Saturday, June 15, 2024

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ የሚያሻሽለው ረቂቅ አዋጅ ይዘትና ፋይዳው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ወንጀለኞች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ብቻ ሳይሆን፣ ሰብዓዊ መብታቸው የሚከበርበትና ፍትሕ የሚያገኙበትን ዋስትና የሚሰጥ ነው። 

የወንጀል ሥነ ሥርዓት በሚለው አገላለጽ ውስጥ ለተፈጸመ ወንጀል ፍትሕ የሚሰጥበት ሥርዓት መኖሩን ያመላክታል። 

ይህ ሥነ ሥርዓት በአንድ አገር ውስጥ ተገንብቷል ለማለት ደግሞ የሕግ አስከባሪና የፍትሕ ተቋማት፣ እንዲሁም ፍትሕ ሰጪ አካላት፣ ፍርድ ቤቶችን ጥርት ባለ ሕጋዊ መዋቅር የሚያገናኝ ሥነ ሥርዓት ማበጀትን ይጠይቃል። 

በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓትና የወንጀል ፍርድ ሒደት እስካሁን ድረስ በዋናነት እየተመራ ያለው፣ 1954 ዓ.ም. ፀድቆ በሥራ ላይ በዋለው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ነው። 

ይህ የሥነ ሥርዓት አዋጅ ከመጽደቁ አምስት ዓመታት ቀደም ብሎ በ1949 ዓ.ም. የፀደቀው የአገሪቱ የወንጀል ሕግ ከ47 ዓመታት በኋላ 1996 .ም. የተሻሻለ ሲሆን፣ በዚህ ሕግ ያልተሸፈኑ የተለያዩ ውስብስብና አዳዲስ የወንጀል ድርጊቶች በመከሰታቸው፣ በሌሎች የተናጠል የወንጀል አዋጆች እንዲተዳደሩ ተደርጓል። ለመጥቀስ ያህልም የሙስና፣ የሽብር፣ የቴሌኮም ማጭበርበር፣ የኮምፒዩተር ወንጀሎችና እነዚህ የሚተዳደሩባቸው አዋጆች ተበታትነው ታውጀዋል። 

ይህ በመሆኑም የተገለጹት ወንጀሎች የሚተዳደሩበት አንድና ወጥ የሆነ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ እስካሁን ድረስ አለ ለማለት አይቻልም። በሥራ ላይ የሚገኘው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ 1954 ዓ.ም. የወጣ ሲሆን፣ ከአገሪቱ የሥልጣን አደረጃጀትም ሆነ ተለዋዋጭ ከሆኑት የወንጀል ዓይነትና ባህሪያት አንፃር ብቁ እንዳልሆነበርካታ የሕግ ባለሙያዎች ጥያቄ ሲያቀርቡበት ቆይተዋል።

ይህንን የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ለማሻሻል 15 በላይ ጥረቶች ከተደረጉ በኋላ፣ በስተመጨረሻ ባለፈው ሳምንት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኳል። 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያፀደቀው ይህ ረቂቅ አዋጅ ከወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ በተጨማሪ፣ ተመሳሳይ ጥያቄ በሕግ ባለሙያዎች የሚነሳበትን የማስረጃ ሕግ በአንድ አጣምሮ የየዘ ነው። 

በዚህም ምክንያት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው ረቂቅ አዋጅ ‹‹የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ሪፖርተር ረቂቅ ሕጉን ያገኘ ሲሆን፣ የሕግ ሰነዱ የያዛቸው አዳዲስና በፋይዳቸው አንኳር የሆኑት አንቀጾች እንደሚከተለው ቀርዋል። 

የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓቱ አንኳር ይዘቶች 

ረቂቁ ከያዛቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል በመሠረታዊነት ሊጠቀሱ የሚችሉት፣ ከዳኝነት ሥርዓቱ ጎን ለጎን ያስቀመጣቸው አማራጭ የወንጀል ጉዳዮች መፍትሔ መስጫ መንገዶች ናቸው። 

በዚህም ረገድ ክስ የተመሠረተበት የወንጀል ጉዳዮች ከመደበኛው የፍርድ ሒደት ውጪ የመፍትሔ ውሳኔ የሚሰጥባቸው አማራጭ መንገዶች ሆነው የተካተቱትምዕርቅ፣ የጥፋተኝነት ድርድርና የባህላዊ ተቋማት ሥርዓት ናቸው።

የአማራጭ መንገዶቹ ዓላማ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት የማኅበረሰቡን ተሳትፎ በማረጋገጥ፣ እውነትን በማውጣት፣ የወንጀል ጉዳዮችን ሰላማዊ፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ዘለቄታዊ ዕልባት እንዲያገኙ ማስቻል መሆኑን ያመለክታል። 

ዕርቅ የሚደረገው ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽና የግል ተበዳይ ጉዳዩን በዕርቅ ለመጨረስ ሲስማሙ እንደሆነና ዕርቁም ከፍርድ በፊት በማናቸውም ጊዜ ሊደረግ እንደሚችል ይደነግጋል።  ዕርቅ በተከሳሽ፣ በግል ተበዳይ፣ በማኅበረሰብ መሪዎች አመልካችነት ወይም በፍርድ ቤት፣ በዓቃቤ ሕግና በመርማሪ ፖሊስ አነሳሽነት ሊፈጸም የሚችል እንደሆነ፣ ማንኛውም በግል አቤቱታ የሚያስቀጣ ወይም ቀላል ወንጀል በዕርቅ ዕልባት ሊያገኝ እንደሚችል የረቂቁ ድንጋጌ ያመለክታል። 

የዕርቅ ስምምነት ሕግና ሞራልን የማይቃረን መሆኑን በማረጋገጥ የሚፈጸም ሲሆን፣ ዕርቁ ከተፈጸመ በኋላ ዓቃቤ ሕግ የዕርቅ የስምምነት ሰነዱን በመመዝገብ መዝገቡን ይዘጋል፣ ክስ ተመሥርቶ እንደሆነም ክሱን ያነሳል፡፡ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ከሆነም ፍርድ ቤቱ የዕርቁን ሰነድ በመመዝገብ መዝገቡን ይዘጋል፡፡ በዕርቅ ስምምነት ያለቀ ጉዳይ ላይ በማንኛውም ጊዜ ክስ ወይም ይግባኝ ሊቀርብበት እንደማይችልም ያመለክታል፡፡ 

ሌላኛው የወንጀል ጥፋተኝነት ድርድር ሲሆንየዚህ አማራጭ መንገድ ዓላማ ተከሳሹ ለተፈጸመው የወንጀል ድርጊት በራሱ ነፃ ፈቃድ የእምነት ቃል እንዲሰጥ፣ እንዲፀፀትና እንዲታረም ዕድል መስጠት እንደሆነ ረቂቁ ያመለክታል።

የጥፋተኝነት ድርድር የሚካሄደው ተከሳሽ ጥፋቱን አምኖና የድርጊቱን አፈጻጸም አሳማኝ በሆነ ሁኔታ በዝርዝር አስረድቶ የክስ ብዛት ወይም ቅጣት እንዲቀነስለት፣ ክስ እንዲነሳለት፣ በፈቃደኝነት ሲስማማ ብቻ እንደሚሆን ረቂቁ ይደነግጋል።  ማንኛውም የወንጀል ጉዳይ በዚህ ሕግ በተደነገገው መሠረት በጥፋተኝነት ድርድር ሥርዓት ታይቶ ውሳኔ ሊያገኝ የሚችል ሲሆንየጥፋተኝነት ድርድር በዓቃቤ ሕግ ወይም በተጠርጣሪው አነሳሽነት ሊካሄድ እንደሚችል ያስረዳል።

በጥፋተኝነት ድርድር ላይ ከተከለከሉ ተግባራት መካከልም የጥፋተኝነት ድርድር ዓላማውን፣ ሕግን፣ የሙያ ሥነ ምግባርን በሚፃረር አኳኋን ማካሄድና በግል ከሳሽ አማካይነት የጥፋተኝነት ድርድር ማድረግ የተከለከሉ ናቸው። ሌላኛው የወንጀል ጉዳይን በባህላዊ ሥርዓት መፍትሔ እንዲያገኝ ማድረግ ሲሆንዓላማውም በማኅበረሰቡ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ እንደሆነ ያመለክታል።

በዚህም መሠረት ማንኛውም በምርመራ፣ የክስ ወይም የፍርድ ሒደት ላይ ያለ የወንጀል ጉዳይ በባህላዊ ሥርዓት ታይቶ ውሳኔ ወይም መፍትሔ ሊሰጥበት እንደሚችል ረቂቁ ያመለክታል።

ይህ ድንጋጌ ቢኖርም ሰብዓዊ መብትን የሚጥስ፣ በሰው ልጅ ክብርና በአገር ደኅንነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ወይም የተከሰሱ እንደሆነ፣ ባህላዊ ሥርዓት ተፈጻሚ እንደማይሆን በረቂቁ ተደንግጓል፡፡ 

በዚህ አማራጭ ሥርዓት ውስጥ ክልከላ የተጣለባቸውን ተግባራት አስመልክቶምተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ በፈጸመው አንድ የወንጀል ጉዳይ ላይ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ባህላዊ ሥርዓቶችን ተፈጻሚ ማድረግ ወይም ተከሳሹ ያልተቀበለውን ባህላዊ ሥርዓት ተፈጻሚ ማድረግ፣ ወይም ባህላዊ ሥርዓቱን ከሌላ መፍትሔ ጋር መቀላቀል የተከለከለ መሆኑን ረቂቁ ያመለክታል። 

በቅድመ ሁኔታነትም ዓቃቤ ሕግ ጉዳዩ በባህላዊ ሥርዓት መፍትሔ እንዲያገኝ ሲወስን፣ የተጠርጣሪውን ወይም የተከሳሹን ፈቃደኝነትና ጥፋተኛ ለማሰኘት የሚያስችል ማስረጃ መኖሩን ማረጋገጥ እንደሚገባው፣ ዓቃቤ ሕግ ወይም ፍርድ ቤት እንደ ነገሩ ሁኔታ ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ ተደጋጋሚ ወንጀለኛ ሆኖ ካገኙት ጉዳዩ በባህላዊ ሥርዓት እንዳይታይ ሊወስኑ እንደሚችሉ ረቂቁ ይደነግጋል።

በባህላዊ ሥርዓት የሚታይ የወንጀል ጉዳይበዓቃቤ ሕግ አነሳሽነት ወይም በግል ተበዳይ ወይም በባህላዊ ሥርዓት ሥልጣን ባለው ሰው፣ እንዲሁም አግባብነት ባለው የመንግሥት አካል፣ ወይም ጉዳዩን በሚያየው ፍርድ ቤት ጠያቂነት ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ ፈጸመ የተባለው የወንጀል ድርጊት በባህላዊ መንገድ እንዲታይ ሊቀርብ የሚችል መሆኑም በረቂቅ ሕጉ ተደንግጓል።

ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሽ ፈጽሟቸዋል የተባሉ ተያያዥ ወይም ተደራራቢ ወንጀሎች ከፊሎቹ በባህላዊ መንገድ ቀሪዎቹ በመደበኛው ሥርዓት ሊታዩ የሚችሉ በሆነ ጊዜ፣ ሁሉም ወንጀሎች በመደበኛው ሥርዓት እንዲታዩ እንደሚደረግ ረቂቁ ይደነግጋል። 

በባህላዊ ሥርዓት እንዲታይ የተወሰነው ጉዳይ ሳይታይ ከቀረ ወይም መፍትሔው በሙሉ ወይም በከፊል ሳይፈጸም ከቀረና ሊፈጸም የሚችልበት ሁኔታ የለም ብሎ ዓቃቤ ሕግ በበቂ ሁኔታ ካመነ፣ ጉዳዩ በመደበኛው ሥርዓት እንዲታይ ሊወስን የሚችል መሆኑንበዚህ መንገድ ከተወሰነም ፍርድ ቤት የዘጋውን መዝገብ በዓቃቤ ሕግ ጠያቂነት በመደበኛው ሥርዓት እንዲቀጥል እንደሚያደርግ ተደንግጓል።

በሥራ ላይ የሚገኘው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ አሁን ካለው የኢትዮጵያ መንግሥት ፌዴራላዊ አወቃቀር ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ፣ ረቂቅ አዋጁ ይህንን የመንግሥት አደረጃጀት ታሳቢ ያደረገ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ የፌደራል መንግሥቱንና የክልሎችን የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥልጣን፣ እንዲሁም የፍርድ ቤቶቻችን አደረጃጀትና የመዳኘት ሥልጣን አካቶ ይዟል። 

በዚህም መሠረት የወንጀል የዳኝነት ሥልጣንን አስመልክቶ የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣኖችን ዘርዝሯል። በመሆኑም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከታች በተዘረዘሩት ጉዳዮች ላይ የወል የዳኝነት ሥልጣን እንዲኖራቸው አድርጓል። 

ከእነዚህም መካከል አፈጻጸማቸው የፌዴራል መንግሥት ወይም በአንድ የክልል መስተዳድር በሚያስተዳድረው የአስተዳደር ክልል ወሰን ያልተገደቡ ወንጀሎች፣ ዓለም አቀፍ ባህርይ ያላቸው ወይም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ ከውጭ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ወንጀሎች፣ ወታደራዊ ወንጀሎች፣ በፌዴራል መንግሥቱ ተቋማት፣ ንብረት፣ ሰነድና ገንዘብ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ በፌዴራል መንግሥቱ ባለሥልጣናትና ሠራተኞች ከኃላፊነት ጋር በተያያዘ የሚፈጸም ወንጀል፣ ለፌዴራል መንግሥቱ ተጠሪ በሆኑ ከተሞች ወይም ቦታዎች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ የጉምሩክና የፌዴራል መንግሥት ግብርና ገንዘብ ነክ ጥቅሞች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ዋነኞቹ ናቸው።

የክልል ፍርድ ቤቶች ደግሞ በአፈጻጸማቸው የክልል መንግሥት ላይ የሆኑ ወይም ከአንድ የአስተዳደር ክልል በላይ ባልሆኑ ወንጀሎች፣ አንድ ክልል ከሚያስተዳድረው የአስተዳደር ክልል በላይ በሆኑ ቀላል የወንጀል ጉዳዮችና ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ባልተሰጡ ጉዳዮች ላይ የመዳኘት ሥልጣን ይሰጣቸዋል። 

በተለይ ድንጋጌው የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ የተለየ የመዳኘት ሥልጣን የሚሰጥ ሲሆን፣ ይህም በአዲስ አበባ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ተቋማት፣ ንብረቶች፣ ገንዘብና ሰነዶች ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ የወንጀል የዳኝነት ሥልጣን እንደሚኖራቸው ረቂቁ ያመለክታል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች በሚል አገላለጽ ለክልልም ሆነ ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከተሰጡ የመዳኘት ሥልጣኖች መካከል አንዱ፣ በኢትዮጵያዊ ዜጋ ላይ ወይም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያ ውጭ ወንጀል ፈጽሞ ሲገኝና ጉዳዩ ወንጀሉ በተፈጸመበት አገር ሕግ መሠረት ዳኝነት ካላገኘ እንደነገሩ አግባብነት የዳኝነት ሥልጣን ይሰጣቸዋል፡፡ በተጨማሪም በውጭ አገር ፍርድ ቤቶች የተሰጡ የወንጀል ፍርዶችን የማስፈጸም ሥልጣን ይሰጣቸዋል። 

ረቂቁ ከያዘው አዳዲስ ድንጋጌዎች መካከል ሊጠቀስ የሚችለው ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ የፍርድ ቅጣት አፈጻጸምን በተመለከተ የተካተቱት አዳዲስ ድንጋጌዎች ሲሆኑእነዚህም የሞት ቅጣት አፈጻጸምንና ቅጣትን ስለማስተላለፍ የተመለከቱት ናቸው።  በዚህም መሠረት የሞት ፍርድ በማንኛውም ምክንያት ሳይፈጸም ከሁለት ዓመት በላይ የቆየ እንደሆነ ወደ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀየር ረቂቁ ይደነግጋል።

በተጨማሪም ማንኛውም የሞት ቅጣት ውሳኔ ይግባኝ ቢቀርብበትም ባይቀርብበትም፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አምስት ዳኞችን በመሰየም ውሳኔውን የማየት ግዴታ ይኖርበታል።  ለዚህም ሲባል ማንኛውም ፍርድ ቤት የሰጠውን የሞት ቅጣት ውሳኔ በተመለከተ ውሳኔውንና የመዝገቡን ግልባጭ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ማስተላለፍ የሚኖርበት እንደሆነ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አምስት ዳኞች በተሰየሙበት የውሳኔውን ትክክለኛነት አረጋግጦ አስፈላጊውን እንደሚሰጥበት ይደነግጋል። 

በመሆኑም የሞት ቅጣት ተፈጻሚ የሚሆነውጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሞት ፍርዱ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑን፣ በይቅርታ ወይም ምኅረት ያልተሻረ ወይም ያልተለወጠ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ቅጣቱ እንዲፈጸም ለአገሪቱ ርዕሰ ብሔር አቅርቦ ሲያፀድቅ እንደሚሆን ይደነግጋል። 

የእስራት ቅጣት ማስተላለፍን በተመለከተ ጥፋተኛ የተባለ ፍርደኛ የሚወሰንበት የእስራት ቅጣት አፈጻጸም ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍለት ጉዳዩን ለሚመለከተው ፍርድ ቤት አቤቱታ ሊያቀርብ እንደሚችል ረቂቁ ይደነግጋል። 

አንድ ፍርደኛ የቅጣት አፈጻጸም ጊዜው እንዲተላለፍለት የሚያቀርበው አቤቱታ ቅጣቱ እንዲተላለፍ የተጠየቀበትን ምክንያትና ማስረጃ፣ እንዲሁም የቅጣቱ አፈጻጸም ለምን ያህል ጊዜ ሊተላለፍለት እንደሚገባ ከቅጣት አስተያየት ጋር ማካተት ይኖርበታል።  ፍርድ ቤቱ በቀረበው አቤቱታ ዓቃቤ ሕግ አስተያየቱን እንዲሰጥበትና አስፈላጊ ሲሆን፣ ማስረጃውን ወይም የባለሙያ አስተያየት ከሰማ በኋላ ከቅጣት ውሳኔው ጋር አብሮ ውሳኔውን መስጠት ይኖርበታል፡፡ 

በዚህ መሠረት የእስር ቅጣት እንዲተላለፍ ከሚያስችሉ ምክንያቶች መካከልም ፍርደኛው በጠና ከመታመሙ የተነሳ በማረሚያ ቤት ቅጣቱን ለመፈጸም የማይችል መሆኑ በሐኪም ሲረጋገጥ፣ ፍርድ ቤቱ ከሕመሙ እስኪድን አስፈላጊ ነው ብሎ ሲወስን ለተወሰነው ጊዜ ያህል ቅጣቱ ሊተላለፍ ይችላል። 

አሥራ ስምንት ወር ያልሞላው ሕፃን ያላት እናት ስትሆን ሕፃኑ ሰላሳ ወር እስኪሞላው ድረስ፣ ነፍሰ ጡር እንደሆነች የእርግዝና ጊዜው እስከሚያበቃና ከወለደች በኋላ ሰላሳ ወር እስኪሆነው፣ ፍርዱ ከተሰጠበት ቀን በፊት ባለው ሁለት ሳምንታት ውስጥ ወላጁ፣ ልጁ ወይም የትዳር ጓደኛው የሞተ ወይም በጠና የታመመ እንደሆነ ከአሥራ አምስት ቀናት ላልበለጠ ጊዜ ሊተላለፍ ይችላል። 

ፍርዱ ከተሰጠበት ቀን ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ የትዳር ጓደኛው የወለደች ወይም ፍርድ ከተሰጠ በሚቀጥለው አንድ ወር ውስጥ የምትወልድ እንደሆነና ከተፈረደበት ሰው ሌላ ረዳት የሌላት እንደሆነ ከአንድ ወር ላልበለጠ ጊዜ፣ ቤተሰቡን የሚንከባከብ ሌላ ሰው ከሌለና ባልና ሚስት በተመሳሳይ ጊዜ የተፈረደባቸው እንደሆነ ሚስት ወይም ከሁለቱም አንዱ ቀደም ብሎ የታሰረ እንደሆነ የተፈረደበት ሰው ለሦስት ወር ላልበለጠ ጊዜ፣ የቅጣቱ አፈጻጸም እንዲተላለፍለት የተጠየቀለት ምክንያት አጣዳፊ ወይም ወቅታዊ ለሆነ የግብርና ሥራ ወይም ባልታሰበ ምክንያት የተፈጠረ በአስቸኳይ ሊከናወን የሚገባው ሥራ እንደሆነ፣ ከሦስት ወር ላልበለጠ ጊዜ ሊተላለፍ እንደሚችል ረቂቁ ይደነግጋል። 

የተፈረደበት ሰው ቀደም ብሎ የጀመረው ሆኖ በሌላ ሰው ሊጠናቀቅ የማይችል ሥራ ወይም ጉዳይ ሲሆንና ሥራው ባለመጠናቀቁ ምክንያት ጉዳት የሚደርስ እንደሆነ፣ ከአንድ ወር ላልበለጠ ጊዜ፣ የተፈረደበት ሰው የጀመረውን ትምህርት ወይም የተማረበትን ፈተና ለማጠናቀቅ እንደሆነና በሌላ ሁኔታ ማጠናቀቅ የማይቻል እንደሆነ ከስድስት ወር ላልበለጠ ጊዜ ወይም ለፈተናው የሚያስፈልገው ጊዜ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ 

ከላይ የተመለከቱት ቅጣቶች አፈጻጸም ሊተላለፍ የሚችለው ፍርድ ቤቱ እስከ አምስት ዓመት እስራት የተፈረደበት ፍርደኛ ለኅብረተሰቡ ደኅንነት አደጋ እንደማይሆን መረጋገጡን፣ የእስራት ቅጣቱን መፈጸም በሚገባው ጊዜ እንዲጀምር ለማረጋገጥ የሚያስችለው በቂ ዋስትና የሚያቀርብና እንዲፈጽማቸው የታዘዙትን የጥንቃቄርምጃዎች የሚያከብር መሆኑን ሲያረጋግጥ እንደሆነ በረቂቁ ተመልክቷል። 

በተጨማሪም ፍርደኛው የተላለፈውን የቅጣት ጊዜ በአግባቡ ጨርሶ የተመለሰ እንደሆነ፣ የተላለፈው የቅጣት ጊዜ እንደ ተፈጸመ ቅጣት የሚቆጠርለት መሆኑንም ያመለክታል። 

ፍርደኛው የተላለፈውን የእስራት ጊዜን ለሌላ ዓላማ ካዋለው፣ ፍርደኛው በማንኛውም መንገድ ለሕዝብ ደኅንነት አደጋ መሆኑ ከተረጋገጠ፣ ያመልጣል ተብሎ በበቂ ምክንያት የሚጠረጠር ከሆነ፣ ቅጣቱ እንዲተላለፍለት ያቀረበው ምክንያት የሌለ ወይም የተቋረጠ ወይም ሐሰተኛ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ የተላለፈው ቅጣት ተቋርጦ እንዲፈጸም ይደረጋል። 

የጊዜ ቀጠሮን በተመለከተ ፍርድ ቤቶች በመታየት ላይ ለሚገኝ የወንጀል ክስ ሊሰጡ የሚችሉት የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ በመጀመርያ እስከ 14 ቀናት ሆኖ፣ በአጠቃላይ ግን ከአራት ወራት ሊበልጥ እንደማይችል ረቂቁ ያመለክታል። 

በመሆኑም በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ምርመራ ካልተጠናቀቀ ፍርድ ቤት ተጠርጣሪውን በዋስ የመልቀቅ መብት በረቂቁ ተሰጥቶታል። 

ማስረጃን በተመለከተ

ፍርድ ቤት ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ይረዳል ብሎ ሲያምን ፍርድ ከመስጠቱ በፊት በዓቃቤ ሕግ ያልተቆጠረ ምስክር ቀርቦ እንዲሰማ ለማዘዝ እንደሚችልእንዲሁም ፍርድ ቤቱ ግልጽ ያልሆነ ነገር ለማጥራት ወይም ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት አስፈላጊ መሆኑን ሲረዳ አስቀድሞ የምስክርነት ቃሉን የሰጠ የዓቃቤ ሕግ ምስክር እንደገና እንዲመሰክር ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል ይደነግጋል።

በምርመራ ጊዜ ለፖሊስ የተሰጠ የምስክርነት ቃል በፍርድ ቤት በማስረጃነት አይቀርብም፡፡ ነገር ግን የዓቃቤ ሕግ ምስክር በፍርድ ቤት ቀርቦ የሚሰጠው የምስክርነት ቃል በፖሊስ ምርመራ ጊዜ ከተሰጠ የምስክርነት ቃል ጋር የሚጣረስ እንደሆነ፣ የምስክሩን ቃል ለማስተባበል ዓቃቤ ሕጉ ወይም ተከሳሹ ሲያመለክት ፍርድ ቤቱ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ሊመለከተው እንደሚችል ተደንግጓል። 

ተቀባይነት የሌለው የዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን በተመለከተም የዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ ተገዶ የሰጠውና በራሱ ላይ ማስረጃ ሆኖ የቀረበ የእምነት ቃል ወይም እንዲያምን የተደረገ ማናቸውም ማስረጃ፣ እንዲሁም በምርመራ ላይ ልዩ የማስረጃ ማሰባሰቢያ ዘዴን የሚመለከቱ የዚህን ሕግ ድንጋጌዎች በመተላለፍ የተገኘ ማስረጃ፣ በአማራጭ መንገዶች አፈጻጸም ወቅት የተገኘ ማስረጃ ወይም የተሰጠ የእምነት ቃል በማስረጃነት መቅረብ አይችሉም። 

የተከሳሹን መልካም የሆነን ወይም ያልሆነን ጠባይ በማስረዳት የተከሰሰበትን የወንጀል ተግባር ለማስረዳት በዓቃቤ ሕግ የሚቀርብ ማስረጃ ተቀባይነት የለውም፡፡ ነገር ግን የተጎጂው ጠባይ መልካም አለመሆኑን ለማሳየት በተከሳሹ በሚቀርቡ ጥያቄዎች ወይም ማስረጃዎች የተረጋገጠውን ፍሬ ነገር ለማስተባበል፣ ዓቃቤ ሕግ የተከሳሹን መልካም ያልሆነ ጠባይ እንደ ማስረጃ ማቅረብ ይችላል። 

የቀድሞ ጥፋቶችና መሰል ተግባራት አሁን የተከሰሰበትን የወንጀል ተግባር ለማስረዳት በማስረጃነት ማቅረብ ተቀባይነት የላቸውምሆኖም የተከሳሹን ማንነት፣ የቀድሞ ዕቅድ፣ አጋጣሚ፣ ዝግጅት፣ ሐሳብ ወይም የነገሩ ሁነት ድንገተኛ አለመሆኑን ለማስረዳት የቀረበ እንደሆነ ተቀባይነት እንደሚኖረው ተደንግጓል። 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -