Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊትምህርትን በኮቪድ-19 ሥጋት ውስጥ

ትምህርትን በኮቪድ-19 ሥጋት ውስጥ

ቀን:

ኮቪድ-19 በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ የተሠሩ ጥናቶች ቫይረሱ በሕፃናት ላይ ያለው ቀጥተኛ ተፅዕኖ ውስን መሆኑን ቢያመላክቱም፣ በትምህርት ላይ ያሉ ሕፃናትና ወጣቶች በበሽታው የመያዝና በሽታውን ወደ ሌሎች የማስተላለፍ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ያሳያሉ፡፡

በተለይ ሕፃናት በሽታውን ከትምህርት ቤት ይዘው ወደ ቤት በመመለስ በዕድሜ ወደገፉና ተጓዳኝ በሽታዎች ወዳሉባቸው የቤተሰብ አባላት የማስተላለፍ ዕድላቸው ሰፊ በመሆኑ ትምህርት ቤቶች የወረርሽኙን ሥርጭት ሊያባብሱ እንደሚችሉ በማመንም አብዛኞቹ አገሮች ትምህርት ቤቶችን ዘግተው ከርመዋል፡፡

  ይህም ከ1.8 ቢሊዮን በላይ ተማሪዎች ቤት እንዲቀመጡ አስገድዷል፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃም 26 ሚሊዮን ያህል መደበኛና ሦስት ሚሊዮን ያህል ኢመደበኛ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ተፈናቅለዋል፡፡ 700 ሺሕ ያህል መምህራን ደግሞ ከመደበኛው ማስተማር ሥራቸው ተስተጓጉለዋል፡፡ 

- Advertisement -

እንደየአገሮቹ የወረርሽኝ ሒደት ደግሞ የተለያዩ አገሮች ትምህርት ቤቶችን መልሰው የከፈቱ ሲሆን፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድ፣ የካናዳዋ ኪዩቤክ ግዛትና አንዳንድ የእሥራኤል ትምህርት ቤቶች ከከፈቱት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ አገሮቹ ትምህርት ቤቶችን በከፊልም ሆነ በሙሉ በሚከፍቱበት ጊዜ በየአገራቸው የነበረው የኮቪድ-19 ሥርጭት መጠን ማሻቀብ ያቆመበትና ወረርሽኙ በአንፃሩ የተረጋጋበት ወቅት ነበር፡፡

ትምህርት ቤቶችን መልሰው ከከፈቱ በኋላ ወረርሽኙ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ባይሆንም በማኅበረሰቡ ውስጥ መልሶ በማንሰራራቱ መልሰው ከዘጉት ውስጥ ደግሞ ደቡብ ኮሪያና ሆንግ ኮንግ ይገኙበታል፡፡

ደቡብ አፍሪካ፣ ካሜሮንና ታንዛኒያ ትምህርት ቤቶችን መልሰው የከፈቱ ሲሆን፣ በደቡብ አፍሪካ ትምህርት ቤቶች ከተከፈቱ በኋላ በመምህራንና ተማሪዎች ላይ የበሽታው ሥርጭት በመጨመሩ ከ25,762 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 968ቱ መልሰው ተዘግተዋል፡፡

ይህንን መነሻ ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) የኮሮና ወረርሽኝ ምላሽ፣ ቀጣይ ዕርምጃዎችና ምክረ ሐሳብ በሚል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሳምንት በፊት ሲያቀርቡም ትምህርት ማስጀመር ከሥጋት ሙሉ ለሙሉ ነፃ መሆን ስለማይችል የአከፋፈት ሒደቱ ከፍተኛ ጥንቃቄና ዝግጅት የሚፈልግ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

ትምህርት ቤቶችን መልሶ ስለመክፈት ሲታሰብ አንድ ተማሪ በትምህርት ቤት ውስጥ በሽታው እንዳይዘው፣ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት በሚጓዝበት ወቅት ሊወስዱ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች እንዲሁም በቤት ውስጥ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ የቤተሰብ አባላትን ከመጠበቅ አንፃር የሚወሰዱ ዕርምጃዎችን ያካተተ ፓኬጅ ሊተገበር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የኮቪድ-19 በሽታን ለመከላከል ከሚወሰዱ ዕርምጃዎች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው እጅና ፊትን አዘውትሮ መታጠብና አካላዊ ርቀት ሲሆኑ ከዚህ አንፃር በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ካሉ ተቋማት ቀላል የማይባል ቁጥር በቂ የውኃ አቅርቦት፣ የንፅህናና መሠረተ ልማት የሌላቸው በመሆኑና በአገር አቀፍ ደረጃ አማካይ የተማሪ ክፍል ጥምርታ 1፡56 መሆኑ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚኖራቸውን አቅም አነስተኛ እንደሚያደርገው ዶ/ር ሊያ በሪፖርታቸው አስቀምጠዋል፡፡

በመሆኑም ትምህርት ቤቶች ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ መልሶ ለመክፈት ከትምህርትና ጤና ሴክተር በተጨማሪ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ፣ የትራንስፖርት፣ የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶችና የሰላም ሚኒስትርና ሌሎችም መሳተፍና በየዘርፎቻቸውም የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ትምህርት ቤት መጀመር ከመወሰኑ በፊት ጠንካራ ግብረ ኃይል በየደረጃው አቋቁሞ ወደ ሥራ ማስገባት፣ በተለያዩ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የኳራንቲን፣ የለይቶ ማቆያና የሕክምና ማዕከላት ተለዋጭ ቦታ እንዲያዘጋጁ በጀት ማመቻቸትም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ተማሪዎችን በሦስት ዙር ትምህርት ማስጀመር

ትምህርት ቤቶችን ዳግም መክፈት በሚቻልበት የውሳኔ ሃሳብ ላይ የትምህርት ሚኒስቴርና የክልል ትምህርት ቢሮ ከፍተኛ ኃላፊዎች መስከረም 12 እና 13 ቀን 2013 ዓ.ም. የመከሩ ሲሆን፣ ደግሞ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን ጋር መክረው ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመጀመሪያው ዙር ጥቅምት 9 ቀን በሁሉም የዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በ2ኛ ዙር ጥቅምት 16 ቀን እንዲሁም በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ጥቅምት 30 ቀን ትምህርት የሚጀምሩ ይሆናል፡፡

የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መቼ ይሁን የሚለውን የመከሩት የትምህርት ሚኒስቴርና የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ሁሉም ተፈታኞች ለፈተና እንዲቀመጡ የሚል ውሳኔ አሳልፈው፣ የ8ኛ ክፍል ፈተና ኅዳር 22 እና 23 ቀን እንዲሰጥና  ፈተና ላይ መቀመጥ የሚችሉት ደግሞ 7ኛ ክፍልን ተምረው ያጠናቀቁና የ8ኛ ክፍልን የአንደኛ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ እንደሚሆኑ አሳውቀዋል።

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በተመለከተ ለፈተናው መቀመጥ የሚችሉት የ11ኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቁና የ12ኛ ክፍልን የመጀመሪያ ወሰነ ትምህርት (ሴሚስተር) የተከታተሉ ብቻ እንደሚሆኑም ገልጸዋል። የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከኅዳር 28 እስከ ታኅሣሥ 1 ቀን የሚሰጥ ይሆናል።

የትምህርት አሰጣጥ ሒደቱን በተመለከተ ለመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚወጣው መመዘኛ በግል ትምህርት ቤቶች ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን፣ የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ መጠን በ2012 ዓ.ም. እንደነበረው ሆኖ፣ ክፍያ የሚፈጸመውም በባንክ በኩል ብቻ ይሆናል፡፡

ኮቪድ-19 ለመከላከል የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች

የዓለም ጤና ድርጅትና የጤና ሚኒስቴር ወረርሽኙን ለመከላከል ባስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ መሠረት፣ ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት በመድኃኒት ማፅዳት፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልና የእጅ ማፅጃ ማሟላት እንዲሁም አካላዊ ርቀትን ማስተግበር የሚችሉ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ማስጀመር ይችላሉ፡፡

ለሌላ አገልግሎት ውለው የነበሩ ትምህርት ቤቶችም አስፈላጊውን የማስተካከያ ሥራ ሊሠራላቸው እንደሚገባና እንደየ ትምህርት ቤቶቹ ነባራዊ ሁኔታ ትምህርት በፈረቃና አንድ ቀን በመዝለል ሊያስተምሩ ይችላሉ፡፡

ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን የኮቪድ ወረርሽኝ ሥጋት በቀነሰ መልኩ ለመክፈት ሊተገበሩ ከሚገባቸው የዝግጅት ሥራዎች ውስጥ የበሽታው ሥርጭት በአንፃራዊ ዝቅተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች መጀመርና ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማስፋት፣ ደረጃ በደረጃ ትምህርት ቤቶችን መክፈት፣ የተወሰኑ የትምህርት ክፍሎችን መክፈትና የበሽታውን ሁኔታ እያዩ ቀስ በቀስ ሌሎች ክፍሎችን ማስጀመር፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎችን ማድረግ፣ የውኃና የሳሙና አቅርቦት ማሟላት የወላጆች፣ አስተማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ያለውን የተማሪ ብዛት መቀነስ የሚያስችሉ ዘዴዎችን መተግበር፣ መስኮቶችንና በሮችን ሁልጊዜ ክፍት ማድረግ፣ አካላዊ ቅርርብን ሊቀንሱ የሚችሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን መተግበር ያስፈልጋል፡፡

በ2013 ትምህርትን መልሶ የመክፈት ስትራቴጂ

ትምህርት ሚኒስቴር በ2013 ዓ.ም. ኮቪድ-19ን እየተከላከሉ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ ለማስቻል ትምህርትን መልሶ የመክፈት ስትራቴጂ ነድፏል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤቶች መሻሻል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ወጋሶ እንዳሉት፣ በስትራቴጂው ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት የፅዳት መጠበቂያ ቁሳቁስ ማዘጋጀት፣ የውኃ አቅርቦት ወጥ በሆነ መልኩ መኖር፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛና የሙቀት መለኪያ መሣሪያ መኖር አለበት፡፡

ተማሪዎች መጽሐፍ እንዳይዋዋሱ የመጽሐፍ እጥረት ባለበት ኅትመት እንዲኖር፣ መዋዋስ እንዲቀር፣ ርዕሰ መምህራን በኮቪድ-19 ላይ ያለውን መረጃ መከታተል፣ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ሕፃናት መለየትና በልዩ ሁኔታ ማስተናገድ፣ ማንኛውም ተማሪ ከታመመ ከወላጅ ተማክሮ ሕክምናና የሥነ ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ በስትራቴጂው ከተካተቱ መስፈርቶች ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም ተማሪ ወይም መምህር በኮቪድ-19 ከተጠረጠረ ትምህርት ለሁለት ሳምንት እንዲዘጋ፣ በአንድ ክፍል ከ25 በታች በአንድ ዴስክ አንድ ተማሪ ብቻ እንዲማር፣ ማድረግ የክፍል እጥረት ባለበት ጊዜያዊ የመማሪያ ጣቢያ እንዲኖር፣ የተማሪ መመግቢያና መውጫ በር በተቃራኒ ሆኖ ተማሪዎች የሚገቡበትና የሚወጡበት እንዲለይ ትምህርት በፈረቃ ሲሰጥ ቀድመው እየተማሩ በነበሩበትና በተከታይ በሚገቡት ተማሪዎች መካከል የአንድ ሰዓት ልዩነት እንዲኖር፣ የአንድ ትምህርት ቤት ተማሪ ከአንድ ሺሕ እንዳይበልጥና ስምንት የመማሪያ ክፍሎች ያሏቸው ትምህርት ቤቶች በአንዴ በክፍል 25 ተማሪ ታስቦ 200 ተማሪ ብቻ እንዲያስተምሩና በተቻለ መጠን የተማሪ ንክኪን እንዲያስቀሩ፣ የክፍል እጥረት ካለ በሦስት ፈረቃ ማስተማር የሚሉት በስትራቴጂው ተጠምጠዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ እንደሚሉት፣ ክፍልንና የተማሪ ንፅህና ማስጠበቅን መተግበር ከባድ ሊሆን ቢችልም ትምህርት መክፈት የሚቻለው በስትራቴጂው የተቀመጡ መሠረታዊ መሥፈርቶች ሲሟሉ ነው፡፡

ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት በኬሚካል ማፅዳት፣ የሙቀት ልየታ መሣሪያ መኖር፣ የአፍና አፍንጫ ጭንብል ማቅረብ፣ መምህራን ተጨማሪ ፈረቃ እንዲያስተምሩ ማድረግ፣ በጡረታ ያሉና ሌሎች በጎ ፈቃደኞችን ማሳተፍ የሚሉትም ይገኙበታል፡፡

በውሳኔዎቹ ላይ ከትምህርት ኃላፊዎቹ ጋር የመከሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንንትምህርት ከመጀመሩ በፊት መማር ማስተማር ለመጀመር የሚያስችል በቂ ዝግጅት መኖሩን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል

በእያንዳንዱ ትምህርት ቤትም ወላጅን፣ መምህራንንና የጤና ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ ተዋቅሮ ትምህርት ቤቱን  ለመክፈት የሚያስችል ግምገማ ማድረግና ግብዓቶች መሟላታቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...