲጠፋ ማድረጉ ተገለጸ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2012 ዓ.ም. የተጀመረውና በ2013 ዓ.ም. እንዲቀጥል የተወሰነው ነፃ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት፣ ተጠቃሚ የሚያደርገው በመንግሥት ሆስፒታል እየታከሙ የሚገኙትን ሕሙማን ብቻ ቢሆንም፣ ለሕሙማኑ ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙ ድርጅቶችና ግለሰቦች ነፃ አገልግሎት መስጠት ተጀምሯል በሚል እሳቤ ከዚህ ቀደም ይረዷቸው የነበሩ ሕሙማንን ድጋፍ እያቋረጡ መሆኑ እንዳሳሰበው የኩላሊት እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት አስታውቋል፡፡

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግለት በደብዳቤ በጠየቀው መሠረት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በዘውዲቱ መታሰቢያ፣ በዳግማዊ ምኒልክና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች ዓምና ነፃ የኩላሊት እጥበት ሕክምና ሲያገኙ ለነበሩ 105 ሕሙማን ዘንድሮ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማራዘማቸውን ተከትሎ፣ በግል የሕክምና ተቋማት ሕክምናቸውን ለሚከታተሉ ሕሙማን ይገኝ የነበረው ድጋፍ እየጠፋ ነው፡፡  

የነፃ ሕክምናውን ዜና የሰሙ ለጋሾች ድጋፉ ለሁሉም ሕሙማን አለመሆኑን ባለመረዳታቸው ያደርጉ የነበረውን ድጋፍ እያቋረጡ መሆኑን ሕሙማኑ ለድርጅቱ የገለጹ ሲሆን፣ ድርጅቱም ሕሙማኑን ለመድረስ በሚያቀርበው የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄ ላይ ከአንዳንድ ድርጅቶች ተመሳሳይ ምላሽ እያገኘ መሆኑን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

 ‹‹ሕሙማኑ በተሳሳተ መረጃ ምክንያት ገንዘብ አጥተው ሕይወታቸውን እንዳያጡ ለሕዝባችን መግለጽ እንፈልጋለን፡፡ ድጋፉን የሚሹ ከሺሕ በላይ ሕሙማን በአዲስ አበባ አሉን፤›› ያሉት አቶ ሰለሞን፣ የምክትል ከንቲባዋ የድጋፍ ውሳኔ በግል ጤና ተቋማት የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚያገኙትን እንደማይመለከታቸውና ረጂዎች እያቋረጡ  ያለውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኅብረተሰቡ የመደጋገፍ ልምዱንና ለሕሙማኑና ለድርጅቱ ሲያደርግ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ በማጠናከር በግል ክሊኒክ ውስጥ ለሚታከሙ የኩላሊት ሕሙማን ድጋፍ እንዲያደርግ፣ የአዲስ አበባን ተሞክሮን በመውሰድም ክልሎች በየክልሉ ላሉት ሕሙማን የገንዘብና የሕክምና ወጪ ድጋፍ በማድረግ ይተባበሩን ብለዋል፡፡

የምሥጋና ቀንን ምክንያት በማድረግ በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት እያደረጉ የሚገኙ ሕሙማንን ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም. የጎበኙት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች፣ በሦስት የመንግሥት ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት እያደረጉ ለሚገኙ ሕሙማን አስተዳደሩ 12 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የ2013 ዓ.ም. ሕክምናቸውን በነፃ እንዲከታተሉ መወሰናቸው ይታወሳል፡፡

የኩላሊት እጥበት የሚያስፈልጋቸው ሕሙማን በሳምንት ሦስት ጊዜ በወር 12 ጊዜ የእጥበት ሕክምናውን ማግኘት ያለባቸው ቢሆንም፣ አብዛኞቹ በወር ከ15 ሺሕ ብር በላይ አውጥተው ለመታከም ስለማይችሉ በሳምንት አንዴ ወይም ሁለቴ ብቻ ሕክምናቸውን የሚከታተሉና ይህንን ማድረግ ያልቻሉት ደግሞ ለሕልፈት የሚዳረጉ ናቸው፡፡

1,300 ያህል ሕሙማን በከባድ ችግር ውስጥ ሆነው በግል ሆስፒታሎች ሕክምናቸውን እንደሚከታተሉ የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ መንግሥት ችግሩን ዓይቶ በመንግሥት ሆስፒታል ያለውን አገልግሎት በማጠናከር ሁሉንም ተጠቃሚ እንዲያደርግና በሆስፒታሎች የሚታየው የግብዓት እጥረት ችግር እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡

በመንግሥት ሆስፒታል የሚከናወን የኩላሊት እጥበት ለአንድ ጊዜ ከእነ መድኃኒቱ 600 ብር ሲሆን፣ በግል ሆስፒታሎች ደግሞ ከ1,300 እስከ 1,600 ብር እንደሆነ የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ በግል ሆስፒታል እየከፈሉ የሚታከሙት ወጪው ከአቅማቸው በላይ በመሆኑና ለሕክምናው በማድላታቸው ለምግብ ችግር መጋለጣቸውን ጠቁመዋል፡፡

ድርጅቱ ለአንድ ሕመምተኛ በወር ከሚያስፈልገው 8,000 ብር 4,000 ብሩን በመደገፍ 80 ሕሙማንን እየረዳ ሲሆን፣ 22 ደግሞ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ በተገኘ ድጋፍ ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡

ድርጅቱ በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ለኩላሊት እጥበት ምቹ አድርጎ የሠራውና ለሆስፒታሉ ያስረከበው ሕንፃ 36 ማሽን የሚይዝ ቢሆንም፣ ከሦስት ዓመት በፊት የነበሩትን ስድስት ማሽኖችን ብቻ ይዞ በመቀጠሉ ሕሙማኑን በሚፈለገው መልኩ ካለማስተናገዱም ባለፈ ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገው መሆኑን አቶ ሰለሞን ጠቁመው፣ መንግሥት ለዚህ ምላሽ በመስጠት ተጨማሪ ማሽኖችን እንዲያስገባና ሕሙማኑን እንዲታደግ ጠይቀዋል፡፡

ኅብረተሰቡም ከዚህ ሕመም ራሱን ለመጠበቅ የአኗኗር ዘይቤውን መቀየርና ሕክምናውን በአግባቡ መከታተልና በአቅራቢያው ወደሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ ኩላሊቱ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ በማወቅ ራሱን እንዲጠብቅም መክረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...