መንግሥት ኅብረተሰቡን እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያወጣቸው ዕቅዶች ላይ ከመጀመርያው ጀምሮ ሲቪል ማኅበራት ቢሳተፉ፣ ዕቅዶች ተግባራዊ ሲሆኑ የሚታዩ ችግሮችን ማጥበብ ይቻላል የሚል ምክረ ሐሳብ ቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (ኢሴማቅ) በኢትዮጵያ እየተዘጋጀ ያለው የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ የሴቶችን ፍላጎትና ችግሮች ምን ያህል ከግምት አስገብቷል በሚል ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት ከሪፖርተር ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት የኢሴማቅ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳባ ገብረ መድኅን መንግሥት የራሱ መረጃ፣ ባለሙያዎችና ዕቅድ አውጪዎች ቢኖሩትም፣ ታች ካለው ኅብረተሰብ ጋር በቀጥታ እየተገናኙ የሚሠሩ ሲቪል ማኅበራት ችግሩን በቀጥታ ስለሚያዩ በሚዘጋጁ ዕቅዶች ላይ ከመነሻው ቢሳተፉ ችግር ፈቺ የሆኑ ዕቅዶችን ማውረድ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
መንግሥት ማንኛውንም ዕቅድ የሚያወጣው ልማት ለማምጣት፣ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ኅብረተሰቡን በእኩል ደረጃ ለመጥቀም ነው ያሉት ወ/ሮ ሳባ፣ ሲቪል ማኅበራት በዕቅዶች ላይ ባሳተፈ መጠን ባለቤትነትን ለመፍጠር፣ ለዕቅዱ የተሻለ ግብዓት ለማግኘትና በሚወጡ ዕቅዶች ላይ የዜጎችን የመሳተፍ መብት ለማረጋገጥ እንደሚጠቅመውም ገልጸዋል፡፡
በየዘርፉ የሚሠሩ ሲቪል ማኅበራት በሴቶችም ሆነ በሌሎች የኅብረተሰቡ አጀንዳዎች ላይ ያተኮሩ ፖሊሲዎችና ዕቅዶች ለምን እንደማይፈጸሙና ለምን እንዳልተፈጸሙ እንደሚያውቁ፣ ሲቪል ማኅበራት በዕቅዶች በተሳተፉ ቁጥርም ታች ያለውን የኅብረተሰብ ችግር ወደላይ በማውጣት ለኅብረተሰቡ የሚወጡ ዕቅዶች ለውጥ የሚያመጡ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚቻል አክለዋል፡፡
ከሥርዓተ ፆታ በተለይ ከሴቶች አካታችነት ጋር በተያያዘ፣ ከሚቀመጡ አቅጣጫዎች፣ ትንተናዎች፣ የቃላት አጠቃቀሞችና ጥቅል አድርጎ ሐሳብን ማስቀመጥን ጨምሮ የተለያዩ ክፍተቶች የሚታዩ በመሆናቸው፣ ጥቅል ሐሳቦች ተተንትነውና ፆታ አመላካች ጠቋሚዎች ተካቶባቸው በመሥራት በዘርፉ ያሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚቻልም አሳስበዋል፡፡
የልማት ዕቅዶች ሲዘጋጁ የመሳተፍ ዕድል እንዳልነበራቸውና የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅዱ ሲዘጋጅ ግብዓት እንዳልሰጡ የገለጹት ወ/ሮ ሳባ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በነበራቸው ስብሰባ በሚወጡ ስትራቴጂዎችና ዕቅዶች ላይ እንዲሳተፉ በጠየቁት መሠረት፣ ሰነዱ ስለተሰጣቸው ክፍተቶችን ለመሙላት የሚችሉ ሐሳቦችን በመረጃና በጥናት አስደግፈው ግብዓት ለመስጠት በትጋት እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹ከመጀመርያው አብረን ብናቅድ ወደኋላ መመለስ ላይኖር ይችል ነበር፤›› ያሉት ወ/ሮ ሳባ፣ አሁንም ያልተጠናቀቁ ነገሮች አሉ በመባላቸው ግብዓት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢሴማቅ በሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የሴቶች ፖሊሲ ላይ እንደ አማካሪ ሆኖ እየሠራ መሆኑን በማስታወስም በሴቶች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በየዘርፉ ያሉ ሲቪል ማኅበራት በዕቅድ አወጣጥ ላይ ከመጀመርያው ቢሳተፉ በጋራ መሠረታዊ ችግሮችን በመፍታት ለውጥ ለማምጣት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡