Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትያልተደላደለው ምርጫ ጉዳይ

ያልተደላደለው ምርጫ ጉዳይ

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ኮቪድ 19 ከሌሎች ነባርና አዳዲስ ችግሮቻችን ጋር እየተረባረበ ወቅታዊውን ፖለቲካችንን ለብቻው፣ ከእነ ብዙ ጣጣው ከመጋፈጥ አግዶናል፡፡ ኮቪድ 19 ከእነ ጭራሹ በዓለምም፣ በኢትዮጵያም ባይኖር ኖሮ እ.ኤ.አ. የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማት ያገኘች ኢትዮጵያ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛና ሁሉን አቀፍ የሆነ፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ፣ መራጩ ፈቃዱን በነፃነትና በሚስጥር የሚገልጽበት ዋስትና ያለው ምርጫ ማካሄድ ትችላለች ወይ? የሚለውን ጥያቄ ብቻውን እንዳንጋፈጠው ከልክሎናል፡፡ ይኼን ጥያቄ ያለ ማድበስበስ፣ ያለ ፍርኃትና ያለ ኃፍረት ደፍረን እንዳንመልሰው የ‹‹ማርያም መንገድ›› ሰጥቶናል፡፡ ከ‹‹ጉድም አውጥቶናል››፡፡ ይህ በገዛ ራሱ ታላቅ ጉዳት ነው፡፡ አለባብሶ ማረስ ነው፡፡ በአረም መመለስን የሚያጠናውት በሽታ ነው፡፡

ኮቪድ ራሱ እንኳን ለኢትዮጵያ ለታላላቆቹም አድገናል፣ ተመንድገናል ለሚሉት አገሮች መከራና መዓት ሆኗል፡፡ አሜሪካ የሚባል አገር ‹‹ቢከፍቱት ተልባ›› ሆኖ ተገኝቷል፡፡ አገሬው፣ ዜጋው፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የጤና ባለሙያውና ጠቢቡ ሁሉ በአሜሪካ እያፈረ፣ ከቪየትናም ጋር ሲያወዳድረው አያያዙና ውጤቱ ይገርማል፡፡ አሜሪካ ከአንድ ሚሊዮን ሕዝቧ 22 ሺሕ ቤት የገባ ሕመምተኛ ሲኖራት፣ የቪየትናም ሕመምተኛ ቁጥር 43 ብቻ ነው፡፡ አሜሪካ ከአንድ ሚሊዮን ሕዝቧ ውስጥ 500 ሰው በሞት ሸንታለች፡፡ የቪየትናም ምጣኔ 0.4 ነው፡፡ በሕዝብ ቁጥር ከእኛ ጋር አቻ የሆነችው ቪየትናም ይህን ስጽፍ ፅኑ ታማሚ የላትም፡፡ የአሜሪካ የፅኑ ታማሚ ቁጥር ሕዝብ 18 ሺሕ አልፏል፡፡

ወደ አኅጉራችንና ወደ አገራችን እንመለስ፡፡ አፍሪካ ባለ 1.2 ቢሊዮን ሕዝብ ነው፡፡ የአኅጉሩ የኮቪድ ታማሚ ቁጥር አንድ ሚሊዮን የገባው በነሐሴ ወር ውስጥ ነው፡፡ ከ24 ሺሕ ሰው በላይ ሞቷል፡፡ የአፍሪካም የበሽታው መስፋፋት በተለይም ከሐምሌ ወር ጀምሮ እጥፍ ድርብ እየሆነ መምጣቱ፣ እኛንም የሚመለከትና የሚያስጠነቅቅ ብዙ ትርጉምና አንድምታ እንዲሁም ምክንያት ያለው ነው፡፡ መጀመርያ ነገር የአኅጉራችን ውስጥ የምርመራና የውጤት ነገር ሁሉንም እውነትና እውነቱን ሁሉ የሚናገር፣ ስለዚህም የመከላከሉንና የ‹‹መደናገጡን›› ነገር በቅጡ የሚያስጨብጠን አይደለም፡፡ የዓለም የጤና ድርጀት የምርመራውን ምጣኔ ሲወስን አንድ ምርመራ በአንድ ሺሕ ሰው በሳምንት ይላል፡፡ የአፍሪካ ከዚህ በታች ነው፡፡ ባለሙያዎቹና ባለጉዳዮቹ የሚነግሩን የሚያስፈራ ነገር እውነት ከሆነ እንደ ኒጀርና ደቡብ ሱዳን ያሉ የባሰባቸው አገሮች፣ ከመጋቢት ወዲህ ያደረጉት ምርመራ በጠቅላላውና በድምሩ እንኳን ከአንድ ምርመራ ከአንድ ሺሕ ሰው በታች ነው፡፡ ይህ ደግሞ የበሽታውን/የሕመምተኛውን ሰው ቁጥር ይደብቃል፡፡ ቫይረሱ ያለ ሥጋት ያለ ጥንቃቄ መተላለፉን መዳረሱን በዝምታ ያበረታታል፡፡

የሟቾች ቁጥርም በተመሳሳይ ችግር እውነቱን ሁሉ የሚናገር አይደለም፡፡ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የመንግሥት ተግባርና የዜጎች ግዴታ ገና ከመሬት ባልተናነሰበት የአስከሬን ምርመራ ውጤት፣ የቀብርና ለቀብር ሥነ ሥርዓት ቅድመ ሁኔታ ባልሆነበት አኅጉር (በእኛም አገር ጭምር) ሁሉንም እውነት ማወቅ በጣም አዳጋች ነው፡፡   

ኮቪድ ብዙ ነገር ሠርቶናል፡፡ ብዙ አድርጎናል፡፡ በጅምላ የምናውቀው ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ ለስንት ሰዎች ምርመራ እንዳደረግን፣ በስንት ሰው ላይ ቫይረሱ እንደተገኘ፣ እንዲሁም የሕዝብ ጤና ጥበቃ ዘርፉና ሚዲያው ድንገትም፣ ዝም ብለውም ‹‹ባቋቋሙት›› ቀደም ተከተል መሠረት ደግሞ የሞቱትን ሰዎች ቁጥር ነው፡፡ በመላው ዓለም በዚህ በሽታ ብቻ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሰዎች ቁጥር አንድ ሚሊዮን በተሻገረበት በዚህ የመስከረም ወር ሁለተኛው አጋማሽ ላይ፣ አገራችን ከአንድ ሺሕ በላይ ዜጎቿን ቀብራለች፡፡ በየቀኑ ከምንሰማውና ከለመድነው ዕለታዊም ሆነ ጠቅላላ የላቦራቶሪ ምርመራ ‹‹ከበሽታው ያገገሙ››፣ ‹‹በፅኑ የታመሙ››፣ ‹‹በበሽታው የተያዙ››፣ ‹‹ሕይወታቸው ያለፈ›› ቁጥር ውስጥ ግን ሕይወት አለ፡፡ መዓት የሐዘን፣ የሰቆቃ፣ የችግርና የመከራ ትኩስ ወሬና መርዶ አለ፡፡ እዚህ ስታትስቲክስ ውስጥ የምንሰማው በቀጥታም ሆነ በሰው በሰው ከምናውቀው ሰው ሞት ይልቅ፣ አሁን ደግሞ ‹‹የሕክምና ወጪው›› የሆስፒታል ክፍያው አዲስ አስደንጋጭ ክውታ ፈጥሯል፡፡ የሕዝብ የጤና ጥበቃ ሥርዓታችን፣ በተለይም የግል የሕክምና ተቋሞቻችን የማይቀመሱ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ የማይጠጓቸው መሆናቸውን ያለ ኃፍረት፣ ያለ ወግ እያረዳን ነው፡፡

በመጋቢት 2012 ዓ.ም. የተዘጉት የአንድ አገር ሕዝብ ያህል (28 ሚሊዮን ሕፃናትና ታዳጊዎች) የሚውሉባቸውና የሚመላለሱባቸው ትምህርት ቤቶች ከመስከረም እስከ ሰኔ በሚዘረጋው አዲሱ የ2013 ዓ.ም. የአካዳሚ ዓመት/ዘመን ይከፈቱ እንደሆነ አገር በመደበኛም፣ መደበኛ ባልሆነ አሠራርም እየመከረ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ነፃ ምክክር፣ አንፃራዊ ነፃ ምክክርና ውይይት በደራበትና እንደ ነገሩና እንደ አቅሚቲ ይህንን ጉዳይ ማስተናገድ በተቻለበት የአገራችን ‹‹ሲቪክ ምኅዳር›› ውስጥ፣ ትምህርት ቤቶች ይከፈታሉ፣ አይከፈቱም ክርክር በነፃ እየተሰማ ነው፡፡ መንግሥትም፣ የመንግሥት የሥልጣን አካላትና ሹማምንቶቻቸውም የፓርቲ ፖለቲካ ባጠናገረው ዕይታ እታማለሁ፣ እከሰሳለሁ ሳይል የጤና ሳይንስን መሠረት አድርጎ አቋሙንና ዕርምጃውን እየገለጸ ነው፡፡ በሌላ ቦታ በተለይም በምዕራብ አገሮች ውስጥ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በትራምፕ አሜሪካ የትምህርት ቤቶች መከፈት ጉዳይ የተበለሻሸበት ዓይነት ፖለቲካ በሌለበት አገራችን ውስጥ (በአሜሪካ የትምህርት ቤቶች መከፈት/አለመከፈት ከወላጆች ወደ ሥራ መመለስ ጋር የተያያዘ ጣጣ አለበት)፣ የኢትዮጵያ የትምህርት ባለሥልጣናት አቋማቸውንና ከአቋማቸው የሚመነጩ ዕርምጃዎቻቸውን ነፃ ሆነው፣ ከሌላው ዘርፍ በተለየና ብዙም በማያሳማ ሁኔታ ነፃ ሆነውና ነፃ መስለው ራሳቸውን ችለው መወሰን ይችላሉ፡፡ የቻሉም ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ይመስኛል የመደበኛው ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር  ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) ትምህርት ቤቶችን የምንከፍተው ጊዜው ስለደረሰ ሳይሆን፣ መክፈት የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ ስለቻልን ወይም የቻልን እንደሆነ ነው ማለት የቻሉት፡፡

ይህ ከፍተኛ ትርጉምና አንድምታ እንዲሁም ትምህርት ያለው ምሳሌ ነው፡፡ በተለይም ለምንነጋገርበት ዋናው የምርጫ ጉዳይ ትልቅ ማነፃፀሪያ ነው፡፡ ጉዳዩን ለማብራራት መጀመርያ የዚህን የትምህርት ጉዳይ ከኮቪድ አኳያ አፍታትተንና ጠጋ ብለን በአጭሩ እንመልከት፡፡ ለዚህ አገልግሎት ሲባል አሁን ያለንበትን የሽግግርና የለውጥ ፖለቲካ ለጊዜው እርግፍ አድርገን እንርሳ፡፡ የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣ አገር አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ከምትገባባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ መግባት ደግሞ ለመንግሥት የተለየ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡ በአገራችን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ መግባት ሳያስፈልግ፣ ለምሳሌ በአዋጅ ቁጥር 200/1992 አንቀጽ 16(3) መሠረት ትምህርት ቤቶችን መዝጋት፣ በወረርሽኝ በሽታ የተያዙ ሰዎችን ከሥራ ቦታቸው ለተወሰነ ጊዜ የማግለልና ሌሎች ተመሳሳይ ዕርምጃዎችን የመውሰድ ሥልጣን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ነው፡፡ ኮቪድ ይህንን ሁሉ የሚያሟላ አደጋና ሥጋት ነው፡፡

በዚህ መነሻና ምክንያት ከመጋቢት 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች ይከፈታሉ? አይከፈቱም? የሚለው ጥያቄ አዲሱ የትምህርት ዘመን ሲጀመር መነሳቱ ተገቢ ነው፡፡ ለሚሰጠው ውሳኔ መሠረት የሚሆነውም ሳይንስ፣ ሳይንሱ ነው፡፡ ኮቪድ የሚገኝበት ሁኔታ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶችን የምንዘጋው ሕይወትን ለመጠበቅ ነው፡፡ የሕፃናት ሕይወትን፣ የሌሎችን ሰዎች ጤንነትን ለመጠበቅ የሚወሰደው ይህ ከተለመደው አሠራር የወጣ የመከላከያ ዕርምጃ ሌላ መብት ይጋፋል፡፡ የመማር መብትን ያስተጓጉላል፡፡ ከማስተማር የወላጆች ግዴታ ጋር ጭምር ይጣላል፡፡ ይህ ግን ተገቢ ዕርምጃ ነው፡፡

ዛሬ ትምህርት ቤቶች ይከፈቱ፣ የለም አይከፈቱም በሚለው ጤናማ አቋምና ክርክር ውስጥ በእኛ አገር ሁኔታ የጤናና የትምህርት ብቻ ሳይሆን፣ በመጠኑም ቢሆን (እንደ አሜሪካ አገር የሚያናጋ ባይሆንም) የኢኮኖሚና የቢዝነስ ጉዳይም አለበት፡፡ በተለይም የግል ትምህርት ቤት መምህራንና ሠራተኞች ገቢ ያሳስባል፡፡ መምህራን የተሰማሩበት ትምህርት ቤትም የንግድ ተቋም ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ በዋናው የውሳኔው መሠረት ማለት በሕዝብ ጤና ሳይንስ ላይ እንጫን ማለታቸው አይቀርም፡፡ ይህ ግን ጤናማ ነው፡፡ በተለይም የሰዎችን መደራጀት፣ ንቁ ተሳታፊ መሆን፣ እርስ በርስም በነፃና ያለ ከልካይ መነጋገር፣ መመካከር የሚያስችል፣ ይህንንም በማድረግ በአካባቢያቸው፣ በአገራቸው፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አወቃቀሮች ላይ ተፅዕኖ ማሳደር የሚያበቃና የሚያደፋፍር ሲቪክ ስፔስ (ሲቪክ ምኅዳር) ባለበት አገር ጉዳዩን ለመወሰን ብዙ ችግር የለበትም፡፡

በአገራችን በየጊዜው በወጡ ሕገ መንግሥቶች ውስጥ ተጽፈው የኖሩት የመደራጀት፣ ሐሳብን የመግለጽ፣ የመሰብሰብ መብቶች መኗኗሪያ ሆነው ባለማወቃቸው የተባለው የሲቪክ ምኅዳር የሚያወላዳ አይደለም፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ቢያንስ ቢያንስ የቅርብ ባለጉዳዮች፣ ወላጆችና መምህራን ድምፃቸውን ማሰማታቸው አይቀርም፡፡ የምንሰማውና ስንሰማው የከረምነውም (ለዚያውም ይህን በመሰለ እልም ያለ ድፍርስ ፖለቲካ ውስጥ) ይህንኑ ነው፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር አሁን ጉዳዩ በሚገኝበት የዕድገት ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የምንከፍተው፣ ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ቤት መሄዳቸውን የምንፈቅደው የ2013 ዓ.ም. ዓመት የትምህርት ዘመን (ኮቪድ ሳይጠፋ፣ እንዲያውም እየተስፋፋ እያለ) ስለደረሰ ሳይሆን ስለተዘጋጀን ነው ያለውም ለዚህ ነው፡፡

ወደ ተከታዩ ጉዳይ የማልፈው ይህን አባባል መነሻ በማድረግ ነው፡፡ ተከታዩ ጉዳይ ደግሞ ምርጫ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ምርጫ የምታካሂደው ጊዜው ደረሰ ብላ ነው? ወይስ ምርጫ ማድረግ የሚያስችል ዝግጅት አድርጊያለሁ፣ የሚያስፈልገውን መሰናዶ ሁሉ አድርጌያሁ ብላ ነው? ዋናው ጥያቄም ይህ ነው፡፡ መግቢያዬ ላይ ኮቪድ ‹‹ጉድ ሠርቶናል›› ነፃ፣ ቀጥተኛ ትክክለኛና ሁሉን አቀፍ የሆነ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ፣ መራጩ ፈቃዱን በነፃነትና በሚስጥር የሚገልጽበት ምርጫ ማካሄድ እንችላን ወይ? የሚለውን ጥያቄ ፊት ለፊት እንዳንጋፈጠው፣ አድበስብሰን እንድናልፈው ረድቶናል፡፡ ከዚህም የተነሳ ብዙ ጉም የሠሩ ጥልፍልፍ ነገሮች ውስጥ ገብተናል፡፡

ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥራና ግዳጅ ውስጥ የገባነው፣ በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ ‹‹ሕጉ ምን ይላል?›› ለሚለው ጥያቄ የሕጉ ቃል ይኼ ነው ማለት የሚችለውና ሥልጣን የተሰጠው አካል ይወስነው ወደሚል የ‹‹መጨረሻ›› አማራጭ ‹‹እጉም›› ያልነው፣ ምርጫማ አይራዘምም የሚል ወገን ወይም ክልል ጋር የለየለትና አደጋ ያረገዘ የካብ ለካብ መተያየት ውስጥ ያስገባን፣ . . ኋላና አሁን መጨረሻ ላይ ደግሞ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ምን ዕለተ ደይን ለሚሉ አማኞች/ታጋዮች/ ፖለቲከኞች የዳረገን፣ ፖለቲከኞቻችን በለውጡና በሽግግሩ ላይ አንድ የጋራ መገናኛ ግቢ ውስጥ መሰብሰብና መሰማማት አለመቻላቸው ነው፡፡

የለውጡ ዓላማ ሕገ መንግሥት መቀየር ወይም ሕገ መንግሥቱን ማረም አይደለም፡፡ የዚህ ምክንያት ሕገ መንግሥቱን የሚቃወሙ፣ ይሻሻል፣ ይታረም የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ሕገ መንግሥቱን የሚደግፉ፣ መሻሻሉን የሚቃወሙ በመኖራቸው ነው፡፡ ዋናው ችግር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ የሐሳብ ልዩነት መኖሩ አይደለም፡፡ የሐሳብ ልዩነትን ማስተናገድ የሚችል ፍጥርጥር ሲያልፍ ባልነካው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ፣ በተለይም የጥላቻ ፖለቲካ ውስጥ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተዘረዘሩት መብቶችና ነፃነቶች፣ እንዲሁም ኃላፊነቶች መኗኗሪያ ይሁኑ ከሚል የበለጠ የጥበብም የፖለቲካም መጀመርያ የሌለ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ይህን ሕገ መንግሥት ይዘን ከአፈና ወደ ሕገ መንግሥታዊነት እንለፍ፡፡ የስም ጌጥ ከሆነ ሕገ መንግሥት ወደሚተገበር ሕገ መንግሥት እንግባ፡፡ ሽግግር የተባለውም ይኼው ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብቶች፣ የምርጫ መብት ራሱ፣ ለምርጫ መብት ዕውን መሆንና መረጋገጥ መሠረትና ቅድመ ሁኔታ የሆኑት የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት መብቶች እውነትም መኗኗሪያ እንዲሆኑ ለማድረግ ደግሞ የመንግሥት አውታራት ከየትኛውም ፓርቲ/ቡድን ወገንተኛነት ነፃ ሆነው መታነፅ አለባቸው፡፡ ምርጫ ውስጥ ስለመግባት በምርጫ ስለማሸነፍ፣ በምርጫ አሸንፎ ቢሮ ገብቶ ሥልጣን ስለመያዝ ከምር መነጋገር የሚቻለው፣ መጀመርያ ቅድሚያ የሚሰጠውን የለውጥና የሽግግር ሥራችንን ስንሠራ ነው፡፡ ይህ በጭራሽ የማይዘለል ሥራ ነው፡፡ ይህ የሚገባው ጠፋ፣ ይህ የሚገባው ጠፍቶ በጋራ አጀንዳ ላይ መረባረብ ቸገረ፡፡ ኮቪድ የመጣው በዚህ መካከል ነው፡፡ ኮቪድ ደግሞ ዋናውን ጥያቄ ፊት ለፊት እንዳንጋፈጠው በግማሽ ዓመት ያህልና ከዚያም በላይ አዘናጋን፡፡

ለዚህ ነው ምርጫ ማካሄድ ያለብን 2012 ዓ.ም. ስለመጣ ነው? ወይስ ምርጫ የሚጠይቀውን ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የሚሻለውን አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ስላሟላን ነው? ብሎ የመጠየቅ ነገር ጠፍቶብን ለብዙ ጣጣና መከራ፣ ለብዙ ጠንቅና መዘዝ ተዳረግን፡፡ ለውጡ ከስደትና ከእስር ቤት የጠራቸው ፖለቲከኞችን ለእስራትና ለስደት የዳረጋቸው ነፃነትና እኩልነት የለም ብለው በመታገላቸው ጭምር ነው፡፡ አገር ውስጥ የመታገሉ ጉዳይ የተስተካከለ የጨዋታ ሜዳና ሕግ ባለመኖሩ ምክንያት ወደ ውጭ የሚገፋ፣ የሚያባርር፣ ወደ እስር ገፍትሮ የሚያስገባ በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ችግር ሳያስወግዱ፣ ይህን ጎዶሎ ሳይሞሉ ወደ ጨዋታ ወደ ምርጫ ዘሎ መግባት የተለየ ውጤት ስለማይኖረው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሽግግሩ መሰናዶ ይፈልጋል፡፡ መሰናዶውም የጨዋታ መሰናዶና ዝግጅት ዓይነት ነው፡፡ የተስተካከለ የሜዳ ዝግጅት ይፈልጋል፡፡ በዚህ የተስተካከለ ሜዳ ውስጥ እንኳን በጨዋታው አጋማሽ ላይ የተጫዋች ቡድኖች የሥፍራ ቅያሪ ይደረጋል፡፡ ጨዋታው በችሎታ፣ በብቃትና በሥነ ምግባር የታነፁ ሰዎች የሞሉት ተቋማዊ አቅም መገንባትን ይጠይቃል፡፡ ፍትሐዊ የጨዋታ መርሐ ግብርና ገለልተኛ ዳኝነት የግድ ይኑረኝ ይላል፡፡ ለጨዋታው ጀርባ ሰጥቶ በሥራው ላይ፣ በጥበቃ ሥራው ላይ የማተኮር ንቁነት ያላቸው የፀጥታና የሕግ አስከባሪዎች ይሻል፡፡ አቤቱታዎችን ያለ አድልኦ ሰምቶና መርምሮ ትክክለኛ ውሳኔ የሚሰጥ አካል ይፈልጋል፡፡ እነዚህ ሳይሟሉ ጨዋታ እንጫወት ማለት መቀለድ ነው፡፡ ምርጫም ተመሳሳይ ቅድመ ሁኔታዎችንና ዝግጅቶችን ይሻል፡፡

መጋቢት 2010 ዓ.ም. ወዲህ የሚነሳውን የኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ መመለስም ያለብን ምንና የትኛውን ዝግጅት አሟልተን ወደ ምርጫ እንግባ እንጂ፣ ውሸት ሆኖ የኖረውን ሲያታልልና ሲያጭበረብር ኖሮ በአምስተኛው ምርጫ ማግሥት (ኅዳር 2008) ‹‹ኧረ ንጉሡ ራቁቱን ነው›› ተብሎ የተጋለጠውን የውሸት ምርጫና ዘመኑን መነሻና ማሥሊያ በማድረግ አይደለም፡፡

ከምርጫ ባህርይዎች መካከል አንዱ ‹‹በየጊዜው›› የሚደረግ፣ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ መካሄድ ያለበት መሆኑ ነው፡፡ የምርጫን ይዘት ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 54(1) ድንግጎታል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ‹‹ሁሉን አቀፍ ነፃ፣ ቀጥተኛ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ ይላል፡፡ 2012 ዓ.ም. ውስጥ ከመስከረም የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ በፊት አንድ ወር አስቀድሞ ምርጫ ካልተካሄደ ሞቼ እገኛለሁ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ አሁን ደግሞ መስከረም 25ን ዕለተ ደይን አድርጎ ማሸበር ይዟል፡፡ ከምርጫ ዘመን ወደ ሌላ የምርጫ ዘመንማ ላለፉት 30 ዓመታት ስንንከባለል ኖረናል፡፡ የሕገ መንግሥት ጉባዔ አባላትን ሳይጨምር ለአምስት ጊዜ ምርጫ አድርገናል፡፡ ከኢሕአዴግ አምባገነንነት ግን ወጥተን፣ የሕዝብ ድምፅንና ፍላጎትን ከድምፅ ካርድ ጋር አግባብተን አናውቅም፡፡

እንሞትለታን የሚሉት ሕገ መንግሥት መኗኗሪያ ይሁን ሲባል የእስካሁኑ ኃጢያታቸውና አንጓላይነታቸው የሚያሳድዳቸው የውሸት ሕገ መንግሥታውያን፣ በመስከረም 25 የሚያስፈራሩትና የሚያታልሉት ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፡፡ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል›› የሚለውን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 58(3) ‹‹ጫፍ›› ይዘው ነው፡፡

ከእነዚህም ጋር እነሱን የታገሉ ኃይሎች ‹‹ግንባር›› ፈጥረዋል፡፡ መጀመርያ ነገር በ2007 ዓ.ም. ምርጫ ‹‹ለአምስት ዓመታት›› ከተመረጠው፣ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት (ማለትም 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ) ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል ከተባለለት አምስተኛው ምርጫ አደራጀው ከተባለው ምክር ቤት/ምክር ቤቶች ጋር፣ ይህ ምክር ቤት/እነዚህ ምክር ቤቶች መስከረም የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ 2008 ዓ.ም.  ያቋቋመውን መንግሥት ከኅዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለመጣልና ለማፍረስ የታገሉ የፖለቲካ ኃይሎች በአንቀጽ 58(3) ከተወሰነው/ከተቆረጠው ቀን ጋር ምን ቀጠሮ ሊኖራቸው ይችላል? ሌላም አለ፡፡ ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፣ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል›› ማለት ምን ማለት ነው?  

የአምስት ዓመቱ የሥራ ዘመን ከማብቃቱ አንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ካልተጠናቀቀ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን አያበቃም ማለትስ ቢሆን? እንዲህ ያለ ሕገ መንግሥትና የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚያውቅና የሚታገስ አገርና ሕገ መንግሥታዊና ፓርላሜንታዊ ዴሞክራሲ መኖሩን ያውቃሉ?

ይህ ሁሉ ግን የሚነሳው ሕገ መንግሥቱ ምን ይላል? ሕገ መንግሥቱ ይታይ፣ ይገለጥ የሚል የትርጉም ጥያቄ ከመጣ ነው፡፡ አዎ እዚያ ውስጥ ገብተናል፡፡ ምርጫም አራዝመናል፡፡ ከዚያ በፊት ግን የዘለልነው ዋና ጉዳይ አለ፡፡ ይህ ምርጫ ስድስተኛው ምርጫ ሳይሆን አዲስ የለውጥና የሽግግር ጊዜ ምርጫ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ምርጫ ደግሞ ከቀድሞዎቹ ተከታታይና ፋይዳ ቢስ ምርጫዎች ውልቃት በኋላ የመጣ የመጀመርያው ምርጫ በመሆኑ አዲስ ቀጠሮ፣ አዲስ የመዘጋጃ ጊዜ ጠይቃል፡፡ አዲሱ የምርጫ የጊዜ ቀጠሮ የሚወሰነውና መቆጠር የሚጀምረውም ለውጡንና የሽግግርን ሒደት ካስጀመረው ሁነት አንስቶ ነው፡፡ እና ምን ምን ዝግጅቶች አድርገን ምንና ምን አሟልተን ምርጫ እናድርግ ይባላል፡፡ በኮቪድ ጊዜ ምርጫ ማድረግ አይቻልም የተባለው በእኛ አቅምና የዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎች አያያዝና ባህል ኮቪድ ‹‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ›› ስለሆነ ነው፡፡

አሁን ከብዙ ውጣ ውረድ፣ ብዙ ጣጣና መፈነጋገጥ ካስከተሉ ውልቃቶች በኋላ ኮቪድንም እየተከላከሉ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ብለናል፡፡ አሁንም ልብ ሊባል የሚገባው በለውጡና በሽግግሩ ጎዳና ላይ የሕዝብ ጤና ጠንቅ የጋረጠውን መሰናክል እያዩና እየተጠነቀቁ ማለፍ፣ ጉዞ መቀጠል ይቻላል መባሉን እንጂ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟልተናል ማለት አይደለም፡፡ ይህንን ይለፍ ገና የሰጠን የለም፡፡ ትናንትም ዛሬም ዝም ብሎና ዘራፍ ብሎ ምርጫ ካላካሄድኩ ሞቼ እገኛለሁ ማለት የ1987፣ የ1992፣ የ1997 መንገድ ነውና ከዚያ ቅዠት እንንቃ፡፡ መስከረም የመጨረሻ ቀን ሰኞንም የአገር ዕለተ ደይን (የምፅዓት ቀን) ማድረግም የውሸትና የቅጥፈት ኃፍረት የለሽ ‹‹መላ›› ነው፡፡ ‹‹ከእኔ በስተቀር ሌላ አምላክ አይመለክም›› ብሎ የምድር ሕግ ማውጣት ነው፡፡

የኢሕአዴግ የእስከ ዛሬው መንግሥታዊ ገዥነት ከነፃና ከትክክለኛ ምርጫ መንጭቶ የሚያውቅ ይመስል፣ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን የወጣበት ብቸኛ መንገድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲውን በነፃነት ከሌሎች ጋር አወዳድሮ በተዓማኒ የምርጫ ሒደት በተገኘ የድምፅ ውጤት ሆኖ የሚያውቅ ይመስል፣ በኢሕአዴግና በመስመሩ የመመራት ነገር ፓርቲው/ግንባሩ ከሌሎች ፓርቲዎችና ሐሳቦች ጋር ውድድር ገጥሞ፣ ሐሳብን በሐሳብ ረትቶ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ይህንንም በሕዝብ ነፃ ድምፅ አረጋግጦ ይመስል መስከረም 25 እና ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ መንግሥት የላትም ማለት ሕዝብን ደግሞ ደጋግሞ መናቅ ነው፡፡ ይልቅስ በመሰናዶው ላይ እንረባረብ፣ ዴሞክራሲን ማደላደል ላይ እንረባረብ፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...