Thursday, June 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ዳኛው ማነውን እንዳነበብኩት. . .

በመስዑድ ሙስጠፋ

ምንም እንኳን ስለተማሪዎች እንቅስቃሴ በርካታ መጻሕፍት በሁሉም ጎራ ተሠልፈው በነበሩ ተጽፎ ያነበብን ቢሆንም በታደለች ኃይለ ሚካኤል የተጻፈውን “ዳኛው ማነው?” የሚለውን መጽሐፍ በተለያዩ ምክንያቶች ለማንበብ ጓጉቼ ነበር፡፡ ብዙዎች ከብዙ ዓመታትም በኋላ የተሠለፉበትን መስመር ለመከላከል በሚመስል መልኩ ጽፈዋል፡፡ ይህ ዳኛው ማነው የሚለው መጽሐፍ ከዳኝነትና ፍርድ በመለስ እውነተኛ ታሪኩን ለማስቀመጥ ሞክሯል የሚለው አስተያየት ይበልጥ ጉጉቴን አንሮት ነበር፡፡ 

የአገሪቱን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በመሠረታዊነት የቀየረውን የያኔውን የፖለቲካ ትግል በተመለከተ ያለፍረጃና ዳኝነት የሆነውን ለዚህ ትውልድና ለታሪክ ለማስቀመጥና ትግሉን ከፊት ሆነው በተለይ ይመሩት ስለነበሩ ጉምቱ “አብዮተኞች” የፖለቲካና ግለሰባዊ ሰብዕናቸው አውቆ ለመረዳት አስፈላጊ ሲሆን እንደነዚህ ዓይነት መጽሐፎች መጻፋቸው ሊበረታታ ይገባል፡፡ በቅርብ ጊዜያት እንኳን በብዙ ሰዎች ዘንድ የተነበበውና ከኢሕአፓ መሥራች አንዱ ስለነበረው ጌታቸው ማሩ በሕይወት ተፈራ “Tower in the sky” በሚል፣ እንዲሁም አማረ ተግባሩ (ዶ/ር) የተጻፈው ‹‹ኃይሌ ፊዳና የግል ትዝታ›› በሚል ስለመኢሶኑ መሥራች ኃይሌ ፊዳ ግሩም መጻሕፍት አንብበን ነበር፡፡

አምባሳደር ታደለች በዚህ ዳኛው ማነው? በሚለው መጽሐፋቸው ወቅቱን መለስ ብሎ ለመቃኘት፣ በትውልድ ተጋሪ ወጣቶች መሀል ስለተፈጠረውና የፖለቲካ ትግሉ ስላስከፈለው ውድ ዋጋ በደንብ ለመረዳትና ከፍረጃና ዳኝነት ወጥቶ የሆነው ምን ነበር? እንዴት ሆነ? ያ ምን አስከተለ? የሚለውን እንድናውቅ በእርግጥ ግሩም ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህ ትውልድ ከዚያ የፖለቲካ ተሳትፎና በወቅቱ ትግሉን ይመሩ ከነበሩ ግለሰቦች የሚማረው ቁምነገር ያገኛል፣ እንዲሁም ለአሁኑ የአገራችን ፖለቲካ የሚያበረክተው ፋይዳ ይኖረዋል የሚልም ጠንካራ እምነት ስላለኝ ከመጽሐፉ ጥቂት ሐሳቦችን ለማንሳት ወደድኩ፡፡

እንደ መግቢያ

አምባሳደር ታደለች ከስዊዘርላንድ ከተማሪነት ሕይወታቸው ጀምሮ አንድ ሁለት እያሉ የጀመሩት የፖለቲካ ተሳትፎን፣ በአጋጣሚ ካወቁት ጉምቱ የፖለቲካ ሰው ጋር ስለነበረው የፍቅር ሕይወታቸው፣ በአገር ውስጥ ለለውጥ በግራና ቀኝ የተሠለፉ የአንድ ትውልድ ተጋሪ ወንድማማቾች መሀል ስለነበረው የፖለቲካ ትንቅንቅ፣ መከዳዳት፣ ጭካኔና አጠቃላይ የወቅቱን የአገሪቱን ሁኔታ ከራሳቸው ትግል ተሳትፎ ጋር እያዋዙ አስነብበውናል፡፡ ለዚህ ግሩም ሥራ ለጸሐፊዋ እጅ እነሳለሁ፡፡

የ1960ዎቹን የፖለቲካ ትንቅንቅ በቅጡ ለሚከታተል ሰው ከሁሉም ጎልተው የሚነሱ ሁለት ስሞችን ያስታውሳል፡፡ የመኢሶኑን ምሁር ኃይሌ ፊዳንና የኢሕአፓን መሥራች ብርሃነ መስቀል ረዳን፡፡ በተለይ ስለኢሕአፓ የትግል እንቅስቃሴ የተጻፉ መጻሕፍት የብርሃነ መስቀልን ስም ወይ በአዎንታዊ አልያም በአሉታዊ መልኩ ማንሳታቸው አይቀርም፡፡

ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ፣ አውሮፕላን ጠልፎ አልጄርያ የሄደውን ስር ነቀል የለውጥ ደጋፊ ቡድንን የመራ፣ በአውሮፓ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ የቻለ፣ በአገር ውስጥ በህቡዕ ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጋር ተዋህዶ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ከባድ ተፅዕኖ መፍጠር የቻለውን ፓርቲ ኢሕአፓን ከመሠረቱት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚነሳ፣ በፓርቲው ውስጥ “አንጃ” ተብሎ እሱ “ክሊኮቹ” በሚላቸው የተገፋና ከደርግና ከራሱ ጓዶች የሞት ቀለበት ለማምለጥ የተንከራተተና በስተመጨረሻው የሕይወት ወቅቱ ላይ የእርምት ዕርምጃ ብሎ በመርሐ ቤቴ ጫካ ውስጥ ገበሬን አንቅቶና አደራጅቶ ትግል ለማድረግ እስከ መጨረሻው ስለተፋለመው ጓድ ይህ መጽሐፍ ብዙ ታሪኮቹን አሥፍሯል፡፡

ግላዊ ሰብዕና ባለ ብዙ ስሙ ታጋይ

በደርግ በተገደለበት ወቅት 36 ዓመት ሊሞላው ሁለት ወር ይቀረው ስለነበረው  የወቅቱን ፖለቲካ ቀያሽ ብርሃነ መስቀል ረዳ የኢትዮጵያን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ የተረዳበት መንገድ፣ ከትግል ጓዶቹ ጋር ስለነበረው የሐሳብ አንድነትና በኋላ ላይ ስለተከሰተው ልዩነት፣ ስለግለሰባዊ ማንነቱና በተለይ ከመሀል አገር ርቆ በመጨረሻዎቹ ጊዜያት በመንዝና መርሐ ቤቴ ሸለቆዎች የእርምት ዕርምጃ ብሎ እስካደረገው እንቅስቃሴ ድረስ ያለው ታሪክ የሚነግረን አንድ እውነት የሰውየውን ላመነበት ነገር እስከ መጨረሻው እንደሚሄድ ነው፡፡

ደሴ ካለው ከወ/ሮ ስህን የጀመረው የትምህርት ጉዞው አድጎ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና እንዲጫወት ያበቃው በትውልድ አጋሮቹ ዘንድ በአነጋጋሪነቱ የሚታወቀው ብርሃነ መስቀል ባለ ብዙ ስም ነበር፡፡ አንዳንዶች “ጓዱ” ሌሎች ደግሞ በደፈናው “ሰውየው” ይሉታል፡፡ ከአልጄርያ እስከ አውሮፓ ከዛም በህቡዕ በአገር ውስጥ ገብቶ ሲንቀሳቀስ በብዙ ስሞች ይታወቅ ነበር፡፡ ዋርሰማ፣ ሱሌይማን፣ ሶሎሞን፣ ቢዘን፣ በዛብህ በላቸው፣ ጥላሁን ታከለ፣ ዘሪሁንና ብዙዎቹ ደግሞ   “ሽማግሌው” ብሎ ብዙዎች ይጠሩት እንደነበር ጸሐፊዋ በመጽሐፋቸው አጋርተውናል፡፡

ከብርሃነ መስቀል ጋር ተስፋዬ ደበሳይ (ዶ/ር) አማካይነት በስዊዘርላንድ የተጀመረው የታደለችና የብርሃነ መስቀል ትውውቅ የመጀመሪያው ወቅት ላይ የተፈጠረው አንድ ታሪክ የሰውየውን መረዳትና አስተውሎ እንድናይ ያደርገናል፡፡ በጭውውታቸው መሀል ያስቃል ያሉትን አንድ ብሔርን ተንተርሶ የተሠራውን ቀልድ ለብርሃነ መስቀል ነገርኩት ይላሉ ጸሐፊዋ፡፡ ባልጠበቁት መልኩ ከመሳቅ ይልቅ ጥልቅ ሐሳብ ውስጥ ብርሃነ መስቀል መግባቱን ይነግሩናል፡፡ ከብዙ ዝምታ በኋላ ብርሃነ መስቀል፡- “ይኸውልሽ እንደዚህ ዓይነቱ በሕዝብ ላይ የሚቀለድ ቀልድ አንዱን ከፍ አንዱን ዝቅ የሚያደርግ ነው፡፡ እኔ አያስቀኝም፡፡ አንቺ ስላወራሽው አይደለም፡፡ በማንኛውም ሕዝብ ወይም ቡድን ላይ ሲቀለድ ምክንያቱ ዞሮ ዞሮ ደስ የማይል ቅራኔን ሊፈጥር የሚችል ስለሆነ ማስቀረት አለብን ማለቴ ነው (ዳኛው ማነው ገጽ 43)፡፡

ከዚህም መልስ በኋላ እኔም እኮ የዚሁ ብሔረሰብ አባል ነኝ በራሴ ብሔር ብቀልድ ምን ችግር አለው ብለው መከራከራቸውን ያነሳሉ ጸሐፊዋ፡፡ አሁንም ብርሃነ መስቀል በመልሱ እንዲህ ማለቱን ይነግሩናል፡፡ ‹‹ታደለች አንቺም ብትሆኚ ያለሽበት ያደግሽበት ኅብረተሰብ አካል ነሽ፡፡ አንቺ ስለተናገርሽው ጉዳዩን ልክ አያደርገውም ለማለት ነው›› (ዳኛው ማነው ገጽ 43)፡፡

ይህቺ አጭር ታሪክ የኢትዮጵያን አንዱ የፖለቲካ ስብራት በዚያን ወቅት ሰውየው እንዴት እንደሚረዳው ለአንባቢያን በደንብ ያሳያል፡፡ በሁሉም የፖለቲካ ልሂቃንና ኅብረተሰቡ ዘንድ ስለብሔርና ማንነት የዚህን ያህል መረዳት ኖሮ ቢሆን አሁን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ቅርፅ ይይዝ ነበር ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡

መሬት ላራሹ

የብርሃነ መስቀል አያት ቀኛዝማች ረዳ በጨፈና ቃሉ ከሚያሳርሱት መሬት ውስጥ ያርስ የነበረው የወሎው አያ ሙሄ ታሪክ በወቅቱ የነበረውን የአርሶ አደሮቻችንን አስከፊ ሕይወት ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ታሪክ ነው፡፡ ብርሃነ መስቀል ስለገበሬው ሕይወት አስከፊነት በተግባር እንዲረዳው ያደረገውም ከዚህ አያ ሙሄ ጋር የነበረው ቅርበትና ጭውውት መሆኑን አይተናል፡፡ በአንድ ወቅት አያ ሙሄ ባለቤቱ ወልዳ ለራሳቸው በቂ እህል ሳይኖራቸው እንኳ ካረሰው እርሻ ላይ ለቀኛዝማች ገቢ ሊያደርግ ሲል ለብርሃነ መስቀል ያጫወተው ልብ ሰባሪ ታሪክ የመሬት ላራሹ ትግልና ውጤቱ ለገበሬው ምን ማለት እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ አያ ሙሄ ለቀኛዝማች ገቢ ያደረገውን እህል የገለጸው ‹‹ከሚስቴ አፍ ነጥቄ ነው ያመጣሁት›› (ዳኛው ማን ነው ገጽ 200) በሚል ነበር፡፡

ይህን የመሰለውን ሥርዓት ለመታገል ምክንያት ከሆኑት ውስጥ ከአያ ሙሄ ጋር ያደርገው የነበረው ጭውውት ስለገበሬው አስከፊ ሕይወት በጥልቀት እንዲረዳ ስለዳረገውም ጭምር እንደሆነ ከመጽሐፉ እንረዳለን፡፡ ይህን ኢፍትሐዊ የመሬት ሥሪት በወቅት ይታገሉ የነበሩ ሁሉም ተራማጅ ኃይሎች ለማስወገድ የበኩላቸውን መወጣታቸውን ታሪክ ሊመዘግበው የሚገባ ሃቅ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በሁላችንም አፍ ውስጥ የማይጠፋውን ታሪካዊውን “መሬት ለአራሹ” የሚለውን መፈክር ብርሃነ መስቀል ረዳ እንደቀረፀውና ለዚህም ታሪክ በሚገባ ሊመዘግበው እንደሚገባ አምባሳደር ታደለች በመጽሐፋቸው አውስተዋል፡፡

መሬት ላራሹ መፈክር በሁሉም ለውጥ ፈላጊ ልብ ውስጥ ከመሰንቀሩ በፊት ብርሃነ መስቀል ይህን የገበሬ ታሪክ በወቅቱ “Something” በሚባለው መጽሔት ላይ በመጣጥፍ መልክ ካቀረበው በኋላ በወቅቱ ይከበር በነበረው የኮሌጅ ቀን ላይ ይህን የመሬት ላራሹን ጥያቄ በድራማ መልክ አቅርቦት እንደነበር በመጽሐፉ ያስታውሱናል፡፡

የድራማው ዋነኛው ጭብጥ

‹‹በፓርላማ የምረጡኝ ዘመቻ በተወዳዳሪነት አንድ ወጣት ፓርላማ ለመመረጥ ዕጩ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ብትመርጡኝ መሬት ላራሹ እንዲሆን አስደርጋለሁ እያለ ይቀሰቅሳል፡፡ ፓርላማው ውስጥ ያለው ትዕይንት ግማሹ ሲያንቀላፋና ሲያዛጋ ያሳይና ወጣቱ ዕጩ ተወዳዳሪ ተነስቶ በንግግሩ መቋጫ ላይ መሬት ላራሹ፣ መሬት ላራሹ፣  መሬት ላራሹ በማለት ሦስት ጊዜ በከፍተኛ ድምፅ ሲጮህ ተመራጭ እንደራሴዎች ከእንቅልፋቸው ይነቃሉ›› (ዳኛው ማነው ገጽ 2006)፡፡

“መሬት መሬት ላራሹ

ተዋጉለት አትሽሹ”

እያለ ለውጥ ፈላጊው ትውልድ ከዘውዳዊው ሥርዓት ጋር ያደረገው ትግልና ተጋድሎ በበኩሌ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱ እጅግ ጉልህ ክስተቶች ውስጥ በቀዳሚነት የማስቀምጠው ነው፡፡ ይህንን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበረውን ኢ ፍትሐዊ የመሬት ሥሪት “መሬት ላራሹ” በሚል ገላጭ መፈክር የቀረፀውና የለውጥ ፈላጊ ትውልድ ድምፅ እንዲሆን ስላደረገው ብርሃነ መስቀል ረዳ፣ ታሪክ ሊመዘግበው ይገባል የሚለውን የአምባሳደር ታደለችን ሐሳብ እጋራዋለሁ፡፡

በአገር ውስጥ የተደረገው ህቡዕ እንቅስቃሴና የአመራር መከፋፈል የአብዮቱን መከሰት ተከትሎ ብዙ የትግሉ አመራር አገር ቤት ገብቶ መታገል እንዳለበት ከተወሰነ በኋላ አብዛኛው የኢሕአፓ አመራር በድብቅ አገር ቤት ገብቶ ነበር፡፡ ከመነሻው የነበረው የትግል መስመር ከገጠር ጀምሮ ወደ ከተማ የሚያድግ ሕዝቡን ያሳተፈ ትግል እንደነበር በዚህ መጽሐፍም ሆነ በሌሎች መጻሕፍት የተገለጸ ነገር ነው፡፡ ይህን ለሕዝብ የሚደረግ ትግልን ብዙዎች ከተደላደለው የአውሮፓ ኑሮ አስትቶ ወደ አገር ቤት እንዲገቡም አድርጓቸውም ነበር፡፡ እዚህ ላይ አንድ በመጽሐፉ የተጠቀሰ ታሪክ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በስዊውዘርላንድ የቅርብ ጓደኛቸው የነበረውና በወቅቱ በነበረው ትግል እሱም ሆነ ወንድሙ መስዋትነት የከፈሉለት አክሊሉ የሚባል ልጅ ከስዊዘርላንድ ወደ አገር ቤት ገብቶ እንዲታገል መወሰኑን ሲነገረው የነበረውን ደስታ ወ/ሮ ታደለች አጋርተውናል፡፡

‹‹በተለይ አክሊሉ ለታለመለት ዓላማ ቃል የገባውን ሊያሳካ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሊቀላቀል የጥቂት ቀናት ጊዜ ብቻ እንደቀረው ብቻችንን ስንሆን በደስታ ይገልጽልኛል፡፡ ለሚያውቀውም ለዕረፍት እንደሚሄድ እየነገረ መሰናበት ጀመረ፡፡ አገሩ ሲመለስ የሚያደርገውን እያሰላሰለ በሐሳቡም መሣርያ ይዞ ሕዝባዊ ጦርነት ሲቀላቀል እየታየው ቆየ›› (ዳኛው ማነው ገጽ 147)፡፡

ይህ የአክሊሉ ታሪክ የብዙዎች ታሪክ ነው፡፡ አክሊሉ በሐሳቡ መሣርያ ይዞ ሕዝባዊ ጦርን ሲቀላቀል የሚታየው አብዛኛው የዚያ ትውልድ ታሪክ ነው፡፡ ይህ ምሥል ቀራጭ የአክሊሉ ድርጊት የዚያን ትውልድ የአገር ፍቅርና ከራስ በላይ ለአገር መስጠትን ያሳያል፡፡ በዚህ ሞራልና ቁርጠኝነት የተጀመረው የህቡዕ እንቅስቃሴ ሌላ የትግል ሥልት መከተሉን ከአውሮፓ መልስ እዚህ ያዩትን ነገር በማስታወስ ያወጉናል፡፡ አሲምባ አገኛቸዋለሁ ብለው ያሰቧቸውን አመራሮች እዚሁ አዲስ አበባ ሲያገኙ መደናገራቸውን አምባሳደር ታደለች ይነግሩናል፡፡

‹‹እኔ የነበረኝ ዕውቀት ብርሃነ መስቀል አሲምባ ይገኛል የሚል ነው፡፡ ስለዚህ እዚያው አሲምባ ባይሆን አቅራቢያው ባለ መንደርም ይሁን ከተማ አግኝቼው አሳይቼው ለመመለስ አስቤያለሁ፡፡ ከአውሮፓ ስመለስ እዚያም ባለሁበት ጊዜ አክሊሉም ሆነ እነ ተስፋዬ ደበሳይና ብርሃነ መስቀል አሲምባ እንጂ አዲስ አበባ አገኛቸዋለሁ ብዬ በፍፁም አላሰብኩም›› (ዳኛው ማነው ገጽ 184)፡፡

እንግዲህ ለአንድ ዓላማ በተሠለፉ የትግል ጓዶች መካከል በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ክፍፍል መፈጠሩን ዘግይተው መረዳታቸውን ጸሐፊዋ አንስተዋል፡፡ በተደጋጋሚ እንደሚጻፈው ፓርቲውን በሚመሩ አመራሮች መካከል በከተማ ትግል፣ የደርጉን ሊቀመንበር ለመግደል በቀረበው ሐሳብና ትግሉን እንዴት እንምራው በሚለው ጉዳዮች ላይ ልዩነት ተፈጥሮ ብርሃነ መስቀልና ጌታቸው ከፓርቲው መታገዳቸው ቆይቶም የሞት ፍርድ በሌሉበት መወሰኑን በብዙ ቦታዎች ተገልጸዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ብርሃነ መስቀል ያላቸውን እንዲህ ያስታውሳሉ፡-

‹‹ከ1968 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ ጥያቄዎች ላይ የፓርቲውን አቋም በማውገርገር የፓርቲውን ፕሮግራምም ሆነ ትግል ሥልት በመለወጥ እምነት አሳጥተውናል፡፡ ኢዲሞክራሲያዊ አሠራርን በመምረጥ ከፓርቲው ፕሮግራም ውጭ በመሄድ አባላትንም ሆነ የማዕከላዊ ኮሚቴውን ሳያወያዩ ክሊክ የምንላቸው የሥራ አስፈጻሚዎች ማተራመስ ከጀመሩ ቆዩ›› (ዳኛው ማነው ገጽ 253)፡፡

ይህን የሚያጠናክር ሐሳብ በተመሳሳይ መልኩ ከማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲታገድ ተደርጎ በኋላም በትግል አጋሮቹ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለው የብርሃነ መስቀል ወዳጅ ጌታቸው ማሩ፣ ለሕይወት ተፈራ የነገራትን በTower in the sky መጽሐፋቸው አሥፍረዋል፡፡

“The issue is not diciplilenery but political. The comrade and I are expelled because we are against the idea of urben gurella warfare, the assassination of Mengistu Hailemariam…”(Tower in the sky page 210)

አምባሳደር ታደለች የሆነውን የጠፋውን ከተመለከቱ በኋላ የተፈጠረውን እንዲህ ነው ያስቀመጡት፡- ‹‹ለቀረፀው ፕሮግራም ተዓማኒነት በመርሳት ከገጠር ወደ ከተማ የሚለውን ትግል ሥልቱን በመለወጥ በአጭር መንገድ በከተማ አመፅ (armed insurrection) ለሥልጣን እበቃለሁ ብሎ ማሰቡ የኢሕአፓ አመራር (ክሊኩ) የአመለካከት ችግር ዋነኛ መገለጫ ነው›› (ዳኛው ማነው ገጽ 422)፡፡

እንግዲህ በዚህና በሌሎች ሐሳቦች ምክንያት የተፈጠረውን የሐሳብ ልዩነት የኢሕአፓ ሥራ አስፈጻሚዎች ያስተናገዱበት መንገድ ከአምባገነናዊው ደርግ ኃይል ዕርምጃ ጋር ተዳምሮ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ የቀየረው የወጣቶች የትግል እንቅስቃሴ በአሳዛኝ ፍጻሜ እንዲቋጭ አድርጎታል፡፡ ስለምን እነዚያ ባለብሩህ አዕምሮ ባለቤት ወጣቶች በዚያን ያህል መግባባት ተሳናቸው? ስለምን ልዩነታቸውን በውይይት መፍታት ተሳናቸው? እንዴት እርስ በርስ በዚያን ያህል ሊጨካከኑ በቁ? የሚሉት ጥያቄዎች ሁሌም ወደ ውስጤ ይመጣል ስለዚያ ትውልድ ሳስብ፡፡ ለአንድ ዓላማ ተሰባስበው ጥቃቅን ልዩነቶችን በመቻቻል መፍታት አለመቻል ይኼው የዚህም ትውልድ ስብራት ሆኖ ቀርቷል፡፡ መንገድ ጀምሮ መበታተን፡፡ በጥቃቅን ጉዳዮች መለያት፡፡ ልዩነትን በጥበብ የመያዝ ድክመት፡፡

አምባሳደር ታደለች በማጠቃለያው ላይ ያሰፈሩትን ቁምነገር የዚህ ትውልድ ፖለቲከኞችም በጥሞና ሊሰሙት ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ‹‹ሐሳብን መፍራት አላዋቂነት ነው፡፡ ፍርኃት በራሱ ጥላቻን ይወልዳል፡፡ ጥላቻ ፀብን ይወልዳል. . . የመደማመጥ ችግራችንም መፍትሔያችን ወደ ኃይል ዕርምጃ እንዲያጋድል ምክንያት ይሆናል፡፡ በኃይል ያሸነፈም ፅዋው እስኪሞላ ድረስ መንበሩን ቢቆናጠጥም ከገባንበትና ከኖርንበት ድህነት ጉስቁልና ጭቆና አዙሪት ሊያወጣን እንደሚችል የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ከበቂ በላይ ያስተምራል›› (ዳኛው ማነው ገጽ 424)፡፡

በተለያየ ወቅት ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በፍፁም የአገር ፍቅር ተሠልፈው መስዋዕት ለሆኑና ለተጎዱ ሁሉ በክብር እጅ እነሳለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውለታችሁ አትረሳም!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በጋዜጠኝነት፣ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካ ሳይንስና በዓለም አቀፍ ግንኙነት ያገኙ ሲሆን፣ በአሁን ወቅት በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ላይ እየሠሩ ይገኛል፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles