Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየእነ አቶ እስክንድር ነጋ የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

የእነ አቶ እስክንድር ነጋ የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

ቀን:

‹‹የምርጫውን ዕድል እንዳናጣ ፍርዱ ሳይጓተት በአጭር ጊዜ ይጠናቀቅልን››

አቶ እስክንድር ነጋ

‹‹የተፋጠነ ዳኝነትና ፍትሕ የመስጠት የሕግም የሞራልም ግዴታ አለብን››

- Advertisement -

ፍርድ ቤት

እነ አቶ እስክንድር ነጋ በተመሠረተባቸው ክስ ላይ የተጠቀሱባቸው የሕግ ድንጋጌዎች፣ ዋስትና እንደማይከለክሏቸው በመከራከር የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ያቀረቡት ጥያቄና ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ ሕገ መንግሥቱንና የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግን በመጥቀስ ያቀረበውን የመቃወሚያ ክርክር የመረመረው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሕገ መንግሥታዊና የሽብር ድርጊት ወንጀል ችሎት ዋስትናውን ውድቅ አደረገው፡፡

ፍርድ ቤቱ ማክሰኞ መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው ብይን እንዳስታወቀው፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ያነሱትን የዋስትና ጥያቄ ሲቃወም፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(6)፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 63 እና 67(ለ) ድንጋጌዎችን በመጥቀስ ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡ ተከሳሾቹ ምንም እንኳን ዋስትና የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ቢኖራቸውም፣ በተጠቀሱት ድንጋጌዎች ግን የዋስትና መብቱ ገደብ እንደተጣለበትና ተከሳሾቹ በተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት ጥፋተኛ ከተባሉ፣ እስከ 25 ዓመታት ሊቀጡ ስለሚችሉ ዋስትናው መፈቀድ እንደሌለበት ተከራክሮ ነበር፡፡

እነ አቶ እስክንድር (አምስት ተከሳሾች) ባቀረቡት የዓቃቤ ሕግን መቃወሚያ ክርክር ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት፣ ምንም እንኳን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(6) የዋስትና መብት ላይ ገደብ የሚጥል ቢሆንም፣ በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች እንጂ እነሱ በተከሰሱበት የወንጀል ድርጊትና የሕግ ድንጋጌ አለመሆኑ ነው፡፡

የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 63 ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የነበረ ሕግ በመሆኑና ከሕገ መንግሥቱ በታች ከመሆኑም ሌላ ሕገ መንግሥቱ በዝምታ የሻረው በመሆኑ፣ በእነሱ ላይ ሊሠራ እንደማይችል በማንሳት ተከራክረው ዋስትናቸው እንዲጠበቅላቸው ደጋግመው ጠይቀው ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ በሁለቱ ተከራካሪ ወገኖች በኩል በቀረበው ክርክር ላይ ብይን ለመስጠት የተመሠረተውን ክስ ሲመረምር፣ የዓቃቤ ሕግ ክስ ብሔርንና ሃይማኖትን ምክንያት በማድረግ በተፈጠረ ግጭት፣ የሰው ሕይወት መጥፋቱንና ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመት እንደደረሰ ቢገልጽም መቼ፣ የትና ማን ምን ያህል ጥፋት እንደፈጸመ ግልጽ ተደርጎ እንዳልተጻፈ በመጠቆም፣ ፍርድ ቤቱ ግልጽ ትዕዛዝ ለመስጠት እንዲያስችለው ክሱን አሻሽሎ እንዲቀርብ ለዓቃቤ ሕግ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

ዓቃቤ ሕግ ሁለት ገጽ የሚሆነውን የክስ ክፍል አሻሽሎ መቅረቡን፣ ፍርድ ቤቱ በችሎት ጠይቆ ማሻሻሉን ካወቀ በኋላ የተሻሻለውን ክስ በችሎት አንብቧል፡፡ ፍርድ ቤቱ በችሎት እንዳሰማው አቶ እስክንድር ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ አቅም ግንባታ በመባል በሚታወቀው አካባቢ፣ በግምት ከሰዓት በኋላ 10፡00 ሰዓት አካባቢ እሱ ያደራጃቸውንና በመሣሪያ የተደገፈ አመፅ ሲያስተባብር እንደነበር ጠቁሟል፡፡

ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት እስከ 12፡00 ሰዓት ድረስ በአራዳ፣ ቦሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ኮልፌ ቀራኒዮና ልደታ ክፍላተ ከተሞች ዘጠኝ ሰዎች፣ ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12፡30 ሰዓት እስከ ከሰዓት 11፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ በንፋስ ስልክ ላፍቶና አራዳ ክፍለ ከተማ አምስት ሰዎች በድምሩ 14 ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ማድረጋቸውን ገልጾ፣ ክሱን እንዳሻሻለ ፍርድ ቤቱ በንባብ አሰምቷል፡፡ በተጠቀሱት ክፍላተ ከተሞች የተለያየ መጠን ያለው ንብረት በድምሩ 187,258,459 ብር መውደሙንም በማሻሻያው አካትቶ ማቅረቡን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተሻሻለውን ክስ አንብቦ እንደጨረሰ ቀደም ብሎ ከአንድ ሳምንት በፊት ክርክር በተደረገበት የዋስትና መብት ጥያቄ ላይ ብይን ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾች ዓቃቤ ሕግ ለዋስትና ማስከልከል የጠቀሰውን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 63 በሕገ መንግሥቱ እንደተሻረ መግለጻቸውን ያስታወሰው ፍርድ ቤቱ፣ ሕገ መንግሥቱ የዜጎችን ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲዊ መብቶችን ያስጠበቀ እንጂ ሕግን ሊያሻሽል ወይም ሊሽር የተደነገገ ሕግ ባለመሆኑ ክርክሩ የሕግ መሠረት ስለሌለው እንዳልተቀበለው አስታውቋል፡፡

ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) ቢሆንም፣ የዜጎች ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች ሳይጣሱ እንዲከበርላቸው ከመደንገግ ባለፈ፣ በዋስትና መብት ላይ ያለው ነገር ስለሌለ እሱንም እንዳልተቀበለው አሳውቋል፡፡

ተከሳሾቹ የተጠቀሰባቸው የሕግ አንቀጽ መነሻው አሥር ዓመታት ሆኖ መዳረሻው 20 ዓመታት ከመሆኑ አንፃር፣ በተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 25 ዓመታት በሚደርስ ፅኑ እስራት ሊያስቀጣቸው እንደሚችል ገልጾ፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክርክር በሚመለከት፣ ፍርድ ቤቱ ከክሱ አንፃር መመርመሩን ገልጿል፡፡

በክሱ ተሻሽሎ እንደቀረበው መቼና የት፣ እነ ማን የሚለው ተለቶ መቅረቡን ጠቆሞ፣ በተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት የ14 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱና ከ187 ሚሊዮን ብር በላይ የወደመ መሆኑ ስለተብራራ፣ የዓቃቤ ሕግ መከራከሪያ ሐሳብን የሚያሟላ ሆኖ እንዳገኘው አስረድቷል፡፡ በመሆኑም አንደኛው ክስ ደግሞ አራቱንም ተከሳሾች ማለት አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ሥዩምና ወ/ሮ አስካለ ደምሌን ስለሚመለከት፣ የዋስትና መብት ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉንና በማረሚያ ቤት ሆነው የክስ ሒደታቸውን እንዲከታተሉ ብይን መስጠቱን አስታውቋል፡፡

አቶ እስክንድር በሌሉበት ክስ ከተመሠረተባቸው አቶ አሸናፊ አወቀና አቶ ፍትዊ ገብረ መድኅን ጋር፣ በቅርቡ በሥራ ላይ የዋለውን የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 6(2) ድንጋጌን በመተላለፍ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም መሰናዳት ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው ቢሆንም፣ ዋስትና እንደማይከለክል ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ነገር ግን አቶ እስክንድር በመጀመርያው ክስ ማለትም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ እና ለ)፣ 35፣ 38 እና 240(1ለ) ድንጋጌን በመተላለፍ፣ አንዱ ወገን በሌላኛው ወገን ላይ የጦር መሣሪያ እንዲያነሳ ማነሳሳት ወንጀል ዋስትና ስለተከለከለ፣ በማረሚያ ቤት ሆኖ ክሱን እንዲከታተል በድጋሚ በመንገር ብይን ሰጥቷል፡፡

በክስ መዝገቡ የተካተተው አምስተኛ ተከሳሽ አቶ ጌትነት በቀለ፣ የተከሰሰበት የወንጀል ድርጊት ዋስትና እንደማይከለክለው በመግለጽ በ30,000 ብር ዋስ ከእስር እንዲፈታና ከአገር እንዳይወጣ ለኤምግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዕግድ እንዲጻፍ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቶ እንደጨረሰ አቶ እስክንድር ከማረሚያ ቤት እስረኞች አያያዝ ጋር በተያያዘ አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ‹‹ከዚህ የልብ ወለድ ክስ በነፃ የምንሰናበት ስለሆነ፣ በምርጫው እንድንሳተፍ ፍርዱ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ፍርድ ቤቱን እንጠይቃን፤›› በማለት ለምርጫ እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡

የሚጠብቃቸውና የሚፈልጋቸው ሕዝብ መኖሩን አስታውቆ፣ ፍርድ ቤቱ የተፋጠነ ፍትሕ እንዲሰጣቸው ጠይቋል፡፡ አቶ እስክንድር ከአንድ ሳምንት በፊት ለፍርድ ቤቱ በውጭ አገር የሚኖሩ ባለቤቱንና ልጁን በስልክ ለማነጋገር እንዲፈቀድለት ጠይቆ የተፈቀደለትና ትዕዛዝ የተሰጠ ቢሆንም፣ ማረሚያ ቤቱ ተግባራዊ ስላላደረገለት በድጋሚ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ይህ ትዕዛዝ የማይፈጸምለት ከሆነ የፍርድ ቤቱ ሒደት መልካም እንደማይሆንም ተናግሯል፡፡

በምርመራ ወቅት ከታሰረበት ፖሊስ ጣቢያ ወደ ማረሚያ ቤት ሲዛወር 20 መጻሕፍትና 30 መጽሔቶችን ማረሚያ ቤት አስተዳደር እንደተረከበውና ሳንሱር አድርጎ እንደሚሰጠው ቢነግረውም ሊሰጠው ስላልቻለ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል፡፡ በማረሚያ ቤት ተገኝተው ለነበሩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ቢያሳውቅ ምላሽ ስላላገኘ ፍርድ ቤቱ ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል፡፡

አቶ ስንታየሁ ደግሞ ባቀረበው አቤቱታ ለሁለት ወራት ፖሊስ ጣቢያ ሲታሰሩ በጨለማ ቤትና በቀዝቃዛ ቦታ መቆየታቸውን አስታውሶ፣ አሁን ደግሞ በማረሚያ ቤት ውስጥ ሌላው እስረኛ የሚያገኘውን አገልግሎት እየተከለከሉ በመሆኑ እንዲፈቀድላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን ሌሎች እንደሚያገኟቸው፣ እነሱም በስልክ ማግኘት እንዳለባቸው ጠይቋል፡፡ የተመሠረተባቸው ክስ የሐሰት እንደሆነም በመግለጽ ሕዝብ እንዲዳኛቸው ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ አቶ ስንታየሁን በማስቆም ‹‹ይኼ የፖለቲካ መድረክ አይደለም፡፡ በአግባቡና በሕጉ መታየት ያለባቸውን እናያለን፡፡ ሁሉንም ነገር ስታቀርቡ በሥነ ሥርዓቱና በሕጉ አግባብ ማቅረብ አለባችሁ፡፡ አንድ ሕዝብ ይዳኛል ማለት ምን ማለት ነው?›› በማለት በተገቢ ሁኔታ እንዲከራከሩ ተናግሯል፡፡ የተፋጠነ ዳኝነትና ፍትሕ የመስጠት የሕግም ሆነ የሞራል ግዴታ እንዳለበት የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ ፍርድ ቤት እስካሠራቸው ድረስ ማንኛውንም እስረኞችን የሚመለከተውን ጉዳይ እንደሚከታተል አሳውቋል፡፡

ዕንባ እየተናነቃት አቤቱታዋን ያቀረበችው ወ/ሮ ቀለብ ደግሞ፣ ‹‹ክስ ቀርቦብናል፡፡ አትናገሩ ማለት ደግሞ የመብት ጥሰት ነው፡፡ ለፍርድ ቤቱ መናገር ካልቻልን ለምን እንመጣለን? የእኔን እውነት ማን ይቀበለኝ? በሐሰት ተከስሻለሁ፡፡ ፍርድ ቤቱ ይስማኝ፣ በአገራችን በሐሰት የፖለቲካ ክስ ተከሰናል፤›› ስትል ፍርድ ቤቱ አስቁሟታል፡፡

ከሥነ ሥርዓት ውጪ መናገር ጥቅም እንደሌለውና ለውጥም እንደማያመጣ ፍርድ ቤቱ ጠቁሞ፣ ‹‹ክሱ ሐሰተኛ ነው ወይም አይደለም›› የሚለው ወደፊት የሚታይና በማስረጃ የሚረጋገጥ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የአገሪቱ ፍርድ ቤት እስከሆነ ድረስ ሊያከብሩት እንደሚገባም አሳስቧል፡፡ የክርክር ሒደቱ ሲያበቃ ነፃ ከሆኑ በነፃ የማይወጡበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ጠቁሞ፣ ሁሉንም ነገር በአግባቡና ሥነ ሥርዓታዊ በሆነ መንገድ መቀጠል እንደሚገባ አስታውቋል፡፡

ወ/ሮ አስካለ የተባለችው ተከሳሽ በበኩሏ ባቀረበችው አቤቱታ፣ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ሁሉንም እስረኛ እኩል እንዲያገለግልና እንዲያስተናግድ ጠይቃለች፡፡ ፀጉሯን ለመሠራት እንኳን እየተከለከለች መሆኑን ጠቁማ፣ የማረሚያ ቤትን ደንብና አሠራር ለእስረኛ ማሳወቅ ወይም መመርያ መለጠፍ ሲገባቸው፣ እሽግ ውኃ አይገባም ተብለው ለሁለት ቀናት ፆማቸውን ማደራቸውንም ተናግራለች፡፡ ቤተሰቦቿ ክፍለ አገር መሆናቸውንና እናቷ 365 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ሊጠይቋት ስለማይችሉ፣ ስልክ እንዲያስደውሏት ስትጠይቅ ‹‹መስመሩ ተበላሽቷል›› በማለት ሊያስደውሏት እንዳልቻሉ በመግለጽ፣ ‹‹እኔ የግፍ እስረኛ ነኝ፣ ሕዝብ ይወቅልኝ›› በማለት ብሶቷን አሰምታች፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን አቤቱታ አዳምጦ እንደጨረሰ በሰጠው ትዕዛዝ ችሎቱ በተቻለው ሁሉ ለክሱ ቶሎ እልባት ይሰጣል ብሏል፡፡ አቶ እስክንድር ከባለቤታቸውና ከልጃቸው ጋር በስልክ እንዲገናኙና ማረሚያ ቤቱ ፈጽሞ መቅረብ አለበት፡፡ ተከሳሾቹ በሃይማኖት አባት፣ በጠበቃቸው፣ በቤተሰቦቻቸውና በጓደኞቻቸው የመጎብኘት መብት እንዳላቸው፣ ማረሚያ ቤቱ ሕክምና እንዲያገኙ እንዲያደርግና ሁሉንም ዓይነት የሰብዓዊ መብቶቻቸውን ፈጽሞ እንዲቀርብ፣ እንዲሁም የአቶ እስክንድርን መጻሕፍት ሳንሱር አድርጎ ለምን እንዳልሰጠ በጽሑፍ እንዲያቀርብ ጥብቅ ትዕዛዞችን ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያቸውን መስከረም 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በሬጂስትራር በኩል እንዲያቀርቡና ዓቃቤ ሕግ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ተከሳሾች በቃል ከሚያደርጉት መቃወሚያ ክርክር ጋር ምላሽ መስጠት እንዲችል፣ በዕለቱ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡ በሌሉበት የተከሰሱትን አቶ አሸናፊ አወቀንና አቶ ፍትዊ ገብረ መድኅንን ፌዴራል ፖሊስ በምርመራ ባጣራበት አድራሻ አፈላልጎ እንዲያቀርብም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡           

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...