በዋካንዳ ኢትዮጵያ
“ዳኛው ማነው?” የተሰኘውን በአምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤል የተጻፈውን መጽሐፍ አንብቤ ስጨርስ እርሳቸው የጠየቁትን ጥያቄ ለመመለስ ሳወጣና ሳወርድ በመጽሐፋቸው ውስጥ ብዙ “ዳኞችን” አየሁ:: ጉልበት፣ ጠብመንጃ፣ ባለጊዜ፣አድር ባይነትና ርዕዮተ ዓለም በአንድ ወገን ሆነው ያሻቸውን ፍርድ ሲሰጡ፣ እንደ ኩራዝ ብርሃን ጭል ጭል የምትል በጎ ህሊና ደግሞ ግራ ቀኙን በመመልከት ዕፁብ ድንቅ የሚያስብል ዳኝነትን ስትሰጥ ትታያለች፡፡ አምባሳደር ታደለችም ይህችን በጎ ህሊና ሲያዩ “እንዴት ሊሆን ቻለ?” በማለት አግራሞትና ጥያቄ እንደ ፈጠረባቸው ተገንዝቤያለሁ፡፡ እኔ እንደገባኝ የእርሳቸው የ“ዳኛው ማነው?” ጥያቄ በመግቢያው ላይ የፍትሕ፣ በመውጫው ላይ ደግሞ የታሪክ ዳኝነትን ነው::
ዳኛ ግራ ቀኙን በመመልከት መበየን እንዲችል መሃል ላይ ያለሰው ወይም ተቋም ነው:: መሀል ላይ ያለ ሰው ወይም ተቋም ሚዛናዊ፣ መረጃዎችን መሰብሰብ፣ማጥለል፣ ማገናዘብና መተንተን የሚችል፣ በመረጃና በማስረጃ ላይ ተንተርሶ ብይን የሚሰጥ ነው፡፡ ነገር ግን በአገራችን የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ መሃል መሆን ተወዳጅ አይደለም፡፡ በደርግ ዘመን “መሀል ሰፋሪዎች ሚናችሁን ለዩ!” በማለት መሀል ላይ የቆመ ዳኛ እንዳይኖር ተደርጓል፡፡ ይህ በጊዜው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ ባህሪ እንጂ የደርግ ብቸኛ ጠባይ አልነበረም፡፡ ስለዚህ መሀል ላይ የነበሩ ልክ “ከወንድሞቿ በላይ ከፍ እንዳለች ማሽላ ወይ ለወፍ አለበለዚያ ለወንጭፍ” እንደሚባለው ለአንዱ ሲሳይ ሆነዋል፡፡ በኢሕአዴግ ዘመንም ቢሆን መሀል የሚባል የለም:: አንድ ሰው በቅንነት ለአገርና ለወገን ይጠቅማል ብሎ የሚናገረውን ሐሳብ የእነ እገሌ ሐሳብ ነው በማለት ይፈረጃል:: ምንም ዕውቀት ቢኖረው እንዲህ ዓይነት ሰው ለከፍተኛ ኃላፊነት አይፈለግም፡፡
የአንድ ጎልማሳ ሰውን ዕድሜ ያህል፣ በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ጭል ጭል ከምትለዋ በጎ ህሊና በስተቀር ተቋሟዊ የሆነ እውነተኛ ዳኛ አለ ለማለት ያስቸግራል:: ይህ ልምምድ ለሃምሳ ዓመታት እንደ ሸረሪት ድር አዕምሯችንን ተብትቦ ስለያዘው፣ ዳኝነትን የምናየው ከራሳችን አቋም አንፃር ብቻ ነው:: ስለዚህ በዳይና ተበዳይን በትክክል ለመለየት አልተቻለም:፡፡ ባለጊዜ የወደቀውን ጥፋተኛ ያደርጋል፡፡ እርሱ ሲወድቅ ደግሞ በሌላ ባለጊዜ ጥፋተኛ ይባላል፡፡ ያ በመጀመሪያ ጥፋተኛ የተባለው ደግሞ ከወደቀበት አንሰራርቶ እኔ ጥፋተኛ አልነበርኩም ይላል:: እንዲህ እንዲህ እያለ እስከ ዛሬ ደርሰናል:: በታሪክም ሆነ በትርክት መግባባትና መስማማት አዳጋች ሆኗል:: መወገን እንጂ መሀል ላይ ቆሞ እንደ ባለ አዕምሮ ማሰብ እንደ ክፉ ነገር ተወስዷል::
ከእውነተኛ ዳኝነት ይልቅ “ሕጋዊነትንና ሕገወጥነትን” ቀላቅሎ መሄድ እንደ ትክክለኛ የትግል አቅጣጫ ይታያል:: ከዚህም የተነሳ ዳኝነትን የሚያዛቡ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ድርጊቶችን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ማየት እንግዳ አይደለም:: ከእኛ በተቃራኒ የቆሙት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ ሲወሰድ መንግሥትን ማወደስ፣ በእኛ ላይ ሲሆን ግን መንግሥትን መኮነን፣ መሳደብ ወይም የሽምግልና ጋጋታ ማብዛት ልማድ ሆኗል:: ለራስ የፖለቲካ ግብ ጥቅም ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥትን ማክበርም ሆነ መጣስ ምንም ልዩነት የላቸውም:: ሕዝብን ለማደናገር ሕገ መንግሥት ሲጣስም ሳይጣስም ተጣሰ ብሎ መጮህ ለጆሮ የሰለቸ “ሙዚቃ” ነው:: ሰዎች በግፍ ከቀዬአቸው ሲፈናቀሉ ዝም ያለ ድርጅትና “አክቲቪስት” አፈናቃዮች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ሰብዓዊ መብት ተጣሰ ይላል::
ምርጫ በራሱ ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ የሚያመጣ ይመስል ምርጫ ካልተደረገ ኢትዮጵያ ትጠፋለች ብሎ ሕዝብ ሲሸበር፣ በታጣቂዎች ንፁኃን ሲገደሉ፣ በምናምንቴዎች የሰው ሕይወትና ንብረት ሲጠፋ፣ በፕሮፓጋንዳ ስም ውዥንብር በመንዛት የሕዝብ ሥነ ልቦና ሲሰለብ፣ የሕዝብ አመኔታን ገደል ከቶ በጮሌነትና በሕገወጥ መንገድ አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ተግባር ሲፈጸም፣ በዚህች አጭር ጽሑፍ ዘርዝሬ የማልጨርሰው የመከራ መዓት በአገርና ወገን ላይ ሲደርስ፣ “አሁንስ ዳኛው ማነው?” ያስብላል:: መሃል ላይ የቆሙ ሰዎችና ተቋሟት በሌሉባት፣ ኖረውም በማይደመጡባትና በማይከበሩባት አገር “ባለጊዜ” እንጂ “ዳኛ” ሊኖር አይችልም::
ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው ለውጥ ሲመጣ “ተደምረሃል?” የሚለው ጥያቄ በተራው ሰው ዘንድ በስፋት ይጠየቅ የነበረው፣ መሀል ላይ መሆን ትክክል አይደለም ከሚለው አጉል አባዜ የመነጨ ነው:: ለለውጡ ድጋፉን ለመግለጽ አዲስ አበባን ያጥለቀለቀው የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ሠልፍ ተሳታፊ፣ በአገር ውስጥ ከሚኖሩትም ሆነ ከውጭ ከመጡ ግለሰቦችና ድርጅቶች “ኪስ” ውስጥ ለመግባት ብዙም ጊዜ አልወሰደበትም:: ምክንያቱም የለመድነው ጎራ ለይቶ መጎሻሸም እንጂ ወደ ግራም ሆነ ወደ ቀኝ ፈጥኖ ከመግባት፣ መሃል ላይ ቆሞና መዝኖ የሚበጀውን መምረጥ አይደለምና::
እንግዲህ የፍትሕና የታሪክ እውነተኛ ዳኛ የምንፈልግ ከሆነ መሃል ላይ የቆሙ ግለሰቦችና ተቋሟት ያስፈልጉናል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ጋር በነበራቸው የውይይት ጊዜ፣ “ሲቪክ ሶሳይቲ ሚዛን የሚያስጠብቅ” ነው በማለት መሃል ላይ ያለ ተቋምን አስፈላጊነት ተናግረዋል:: ይህ መሃል ላይ ላሉና ለመሆን ለሚፈልጉ ትልቅ ተስፋ ነው:: ምክንያቱም ከረጅም ዓመታት በኋላ መሃል ላይ መቆም ጥሩ መሆኑን ከገዥው ፓርቲና መንግሥት በይፋ ስለሰማን ነው:: ይህ መልካም ጅምር ከግብ እንዲደርስ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግሥት መሃል ላይ ያሉ ተቋማትን ለራስ ፍላጎት መጠቀሚያ ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል:: ተቋማቱም የመንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች መጠቀሚያ ከመሆን ራስን ማፅዳት ይጠበቅባቸዋል:: በትክክል መሃል ላይ የቆሙ ተቋሟትን ማዳመጥና ማክበር ተገቢ ነው:: ይህ ሲሆን በአገራችን ኢትዮጵያ ዳኛ ይኖራል፣ ዴሞክራሲም ያብባል፣ በጎ ህሊና ያላቸው “ትልቅ ሰው” የምንላቸውም ይበዛሉ::
ከዚህ በተጨማሪ ብዙ የተባለለት የፍትሕና የርትዕ አካል መሀል መሆን እጅግ አስፈላጊ ነው:: በዚህ አካል ላይ የፓርቲዎችም ሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ለቡድን እንጂ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ መልካም አስተዳደር፣ ዕድገትና ዴሞክራሲ ጥቅም የለውም:: በጎ ህሊና ያላቸው፣ መሀል ላይ የቆሙ፣ ለእውነት ተገዥ የሆኑ፣ ለገንዘብ የማይጓጉ፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ሰውን የሚያከብሩ፣ በሙያቸውና በሰብዕናቸው የተከበሩ ሰዎችን በዚህ ተቋም ውስጥ ማብዛት እውነተኛ ዳኛ እንዲኖረን ያደርጋል::
የሃይማኖት ተቋማትም መሀል ላይ የቆሙ ነበሩ ማለት አይቻልም:: ባለጊዜና ጉልበተኛ ወደፈለገው ሲጎትታቸው፣ እንደፈለገው ሲያምሳቸው ብዙ ዓመታትን አስቆጥረዋል:: ዛሬም ቢሆን ሳይጎተቱ ለመጎተት ራሳቸውን ያዘጋጁ፣ ጭርስኑ ጎራ ለይተው ከፖለቲከኞች የማያንስ የመከፋፈል ሥራ የሚሠሩ የሃይማኖት መሪዎች ይስተዋላሉ:: በግላቸው የፈለጉትን መሆን ይችላሉ፡፡ ተቋሙን ግን መሃል ላይ እንዲቆም መተው ለሃይማኖቱም ለአገርም ይጠቅማል:: ምክንያቱም የሃይማኖት ተቋማት መሃል መሆን በጎ ህሊናና ሚዛናዊነት ያላቸው ዜጎችን በማዘጋጀትና በማፍራት እውነተኛ ዳኞች እንዲኖሩን ያደርጋል:: በእኔ ዕይታ፣ ከታዋቂ የሃይማኖት መሪዎች መካከል፣ እስካሁን ድረስ በሙስሊሙም ሆነ በክርስቲያኑ ዘንድ የዳኝነትን ማዕረግ የተጎናፀፉ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ ይመስሉኛል:: እርሳቸውን ያነሳሁት ታዋቂ ስለሆኑ ነው እንጂ ሰው የማያውቃቸው፣ ሚዛናዊ የሆኑ፣ የሚመሩትን ምዕመን በጎ ህሊና እንዲኖረውና እንዲያመዛዝን የሚያስተምሩ መኖራቸውን አውቃለሁ:: እንደ እነዚህ ዓይነት ያሉ መሪዎችን በሁሉም የእምነት ተቋማት ፈጣሪ እንዲያበዛልን ምኞቴ ነው::
ሰው አዕምሮ ያለው ፍጡር ነው:: የተፈጠረውም ማመዛዘን እንዲችል ሆኖ ነው:: ስለዚህ የሰው ልጅ የሆነ ሁሉ መሀል ላይ በመቆም የሠራቸውንና የሄደበትን ጎዳና ለማየት ከህሊናው ጋር የሚሟገትበት ጊዜ ሊኖረው ይገባል:: በራሱ ላይ ዳኛ ያልሆነ እንዴት ብሎ ሌላውን ሊዳኝ ይችላል? ህሊናን የጣለ ሰው መሪ ከሌለው መርከብ ጋር ተመሳሳይ ነው፣ ከአደጋ አያመልጥም:: ሲሳሳት የማይፀፀት ሰው ህሊናውን ጥሏልና ከሰው ተራ ወጥቷል:: መሃል ላይ የቆሙ ሰዎች ብዙዎችን ከስህተት ይታደጋሉ:: በጎ ህሊና ያላቸውና መሃል ላይ የቆሙ በርካታ ሰዎች ኖረው ቢሆን ኖሮ ብዙ ወገኖቻችን በሕይወት ይኖሩ ነበር:: ስለዚህ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ ሐኪሞች፣ መምህራን፣አገልግሎት ሰጪዎች፣ በአጠቃላይ በሙያቸው የሚያገለግሉ ሁሉ መሃል ላይ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ መሃል ላይ እንዲሆኑም ከመንግሥትና ከፓርቲዎች ተፅዕኖ ሊላቀቁ ይገባል::
በመጨረሻም የተጀመረው ለውጥ ግንባር ቀደም መሪዎችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከላይ የዘረርኳቸው ተቋማት ፍሬ እንዲያፈሩ የድርሻቸውን ይወጣሉ የሚል እምነት አለኝ:: ነገር ግን እንደ ቀደምቶቹ ባለጊዜዎችና ጉልበተኞች መሃል ላይ የቆሙትን በማሸማቀቅ፣ የሰውም የተቋማትም ዳኞች ማፍራት እንዳንችል ቢያደርጉ የታሪክ አቅጣጫን የሚዘውር፣ መንግሥታትን የሚያስነሳና የሚጥል ፈጣሪ የምንጊዜም ዳኛ መሆኑን መርሳት የለባቸውም:: የእርሱ ዳኝነት በዚህም በወዲያኛውም ዓለም ነውና በተቻለን መጠን በእርሱና በሰዎች ዘንድ በጎ ህሊና እንዲኖረን መትጋት ለሁላችንም ይበጃል::
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡