በወሰን ውዝግብ ምክንያት ለታገዱ 9000 ቤቶች የተባለ ነገር የለም
በተመስገን ተጋፋው
ከአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በፊት የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕጣ የወጣባቸው 13ኛ ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ በወቅቱ በተፈጠረ ውዝግብ ለባለዕድለኞቹ ሳይተላለፉ የቆዩ ቢሆንም መስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ለዕድለኞቹ ቁልፍ ማስረከብ ተጀመረ፡፡
ቁልፉን ያስረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ሲሆኑ፣ 52,000 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ዕጣ ለደረሳቸው ዕድለኞችና 22,000 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ደግሞ ለተፈናቃይ አርሶ አደሮች ቁልፍ ማስረከብ ጀምረዋል፡፡
የጋራ ቤቶቹ ዕጣ በወጣበት ዕለት በወቅቱ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ የነበሩት ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) እና የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር የነበሩት አቶ ዣንጥራር ዓባይ (አሁን በምክልት ከንቲባ ማዕረግ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣን) ዕጣ የወጣባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች የቁልፍ ርክክብ ወዲያውኑ እንደሚፈጸም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ዕጣው በወጣበት ማግስት የካቲት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በተለይ ኮዬ ፈጬ አካባቢ በተገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ ተቃውሞ በመነሳቱ፣ ለዕደለኞቹ ቁልፍ ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡ የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ወሰን ውዝግብ በመነሳቱም 9,000 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ታግደው እንዲቆዩ በማድረግ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመረጠና የተዋቀረ ኮሚቴ የወሰን ውዝግቡን እንዲፈታ አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር፡፡ ከአስተዳደሩና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጣ ኮሚቴ ስለድንበሩ አጥንቶ ለሕዝብ ይፋ ባያደርግም፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቁ ተጠቁሟል፡፡
ውሳኔው ምን ይሁን ምን ሳይገለጽ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ከኃላፊነታቸው ተነስተው ሚኒስትር ተደርገው ከተሾሙ በኋላ፣ ወ/ሮ አዳነች ምክትል ከንቲባ ሆነው በተሾሙ አጭር ጊዜ ውስጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ለዕድለኞቹ እንዲተላለፉ በወሰኑት መሠረት መስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ቁልፍ ማስረከብ ጀምረዋል፡፡
የቁልፍ ርክክቡ የተጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዕጣ ለወጣላቸው 51,229 ነዋሪዎችና 22,915 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ነው፡፡ በልማት ምክንያት ለተነሱ አርሶ አደሮች፣ የቤቶቹን ዋጋ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ በመሸፈንና ካርታ በማዘጋጀት እንዲሰጣቸው መደረጉም ተገልጿል፡፡
ከሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎት ውስጥ ዋነኛ የሆነውን መኖሪያ ቤት አጥተው በከፋ የኑሮ ውድነት ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን ችግር ለማቃለል፣ በአጠቃላይ 74,144 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ማስረከባቸውን ወ/ሮ አዳነች ተናግረዋል፡፡
በጋራ የመኖሪያ ቤቶች የማስተላለፍ ሒደት ላይ በማኅበረሰቡ ዘንድ ቅሬታዎችና ትችቶች ሲቀርቡ የቆዩ እንደነበር፣ እነዚህንም ቅሬታዎች በመመልከት በዘርፉ ላይ ሰፊ ሥራ ለመሥራት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ እየቆጠቡ ያሉ 18 ሺሕ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም በቅርብ ቀን ዕጣ እንደሚወጣላቸው፣ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ያሉ 650 ሺሕ የሚሆኑ ነዋሪዎች ደግሞ እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሁንም ቢሆን አቅርቦቱና ፍላጎቱ ያልተጣጣመውን የጋራ የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ፣ አስተዳደሩ ተጨማሪ አማራጮችን ይዞ መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሠረት የፋይናንስ፣ የመሬት አቅርቦቶችን በማመቻቸትና የልማት ተነሺው ተገቢ ካሳ የሚያገኝበትን አሠራሮች በመዘርጋት የሚተገበር መሆኑን፣ የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን ከልማት አጋሮች ጋር በጋራ በመሆን ያለውን ችግር ለማቃለል ተጠናክሮ የሚሠራ መሆኑን ወ/ሮ አዳነች አስረድተዋል፡፡
ከመሠረታዊ የገቢ ምንጫቸው ተፈናቅለው በቂ ካሳ ያልተሰጣቸውን አርሶ አደሮችንና የመኖሪያ ቤታቸውን አጥተው በእንግልት ላይ ላሉ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በተለየ ሁኔታ ልዩ ትኩረት በመስጠት የዕድሉ ተካፋይ እንዲሆኑ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ የጋራ የመኖሪያ ቤት ዕድለኛ ለሆኑትና በልማት ምክንያት ተነስተው ለነበሩ ነዋሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል፡፡
የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሰናይት ዳምጠው (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ የ20/80 ዕጣ ከደረሳቸው 32,653 ነዋሪዎች ውስጥ ውላቸውን አጠናቀው የጨረሱት 7000 ሲሆኑ ቁልፍ የተረከቡ ደግሞ 245 እንደሆኑ በቀጣይም ከመስከረም 22 እስከ ጥቅምት 12 ቀን ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ርክክቡ እንደሚቀጥል አክለዋል፡፡ የ40/60 ዕጣ ከወጣላቸው 18,576 ቤቶች ውስጥ 17,216 ቤቶች ውላቸውን እንዲጨርሱ የተደረገ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 14,296 ዕድለኞች ቁልፋቸውን መረከባቸው ተጠቁሟል፡፡ የተቀሩትም በተመሳሳይ ሁኔታ በቀጣይ እንደሚረከቡ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
በከተማው ያለውን የቤት ችግር ለመፍታት የተለያዩ አማራጮችን በማቅረብ ሰፊ ሥራዎችን በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ሰናይት (ኢንጂነር) ጠቁመው፣ ከእነዚህ ውስጥም የ20/80 እና የ40/60 የጋራ የመኖሪያ ቤት ፕሮግራም እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የርክክብ መርሐ ግብሩም የተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ አመራርና የአገር ሽማግሌዎች በተገኙበት መስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡ ለ13ኛ ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባለዕድለኞችንና የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን የጋራ የመኖሪያ ቤት የመሠረተ ልማት ለማሟላት ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል ለተባሉ አመራሮች ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡