በሔለን ተስፋዬ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አምስት መስቀለኛ መንገዶችን ሊገነባና 3,000 የከተማ አውቶብሶችን ሊገዛ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ጨምሮ ስድስት የመሠረተ ልማት ተቋማት፣ ለሚከታተላቸው ኮሚቴ ዕቅዳቸውን አቅርበዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ በ2013 በጀት ዓመት ዕቅዱን እንዳስታወቀው፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሻሻልና በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ለመግባት 3,000 የከተማ አውቶቡሶችን ግዥ ለመፈጸም በሒደት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አካሉ አሰፋ እንደተናገሩት፣ በትራንስፖርት ዘርፍ የሚነሱ ተግዳሮቶች የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣን መሆኑን ጠቁመው፣ በተያዘው በጀት ዓመት የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን ከፍ ለማድረግ መንግሥት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በዓለም ባንክ ድጋፍ አማካይነት በቴክኖሎጂ የማልማት እንቀስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት የሕዝብ ትራንስፖርት አቅርቦት ከአሥር ሺሕ በላይ የነበረ መሆኑን አስታውሰው፣ በተያዘው በጀት ዓመት አቅርቦቱን ወደ 12,000 ከፍ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የተገልጋዮችንም ቁጥር 2.7 ሚሊዮን ወደ ሦስት ሚሊዮን ከፍ በማድረግ ተደራሽነቱን የላቀ እንዲሆን እየሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡
የታሪፍ ማሻሻያ በማድረግ 300 መስመሮችን በመፈተሽና በማዘመን ሥራ በቴክኖሎጂ ታግዞ ውጤታማነት ያለው ሥራ ለማሠራትም መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
ሌላው ለኮሚቴው ዕቅዱን ያቀረበው የአዲስ አበበ መንገዶች ባለሥልጣን ሲሆን በበጀት ዓመቱ አምስት መስቀለኛ (መገጣጠሚያ) መንገዶችን በመሥራትና በማስፋት እንዲሁም ለእግረኞች መንገዶችን በመሥራት የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ ማቀዱን አስታውቋል፡፡
የመንገዶች ጥገና ለማከናወን 11 ቢሊዮን ብር በጀት የጠየቀ ቢሆንም፣ የተፈቀደለት ግን 5.6 ቢሊዮን ብር መሆኑን የጠቆሙት የዕቅድ፣ በጀትና ስትራቴጂክ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ አዲሱ አሰፋ፣ የባለሥልጣኑ ዕቅድ ምንም እንኳን የተጠየቀውን ያህል በጀት ባይፈቅድም ሥራውን ለማቀላጠፍ የግል ዘርፉን ተሳታፊ በማድረግ መንገዱን ተደራሽና ሥራውን ቀልጣፋ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
ሌላው በኅብረተሰቡ ዘንድ ወቀሳ የሚሰነዘርበት የመሠረተ ልማት አውታር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲሆን የክፍያና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ አሠራሮትን መዘርጋቱን ለኮሚቴው አስታውቋል፡፡
የአገልግሎት ፕላኒንግና ሪፖርቲክ ክፍል የተወከሉት አቶ አወል ካሳ እንደተናገሩት፣ የኤለክትሪክ መሠረተ ልማት ተደራሽ ለማድረግና ለማስፋፋት 428 ኪሎ ሜትር መካከለኛና 556 ኪሎ ሜትር ዝቅተኛ መስመር ለመዘርጋት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኃይል መቆራረጥ መቀነስ፣ ክብነት መቀነስ፣ የግብዓት አቅርቦት ማሻሻልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሳደግ 2013 በጀት ዓመት ዕቅዳቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የውኃ አቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ከፍተኛ ችግር መሆኑን በቀረበው ሪፖርት ለኮሚቴው ያስታወቀው የአዲስ አበባ ውኃና ፈሳሽ ባለሥልጣን ሲሆን፣ በ2012 በጀት ዓመት የነበረው የውኃ አቅርቦት 554 ሺሕ ሜትር ኪዩብ እንደነበር አስታውሰው፣ በ2013 በጀት ዓመት ወደ 644 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ከፍ ለማድረግ (ለማሳደግ) ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ተገልጿል፡፡
የባለሥልጣኑ የደንበኞች አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ አርዓያ እንደተናገሩት፣ በ2012 በጀት ዓመት ከ37 እስከ 42 በመቶ የነበረውን የውኃ ብክነት ለመቀነስ መታሰቡንና 14,000 የመደበኛ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን የነበረውን በበጀት ዓመቱ ወደ 44,000 ብር ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን ተገልጿል፡፡
የመሠረተ ልማት ትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙላ ንጉሥ እንደገለጹት፣ ቋሚ ኮሚቴው በትራንስፖርት፣ በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ፣ በውኃና ፍሳሽ በኮሚቴው አማካይነት ቁጥጥር የሚደረግ መሆኑን ገልጸው፣ በ2013 ያቀዱትን ተግባራዊነቱንና አፈጻጸሙ ዙሪያ ክትትል እንደሚደረጉ ገልጸዋል፡፡
አቶ ሙላ እንደተናገሩት፣ ሴክተሮቹ በዕቅዳቸው መሠረት መሥራታቸው አተገባበር ላይ ያላቸውን እንቅስቃሴ ምን ይመስላል የሚለው ቋሚ ኮሚቴው በየጊዜው እንደሚከታተሉ ገልጸዋል፡፡ የኅብረተሰቡንና የመንግሥት ፍላጎት አቅም የማይመጣጠን ቢሆንም፣ ዕቅዳቸው በተያዘለት ጊዜና በተገቢው መሠረት መሠራቱን ይፈትሻል ያሉት አቶ ሙላ ናቸው፡፡