በኦሮሚያ ክልል በአሰላ አካባቢ 100 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ የንፋስ የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት ሊገነባ ነው።
የንፋስ ኃይል በመጠቀም ለማመንጨት የታቀደው የኤሌክሪክ ኃይል ፕሮጀክት በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱን ዕውን ለማድረግ የሚያስፈልገው 146 ሚሊዮን ዩሮ (ከ5.8 ቢሊዮን ብር በላይ) የበጀት ፍላጎትም ከዴንማርክ መንግሥት በዕርዳታና በድጋፍ መልክ ተገኝቷል።
ለፕሮጀክቱ ከሚያስፈልገው 146 ሚሊዮን ዩሮ ውስጥ 117.3 ሚሊዮን ዩሮ ያህል ዳንሴክ ግሩፕ ከተሰኘው የዴንማርክ ባንክ በብድር የተገኘ ሲሆን፣ የተቀረውን የገንዘብ መጠን ደግሞ የዴንማርክ መንግሥት በዕርዳታ ለመስጠት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።
ፕሮጀክቱ የሚጠይቀውን አጠቃላይ ወጪ በድጋፍና በብድር ለመደገፍ የዴንማርክ መንግሥትና ዳንሴንክ ግሩፕ የተሰኘው ባንክ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት የፈጸሙ ሲሆን፣ ይህንንም ስምምነት የሕዝብ የወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ አፅድቆታል።
በብድር መልክ የተገኘው 117.3 ሚሊዮን ዩሮ የአምስት ዓመታት የዕፎይታ ጊዜን ጨምሮ በ20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚከፈል ነው፡፡ የዴንማርክ መንግሥት በብድሩ የሚከፈለውን ወለድ ለመሸፈን በመስማማቱ፣ ከብድር ወለድ ክፍያ ነፃ መሆኑን በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈረመው የስምምነት ሰነድ ያስረዳል።
የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱን ዕውን ለማድረግ የሚያስፈልጉ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ተርባዮኖች በሙሉ ከዴንማርክ የሚገዙ ሲሆን፣ ዕቃዎቹን የማቅረብና ፕሮደክቱን በበላይነት የማስተዳደር ኮንትራት ሲመንስ ከተባለው የዴንማርክ ኩባንያ ጋር መፈረሙን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በምሥራቅ ኦሮሚያ በኢተያ ወረዳ የሚገነባ ነው። ፕሮጀክቱ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም የሚኖረው ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው 3.45 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ 84 ሜትር ከፍታ ያላቸው 29 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ይኖሩታል ተብሏል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከንፋስ ኃይል እያመነጨች ያለውን 324 ሜጋ ዋት የኃይል መጠን ከፍ እንደሚያደርገው፣ የአሰላውና በአይሻ እየተገነባ ያለው 120 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም የሚኖረው የንፋሰ ኃይል ማመንጫ ሲጠናቀቅ፣ አገሪቱ ከንፋስ ኃይል የምታገኘው አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል 544 ሜጋ ዋት እንደሚደርስ ይጠበቃል።