አሜሪካ ለኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ግምታቸው 2.9 ሚሊዮን ዶላር የሆነ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችና የሥልጠና ቁሳቁሶች አበረከተች፡፡ በኢትዮጵያ የአሜሪካን ኤምባሲ ማክሰኞ መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ዕርዳታውን ያበረከተው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ነው፡፡ የዕርዳታው ዓላማም የአገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ ሶማሊያ ውስጥ የሚገኘውን የአልሸባብንና የሌሎች አሸባሪ ኃይሎችን ጥቃት ለማክሸፍ የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ መሆኑን ኤምባሲው በመግለጫው አመልክቷል፡፡ በዚህም መሠረት ላንድክሩዘሮች፣ የሠራዊት ማጓጓዣ ካሚዮኖች፣ አምቡላንሶች፣ የጭነትና የነዳጅ ተሽከርካሪዎች፣ የውኃ ታንከሮች፣ ለዘመቻ ማዕከል የሚያገለግሉ ኮምፒዩተሮችና የምሽት መመልከቻ መሣሪያዎች የአሜሪካ ፀረ ሽብርተኝነት አጋር ለሆነው የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ድጋፍ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡ አሜሪካና ኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት ሰላም ለማስከበርና ሽብርተኝነትን ለመከላከል አጋር ከመሆናቸውም በላይ፣ የጋራ ወታደራዊ ሥልጠና እንደሚያካሂዱም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት በቅርቡ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን የመጀመሪያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌት በማከናወኗ ምክንያት፣ ለተለያዩ ዘርፎች የሚውል ውስን ዕርዳታ ማቋረጡ ይታወሳል፡፡ በምሥሉ ላይ የሚታዩት የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ለአገር መከላከያ ሚኒስቴር ያበረከታቸው ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ ፎቶ፡- በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ