Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ተኩሰው በመግደል በተጠረጠሩት ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሠረተ

ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ተኩሰው በመግደል በተጠረጠሩት ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሠረተ

ቀን:

ከሦስት ወራት በፊት ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት 3፡30 ሰዓት ላይ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ተኩሰው በመግደልና በመተባበር ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በዋሉት አራት ግለሰቦች ላይ፣ መስከረም 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ መንግሥትና የሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ክስ ተመሠርቶባቸዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው ተከሳሾች፣ ድምፃዊ ሃጫሉን በእርሳስ ሽጉጥ ከኋላ በግራ ደረቱ በኩል በመምታት ገድሎታል የተባለውና በቅፅል ስሙ ጥላዬ የሚባለው ጥላሁን ያሚ ባልቻ፣ ወንጀሉን ለመፈጸም የተባበሩት አቶ ከበደ ገመቹ፣ አቶ አብዲ ዓለማየሁና ሟችን ወደ መገደያ ቦታው የወሰደችው ወ/ሪት ላምሮት ከማል ናቸው፡፡

ተከሳሶቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀናለ)፣ እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቅርቡ በሥራ ላይ የዋለውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3(2) ድንጋጌዎችን በመተላለፍ፣ የወንጀል ድርጊቱን መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አመልክቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንደገለጸው፣ ተከሳሾቹ የያዙትን የፖለቲካ ርዕዮት ለማሳካት ሰዎችን በመግደል ሕዝብንና መንግሥትን ለማስገደድ አስበዋል፡፡ በመሆኑም በቀጥታ ድምፃዊውን የገደለው ጥላሁን የተባለው ተከሳሽ ካልተያዘና ያባቱ ስም ካልታወቀው ገመቹ ከተባለ የኦነግ ሸኔ አባልና ሌላ ግለሰብ ጋር ሆነው፣ ቀኑ በትክክል ባልታወቀበት በሰኔ ወር ውስጥ ቃሊቲ አካባቢ ሲገናኙ እንደነበር ገልጿል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ለኦሮሞ ሕዝብ ስላልጠቀመ አብረው በመሥራት መንግሥትን ማስወገድ እንዳለባቸው፣ ይኼንን ለማሳካትም በተመረጡ ሰዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ መዶለታቸውን ክሱ ይጠቁማል፡፡

ገዳዩ ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅ ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ፣ አባሪ ለመጨመር በሰኔ ወር እዚያው አቃቂ ከበደ ገመቹና አብዲ ዓለማየሁ የተባሉትን ተከሳሾች በተልዕኮው እንዲሳተፉ በማስማማት ስለወንጀሉ አፈጻጸም በጋራ ማሴራቸውንም የክስ ቻርዱ ያስረዳል፡፡ ገመቹ የተባለው ተከሳሽ በሕገወጥ መንገድ ገዝቶት በቤቱ አስቀምጦት የነበረውን ስታር ሽጉጥ ከአምስት ጥይቶች ጋር ለጥላሁን (ገዳይ) በመስጠት፣ የሚገደለው ሰው ማን እንደሆነ እስከሚነገራቸው ድረስ በተጠንቀቅ ሲጠብቁ እንደነበር ክሱ ያብራራል፡፡

ላምሮት የተባለችው ተከሳሽ ቀኑ በትክክል ባልታወቀበት በሰኔ ወር ስሙ ካልታወቀ የኦነግ ሸኔ አባል ጋር ሜክሲኮ አካባቢ ተገናኝተው፣ መንግሥት ለኦሮሞ ሕዝብ ያልጠቀመው  በመሆኑ ሕዝቡ መንግሥትን ከሥልጣን እንዲያወርደው በሕዝብ የሚወደዱና ተቀባይነት ያላቸውን የተመረጡ ሰዎችን መግደል አስፈለጊ ስለመሆኑ መመካከራቸውንም ክሱ ይገልጻል፡፡ ከአስፈላጊና ተቀባይነት ካላቸው ሰዎች መካከል ድምፃዊ ሃጫሉ አንዱ መሆኑን ስሙ ያልታወቀው የኦነግ ሸኔ አባል ለላምሮት ነግሯት፣ ሃጫሉን ስታገኘው ለእርሱ ቀድማ በማሳወቅ ዕርምጃ ወደሚወሰድበት ቦታ እንድታደርስለት የሰጣትን ተልዕኮ መፈጸሟን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ላምሮት በተሰጣት ተልዕኮ መሠረት ሟችን ስታገኘው ላልተያዘው የኦነግ ሸኔ አባል ስታሳውቀው ገዳዮቹ ከገላን ኮንዶሚኒየም ወደ እንዶዴ ባቡር ጣቢያ መግቢያ ላይ ዝግጁ መሆናቸውን ነግሯት፣ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. 12፡00 ሰዓት ላይ ሃጫሉን በመቅጠር በራሱ መኪና እየሄዱ እያሉ፣ ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ ሲደርሱ ወደ እንዶዴ ባቡር ጣቢያ በኩል እንዲወስዳት እንዳደረገችውም ክሱ ያብራራል፡፡

በዚህ ጊዜ ገመቹ የተባለውና ያልተያዘው ግብር አበር ለጥላሁን (ገዳይ)፣ ለአብዲና ለከበደ በማሳወቅ ዕርምጃ እንዲወስዱ እንዲዘጋጅ ነግሯቸው ሲጠባበቁ መኪናው መድረሱን ሲነግራቸው፣ ተሽከርካሪውን ተከትለው በመሄድ እንዶዴ ባቡር መግቢያ ላይ በግምት ከምሽቱ 3፡30 ሰዓት ላይ ላምሮት ‹‹ጤንነት ስላልተሰማኝ አውርደኝ›› ስትለው መንገድ ዳር ላይ አቁሞ እንዳለ ጥላዬ የሚባለው ተከሳሽ ይዞት በነበረው ስታር ሽጉጥ በመተኮስ የሃጫሉን የግራ ደረት ከኋላ በኩል መትቶ እንደገለደው ክሱ ያብራራል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ በፈጸሙት የሽብር ድርጊት ወንጀል ክስ እንደ መሠረተባቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...