ሀገር አቀፍ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ የስልጣን ዘመናቸው የተራዘመላቸው የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ተጨማሪ የስራ ዘመናቸውን ዛሬ በጋራ ባካሄዱት ስብሰባ በይፋ ጀመሩ።
በምክር ቤቶቹ የጋራ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ፤ የፌዴራሉ መንግስት ምክር ቤቶቹን ጨምሮ በዘንድሮው የስራ ዘመን ለህግ የበላይነት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ካልተቻለ ዲሞክራሲን ተለማምዶ መተግበር አዳጋች ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ፣ “ዲሞክራሲን የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን ዲሞክራሲ የሚጠይቀውን ስራ የሚተግበር ዜጋ እንዲፈጠር ትኩረት ይሰጣል ብለዋል።ለዚህም የዲሞክራሲ መጎልበትና የሰለጠነ ፖለቲካን የሚያጠናክሩ ስራዎች ትኩረት ይሰጣቸዋል” ብለዋል።
የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥም ሲባል በዘንድሮው ዓመት ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራው ቁልፍ ጉዳይ በኢመደበኛ መልኩ ነፍጥ ያነገቡ ኃይሎችን እንዳይኖሩ ማድረግ እንደሆነ በአጽንኦት ተናግረዋል። የሐይማኖት አባቶች ፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ ዲፕሎማቶች እና ሚንስትሮች የምክር ቤቶቹን የጋራ ስብሰባን በዕንግድነት ታድመዋል።