Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አቢሲኒያ ባንክ ቨርቹዋል የባንክ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ካሉ የግል ባንኮች መካከል አንዱ የሆነውና 25ኛ ዓመቱን ለማክበር ዋዜማ ላይ የሚገኘው አቢሲኒያ ባንክ፣ ለአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ አዲስ የሆነው አንድን ቅርንጫፍ ተክቶ ሊሠራ የሚችለውን የቨርቹዋል የባንክ ማዕከል ሥራ አስጀመረ፡፡

በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ውስን የሚባል አበርክቶ ይኖረዋል ተብሎ የሚታመንበት ይህ አገልግሎት ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶችን ከማስፋት ባሻገር አንድ ቅርንጫፍ ሊሰጣቸው ይችላሉ የተባሉ ሁሉንም አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡

ከ15 በላይ የሆኑ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችለው ይህ ቴክኖሎጂ አንድ ደንበኛ ወደ ባንክ ቀርቦ ሊያገኝ ይችላቸው የነበሩ አገልግሎቶችን 24 ሰዓት የሚሰጥ ነው፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ እንደገለጹት ‹‹የቨርቹዋል የባንክ ማዕከሉ ደንበኞች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት በርቀት ባሉ የደንበኛ አማካሪዎች በመታገዝ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በማሽኑ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተመለከተ ከተሰጠው ማብራሪያና የአገልግሎት አሰጣጡ በተግባር እንደታየው፣ ማሽኑ ቼኮችን ይመነዝራል፡፡ የጭ ምንዛሪ መመንዘር ከተፈለገም ይህንኑ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ገንዘብ ገቢ ማድረግና ማስወጣትም ይቻላል፡፡ የሒሳብ ደብተር ሳያስፈልግ ገንዘብ ማስቀመጥ የሚያስችል የሐዋላና ሌሎች ገንዘቦችንም ማስተላለፍ የሚቻልበት መሣሪያ ነው፡፡ የተለያዩ ክፍያዎችን ለመፈጸምም ይህንን ማሽንን መጠቀም ይቻላል፡፡

ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችም ወደ ቅርንጫፉ መሄድ ሳያስፈልግ ማከናወን የሚያስችል ስለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የአቢሲኒያ ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ ኦፊሰር ወ/ሮ ሶስና መንገሻ እንደገለጹት፣ በሥራ ሰዓት በቅርንጫፎች የምንሰጣቸውን አገልግሎቶች፣ በሥራ ሰዓት ሳንገደብ 24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

አገልሎቱ የቪዲዮ ቴክኖሎጂን ይጠቀማል ያሉት ወ/ሮ ሶስና ኢንተር አክቲቭ ቴክኖሎጂዎች ላይ ሆኖ የአንድ ደንበኛ የሚፈልገውን አገልግሎት በሚጠይቅበት ጊዜ አገልግሎቱን ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህን አገልግሎት ለመጠቀም ደንበኞች የአቢሲኒያ ባንክ ደንበኞች ካሁኑ ምንም ዓይነት የሚጠበቅባቸው መሥፈርት የማይጠየቅ ሲሆን፣ በቅርንጫፍ እንደሚያገኙት አገልግሎት መቀመጫቸው በማስገባት የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ፡፡

የሌሎች ባንኮች ደንበኞችም ቼኮቻቸውን አጥንተው ቼኮቻቸውን መሰንዘር የሚያስችልም ነው፡፡

ባንኩ የአምስት ዓመት የስትራቴጂ ዕቅዱን ሲነድፍ ለደንበኞች ምቾቱን የጠበቀና የላቀ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ሲባል ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የሚያመላክተው የባንኩ መረጃ፣ በዕለቱ አገልግሎት የጀመረውም የቨርቹዋል የባንክ አገልግሎት የሥራ ስትራቴጂ አንድ አካል ነው ተብሏል፡፡

ይህ ማዕከል በአይቲኤም. የሚታገዝና ደንበኞች ምቾታቸው ተጠብቆ የባንክ ቅርንጫፍ የተገደበ የጊዜ ሰሌዳ ሳያስጨንቃቸው በቅርንጫፍ የሚያገኙትን አገልግሎት በቀን ለ24 ሰዓት፣ በሳምንት ለሰባት ቀናት አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል ነው፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አክክለው እንደገለጹት ደግሞ ለአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ብሎም የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት አቅዶ ወደ ሥራ እየተገባ ሲሆን፣ ቴክኖሎጂውን በማስተዋወቅ ረገድ ባንካቸው ፋና ወጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ደንበኞች በዚህ ደኅንነቱ በተጠበቀ ማዕከል በአይቲኤም ከሚያገኟቸው አገልግሎቶች መካከል ሒሳብ መክፈት፣ ገንዘብ ተቀማጭ ወይም ወጪ ማድረግ፣ ቼክ መመንዘርና ተቀማጭ ማድረግ፣ የአገር ውስጥ ሐዋላ፣ ገንዘብ ማስተላለፍ፣ እንደ ሞባይል ባንኪንግ፣ ኢንተርኔት ባንኪንግ፣ ካርድ ባንኪንግ ሞባይል መኒ ያሉ የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶችን ለማግኘት ምዝገባ ማከናወን ላይም ነው ብለዋል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ ያስተዋወቀው ይህ አገልግሎት ከወቅታዊ የብር ኖት ቅያሬ ጋር ተያይዞ የብርኖቶችን ለመለወጥ የሚያስችል ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡ በዚህ ረገድ የሚሰጠውን አገልግሎት በተመለከተ እንደተገለጸው ‹‹በአሁኑ ጊዜ በአገራችን እየተከወነ ያለውን የገንዘብ ኖት ቅያሪን በተሻለ መስተንግዶ ፍጥነት ለማከናወን፣ ዓለምን እየፈተነ ያለውን የኮሮና ወረርሽኝ በመከላከል ረገድ ደንበኞች ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲስተናገዱ በማድረግ፣ ቴክኖሎጂው ወረቀት አልባ የባንክ አገልግሎትን በማስፋፋት ረገድም ለሥነ ምኅዳሩ ተስማሚ የሆነ አሠራር ይዞ የመጣ ከመሆኑ አኳያ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው›› በሚል ነው፡፡

ይህንን አገልግሎት ቦሌ መድኃኒዓለም አካባቢ በሚገኘው የባንኩ ቅርንጫፍ ከሚገኝበት ያስመረቀው አቢሲኒያ ባንክ፣ ተመሳሳይ በዕለቱ በአዲስ አበባ ሌሎች ሦስት ቦታዎች ላይ አገልግሎቱን አስጀምሯል፡፡ በቀጣይም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች 15 በቀጣይ ሦስት ወር ውስጥ ማሽኖችን በመትከል አገልግሎቱን ያሰፋይ ተብሏል፡፡

በዚህ አገልግሎት ዙርያ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መሠረት ታዬ፣ ከዚህ በኋላ ዓለም በቴክኖሎጂው ላይ ያተኩራል፡፡ ባንካቸው አሁን ይህንን አገልግሎት በመጀመር ለአገሪቱ እንዳስተዋወቀ ሁሉ ሌሎች ቴክኖሎጂን ያማከሉ አገልግሎቶችን በማከል ዘመናዊ አሠራሩን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ ያስጀመረውን ይህንን አገልግሎት መርቀው የከፈቱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ በበኩላቸው፣ እንዲህ ያለው የባንክ አገልግሎት ዘርፉን ለማዘመን ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸው፣ ሌሎች ባንኮችም መሰል አገልግሎት ላይ እንደማሳተፉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ ስለጀመረው የቨርቹዋል ባንክ አገልግሎት በዓይነቱ የመጀመሪያ መሆኑንና ኅብረተሰቡን ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዛቸው ስለመሆኑ ጠቅሰው፣ ሌሎች ባንኮችም በተመሳሳይ የቨርቹዋል የባንኪንግ አገልግሎቶችም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶችን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ በብሔራዊ ባንክም የዘመናዊ የባንክ ቴክኖሎጂ እንዲኖር ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ባንኮች እንዲህ ባለው ዘመናዊ አገልግሎቶች ውስጥ መግባታቸው የባንክ ሥርዓቱን በተሻለ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ በእጅጉ ያግዛሉ፡፡

አቢሲኒያ ባንክ 25ኛ ዓመቱን በቅርቡ የሚያከብር ሲሆን፣ ከግል ባንኮች ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካደረሱ የግል ባንኮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ባንኩ በተለይ በ2012 ሒሳብ ዓመት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ዕድገቱ ከሁሉም የግል ባንኮት ብልጫ እንደነበረው ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች