Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአንጋፋው የአየር መንገድ ባለሙያ ጎበና ሚካኤል እምሩ አረፉ

አንጋፋው የአየር መንገድ ባለሙያ ጎበና ሚካኤል እምሩ አረፉ

ቀን:

በአፍሪካ የአቪዬሽን ታሪክ አሻራ ያሳረፉት ጎምቱ የአየር መንገድ ባለሙያና የልጅ ሚካኤል እምሩ ልጅ ጎበና ሚካኤል እምሩ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች ለ27 ዓመታት፣ በሩዋንዳ አየር መንገድ ለስድስት ዓመታት፣ በአጠቃላይ በአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ለ34 ዓመታት ያገለገሉት አቶ ጎበና ሚካኤል በተወለዱ በ58 ዓመታቸው፣ ሰኞ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በሩዋንዳ ኪጋሊ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ በሥራ ላይ ባለፉት ስድስት ዓመታት በኖሩባት ኪጋሊ በገጠማቸው ድንገተኛ ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው፣ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሩዋንዳ ኪጋሊ የሩዋንዳ አየር መንገድ ዋና መሥሪያ ቤት ድንኳን ተጥሎ የመታሰቢያና የስንብት ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን፣ የሩዋንዳ አየር መንገድ ማኔጅመንትና ሠራተኞች ለአቶ ጎበና የነበራቸውን አክብሮትና ፍቅር የገለጹበት ሁኔታ፣ የአቶ ጎበና ቤተሰቦችንና ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻቸውን ጭምር ያስደመመ ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የአቶ ጎበና አስከሬን ከኪጋሊ በክብር ወደ እናት አገራቸው ተሸኝቶ ማክሰኞ ማታ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሲደርስ ቤተሰቦቻቸው፣ ዘመድ አዝማድ፣ ጓደኞቻቸውና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማኔጅመንትና ሠራተኞች አቀባበል አድርገዋል፡፡ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ረቡዕ መስከረም 13 ቀን 2013 ዓ.ም. በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የቅርብ ዘመድ ከነበሩት አባታቸው ልጅ ሚካኤል እምሩና እናታቸው ወ/ሮ አልማዝ ተክለ ሐዋርያት በአዲስ አበባ የተወለዱት ጎበና ሚካኤል፣ የሕፃንነት ዕድሜያቸውን አባታቸው በአምባሳደርነት ባገለገሉባቸው በሩሲያና በስዊዘርላንድ አሳልፈዋል፡፡ ትምህርታቸውን በስዊዘርላንድ ኤኮል ትምህርት ቤት የጀመሩት አቶ ጎበና በመቀጠል በአዲስ አበባ አሜሪካ ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሒሳብ ትምህርት የመጀመርያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በኤርላይን ማርኬቲንግና ፋይናንስ በዲፕሎማ የተመረቁ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንፎርሜሽን ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪ ሠርተዋል፡፡

በወጣትነት ዕድሜያቸው ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የገቡት ጎበና ሚካኤል፣ 27 ዓመታት ባገለገሉበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባተረፉት ተወዳጅነት ሩሲያዊት ሞግዚታቸው በሕፃንነታቸው ባወጣችላቸው ‹‹ጌና›› በሚለው ስም ይጠሩ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ በስፔስ ኮንትሮል ክፍል ሥራ የጀመሩት አቶ ጎበና የዋጋ ትመና ክፍል ሥራ አስኪያጅ፣ የሽያጭ ክፍል ኃላፊ፣ የማርኬቲንግ አውቶሜሽንና የማርኬቲንግ ሰፖርት ሲስተም ፕሮጀክት ማናጀር በመሆን አገልግለዋል፡፡ የማርኬቲንግ ኢንፎርሜሽን ክፍል ኃላፊ ሆነው ያገለገሉት አቶ ጎበና በኢትዮጵያ አየር መንገድ በውጭ ጣቢያዎች የፈረንሣይ ፓሪስ  ጣቢያ ኃላፊ፣ የደቡብ አውሮፓ ክልል ኃላፊ በመሆን በሮም ከተማና የሰሜንና ደቡብ አሜሪካ አካባቢ ኃላፊ በመሆን በዋሽንግተን ዲሲ ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የለውጥ ፕሮግራምን የመሩ ሲሆን፣ የዓለም አቀፍ ሽያጭ ምክትል ፕሬዚዳንት በስተመጨረሻም ዋና ኮሜርሽያል ኦፊሰር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በጡረታ በመገለል ወደ ኪጋሊ ያቀኑት አቶ ጎበና የሩዋንዳ አየር መንገድ ዋና ኮሜርሽያል ኦፊሰር በመሆን ለስድስት ዓመታት ባገለገሉበት ወቅት፣ ለአየር መንገዱ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ሩዋንዳውያን ወዳጆቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ በስንብት ፕሮግራሙ ላይ ሐዘናቸውን የገለጹት የሩዋንዳ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ይቮን ማንዚ ሚኰሎ፣ አየር መንገዳቸው ታላቅ ሰው እንዳጣ በከፍተኛ የሐዘን ስሜት ውስጥ ሆነው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በሩዋንዳ አየር መንገድ ውስጥ ተወዳጅ ሰው ነበር፡፡ ኩባንያችን ያለሱ እንደ ድሮ አይሆንም፡፡ እንደባልደረባ ብቻ ሳይሆን እንደ ታላቅ ወንድማችን ነበር የምናየው፡፡ በእጅጉ ይናፍቀናል፤›› ብለዋል፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግርማ ዋቄ የአቶ ጎበና የረዥም ዓመት ወዳጅ ናቸው፡፡ አቶ ግርማ አቶ ጎበናን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኟቸው እ.ኤ.አ. 1984 በወጣትነታቸው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስፔስ ኮንትሮል ክፍል ውስጥ ሲያገለግሉ ነበር፡፡

‹‹ገና በወጣትነቱ ነበር የማውቀው፡፡ ታታሪና ጠንካራ ሠራተኛ ነበር፡፡ በትንሹ የማይረካ ለዝርዝር ጉዳዮች ትኩረት የሚሰጥ ሰው ነበር፤›› ብለዋል አቶ ግርማ፡፡ የሩዋንዳ አየር መንገድ ቦርድ ሰብሳቢና የሩዋንዳ የትራንስፖርት ሚኒስትር የአቪዬሽን ጉዳዮች አማካሪ ሆነው ያገለገሉት አቶ ግርማ፣ ከአቶ ጎበና ጋር በኪጋሊ ለሦስት ዓመታት አብረው ሠርተዋል፡፡ ‹‹ፈሪኃ እግዛብሔር ያለው ጥሩ ሰው ነበር፡፡ ከሁሉ የሚገርመኝ ያለውን ዕውቀት ያለስስት ለባልደረቦቹ ለማካፈል የነበረው ቁርጠኝነት ነው፤›› ያሉት አቶ ግርማ፣ አቶ ጎበና ኪጋሊ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሩዋንዳ አየር መንገድ ማኔጅመንትና ሠራተኞች ከፍተኛ ተወዳጅነት እንዳተረፉ መስክረዋል፡፡ ‹‹እሱም አገሩንና ሕዝቡን ይወድ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ የሩዋንዳ አየር መንገድ ሠራተኞችና ሌሎች ሩዋንዳውያን ለአቶ ጎበና ያላቸውን ፍቅር የገለጹበት መንገድ እንዳስገረማቸው አቶ ግርማ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በርካታ የሐዘን መግለጫዎች ከኪጋሊ በስልክና በኢሜይል እየደረሳቸው እንደሆነ አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ የአቶ ጎበና ሚካኤል ድንገተኛ ሞት አስደንጋጭና አሳዛኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ተወልደ ለሪፖርተር በላኩት መልዕክት ከአቶ ጎበና ጋር ላለፉት 34 ዓመታት እንደሚተዋወቁ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አቶ ጎበና ተግባቢና ያመነበትን በግልጽ የሚናገር ሰው ነበር፤›› ያሉት አቶ ተወልደ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

አቶ ጎበና አፍሪ አቪዬሽን የተሰኘ አማካሪ ኩባንያ ከኢትዮጵያውያን ወዳጆቻቸው ጋር መሥርተዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያና በሩዋንዳ ብቻ ሳይሆን በመላ አፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ታዋቂ ባለሙያ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ነዋሪነታቸውን በኡጋንዳ ያደረጉት ጀርመናዊው ዕውቁ የአቪዬሽንና የቱሪዝም አማካሪና ጋዜጠኛ ፕሮፌሰር ወልፍጋንግ ቶም፣ የአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ታላቅ ሰው እንዳጣ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ጎበና የአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዋና ታማኝ የመረጃ ምንጫችን ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በፈረንሣይ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሔኖክ ተፈራ፣ በአቶ ጎበና ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሳዛኝ ቀን፣ በጣም ቀና እና ታላቅ ባለሙያ ነበር፡፡ ከእርሱ ጋር አብረን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በማገልገሌ ኩራት ይሰማኛል፡፡ ለቤተሰቦቹ፣ ለጓደኞቹና ለሥራ ባልደረቦቹ መፅናናትን እመኛለሁ፤›› ብለዋል አምባሳደር ሔኖክ፡፡

አቶ ጎበና ሚካኤል ባለፈው መጋቢት ወር በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል በተካሄደው ‹‹አቪዬሽን አፍሪካ›› ጉባዔ ላይ፣ የሩዋንዳ አየር መንገድን በመወከል ተሳትፈዋል፡፡ አቶ ጎበና ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...