Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአብረን ነንና. . . አትለያዩን!

አብረን ነንና. . . አትለያዩን!

ቀን:

በሪያድ አብዱል ወኪል

እንደ መግቢያና መግባቢያ. . .

የኢትዮጵያ ሬዲዮ “ቅዳሜን ከእኛ ጋር” እና የእሑድ ማለዳ የመዝናኛ መሰናዶዎች በጉጉት ይጠበቁ በነበረበት አንድ ወቅት፣ ተወዳጁና ትሁቱ ድምፃዊ ንዋይ ደበበ በእንግድነት ተጋብዞ ከመርሐ ግብሩ አዘጋጆች ጋር ስለሥራዎቹና የሕይወት ገጠመኞቹ ተጨዋውቶ ነበር፡፡ በዚህ ጭውውት ላይም “አገሬን አልረሳም!” ስለሚለው ድንቅ ሙዚቃውና የሙዚቃ ግጥሙ ውልደት ሲተርክ ማድመጤን አስታውሳለሁ፡፡

ድምፃዊው የክርስትና እምነት ተከታይ ባለቤቱ ደግሞ ከሙስሊም ቤተሰብ መሆኗን አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያችን ሁለቱ እምነቶች በአንድ አብሮ ኑሮ ባሻገር እንዲህ ተጋምደው የሚኖሩባት አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያውያኑም ከአንዋርና ከራጉኤልም ሆነ፣ ከሩፋኤልና ከሼህ ሆጀሌ ተቋማዊ ጉርብትና ባለፈ፣ በኅብረተሰባዊው አኗኗርም ከሺሕ ለዘለጉ ዓመታት አብረን የምንኖር ነን፡፡ ከላይ የጠቀስኩላችሁ የንዋይ “አገሬን አልረሳም!” የሙዚቃ ግጥም ተሠርቶ ዜማው በመሄድ ላይ እያለ የአርቲስቱ ባለቤት፣ ‹‹ምነው አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማቱን ሁሉ ስትዘረዝር አንድ መስጂድ እንኳን. . .?!›› ብላ ታስታውሰውና በግጥሙ ውስጥ ያቺ አንዲት ቃል እንድትካተት ይደረጋል፡፡ ቃሏም የዘፈኑን ሙሉ ታሪክና ምሰላ ብቻ ሳይሆን አቀባበሉንም የቀየረች ሆነች፡፡

‹‹የዜማ የቅኔ – የቀሳውስት አገር

የቅዱስ ገዳማት – የታቦታት ደብር፣

ፋሲለደስ አክሱም – የታሪክ መዘክር

መስቀል ጽላታችን – የእምነታችን ሚስጥር፣

ገዳማት መስጊዱ – ሐውልታችን ሳይቀር

አገሬ ሰው አረ እንዴት ነው – አገሬ አፈሩ አረ እንዴት ነው?

አገሬ ወንዙ አረ እንዴት ነው – ወፉ አራዊቱ አረ እንዴት ነው?››

አርቲስቱ “ወገኔን አልረሳም!” ቢልም ከወገኖቹ ግማሽ ቁጥር የሚይዙትን ሙስሊሞችንና የእነዚሁ ወገኖች አካል የሆነች ውድ ባለቤቱ ቤትና ፊትለፊቱ አስቀምጦ ረስቷት ነበር፣ “አገሬን አልረሳም!” ቢልም የአገሩና የአገራችን ነባራዊ እውነትና መለያ የሆነውን የቀለማት ኅብራዊነት ዘንግቶ ነበር፡፡ ጥሩ ነገሩ ንዋይ ልበ ቀና ነውና ከታሪካዊ ስህተት ድኗል “አገሬን አልረሳም!”ም በሁላችንም አንደበት እኩል ተወድዶ መዘፈን ብቻ ሳይሆን፣ በታላቅ ክብር የሚዘመር አገራዊ ዜማ ለመሆን በቅቷል፡፡ ከላይ ያሰመርኩባት “መስጊዱ” የምትለው አንዲት ቃል ከግጥሙ ውጪ ሆና ቢሆን ብላችሁ አስቡና ቃሏን በመግደፍ ግጥሙን አንብባችሁ ገፅታና ፍርዱን ለህሊናችሁ ስጡ፡፡

ግን ለምን? ፖለቲከኞቻችንን እጠይቃለሁ!

ይህ ጥያቄ አብሮኝ የቆየና በተለያዩ አጋጣሚዎችና የኅትመት ብዙኃን መገናኛዎቻችን በኩል የማነሳው ቢሆንም ከሪፖርተር ጋዜጣ የመስከረም ወር ቀዳሚ ዕትም ያነበብኩት የችሎት ዘገባ ነው፣ ለዚህች ማስታወሻ ጽሕፈት አሁናዊ ምክንያት የሆነው፡፡ ዘገባው የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) የበላይ ኃላፊ የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በሌሎች ስድስት አመራሮችና አባላት ላይ ለሽብር መሰናዳትን ጨምሮ፣ “ከመንግሥት ሥልጣን” ጋር በተያያዙ ክሶች እንደ ተመሠረቱባቸው አነበብኩ፡፡

ከሳምንታት በፊት እዚሁ ጋዜጣ ላይ እንደገለጽኩት የለውጥ እንቅስቃሴው በለውጥ ቀልባሽና አስመሳይ ሥልጣን ወዳዶች እጅ ገብቷልና ክሶቹም ሆኑ ክሶቹ ይፋ የተደረጉባቸው ጊዜዎች ከአሻጥር ያለፈ አያሳምኑኝም፡፡ አሁን ባለው የፖለቲካ ዓውድና ጉዳዩም በፍርድ ቤት የተያዘ በመሆኑ ዝርዝሩ ይቆይ፡፡ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጭብጥ ውስጥ ብሔርና ሃይማኖቶችን ለማጋጨት ሠርተዋል ሲል ሲል ምርጫ ቦርድ በሕጋዊ መንገድና በመሥፈርቱ መሠረት ገምግሞ የሰጣቸውን ዕውቅናም ወንጀል ያደረገ መምሰሉ ለጊዜው ይቆየን፡፡

በዘገባው እንደተገለጸው ‹‹በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ውስጥየኦሮሞና ትግራይ ተወላጆች እንዳይካተቱ፣ የእስልምና እምነት ተከታዮች በተቻለ መጠን እንዳይኖሩ ወይም የእስልምና እምነት ተከታዮች ከተካተቱም ተፅዕኖ መፍጠር የማይችሉ መሆን እንዳለባቸው’ በመወሰን፣ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ያገለለ እንዳይመስል ፓርቲው በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ የሚሳተፉ ሙስሊሞችን ፎቶ ጎላ አድርገው በማንሳት በማኅበራዊ ሚዲያ ያሠራጩ. . .›› እንደነበር ገልጿል፡፡ ነጥቤ ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡ የተጠቀሱትና ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች፣ እንዲሁም የሃይማኖት ተከታዮችን በእጅጉ ያሳዘኑ ንግግሮች “ታላላቅ” ከሚባሉ ፖለቲከኞቻችን ሳይቀር በተደጋጋሚና ከአደባባይ ተሰምተዋል፡፡

ይልቁንም “የአንድነት ኃይል” ነኝ በሚለው ሃሳዊ የአንድነት ጎራ ውስጥ የሚሠለፉት እንዲህ ያሉት ፖለቲከኞቻችን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚረዱበትን መንገድ ለመከለስ (Re-branding) አለመፈለግ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችንም ተጭነው ለመያዝ ይታገሉ፡፡ በዚህ ረገድ ባልደራሱ የተለየ ኃጢያት ይሸከማል ብዬ አላምንም፡፡ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ብያኔ ላይ ከስድሳ ዓመታት በኋላም ካልተስማማንና መግባባት ካቃተን ንግግሮቻችንን ሁሉ የእምቧይ ካብ ነበሩ ማለት ይሆን? ከያኒው “ለካ አልተደማመጥንም!” ማለቱ ይህንን ይመስለኛል፡፡

ከኢሕአዴግነት ወደ ብልፅግናነት ቆዳና ኢኮኖሚያዊ ርዕዮቱን ከቀየረው ስብስብ አንስቶ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ይበልጥ መሠረቴ ነው ለሚሉት ወገን መሟገታቸውና በግላጭም ባይሆን መሥራታቸው እንግዳ ወንጀልነቱ አይታየንም፡፡ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ስለብልፅግናው ፍጥረትና አገነባብ ከነገሩን መንፈቅም አልሆነውም፡፡ ዋናው ቁም ነገር የፖለቲካ ድርጅቶች ውግንናና አሠላለፍ ሳይሆን የአገረ መንግሥቱ አገነባብና ከትናንት እስከ ዛሬ በነበሩ፣ ባሉና በሚኖሩ የጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተነጋግሮ በመግባባት ለአድሏዊነት የማይመች ሥርዓትን መገንባቱ ነው፡፡

የባልደራስ ሰዎችም ሆኑ ሃይማኖታዊ ምልከታና ውግንናቸውን ወደ ፖለቲካው ጎራ የሚደባልቁ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰብ ፖለቲከኞች ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በገዛ አገሩ ጉዳዮች ላይ እንኳ ከአቻ ክርስቲያንና የሌሎች እምነት ወንድሞቹ ጋ ሚናውን እንዳይወጣ ብቻ ሳይሆን፣ ተሸማቅቆ እንዲኖር ፈልገዋል፡፡ ብሎም የኢትዮጵያዊነት በያኝና ዜግነት ሰጪ መሆናቸውንም ወደውታል፡፡ ይኼ በራሱ ወንጀል አይደም፡፡ ኅብረተሰቡም ዛሬ ሳይሆን ገና ድሮ ያውቃቸዋልና በእንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ምክንያትነት ከወገኖቹ ጋ የሚገባበት ግጭት አይኖርም፡፡

ይልቁንስ ጥያቄው መሆን ያለበት በሕገ መንግሥታችን አሥራ አንደኛው አንቀጽ ሥር ተጽፎ የምናገኘውና ከዚሁ ሕግ ስድስት ዓብይ መርሆዎች አንዱ ሆኖ ተግባራዊነት ግን የራቀው የመንግሥታዊ ሥርዓትና ሃይማኖቶች ልይይት (Secularism) ጉዳይ ላይ የመንግሥትን ሥልጣን የያዘው አካል ራሱ ምን ያህል እየሠራበት ነው የሚለው ይመስለኛል፡፡ ዛሬስ መንግሥትና ሃይማኖት ምን ያህል በሥራ ተራርቀዋል፣ ከሕዝብ ትራንስፖርቶችና አደባባዮች ጀምሮ አገልግሎት ሰጪዎዎቹ ተቋማትስ?! እዚህ ብጠቅሳቸው በብዙ ሊያቀያይሙን የሚችሉ ግድፈቶችን የማየው ከመንግሥትና ከራሱ ዲፕሎማሲያዊ ሠፈር እንጂ፣ ሐሳባቸውን የማስፈጸም አቅም ካልተሰጣቸው ተቃዋሚዎች አይደለም፡፡ ከአገረ አሜሪካ መሥራች አባቶች አንዱ የሆኑት ቶማስ ጃፈርሰን “A Wall of Separation” ሊበጅለት እንደሚገባ የተናገሩለት የሃይማኖትና መንግሥታዊ አሠራር ተዛንቆ በተቻለ መጠን መሠረቱ ሊጠብቅ ይገባል፡፡

ግን ለምን? መገናኛ ብዙኃኑንም እሞግታለሁ!

የኢትዮጵያችን ብዙኃን መገናኛዎችና የሙስሊሞች ቀዳሚ ግንኙነት በጥሩ ምልከታ የተቃኘ አልነበረም፡፡ በሥርዓተ መንግሥቱ አድሏዊነት ሳቢያ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ሙስሊሞች›› ማለታቸው ይቅርታ እንደማያስነፍጋቸው ይሰማኛል፡፡ ችግሩ ሥርዓታዊ ስለነበርና ግለሰባዊ ስላልሆነ፡፡ ያ ክፉ ሥርዓት በሕዝቦች ትግል ተቀብሯል፡፡ ይህ ማለት ግን ምልሰቱን የሚፈልጉና በኅትመቶቻቸው ይህንኑ ደግመው ያስነበቡን የሉም ማለት አይደለም፡፡ ደርግ ከላይ ለጠቀስኩት “ግድግዳ” መሠረት ቢያስይዝም ኢሕአዴግ ለተግባራዊነቱ ሰንፎና መጠቀሚያነቱንም ሞክሮ ወድቋል፡፡ አለመታደል ሆኖ ሁለተኛው የኢሕአዴግ ትውልድ ክፉ ትምህርቱን ወርሷልና ብዙኃን መገናኛዎቹን በዚያው ጎዳና እያስኬዳቸው ይመስላል፡፡

የብዙኃን መገናኛዎቹ ዘገባዎችና ፍርኃታቸው የሚመነጨው ካለማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ የመንግሥታቸው አቋም ላይ እርግጠኛ ካለመሆንም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመንግሥት የኅትመት መገናኛ ብዙኃን ድርጅት ሆኖ ከተመሠረተ ሰማንያ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በአማርኛ ቋንቋና በዕለታዊነት ከሚታተመው የዕድሜ አንጋፋውአዲስ ዘመን” ጋዜጣና በየሁለት ወሩ ከሚከሰተው “ዘመን” መጽሔት በተጨማሪ፣ የተለያዩ ቋንቋዎች ኅትመቶችም አሉት፡፡ ድርጅቱ ከሳምንታት በፊት ባስነበበው ከሙያ የተጣላና ‹‹የእምነቱን ከፍተኛ አባቶች›› ምንጭ አድርጌያለሁ ባለው “ዘገባ” ‹‹ግብፅ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ከጎኗ ለማሠለፍ የምታደርገው ጥረት ከእምነቱ አስተምህሮ ውጪ መሆኑ ተገለጸ!›› ብሎ ነበር፡፡

የሙስሊም ስሜዎችን እንኳን አስተካክለው ለመጥራትና ለመጻፍ ሲቸገሩ በአግራሞት ከምታዘባቸው “የብዙኃን” መገናኛዎቻችን እንዲህ ያሉ ዘገባዎችን ማንበብ፣ አልያም ማድመጥ እንግዳዬ አይደለም፡፡ በተለይም ከ“ድምፃችን ይሰማ!” የመብት ማስከበር እንቅስቃሴ በኋላ ሆነኝ ብለው ስያሜና መረጃዎችን የሚያሳስቱ ዛሬም የኅትመት ዘርፉ ላይ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ይኼ ዘገባ ግን ታላቁን የህዳሴ ግድብ የሙስሊሞችም ያይደለና ሙስሊሞቹም ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ይመስል፣ ስለልማቱ ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጠ ሆኖ በርካቶችን አሰዝኗል፡፡ ስህተቱ ታምኖም ይቅርታ የተጠየቀበት አይመስለኝም አልተለመደማ!

ኢትዮጵያ በቅርቡ የብዙኃን መገናኛዎች ፖሊሲን አስተዋውቃለች፡፡ የፖሊሲውን የመጨረሻ ቅጂ እንጂ ከፅድቀቱ በኋላ የወጣውን ሰነድ አግኝቼ ባልመለከተውም፣ ኢትዮጵያን እንዲመስሉ  ለመሥራት ሲተለም ሃይማኖታዊ ብዝኃነታችን ተገድፏልና ከአጀንዳ መረጣ ጀምሮ የእስካሁኑን ሒደት እንዳያስቀጥል ያሠጋል፡፡ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊያት ሁሉ እንጂ የአንድና ሁለት ብሔሮችና ሁለት ሃይማኖቶች አለመሆኑን ደጋግሞ መንገሩም ያሰለቻል፡፡

ከላይ ‹‹በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ውስጥየኦሮሞና ትግራይ ተወላጆች’ እንዳይካተቱ›› የተባለው ፖለቲካዊ ነፀብራቅ በብዙኃን መገናኛዎች ዘገባ ላይም ታይቷል፡፡ ብዝኃነታችንን ተቀብሎ ይህችኑ የብዝኃነት አገር የሚመስሉ የብዙኃን መገናኛዎች ሳናዘጋጅ፣ አሁን እንደታሰበው ብሔርና ክልል ተኮር መገናኛ ብዙኃንን “መዝጋት አለብን!” ማለቱ በራሱ ከጨፍላቂ አስተሳሰብ ያለመውጣት ፍላጎት ይሆናል፡፡

ግን ለምን? በጠቢባኑ እገረማለሁ!

ኢትዮጵያችን የተናጠልና የጋራ ማንነት ያላቸው ሕዝቦች መኖሪያ ነች፡፡ እንደየትኛውም አገር በጠቢቡና ከያኒዎቿ በኩል በተለያዩ ምሰላዎች ገጽታዋ ይሠራል፡፡ ልዩነቶችን ተሸጋሪ “የጋራ እሴቶች” ተበጅተውም አገራዊ አንድነቱ ይጠናከርባቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ከሰሞኑ የብር ኖቶች ኅትመት ላይ እንዳስተዋልነው “ጥበብ” ጉልበቷ ብዙ ነው፡፡ ከኢትዮጵያችን ጠቢባን የተወሰኑቱ ግን እንደ ፖለቲከኞቹ ሁሉ ይህንን ጉልበት ለጋራ አገራዊነት አይጠቀሙበትም፡፡

“The Style is The Man!” እንዲሉ የሥነ ጽሑፉ ዘርፍ መቅድማችን ጅማሮውን ያደረገበት ጦቢያ ወይም በሌላ አጠራሩ ልብ ወለድ ታሪክ፣ “እኛና እነሱ” በሚል የአረማዊና ክርስቲያን ከፋፋይ ውገና ሲሆን ይኼ ተምሳሌትና “ውክልና” ዛሬም ድልድዩን ያልሰበረባቸውና ሐሳቡን ያልቀየረባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ አዳዲስ የጋራ እሴቶች ሳይፈጠሩ መቅረታቸውና የተፈጠሩትንም ለማጠናከር ባለመቻሉ የቀደሙትን መገፋቶች በየዘርፉ ለመመለስ ጥረቶች አሉ፡፡

ለዚህ ማስታወሻ መነሻ የሆነው የክስ ጉዳይ በፖለቲካው መስክ ማሳያ ይሁነን እንጂ፣ ለብዝኃነታችን ስሱ ልብ ከነበረው ጋሽ ስብሃት ለአብ ገብረ እግዚአብሔርና ከሌሎች ቀዳምያን ጥቂቶች በቀር የታሪካችንን አተራረክ ትተነው እንኳ፣ የማኅበረሰብ ሥዕላቸውና የአገር ምሰላቸው ላይ ችግሮች ይበረክቱባቸዋል፡፡ ያልታተሙ ቢሆኑም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እነዚን ጉዳዮች ርዕሳቸው ያደረጉ ጥናቶች እንዳሉም አውቃለሁ፡፡ ከቅርቦቹ የድኅረ ዘመናውያን ፈለጎች አዳም ረታና አለማየሁ ገላጋይ በውክልናና እኩል መቆርቆር ረገድ የታሻሉ ይመስሉኛል፡፡

ወደ ፊልሙ ዘርፍ ስንሻገር በሆሊውድ የአዲሱ ዘመን ፊልሞች ታሪክ ውስጥ የምንጊዜም ምርጥ ዳይሬክተር የሚባልለት ማርቲን ስኮርስ ስለፊልም ምንነት ሲገልጽ፣ “Cinema is a matter of what is in the frame and what is out.” የሚል ብያኔን ሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህ ድፍየና መሠረት ከፊልሞቻችን የጥቂቶቹን ጭብጥ በጋሽ ፈቃደ አዘዘ (ዶ/ር) አተረጓጎም በብድግ ብድግ (Randomly) ወስደን ብንገመግም፣ ፍሬሙ ውስጥ ያለውንና እንዳይኖር የሚፈለገውን ማኅበረሰብ የሚገልጽልንን ምሥል እናገኛለን፡፡

ሰው ልጆች ምናብ በዲጂታል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎች መሣሪያነትና ሉላዊነትን መርሁ ባደረገው ነባራዊ ዓለም ዕገዛ ሐሳብና እሱነቱን መግለጽ ብቻ ሳይሆን፣ ይህንኑ ወደ እውነታ ቀይሮና ምድር አውርዶ ሊኖረው መትጋት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ቴዎድሮስ ተሸመ የክፉና ደጉን አብሮነታችንን በተለያዩ ፊልሞቹ በመቅረፁ ረገድ የተሳካለት ነው ብዬ ብጽፍ አልሳሳትም፡፡ ለዚህም ባለበት ምሥጋና ይድረሰው፡፡ ታምሩ ብርሃኑም እንዲሁ፡፡ ፊልም በምሥል አማካይነት ማለት የፈለገውን ይላል፣ በተምሳሌቶቹም መልዕክቱን ያስተላልፋል ይባላልና፡፡

ሰው አሳቢ ፍጡር ነው፡፡ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነታችን በተለያዩ ማኅበራዊ የሕግና የክልከላ ጥላ ሥር መጋረዱ የፈጠራ ብቃትን የሚቀንስ ስለመሆኑ ቢታመንም፣ የሰው ልጆች ሐሳባቸውን ወደ ሌሎች ከሚያስተጋቡባቸው “ጥበባዊ ሥራዎች” ዘመነኛው የሲኒማ ጥበብ ፊልመኞቹ ሐሳባቸውን ከየትም ሳይሆን፣ ከማኅበረሰቡና ከዙሪያቸው ነው የሚቀዱት ይለናል፡፡ ድርሰቱ ላይ ነብስ የሚዘራውና በኢትዮጵያችን የፊልም ሥራ ውስጥ ዕውቅናና መጠሪያውን የምንሰጠው ዳይሬክተርም ሆነ የፊልሙ ደራሲና ጽሑፍ ነዳፊ የሆነው ግለሰብ፣ አንድ ዓይነት የኑሮና አኗኗር ሁኔታ ውስጥ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል በጣም ጠባብ ነውና “አንድ ዓይነት” መረዳቶችን ካልፈጠሩ በቀር ሊኖራቸው አይችልም፡፡

ሥርዓተ ማኅበራችንና እነሱ!

ፊልመኞቻችን ማኅበረሰቡ እንዴት እየኖረ እንደሆነ አንድም ግንዛቤው የላቸውም፣ አልያም በጋራ በፈጠሩት መረዳት ይህንን ዓይነቱን ኑረት ሆነኝ ብለው ይገድፉታል፡፡ ኪነት የአመለካከት አድማስን በማስፋት ማኅበረሰባዊ አጀንዳን የመቅረፅና ይህንኑ አጀንዳ የመምራት ሚና እንደሚኖረው እሙን ነው፡፡ ፊልሞቻችንም ኪነትን ለኪነታዊ እርካታዋ ብቻ (Art for arts sake and self-expression) እንዲውል አልመው ቢነሱ እንኳን አሻራ ይተዋሉ፡፡ ወፍ እንዳገሯ ትጮሃለች፣ ሰውም አካባቢውን ይመስላል:: ፊልሞቻችንና ፊልመኞቻችንስ?! በአንድ የራዲዮ ድራማ ላይ በዓረብኛ የተጻፈበትን ምርት ለመግለጽ “እስላምና ተጽፎበታል” ስትል እንደሰማኋት ተዋናይት የማያውቁትን ማኅበረሰብ ሊገልጹት አይቻልም፡፡

ዓለማዊነታቸው እስኪያጠራጥር ድረስ ሃይማኖታዊ ትርክቶችንና ተናጠላዊ ገጽታዎችን የሚደጋግሙ ፊልሞች በርካታ ናቸው፡፡ ለምን ይሆን ሁልጊዜ እዚያው ላይ የሚዞሩት? ስላልተለመደ? እንደዚያ ብቻ እንዲያስቡ ሆነው ስለተቀረፁ? እውነታው ያ ስለሆነና በዚያ ሁኔታ ውስጥ ስለታጠሩ ወይስ ሌላ? ምናልባት ሙያዊ ትንተናን ይፈልግ ይሆናል፡፡ መምህር ወሰንየለህ ጥላሁን “የፊልም ጥበብ ቅኝት” ብሎ ወደ አማርኛ የመለሰውን “The Art of Watching Films” መነሻ በማድረግ፣ ‹‹አብዛኞቹ የአገራችን ፊልሞች ገፀ ባህሪ ተኮር እንደ መሆናቸው የሚፈልጉትን ነገር አጉልተው ለማሳየትና ለማንፀሪያነት ወይም የተመልካቹን ሰብዕና በዚያ መንገድ ለመቅረፅ ይጠቀሙበታል፤›› በማለት ገፀ ባህሪ ደግሞ አካባቢውን ነው መምሰል ያለበት ይለናል፡፡

ማኅበራዊ ችግር አንዱ የፊልም ማዕከላዊ መልዕክት የሚተላለፍበት ቢሆንም በዘርፉ ያለመታደላችንን በመጠቆም በፊልም ውስጥ ተግባቦታችን በምሳሌ የታጀበና መልዕክቶችም የሚተላለፉት በተምሳሌት መሆኑን ሲገልጽ፣ ‹‹ለምሳሌ እንደ ሰንደቅ ዓላማና መስቀል ያሉ ነገሮች ከተመልካቹ ስሜቶችና እሴቶች ጋር ከፍተኛና ረቂቅ ጥምረቶች ያሏቸው ናቸው፡፡ የተመልካቹ ምላሽ በተምሳሌቱ ለተወከለው ሐሳብ ካለው አመለካከት ጋር ትስስር ይኖረዋል፡፡ ችግሩ ከተመሳሳይ ባህል የመጡ ሰዎች ብቻ ናቸው አጠቃላይ ሐሳብና መልዕክቱን ሊረዱ የሚችሉት፤›› በማለት በዚህ ረገድ አራት ዋና ዋና ተምሳሌት የመፍጠሪያ መንገዶች ቢኖሩም፣ በአገራችን የተለመደው ግን ለነገሩ ትኩረትና ዋጋ ሰጥቶ ያንኑ መደጋገም ነው ይለናል፡፡

በሌላ በኩል ፊልም ሠሪዎቹ ራሳቸው ተምሳሌቶችን ሲፈጥሩም፣ ‹‹ተራኪው ነገሮች ተምሳሌታዊ ትርጉም እንዲሸከሙ ሲያደርግ ጣምራ ግቦች ይኖሩታል፡፡ አንደኛው ዓላማ ተምሳሌት የሆነውን ነገር የሚፈጥረውን ትርጉም፣ ስሜትና ሐሳብ ማስፋፋት ሲሆን ሁለተኛው ዓላማ የተጠቀመው ነገር እንደ ተምሳሌት አገልግሎት ላይ መዋሉን ግልጽ ማድረግ መቻል ነው፤›› በማለት የችግሩን ምንጭ በገደምዳሜ ይጠቁመናል፡፡ ኢትዮጵያውያን የሺሕ ዓመታት አብሮነታችንን ለማሳየት የግድ ከሆነ ከዓረብ አገር ፈንጂ በላፕቶፕ መልክ ወደ አገር ሲገባ ማሳየት ላይኖርብን ይችላል፡፡

በእርግጥ ፊልሞቹ በፖሊሲ ለመመራት ገና የሁለት ዓመት ዕድሜም ነውና በዘርፉ ከአኅጉራችን ቀዳሚዎቹ ሆነንም እዚያው ዳዴው ላይ ነን፡፡ ኢትዮጵያውያን እነዚህን ሁሉ ዘመናት አብረን በአንድ ኖረናል፡፡ በፊልሞቻቸው የኅብራዊነት ቀለማት በሚያስቀኑት እንደ ህንድና ናይጄሪያ እንኳን ሠፈር ለይተን አልሠፈርንም፡፡ ክልል ለይተንም አንኖርም፡፡ ይልቁንም በንዋይ ደበበ ቤተሰብ እንዳስመለከትኳችሁ ተጋብተንም ተዋልደናልም፡፡ ኢትዮጵያውያን አንድና ተመሳሳይ ትምህርት ቤት ውስጥ በአንድና ተመሳሳይ ትምህርት፣ በአንድ ዓይነት መለዮና በአንድ ክፍል ውስጥ ነው የምንማረውም የተማርነውም፡፡ በሥራውም ዓለም ቢሆን ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በግፊት የገባበት ንግድ ላይ ቢበዛም አብረን ነን፡፡ ማኅበረሰባችን በለቅሶው፣ በሠርጉ፣ በዕድርና በዕቁቡ አንድ ላይ ነው ሚኖረው፡፡ በማኅበራዊ ሕይወቱ አብረን ስለመሆናችን እንዲረሳና በጋራ እየተኖረ በገደምዳሜ ብቻ መጠቀሱ እንግዳ ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ይህንን እውነታ ወደ ጎን የገፋነውና የጥበብ ሥራዎቻችንም የዘነጉት? ይህንን ስል ግን ሙስሊሞችም የሆኑትን ሆነው እንዲሳሉ እንጂ በሌላ እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡

በሌላ በኩል እዚሁ ኅብረተሰብ ውስጥ እያለ እንደሌለ መቆጠሩ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ባለበት ቦታ ላይም ቢሆን የማይኖረውን ሕይወት እንደሚኖረው ማስመሰልና የተሳሳተ ገጽታ መስጠትም አለ፡፡ በእርግጥ የችግሩ አንዱ አካል እንጂ ሁሉም አይደለም ብዬ የማምን ቢሆንም ከያንያኑ በአንድ ቤተ እምነት ውስጥ የጀመሩትን ሃይማኖትን የማጉላት ነገር ሌላውን ገጽታ እንዳያዩ ቢያዩም፣ እንዲገድፉት የማድረግ ተፅዕኖ እንደፈጠረ ይሰማኛል፡፡ ይህ ማለት ግን ሃይማኖተኛ አይሁኑ ለማለት ሳይሆን ሌላውንም የሕዝብ አካል ከአገራዊ ጉዳይ አታጉድሉት ነው፡፡ በሐሳብ ጥንካሬያቸው ከገነኑ ፊልሞቻችን አንዱ በሆነውና ሰኔ 30 በተሰኘው ፊልም ውስጥ ባገኘሁት ኃይለ ቃል ማስታወሻዬን ለማሳረግ ወደድኩ፡፡ ‹‹ማኅበረሰቡን ለመዳኘት በቅድሚያ ማኅበረሰቡንና ራስን ማወቅ ይገባል!›› ፊልሞቻችን ኢትዮጵያዊውን ኅብረተሰብ አትመስሉምና እኛን ምሰሉ፡፡

-ሰላም ለእናንተ ይሁን!-

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...