Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የገንዘብ ለውጡና ሕገወጥ ንግድ 

መንግሥት የብር ኖት እንዲለወጥ ከወሰነባቸው ምክንያቶች አንዱ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስና የተረጋጋ ገበያ ለመፍጠር በመሻት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ይህ ዕቅዱ ትክክል እንደሆነ በርካቶች የሚስማሙበት፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም ትክክለኛ ዕርምጃ እንደሆነ ሲገልጹ የሰነበቱት ጉዳይ ነው፡፡

ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ባንክ የማያውቀው ገንዘብ በሚሽከረከርበት ኢኮኖሚ ውስጥ፣ ከሚመረተውና ገበያ ላይ ከሚገኘው ምርትና ሸቀጥ በላይ በርካታ ገንዘብ ጥቂቱን ምርት የሚያሳድድበት ሁኔታ እንደተፈጠረ ይህም የዋጋ ግሽበት እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከፍተኛ ክምችት ያለው ገንዘብ መደበኛ ኢኮኖሚው ውስጥ ከባንክ ውጭ በመንቀሳቀሱ በርካታ ሕገወጥ ድርጊቶችን ለመፈጸም አመቺ ሆኗል፡፡ ሕገወጥ ተግባራት ገበያውን መረበሻቸውና ለተጋነነ ዋጋ ምክንያት መሆናቸው እርግጥ ነው፡፡

ከባንክ ውጪ በሚዘዋወረው ገንዘብ ምክንያት የሚፈጠር የተናወጠ የግብይት ሥርዓት፣ በጥቅሉ ሲታይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከመጉዳቱ ባሻገር፣ የዋጋ ግሽበት ሥር እንዲሰድና የዜጎችን አቅም እንዲፈታተን የሚችልበት ጉልበት ማግኘቱ ትልቁ ችግር  ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢኮኖሚውን ከሚፈታተኑ ሥርዓት አልበኝነቶች መካከል ሕገወጥ ንግድ እንዲስፋፋና ሕጋዊ ነጋዴዎችም በወጉ እንዳይሠሩ ደንቃራ የሆነው የኮንትሮባንድ ንግድ መበራከት ይጠቀሳል፡፡ የዚህ ንግድ ሥራ መዛመት አንዱ መነሻው ከባንክ ውጪ የተከማቸው ገንዘብ ነው፡፡

እንዲህ ያለው ሕገወጥ ተግባር በሰፋና በተስፋፋ ቁጥር የሚያስከትለው ቀውስ ኢኮኖሚውን ሊደፍቀው እንደሚችል ሲገለጽ፣ ማሳያው የዋጋ ግሽበት አንዱ መሆኑ ነው፡፡ የዜጎች የገቢ አለመመጣጠን እንዲስፋ ማድረግ፣ ጥቂቶች ብቻ የሀብት ባለቤቶች የመሆን አቅም እንዲኖቸው ማድረግ በኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎችቹ ሲገለጽ፣ ሄዶ ሄዶ የመንግሥትን አቅም በመፈታተን ሥርዓት የማስፈን ብቃቱንና መንግሥትነቱን አደጋ ላይ የሚጥልበት መዘውር መፍጠሩ አይቀሬ ሊሆን ይችል ነበር፡፡

ስለዚህ የገንዘብ ብር ኖት ለውጡ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ዘርፈ ብዙ ከመሆናቸው አንጻር በተለይ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከልና ጤናማ የገበያ ሥርዓት እንዲፈጠር በማድረግ እንዲሁም ሸማቹን መደገፍ ጭምር ነው ከተባለ እንደባለው የሚፈለገውን ለማምጣት በአንድ የብር ለውጥ ክዋኔ ብቻ የሚፈለገው ግብ ላይ አያደርስም፡፡

የገንዘብ ለውጡ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ በትክክል የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስ የሚያግዙ አሠራሮችን ሥራ ላይ ማዋል፡፡ ባለድርሻ አካላት ተረባርበው መሥራትን የሚጠይቅ ጭምር ነው፡፡ ገበያውን የሚያውኩ እንደ ኮንትሮባንድ ያሉ ንግዶችን አደብ ማስያዝን ጭምር ይጠይቃል፡፡

በጥሬ ገንዘብ የሚፈጸሙ ግብይቶችን እየቀነሱ እንዲሄዱ ማድረግና አሁን ካለው የተሻለ ሕግ መቅረጽንም ይጠይቃል፡፡ በእርግጥ ይህንን ለማድረግ ብሔራዊ ባንክ ተግባራዊ እያደረገ ቢሆንም ወቅታዊውን ሁኔታ ያገናዘቡ አዳዲስ አሠራሮች እንዲተገበሩ ካልተደረጉ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን ሊገቱ የሚችሉ ዘዴዎችን ሥራ ለይ ማዋል ካልተቻለ የዋጋ ግሽበቱን እንዲህ በቀላሉ ለማርገብ ከባድ እንደሚሆን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

በተለይ የአገሪቱን የዋጋ ግሽበት ከሚያሳድጉ ምክንያቶች አንዱ በጥሬ ገንዘብ ከባንክ ውጪ የሚፈጸሙ ግብይቶችና በጥቁር ገበያ በሚሸመት የውጭ ምንዛሪ የሚፈጸሙ ግብይቶች መሆናቸውን ተገንዝቦ ለዚህ የሚበጅ ዕርምጃ መውሰድም ይገባል፡፡ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን ለገበያ የሚያቀርቡ አካላት አጠቃላይ የግብይት ሒደቱን መፈተሽም የግድ ይላል፡፡

በተለይ የዋጋ ግነት የሚታይባቸውን ምርቶች የሚያቀርቡ ማንኛውንም ግብይት ሲፈጸም ባንክን መሠረት አድርገው እንዲሠሩ ማድረግ ግድ ይላል ማለት ነው፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ ርካሽ የሚባሉ ምርቶች ኢትዮጵያ ላይ ዋጋቸው እንዲቆለል የሚሆነው ግብይቶቹ ባንክ ሳይረግጡ እዛው አየር በአየር ስለሚፈጸሙና አጠቃላይ የግብይት ሒደቶች በግድም እንዲዘምኑ በማድረግ ቁጥጥር ማድረግ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል ይጠቅማሉ፡፡

በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ለዋጋ ግሽበት መንስዔ ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ገደብ የሌለው የትርፍ ህዳግ መኖሩ ነው፡፡ በግብይት ውስጥ እንደ ትልቅ ነቀርሳ ሆኖ  የሚታየው የትርፍ ህዳግ ልቅ መሆን ነው፡፡

በነፃ ገበያ ስም ስንጥቅ ብቻ ሳይሆን ሰቅጣጭ በሆነ መንገድ የሚያተርፉበት መጠን ገበያውን ስድ አድርጎታል፡፡ ስለዚህ በተለይ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች  የትርፍ ህዳግ እንዲኖር ማድረግ ካልተቻለና ሌሎች አጋዥ ሥራዎች ካልተሠሩ፣ የዋጋ ግሽበትን መከላከል አስቸጋሪ  መሆኑ አይቀርም፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ለዋጋ ግሽበት ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው ሌላው ጉዳይ የባንኮች የብድር ወለድ ምጣኔ ከፍተኛ ሆኖ መቆየቱና ይህንን የሚገድብ አሠራርም ሆነ ሕግ ያለመኖሩ ነው፡፡ በእርግጥ ለብድር የሚውል ገንዘብ እጥረት መኖሩ የብድር ምጣኔውን ሊያሳድገው የሚችልና አንዳንድ የመንግሥት አስገዳጅ ሕጎች ለምሳሌ እንደ 27 በመቶ የቦንድ ግዥን የመሰሉ መመርያዎች ለብድር ወለድ ምጣኔው ዕድገት አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡

ሌሎች ምክንያቶችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አሁን ደግሞ የ27 በመቶው የቦንድ ግዢ መመርያ ተነስቷል፡፡ በሰሞኑም የብር ለውጥ ባንኮች ያላሰቡት አዳዲስ ቆጣቢዎች ከማግኘት በላይ በመቶ ሚሊዮኖች የሚሆን አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ እየሰበሰቡ መሆናቸውም ታሳቢ ተደርጎ የወለድ ምጣኔያቸውን ተመጣጣኝ እያደረጉ ካልተሠራ የብር ኖት ለውጡ ብቻ የዋጋ ግሽበትን መቀነስ አይችልምና ከብር ኖቱ ለውጥ መጠናቀቅ በኋላ የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ተጨማሪ ሕግጋት ያስፈልጉናል፡፡ ተጨማሪ አሠራሮችን መተግበርን ይጠይቃል ማለት ነው፡፡ 

ፖሊሲ አውጪዎችና ሌሎቹም ከብር ለውጡ የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ለዋጋ ግሽበቱ አጋዥ የሚሆኑ ፖሊሲዎችን ማሰላሰልና የብር ኖት ለውጡ ያስገኘውን ውጤት በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሰዓት እንደ ሸማች የዋጋ ንረቱን ከብዷል፡፡ መፍትሔም ያሻል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት