አዋጁ ቢነሳም ጭምብል ሳያደርጉ መንቀሳቀስ በሕግ ያስቀጣል ተብሏል
በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ ምክንያት ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመነሳቱ፣ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት መባባሱንና ሥጋት መፍጠሩን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ጤና ሚኒስቴር ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ቫይረሱን ለመከላከልና ለመግታት የሚያግዝ መመርያ ይፋ ሲያደርግ እንደተገለጸው፣ በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱ ከታወቀበት ከመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ሥርጭቱን ለመቀነስና ለመግታት የኮቪድ መከላከል ግብረ ኃይል ከማቋቋም በተጨማሪ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ነበር፡፡ አዋጁ በአገሪቱ ላይ ያስከተለውን በተለይ ኢኮኖሚያዊ ጫናና ሌሎች ተግዳሮቶችን መሠረት አድርጎ በመነሳቱ፣ ሥርጭቱ መባባሱንና የከፋ ጉዳት ያደርሳል የሚል ሥጋት መፍጠሩ ተነግሯል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፣ ኅብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት የሚያስተላልፏቸውን መመርያዎችና አስተምህሮዎች በመቀበል፣ ኅብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴውን በጥንቃቄ እንዲፈጽም ወይም እንዲተገብር አሳስበዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ምርመራ አድርጎ የተረጋገጠበት ሰው ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ መግባት እንደማይችል፣ ማንኛውም ሰው የተከለከሉ ተግባራትን ወደ ጎን ትቶ ቫይረሱ ሊተላለፍ በሚችልበት ሁኔታ ንክኪ ማድረግ እንደሌለበት፣ ለሰላምታም ይሁን ለሌላ ዓላማ እጅ ለእጅ መጨባበጥና መተቃቀፍ የተከለከለ መሆኑን አዲስ ይፋ በተደረገው መመርያ መደንገጉን ሚኒስትሯ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርገዋል፡፡
ከአምስት ዓመት በታች ካሉ ሕፃናት በስተቀር ማንኛወም ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ጭምብል) ሳያደርግ መንቀሳቀስ በሕግ የሚያስቀጣ መሆኑንም ዶ/ር ሊያ አስታውቀዋል፡፡
ምንም እንኳን አዋጁ ከተነሳ በኋላ የትራንስፖርት አገልግሎት ተመልሶ መጨናነቅና ከፍተኛ የሆነ መጠጋጋት የተፈጠረ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም፣ ሚኒስትሯ ግን ኅብረተሰቡ ርቀቱን በሁለት ሜትር መጠበቅ እንዳለበት እየገለጹ መሆናቸው አብሮ የሚሄድ እንዳልሆነ ተገልጋዮች እየገለጹ ነው፡፡ ሚኒስትሯ ግን ባስተላለፉት መመርያ እንደገለጹት በገበያዎች፣ በትራንስፖርት መሳፈሪያ ቦታዎች፣ ሕዝባዊ አገልግሎቶች በሚሰጥባቸው ሥፍራዎችና በሌሎች ሕዝብ በሚያጨናንቁ ቦታዎች ርቀት መጠበቅ አለበት፡፡
ማናቸውም የግልም ሆኑ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች፣ ትምህርት የሚጀመርበት ትክክለኛ ቀን ተቆርጦ መመርያ ሳይደርሳቸው መክፈት እንደማይችሉ የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ የሕፃናት ማቆያ ማዕከላትም አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩት መመርያ ወጥቶላቸው እንዲጀምሩ ሲነገራቸው ብቻ መሆኑንና እስከዚያው ዝግ ሆነው እንዲቆዩ አሳስበዋል፡፡
ከትራንዚት መንገደኞች በስተቀር የኳራንቲንና የድንበር ላይ የጤና ቁጥጥር አሥር ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ሁሉ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተናግረው፣ ከመጣበት አገር ነፃ መሆኑን ማስረጃ ቢኖረውም እንኳን በመዳረሻ ቦታዎች ድጋሚ ምርመራ እንደሚደረግለትና ለሰባት ቀናት በአድራሻው ክትትል እንደሚደረግለት አስታውቀዋል፡፡
የቀብር፣ የሠርግና የማኅበራዊ ሥነ ሥርዓትን በሚመለከትም ከ50 ሰዎች ባልበለጠና ርቀትን በጠበቀ ሁኔታ በጥንቃቄ እንዲካሄድ የተላለፈው መመርያ፣ በዚያው እንዲቀጥልና አገልግሎት የሚሰጡ ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶች፣ መዝናኛና ሥፍራዎች በጠረጴዛ ሦስት ሦስት ሰዎች ብቻ ማስተናገድና ጥንቃቄ ማድረግ ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሲኒማ ቤቶች፣ ቴአትር ቤቶችና የሥዕል ጋለሪዎች አንድ አራተኛ ተመልካቾቻቸውን ብቻ ማስተናገድ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ ከማረሚያ ቤቶች በስተቀር ማገገሚያ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን መጠየቅ መከልከሉንም ዶ/ር ሊያ አሳውቀዋል፡፡