Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ክብር ለታማኝነት

የገቢዎች ሚኒስትር ታማኝ ግብር ከፋዮች ናቸው ያላቸውን ግለሰቦችና ተቋማትን በመለየት ዕውቅና መስጠት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

በ2012 በጀት ዓመትም ሚኒስቴሩ ታማኝ ግብር ከፋዮች ብሎ በተለያየ ደረጃ ለመረጣቸው ወደ 220 ግለሰቦችና ኩባንያዎች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ገቢ ባደረጉት የገንዘብ መጠን በተለያዩ ደረጃዎች ተከፋፍሎ የተሰጠውን ዕውቅና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እጅ ተቀብለዋል፡፡

የዘንድሮውን የዕውቅና አሰጣጥ ለየት የሚያደርገው ታማኝ ተብለው የተለዩት ግብር ከፋዮችን ከማመሥገንና ዕውቅና ከመስጠት ባለፈ በአገሪቱ ያሉ አገልግሎት ተቋማት ለእነዚህ ታማኝ ግብር ከፋዮች ቅድሚያ መስተንግዶ ያገኙ ዘንድ መወሰኑ ነው፡፡ ዕውቅና ፕሮግራሙ በተካሄደበት ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ታማኝ ግብር ከፋዮች ለሌሎችም ምሳሌ እንዲሆኑ፣ ዕውቅናቸውም ትርጉም ያለው እንዲሆን የአገልግሎት ተቋማት እነዚህን ታማኝ ግብር ከፋዮች ቅድሚያ ሰጥቶ የማስተናገድ ባህልን መለማመድ አስፈላጊ ስለመሆኑ ጠቅሰው ነበር፡፡

እንደ ምሳሌ ያነሱትም እነዚህ ታማኝ ግብር ከፋዮች የአየር መንገድን አገልግሎት ሲሹ ከሌሎች መንገደኞች በተለየ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲስተናገዱ ማድረግ የሚቻል መሆኑ አንዱ ነው፡፡ ሌሎችም የአገልግሎት ተቋማት በተመሳሳይ እነዚህን ምሳሌ የሚሆኑ የግብር ከፋዮች የማስተናገድ ልምድ መዳበር እንዳለበት አሳስበውም ነበር፡፡ ይህ ማሳሰቢያ በተሰጠ በቀናት ልዩነት ይኼው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት በተግባር እንዲውል ገቢዎች ሚኒስቴር በአገልግሎት ተቋማት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ይስተናገዱ የተባሉ ግለሰቦች ኩባንያዎችን ስም ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ እንግዲህ ታማኝ ግብር ከፋዮች በየትም ቦታ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲስተናገዱ በማድረግ ሌሎችም የሚማሩበት ብሎም የሚበረታቱበት ይሆናል ተብሎ ታምኖበታል፡፡

በዚሁ ፕሮግራም ላይ በተመሳሳይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተሰማው ከዕውቅናው ባሻገር ሌሎች ማበረታቻዎች እንደሚኖሩ ነው፡፡ እንዲህ ያለው የዕውቅና አሰጣጥ በእርግጥም የሚበረታታ፣ እንደተባለውም ለሌሎች መማሪያ ይሆናል፡፡ ሌሎችም በታማኝነት ግብራቸውን ከፍለው አገርና ሕዝብን በመጥቀም ተግባራቸው ቢመሠገኑ ትክክል ነው፡፡ ብሎልን እንዲህ ባለ ደረጃና ታማኝት የምናወድሳቸው ብሎም በዚህ በጎ ተግባራቸው ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የማስተናገዱ ታማኝ ግብር ከፋዮች ይበርክቱልን እንላለን፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን ባሳለፍነው ሳምንት የታማኝ ግብር ከፋዮች ተብለው የተለዩት ግለሰቦችና ኩባንያዎች ቁጥር በ220 ብቻ የመገደቡ ነገር ታማኝ ግብር ከፋዮቻችን እነዚህ ብቻ ናቸው? ብሎ መጠየቅ ግን ተገቢ ነው፡፡ ታማኝ ግብር ከፋይ ከፍተኛ የሆነ ግብር የሚከፈልም ብቻ አይደለም፡፡ በእርግጥ አመራረጡ የገንዘብ መጠን ሊኖረው ይችላል፣ መነሻ ተደርጎ የተቀመጠ ወለል ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለው የዕውቅና አሰጣጥ የመሥፈርቱ የደረጃ አሰጣጥና ሌሎች ምዘናዎች በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ታማኝ የግብር ከፋይ ባስገባው ገቢ ብቻ የሚመዘን እንዳይመስልም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ እንዲያውም ከሒሳብ አያያዛቸው ጀምሮ የመንግሥትን ግብር በተገቢው መንገድ በማስገባት ድርብ ድርብርብ በሆነ አፈጻጸም አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ ግብር ከፋዮችንም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ አመራረጡ ሒደት በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ሌሎች እንዲበረታታ ከተፈለገም ለዕውቅና የሚያበቃቸውን ምዘና ሁሉም ማወቅ አለበት ማለት ነው፡፡  

በታማኝነት ግብራቸውን የሚከፍሉ የአነስተኛ ቢዝነስ ተቋማትንም ለብቻቸው በመመዘን ተመሳሳይ ዕውቅና መስጠት ለነገ ከፍተኛ የሆነ ግብር ከፋዮችን ማፍራት የሚቻልበት አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡  ከሥር በታማኝነት ግብር የመክፈል ልምድ ልምምዱ ከታች ቢጀምር ጠቀሜታው የበዛ ይሆናል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት የዕውቅና ፕሮግራም እንዲህ ካለው ብዥታ ባሻገር አነጋጋሪ ሆኖ ሊቀርብ የሚችለው አንኳር ጉዳይ ደግሞ የዕውቅና ፕሮግራሙ የተሰጠበት ወቅት ነው፡፡

የዕውቅና ፕሮግራሙ የተዘጋጀበት ወቅት ለምን የሚል ጥያቄ የሚያስነሳው ደግሞ የ2012 ዓ.ም. ታማኝ ግብር ከፋዮች ተብለው የተመረጡት ግለሰቦችና ድርጅቶች እንዴት ሊመረጡ ቻሉ? የሚለውንም ጥያቄ ስለሚያስከትል ነው፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ ሕግ መሠረት ግብር ከፋዮች እንደየቢዝነስ የፈቃድ ደረጃ ልካቸው ወይም ዓመታዊ የሽያጭ መጠናቸው ታይቶ ግብራቸውን የሚከፍሉበት የጊዜ ገደብ በሕጉ የተቀመጠ ነው፡፡

ስለዚህ በተለይ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የሚባሉት የ2012 ዓ.ም. ዓመታዊ ግብራቸውን የሚከፍሉት እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የ2012 ዓ.ም. የግብር ከፋዮች በተለይ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን ገና አይከፍሉም ማለት ነው፡፡

አሠራሩ ይህ ከሆነ የ2012 ዓ.ም. ግብር ከፋዮ ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ከመድረሱ በፊት ወይም በተግባር ግብሩን ሳያስገቡ ነው የተመረጡት? ወይስ ይከፍላሉ ተብሎ ታሳቢ ተደርጎ ነው? የ2012 ዓ.ም. ታማኝ የግብር ከፋዮች ተብለው የተለዩትና ዕውቅና የተሰጣቸው? የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ ያስነሳል፡፡

በእርግጥ የ2012 በጀት መዝጊያ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. መሆኑ ይታወቃል፡፡ እና በዚያ የሒሳብ መዝጊያ ወቅት ኩባንያዎቹ የሒሳብ ሪፖርታቸውን አቅርበው ሊከፍሉ የሚችሉት ገንዘቡ ተሠልቶ ወይም ተመዝግቦ ነው፡፡ ከተባለም ይኼው መገለጽ አለበት፡፡ ካልሆነ ግን የ2012 በጀት ዓመት ግብር ተጠናቅቆ ሳይከፈል ማን ምን ያህል እንደከፈለ እንኳን ሳይታወቅ ቀድሞ ዕውቅና እየተሰጠ ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለዚህም ነው የዕውቅና መስጪያ ጊዜው ትክክል ነው ወይ? የሚል ጥያቄ የሚነሳው፡፡

ይህ ብቻ አይደለም ዕውቅና ፕሮግራሙን የተመለከተ ዕውቅና ከተሰጣቸው ግሰቦች ወይም ኩባንያዎች የበለጠ ግብር ለመክፈል እየተዘጋጁ ያሉት ጥቂት የማይባሉ የንግድ፣ የንግድና ኅብረተሰቡ አባላትም በዚህ የዕውቅና ፕሮግራም አሰጣጥና ምዘናው ላይ፣ እንዲሁም ጊዜው ላይ ጥያቄ ሲያነሱ እየተሰማ ነውና የገቢዎች ሚኒስቴር በዚህ ዙሪያ ግልጽ ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ ዕውቅና መስጠቱ የሚበረታታውና የመሆኑን ያህል አጠቃላይ ምዘናውና አጠቃላይ ሐዲቱ ላይ ጥያቄ እየተነሳ በመሆኑ ምላሽ ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም በታማኝ ግብር ከፋይነታቸው የተመረጡት ግብር ከፋዮችን ስናበረታታ ዕውቅናው ሲገባቸው ይህንን ያጡ ለምን ማለታቸው ስለማቀር በተግባርም እየተሰማ በመሆኑ ለከርሞ ለሚኒስቴሩ እንደ ቤት ሥራ የሚወሰድ ይሆናል፡፡ እንዲህ ያለው ዕውቅና አስፈላጊነት የሚያሻማ ሲሆን፣ አሠራሩንም ማሳመር የበለጠ ትርጉም ይኖረዋል፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት