Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዳሸን ባንክ ለጎርጎራ ኮይሻና ወንጪ ፕሮጀክቶች 30 ሚሊዮን ብር መደበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዳሸን ባንክ ቦርድ አመራር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ‹‹ገበታ ለአገር›› የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ በጎርጎራ፣ በወንጪና በኮይሻ ለሚገነቡ የቱሪስት መስህቦች ለእያዳንዳቸው 10 ሚሊዮን ብር በመመደብ በጠቅላላው 30 ሚሊዮን ብር እንደሚያዋጣ አስታወቀ፡፡

ሰሞኑን የባንኩ የቦርድ ውሳኔ  የሰጠበት ዓብይ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ባቀረቡት ጥሪ መሠረት፣ ‹‹ገበታ ለአገር›› በተሰኘውና በጎርጎራ፣ በወንጪና በኮይሻ ለሚገነቡት መስህቦች ለእያንዳንዳቸው አሥር አሥር ሚሊዮን ብር የሚደርስ ሆኖ በጠቅላላው 30 ሚሊዮን ብር ለማዋጣት መወሰኑ ነው፡፡ የባንኩ ቦርድ ውሳኔ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት ባሻገር በሸገር ፕሮጀክት የታየውን ውጤት መነሻ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡

ባንኩ ለአገራዊ ፕሮጀክቶች ከሰጠው ድጋፍ ባሻገር አዲሱን የብር ኖት ወደ ገበያ ማስገባት ከተጀመረ ሁለት ሳምንት ማስቆጠሩን በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ የብር ኖት ለውጡ ትግበራ የተጀመረበትን 15ኛ ቀን በማስመልከት ዳሸን ባንክ በሰጠው መግለጫ፣ በሁለት ሳምንት ውስጥ ከ25 ሺሕ በላይ አዳዲስ ደንበኞች አዲስ የቁጠባ ሒሳብ መክፈታቸውን አስታውቋል፡፡ ባንኩ በእነዚህ አዳዲስ ደንበኞች ብቻ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ ችሏል፡፡ የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ሐሙስ መስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት፣ ባንኩ በሁለት ሳምንት ውስጥ ያሰባሰበው አዲስ የቁጠባ ሒሳብ 700 ሚሊዮን ብር እንደሆነና ይህም ከብር ለውጡ ጋር በተያያዘ ዜጎች በእጃቸው የሚገኘውን ገንዘብ ወደ ባንክ እያመጡ እንደሚገኙ ያሳያል ብለዋል፡፡

በዳሸን ባንክ ብቻ በየቀኑ ከ1,660 በላይ አዳዲስ ደንበኞች ሒሳብ እየከፈቱ ሲሆን፣ በየቀኑ ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ አዲስ የቁጠባ ገንዘብ ገቢ መደረጉን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል፡፡ በ15 ቀናት ውስጥ ዳሸን ባንክ በሁሉም ቅርንጫፎቹ የአምስት ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የብር ኖቶች አሠራጭቷል፡፡ ከአምስት ቢሊዮን ብር ውስጥ 4.6 ቢሊዮን ብር ከብሔራዊ ባንክ የቀረበለት ሲሆን፣ ቀሪው መጠን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከሌሎች ባንኮች የተውጣጣ ነው፡፡

አዲሶቹን የብር ኖቶች በሁለት መንገድ ወደ የቅርንጫፎቹ እንደሚያሠራጭ የገለጹት አቶ አስፋው፣ አንዱ በራሱ የገንዘብ ማመላለሻ ተሽከርካዎች አማካይነት ሲሆን፣ ሁለተኛው በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ነው፡፡ ነባሩን የብር ኖት ከማሰባሰብ አንፃር ዳሸን ባንክ በሁሉም ቅርንጫፎቹ 4.2 ቢሊዮን ብር ነባር ኖቶች ወደ ባንኩ ማሰባሰቡን ጠቅሰዋል፡፡ በጠቅላላው ሲታይ ነባሩን የብር ኖት በአዲስ የመተካቱ ሥራ ያለ ምንምና ይህ ነው የሚባል እንከን በሌለው ሁኔታ እያካሄደው ይገኛል ብለዋል፡፡ በለውጥ እንቅስቃሴው በጎ ነገር ተመልክተናል የሚሉት አቶ አስፋው፣ ጉዳዩ አገራዊ በመሆኑ ባንኮች ከውድድር ይልቅ በትብብር እየሠሩ መሆናቸው በጎ ያሉት መገለጫ ነው፡፡

የባንኮች ትብብር የብር ኖት ለውጡ በአግባቡ እንዲተገበር እንዳገዘ ጠቅሰዋል፡፡ ሐሰተኛ ገንዘብ ወደ ዳሸን ባንክ መጥቶ እንደሆነ ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ፣ በገንዘብ ለውጡ ሒደት እንዲህ ያለው ነገር የሚጠበቅ ቢሆንም፣ በጥንቃቄ እየተሠራበት በመሆኑ የሐሰት ብር ኖቶችም ወደ ባንክ እንዳይገቡ የተለያዩ ጥቃቄዎች እየተደረጉ በመሆናቸው ችግር እንዳልተፈጠረ አስታውቀዋል፡፡ አሮጌውን የብር ኖትም በሚመለከት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ተደርጎ ቅበላ እየተደረገ እንደሚገኝ ያመላከቱት አቶ አስፋው፣ የባንኩ ሠራተኞች በተሰጣቸው መመርያ መሠረት እየተፈተሹ እንደሚበቀሉ አስታውቀዋል፡፡ ሆኖም በአንዱ የባንኩ ቅርንጫፍ ሐሰተኛ የቀድሞ የብር ኖት ሊገባ ሲል መያዙን ገልጸዋል፡፡ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ተደርጎ ምርመራ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

አዲሱ የብር ኖት በአሁኑ ወቅትም ሆነ ወደፊትም ቢሆን፣ በኖቶቹ ላይ የተካተቱት የደኅንነት መቆጣጠሪያዎች ጠንካራና በቀላሉ በሐሰተኛ ኖቶች ሊጭበረበሩ የማያመቹ በመሆናቸው፣ ሥጋት እንደማይገባቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የአዲሱን የብር ኖት ለመቅዳት  እንደተሞከረ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በአዲሶቹ የብር ኖቶች ተመሳስሎ የተገኘ ሐሰተኛ ገንዘብ ለፖሊስ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ በአንድ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ ይህ ሙከራ ተከስቷል ተብሏል፡፡ ለሙከራ በሚመስል መንገድ የተደረገ እንደመጣ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ አዲሱ ሐሰተኛ የብር ኖት ላይ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ሁሉም ባንኮችና ኢንሹራንሶች እንዲሁም አነስተኛ የገንዘብ አቅራቢ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተረከቡትን ከ2.9 ቢሊዮን ብር በላይ አዲስ የብር ኖት በየቅርንጫፎቻቸው እያሠራጩ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ባንኮችም በመጀመርያ ዙር የተከረቡትን አዲስ ገንዘብ በተሳካ ሁኔታ በመቀየር ማሠራጨታቸውን እያስታወቁ ነው፡፡

እንደተገመተውም የብር ኖት ለውጡ ለባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ማደግና መበራከት አስተዋጽኦው ትልቅ ሆኗል፡፡ ባንኮች በርካታ አዳዲስ ቆጣቢዎችን እያፈሩ ነው፡፡ በ15 ቀናት ውስጥ ብቻ በገንዘብ ለውጡ ሰበብ በተከፈቱ አዳዲስ የቁጠባ ሒሳቦች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ተችሏል፡፡ የተቀማጭ መጠናቸው ከ20 እስከ 25 በመቶ ጭማሪ ያሳዩ ባንኮች ታይተዋል፡፡

አቶ አስፋው በመግለጫቸው ሰፊ ማብራሪያ የሰጡበት ጉዳይ፣ ባንኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አኳያ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ነው፡፡ በቅርብ ጊዜያት ብቻ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች