Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየተራዘመው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን መስከረም 25 ቀን በይፋ...

የተራዘመው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን መስከረም 25 ቀን በይፋ ይጀመራል

ቀን:

የትግራይ ክልላዊ መንግሥትን ለማገድ ሕጋዊ መሠረት እንዳለ ተነገረ

 በኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት የአምስት ዓመት የምርጫ ዘመናቸው የተራዘመው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ተጨማሪ የሥራ ዘመን፣ ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በጋራ በሚያካሂዱት ስብሰባ በይፋ ይጀመራል። 

ሁለቱም ምክር ቤቶች በዓመታዊ እረፍታቸው ላይ የሰነበቱ ሲሆን፣ ከአምስት ዓመት በላይ የተራዘመውን ተጨማሪ የሥራ ዘመን ሰኞ በሚያደርጉት የጋራ ስብሰባ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሳህለወርቅ ዘውዴ ምክር ቤቶቹ በተጨማሪ የሥራ ዘመናቸው ትኩረት ሰጥተው የሚተገብሯቸውን ዓበይት ተልዕኮዎች አስመልክቶ በሚያደርጉት ንግግር እንደሚጀምሩ፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የሁለቱ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ሰኞ ከቀትር በኋላ በሚያደርጉት የሥራ ዘመን መክፈቻ ስብሰባ የሚጀመር ሲሆንስብሰባውም የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በሚያስችል ሰፊ አዳራሽ ለማካሄድ ተብሎ በተመረጠው በጠቅላይ ሚኒስትር ሕፈት ቤት የሚገኝ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ይካሄዳል፡፡

በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ታዋቂ ሰዎችና ዲፕሎማቶች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚገኙዓለም አቀፍ ተወካዮች ይገኛሉ። 

በነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም. ይካሄል ተብሎ የጊዜ ሰለዴ የወጣለት አገር አቀፍ ምርጫ በኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ባለመካሄዱ፣ የሁለቱ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ምርጫ ተደርጎ በሕዝብ በሚመረጡ ወኪሎች እስኪተኩ ድረስ፣ በሥራ ላይ እንዲቆዩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሰጠው በሕገ መንግሥት ትርጉም መወሰኑ ይታወቃል። 

በዚህ ውሳኔ ላይ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርተዎች ተቃውሞ እያቀረቡበት ሲሆን፣ የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው ሕወሓት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።  ሕወሓት የትግራይ ሕዝብን በመወከል 38 ወንበሮች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉት ሲሆን፣ ሰኞ በሚጀመረው የምክር ቤቱ ስብሰባ አባላቱ እንዳይገኙ በመወሰን ትዕዛዝ ማስተላለፉን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የፓርላማ ተመራጭ የሆኑት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ለትግራይ ክልል ሚዲያ ሰሞኑን ገልጸዋል። 

አቶ አስመላሽ ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም የሚኒስትሮች ምክር ቤቶች ሕጋዊነት እንደሌላቸው በመግለጽ፣ የሕወሓት አባል የሆኑ ተመራጮች በእነዚህ ምክር ቤቶች እንዳይሳተፉ ትዕዛዝ ማስተላለፉን አስታውቀዋል። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ከመስከረም 25 ቀን በኋላ ሕጋዊነት ያለው መንግሥት የለም ተብሎ ለሚነሳው ክርክር ከሁለት ሳምንት በፊት በሰጡት ምላሽ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተቋቋሙ የአገሪቱ ተቋማት ውሳኔዎችን ማክበር እንደሚገባ የሚገልጽ ምላሽ ሰጥተዋል። 

ለሕገ መንግሥቱ መገዛት የሚጀምረው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተቋቁመው ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን ኃላፊነት መሠረት ያደረገ ውሳኔ የሰጡ ተቋማትን በማክበርና ውሳኔያቸውን በመፈጸም እንደሆነ የተናገሩት አፈ ጉባዔው፣ ውሳኔያቸውን በተመለከተ የፖለቲካ ልዩነት ወይም እይታ ቢኖር እንኳን ልዩነቱን ገልጾ ለውሳኔው መገዛት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል መሆኑን አስገንዝበዋል። 

ከዚህ ውጪ መሆን ግን በሕግ እንደሚያስጠይቅ አስታውቀዋል፡፡  የተራዘመው ምርጫ 2013 ዓ.ም. እንዲካሄድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጥቂት ሳምንታት በፊት መወሰኑ ይታወሳል።

ይህ በዚህ እንዳለ ዓርብ መስከረም 22 ቀን 2013 ዓ.ም. የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ፣ ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ ያልሆኑና ሰላም የማይፈልጉ ቡድኖች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል በቂ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት መኖሩን አስታውቀዋል፡፡ ከእነዚህ ቡድኖች ውስጥ አንዱ ነው ያሉት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ኢሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ምርጫ ማካሄዱን፣ ይህም ተግባሩ ሕገ መንግሥቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት ከሚወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል የትግራይ ክልልን ሕግ አውጭና ሕግ አስፈጻሚ ማገድ፣ ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ስለዚህም ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ መንግሥት ማቋቋም፣ እንዲሁም የፌዴራል የፀጥታ አካላትን በማሰማራት ሕገ መንግሥቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት መቆጣጠር ሕጋዊ መሠረት እንዳለው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ