የፍትሕ ጉዳይ ማንንም ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ማንኛውም ነገር ዋስትና የሚኖረው ለፍትሕ ክብር ሲሰጥ ነው፡፡ የፍትሕ መለያ የሆነችው ዓርማ ዓይኗ በጨርቅ መሸፈኑ፣ ፍትሕ ለማንም የማያዳላና ገለልተኛ የመሆኑ ማሳያ ምሳሌ ነው፡፡ የሰቆቃ ምዕራፍ ተዘግቶ ፈውስ የሚገኘው ደግሞ በኢትዮጵያዊ ፍትሕን ማስቀድም ሲቻል ነው፡፡ ፍትሕ ተረግጦ ሰቆቃ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ኃይሎች፣ በማናቸውም መንገድ ፖለቲካዊ ቀውስ ለመቀስቀስ ሲሯሯጡ አብሮ መንጎድ አይገባም፡፡ እነሱ በሰብዓዊ ፍጡራን ሥቃይና ሰቆቃ ላይ እያላገጡ ተጠያቂነትን ከብሔር፣ ከሃይማኖት፣ ከፆታ፣ ከፖለቲካ አቋምና ከመሳሰሉት ጋር ሲያገናኙ፣ በስሜታዊነት ሳይሆን በምክንያታዊነት መብለጥ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ካሁን በኋላ መቼም ቢሆን ፍትሕ የማንም መጫወቻ እንዳይሆን ለተቋማት ግንባታ መረባረብ ይገባል፡፡ በተለይ የፍርድ ቤቶች፣ የምርጫ ቦርድ፣ የሚዲያ፣ የደኅንነትና የፀጥታ ኃይሎች ነፃነትና ገለልተኝነት ዕውን እንዲሆን ጥርስን ነክሶ መሥራት የግድ ይላል፡፡ በተጨማሪም የፍትሕ አካላት ነፃነትና ገለልተኝነት በሕግ ማዕቀፍ ሲረጋገጥ፣ የሥይና የሰቆቃ ታሪካችን ምዕራፍ በአግባቡ ይዘጋል፡፡ ነፃነቱን የሚፈልግ ማንም ሰው ስለኃላፊነቱ ጭምር በመረዳትና ከአጓጉል ድርጊቶች በመታቀብ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሕ እንዲሰፍን የበኩሉን ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡ ፍትሕ ከሌለ ነፃነት የለም፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ተጠምቶ የኖረው ፍትሕ ነው፡፡ ፍትሕ በመጥፋቱ ምክንያት ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የጭቆና ቀንበር ሲሸከሙ ኖረዋል፡፡ ሕይወታቸውን ገብረዋል፡፡ አካላቸው ጎድሏል፡፡ ንብረታቸው ተዘርፏል፡፡ ሰብዓዊ ክብራቸው ተዋርዶ የድህነት መጫወቻ ሆነዋል፡፡ አምባገነኖች እየተፈራረቁባቸው መፈጠራቸውን እስኪጠሉ ቀጥቅጠዋቸዋል፡፡ ይህ መቼም ቢሆን የማይካድ የታሪካችን አካል ነው፡፡ ለአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት መወገድና ለዘውዳዊው አገዛዝ ማክተም ምክንያቱ የፍትሕ ዕጦት የወለደው መንገፍገፍ ነው፡፡ ለደርግ ሥርዓት መገርሰስ ሰበቡ የፍትሕ መደርመስ ያመጣው ሰቆቃ ነው፡፡ የኢሕአዴግ የ27 ዓመታት የጭቆና ጉዞ በለውጥ ኃይሎች አማካይነት እንዲያበቃ የተደረገው፣ በፍትሕ ዕጦት ምክንያት የደረሰው ከመጠን ያለፈ መንገሽገሽ ነው፡፡ ሥርዓቶቹ አንዳቸው ከአንዳቸው ስህተትና ውድቀት መማር ባለመቻላቸው በሕዝብ ላይ የዘነበው መከራ፣ የፍትሕ ያለህ ከማለት አልፎ የአገርን ህልውና የሚፈታተን ሥጋት እየደቀነ እዚህ ተደርሷል፡፡ አሁን ምርጫ ለማድረግ መሰናዶ በሚደረግበት ወቅት ከምንም ነገር በላይ መቅደም ያለበት የአገር ህልውና በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋነኛ ትኩረት ፍትሕ ለማስፈን የሚረዱ ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ ርብርብ ማድረግ ነው፡፡ ፍትሕ አገራዊ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ ‹በሕግ አምላክ፣ ሕግ ይከበር› ማለት የተለመደ የሕዝባችን የሕግ አክባሪነት መገለጫ ነበር፡፡ ጉልበተኞች አገር ሲያምሱና ሲያተራምሱ ሕግ ማክበር ቀርቶ ሥርዓተ አልበኝነት ያደረሰው መጠነ ሰፊ ጥፋት አይዘነጋም፡፡ አሁንም የመንግሥትን የሥልጣን ልጓም የያዘው አካልም ሆነ፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ተዋናይ የሆኑ ሁሉ ከምንም ነገር በፊት የፍትሕ ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይገባል፡፡ የፍርድ ቤቶች ነፃነት አስተማማኝ መሆን አለበት፡፡ የፍርድ ቤቶች ውሳኔ በመንግሥት አስፈጻሚ አካልም ሆነ በማንም መሻር የለበትም፡፡ አገር የምትመሩም ሆነ ሥልጣን ለመያዝ የምትፎካከሩ ፍትሕን አስቀድሙ፡፡ የሕግ የበላይነት ሲጠፋ ፍትሕ ሸቀጥ ይሆናል፡፡ ጉልበተኞች አቅመ ደካሞችን ያጠቃሉ፡፡ ሥልጣናቸውን ያላግባብ የሚጠቀሙ በደላቸው ከሚታገሱት በላይ ይሆናል፡፡ ፍትሕ ፍለጋ የሚባዝኑ ወገኖች በአገራቸው ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ሦስቱ የመንግሥት አካላት ማለትም ሕግ አውጭው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው እየተናበቡና የእርስ በርስ ቁጥጥር እያደረጉ መሥራት ካልቻሉ ስለፍትሕ መነጋገር አይቻልም፡፡ የአስፈጻሚው አካል ጡንቻ እየበረታ ሁለቱ አካላት እየኮሰመኑ ሲሄዱ፣ ለዕለት እንጀራው ከሚማስነው ዜጋ ጀምሮ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የተደራጁ ጭምር ተስፋ ቢስ ይሆናሉ፡፡ ፍትሕ በሌለበት አፈና እንጂ ነፃነት አይኖርም፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመናትን አብሮ የተሻገረው ክፉና ደግ ጊዜያትን በአንድነት አሳልፎ ነው፡፡ ብሔር፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ ባህልና የመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይገድቡት እዚህ ዘመን የተደረሰው፣ ከመለያየት ይልቅ በአንድነት የሚያኖሩት የጋራ እሴቶች ስለሚበዙ ነው፡፡ ይኼንን የመሰለ ታላቅና ባለ ታሪክ ሕዝብ ይዞ የዘመናት ድህነትን ታሪክ ማድረግ ሲገባና ከሠለጠኑት አገሮች ተርታ መሠለፍ ሲቻል፣ ፍትሕን በመናድ በሕገወጥነት አገር ማተራመስ ዕብደት ነው፡፡ ይህችን ታሪካዊት አገር በዕድገትና በብልፅግና የአፍሪካ ፈርጥ ማድረግ እየተቻለ፣ ሕዝቡን በፍትሕ ዕጦት ተስፋ ቢስ ማድረግ ነውር ነው፡፡ በሕግ የበላይነት የምትመራ ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት በጋራ መክሮና ዘክሮ መደላድሉን ማመቻቸት እየተቻለ፣ ፍትሕን በማዛባት አገርን የአምባገነንነት መጫወቻ ለማድረግ መማሰን ከሚታገሱት በላይ ነው፡፡ ለፍትሕ፣ ለሰላምና ለነፃነት መስፈን ተባብሮ መሥራት ሲገባ ሕገወጥነትን ማበረታታት የለየለት ወንጀል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት አብረው መኖር የሚችሉት የሁሉም ነገር ምሰሶ የሆነው ፍትሕ ሲሰፍን ነው፡፡ የፍርድ ቤቶች ነፃነት ተከብሮ ዜጎች የሕግ ከለላ እንዳላቸው እምነት ሲኖራቸው፣ እንዲሁም በጉልበታቸው እንዳሻቸው መሆን የሚፈልጉ በሕግ አደብ ሲገዙ አገር ተስፋ ይኖራታል፡፡
‹‹የማን ቤት ጠፍቶ የማን ሊበጅ፣ የአውሬ መፈንጪያ ይሆናል እንጂ›› ከሚል የጀብደኞች ኋላቀር አስተሳሰብ ውስጥ መውጣት ይገባል፡፡ የጋራ የሆነች አገርን የፍትሕ አምባ ማድረግ ሲገባ፣ ለግልና ለቡድን ጥቅም ሲባል ብቻ ጉልበትን መምረጥ በታሪክና በትውልድ ያስጠይቃል፡፡ ከዚህ ቀደም የሕግ የበላይነትን በመጋፋት የተፈጸሙ አሳዛኝ ተግባራት አገርን ችግር ውስጥ መክተታቸው አይዘነጋም፡፡ ፍትሕ የጉልበተኞች መጫወቻ በመደረጉ የተፈጠረው ምሬት ምን እንዳስከተለም ይታወቃል፡፡ በፍትሕ ሲያላግጡ የነበሩ በተራቸው ፍትሕ ሲለምኑ ታይተዋል፡፡ አሁንም ከእንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ ለመውጣት መንግሥት በአፅንኦት ራሱን ይመርምር፡፡ ፍትሕ ተነፍገናል የሚሉ ወገኖች በትክክለኛው መንገድ ቅሬታቸው ይሰማ፡፡ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ተፈጽመውባቸው ከሆነም በፍጥነት ማስተካከያ ይደረግ፡፡ በርካታ አንፀባራቂ የሕግ ማሻሻያዎች እየተደረጉባት ባለች አገር ውስጥ የፍርድ ቤቶች ውሳኔ አልከበር ብሎ ዜጎች መሰቃየት የለባቸውም፡፡ በተንዛዛ የጊዜ ቀጠሮ ዜጎችን ከማንገላታት ታልፎ የዋስትና መብት ሲከበርላቸው እንቅፋት መፍጠርም አይገባም፡፡ በወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡ ዜጎች እስኪፈረድባቸው ድረስ እንደ ንፁህ የመገመት ሕጋዊ መብት ስላላቸው፣ ፍትሕን ሊያዛቡ ከሚችሉ አላስፈላጊ ድርጊቶች መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ፍትሕ የማንም ሰው መተማመኛ ሁነኛ መሣሪያ መሆኑ በተግባር መረጋገጥ አለበት፡፡
አገርን ወደ ብሔራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለማሸጋገር ዋነኛው መንገድ ፍትሕ ማስፈን ነው፡፡ ይህ መግባባት የሚፈጠረው ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል መሆናቸውን በመቀበል፣ ከአድሎአዊና ከአግላይ አስተሳሰቦች በመላቀቅ፣ ከኢትዮጵያዊነት መልካም እሴቶችና ጨዋነቶች በተፃራሪ ባለመገኘት፣ ኢሞራላዊ ድርጊቶችን ከመፀየፍ ባሻገር በማጋለጥ፣ ለአምባገነኖች ጠበቃ ባለመሆን፣ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር በመታገል፣ ሕዝብን በማክበርና ለአገር እስከ መስዋዕትነት በሚያደርስ ደረጃ ኃላፊነት በመወጣት ነው፡፡ ማኅበረሰባዊ ቁስሎች ሽረው በነፃነት ለመኖር የሚፈልግ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ ከስሜታዊነት በመላቀቅ በምክንያታዊነት መመራት አለበት፡፡ እያንዳንዱ ሰው ለሠራው በጎ ተግባር እንደሚመሠገነው ሁሉ፣ ሲያጠፋ ደግሞ ተጠያቂነት እንዳለበት መተማመን ይገባል፡፡ ሙገሳን ለራስ ወስዶ ተጠያቂነትን ከወጡበት ማኅበረሰብ ጋር ማገናኘት በራሱ ወንጀል ነው፡፡ በማንኛውም ዓይነት ወንጀል የሚጠረጠር ማንም ሰው በተገቢው መንገድ ፍትሕ ፊት የሚቀርብበት አሠራር ተግባራዊ ከሆነ፣ በብሔርና በሃይማኖት ከለላ ለመደበቅ መሞከር ዋጋ ቢስ ይሆናል፡፡ የፍትሕ ዓርማ ዓይኗን የሸፈነችበት ጨርቅ የገለልተኝነቷ ምሳሌ መሆኑን በተግባር በማረጋገጥ፣ ፍትሕ የሕዝብና የአገር ጋሻ እንዲሆን በፅናት መቆም ያስፈልጋል፡፡ ፍትሕ በሌለበት ነፃነት የለምና!