Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የልማት ድርጅቶች ከ8.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘታቸው ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አየር መንገድና ንግድ ባንክ 83 በመቶ አመንጭተዋል

ከተሸጡ ድርጅቶች 2.1 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በ2012 ዓ.ም. አፈጻጸማቸው ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ከማስገኘታቸው በተጨማሪ፣ ምርትና አገልግሎታቸውን በውጭ ምንዛሪ ከሚሸጡ ድርጅቶች 8.67 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገለጸ፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገብረ መስቀል መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንዳስታወቁት፣ በ2012 ዓ.ም. በውጭ ምንዛሪ እንደሚገኝ ከሚጠበቀው 12.52 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 8.67 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ ለዚህ ገቢ መገኘት የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትየጵያ ንግድ ባንክ 83 በመቶውን በመያዝ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው ብለዋል፡፡ እንደ ኤጀንሲው መግለጫ አየር መንገዱ 3.75 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት የ43.2 በመቶ ድርሻ ሲይዝ፣ ንግድ ባንክ በበኩሉ 3.44 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት የ40 በመቶ ገደማ ድርሻ ወስዷል፡፡

በተሸኘው ዓመት ከ21 የልማት ድርጅቶች ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ጠቅላላ የገቢ መጠን ከ338 ቢሊዮን ብር በላይ ነበር ያሉት አቶ በየነ፣ ከታቀደው ገቢ 89 በመቶ መሳካቱንና 300.5 ቢሊዮን ብር መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ገቢ ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ122 ቢሊዮን ብር ማስገኘቱ ቀደም ብሎ ሲገለጽ፣ ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ ከ47.7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገባቱ ታውቋል፡፡ በትርፍ ረገድ ኢትዮ ቴሌኮም ከ28 ቢሊዮን ብር በላይ ማስመዝገቡም ተጠቅሷል፡፡

በጠቅላላው ከ21 የልማት ድርጅቶች እንቅስቃሴ ይጠበቅ የነበረው የትርፍ መጠን ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ቢሆንም፣ በውጤቱ 56 ቢሊዮን ብር ያህል ተመዝግቧል፡፡ ከታቀደው የትርፍ መጠን 79 በመቶው ተሳክቷል፡፡ በዚህ መሠረት ለመንግሥት የትርፍ ድርሻ ክፍያ በመፈጸም ረገድ ንግድ ባንክ ስምንት ቢሊዮን ብር ገቢ ሲያደርግ፣ ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ ማስገባቱን አቶ በየነ አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለኤጀንሲው ተጠሪ ከሆኑና የትርፍ ድርሻ ክፍያ መፈጸም ከሚጠበቅባቸው ድርጅቶች ይጠበቅ የነበረው ክፍያ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ነበር፡፡

ድርጅቶቹ ያለባቸውን የአገር ውስጥና የውጭ ዕዳ ከመክፈል አኳያም አፈጻጸማቸው ታይቷል፡፡ 16.9 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ዕዳ እንዲከፍሉ ታቅዶ፣ 15.3 ቢሊዮን ብር ክፍያ መፈጸማቸው ተገልጿል፡፡ በውጭ ዕዳ ረገድ 604 ሚሊዮን ዶላር መክፈላቸው ተጠቅሷል፡፡ ከዘህ ውስጥ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ በኢትዮ ቴሌኮም የተከፈለ ነው፡፡

የመንግሥት ይዞታ ሥር የነበሩና ወደ ግል ከተዛወሩ የልማት ድርጅቶች ሽያጭ መከፈል የነበረበትና ሳይከፈል በመቆየቱ በቅጣትና ወለድ ታሳቢ ቢደረግም፣ በኮሮና ተፅዕኖ ምክንያት ለሌሎች ድርጅቶች የተደረገው የወለድና ቅጣት የማንሳት ምሕረት፣ እነዚህን ድርጅቶችም ለገዙ ኩባንያዎች ታሳቢ ተድርጓል፡፡ በዚህ መሠረት ኤጀንሲው እንዲከፈል የሚጠብቀው 3.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2012 ዓ.ም. 330 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደተደረገ፣ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ 1.8 ቢሊዮን ብር ክፍያ በማግኘቱ በጠቅላላው የ2.1 ቢሊዮን ብር ክፍያ እንደተፈጸመለት አስታውቋል፡፡ ይህ ገንዘብ ከተሸጡ ድርጅቶች እንዲከፈል ከሚጠበቀው 60 በመቶ የሚሸፍን ነው፡፡ 1.2 ቢሊዮን ብር ያልተሰበሰበ ቀሪ ክፍያ እንደሚቀረው ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በ2013 ዓ.ም. ኤጀንሲው ከሚያስተዳድራቸው ድርጅቶች 376.6 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚጠበቅ አቶ በየነ ገልጸዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም. ከተገኘው የ22 በመቶ ጭማሪ ተደርጎበታል፡፡ በትርፍ ረገድም የ36 በመቶ ጭማሪ የታከለበት 74 ቢሊዮን ብር ገደማ ከታክስ በፊት ትርፍ እንደሚገኝ ይጠበቃል፡፡ በውጭ ምንዛሪ ላይ ካለፈው የ14 በመቶ ቅናሽ የተደረገበት 7.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መታቀዱ ታውቋል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ በአሁኑ ወቅት 21 ድርጅቶች በሥሩ እያስተዳደረ ሲሆን፣ በ2012 ዓ.ም. 20ዎቹም አትራፊ ሆነው ዓመቱን ማጠናቀቃቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡ ብቸኛው ኪሳራ የደረሰበት የልማት ድርጅት ስኳር ኮርፖሬሽን ሆኗል፡፡

በዚህ ዓመት እንቅስቃሴ 71.5 ቢሊዮን ብር ኢንቨስት ለማድረግ መታቀዱ ሲጠቀስ፣ አብዛኛው ወይም 98 በመቶው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በዓመቱ 11 ድርጅቶች ወደ ግል እንደሚዛወሩ ሲገለጽ፣ አብዛኞቹም የስኳር ፋብሪካዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች