Thursday, June 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከአጥፍቶ ጠፊ ፖለቲካ መላቀቅ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ ሰላም ከሌለ ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ሰላም ለማስፈን ደግሞ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ በሙሉ የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት መወጣት ካለባቸው መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከሥልጣን በላይ ሕዝብና አገር አሉ፡፡ ራስን ከሕዝብና ከአገር በላይ ማሳበጥ ሰላም ያደፈርሳል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች አለመግባባት ምክንያት የሚፈጠር የሰላም መደፍረስ በርካታ ችግሮች ያስከትላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለይ በገዥው ፓርቲና በሕወሓት አመራሮች መካከል የሚስተዋለው አገርን ችግር ውስጥ የሚከት አደገኛ ቅራኔ በፍጥነት መላ ሊፈለግለት ይገባል፡፡ ለጦርነት የሚያነሳሱና ኃላፊነት የማይሰማቸው ንግግሮችን የሚያደርጉ ባለሥልጣናት አንደበታቸውን መግራት አለባቸው፡፡ ሥልጣን ከአገር ህልውና በላይ ስላልሆነ አደብ መግዛት የግድ ይሆናል፡፡ በሥልጣን ምክንያት የተፈጠረ ልዩነት የቅራኔ ምንጭ ሆኖ አገር መበጥበጥ የለበትም፡፡ ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ባለሥልጣናትም ሆኑ ከበስተጀርባ ሆነው የሚያሟሙቁ፣ ከአጥፍቶ ጠፊ ፖለቲካ ካልታቀቡ እሳቱ እነሱንም አይምራቸውም፡፡

‹‹የምትለብሰው የላት የምትከናነበው አማራት›› እንደሚባለው፣ በአሁኑ ጊዜ በድህነትና በኋላቀርነት በምትማቅቅ አገር ውስጥ እናውቃለን ባዮች ማገናዘብ አቅቷቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ለማውጣት መረባረብ ሲያዋጣ፣ ከሥልጣን በፊት አገርና ሕዝብ ማስቀደም ያቃታቸው በገሃዱ ዓለም የሚቃዡ ፖለቲከኛ ተብዬዎች እንደ እንጉዳይ ፈልተዋል፡፡ ኢትዮጵያ እጀግ በጣም ሰፊ ለም መሬት፣ አመቺ የሆነ የአየር ንብረትና ጠንካራ ወጣት የሰው ኃይል ይዛ ትራባለች፡፡ የአፍሪካ የውኃ ማማ እየተባለች ትጠማለች፡፡ የገዘፈ ታሪክ ባለቤት ሆና የአገሮች ጭራ ናት፡፡ አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናት ተመጣጣኝ ምግብ ስለማያገኙ ይቀነጭራሉ ወይም ይሞታሉ፡፡ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ካሉት በታች፣ ከሞቱት በላይ ሆነው ከአንገፍጋፊው ድህነት ጋር ይታገላሉ፡፡ ሚሊዮኖች መጠለያ አልባ ናቸው፡፡ በከተሞች በሚያሳዝን ሁኔታ የከተማ ነዋሪዎች የትራንስፖርት፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶችን የሚያገኙት በኋላቀር አሠራሮች ነው፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ ብዙዎች ከተሞች የቆሻሻ መጣያ ናቸው፡፡ ድህነት ያመሰቃቀላት አገር ታቅፎ እንደ ደላቸው አገሮች እዚህ ግቡ በማይባሉ ጉዳዮች መተራመስ ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ ከመጠን ያለፈ ድህነት ሕዝቡ አናት ላይ እያናጠረ በከንቱ ግብዝ መሆን አያዋጣም፡፡ ለግል ሥልጣንና ጥቅማ ጥቅም ሲባል በአገር ላይ መዶለት ነውር ነው፡፡ ለሺዎች ዓመታት በሞፈርና በቀንበር የሚከናወነውን እርሻ ለማዘመን የረባ ፖሊሲ የማያወጡ የሥልጣን ጥመኞች፣ አገርን ለመበታተን የአጥፍቶ ጠፊ ጎዳና ሲይዙ ዝም መባል የለበትም፡፡

ግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል እያስቆጠረ ያለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዞ፣ በአመዛኙ ከዴሞክራሲያዊነት ጋር የተጣላ እንደሆነ ብዙዎችን ያስማማል፡፡ የኮሙዩኒስት ርዕዮተ ዓለም እንከተላለን ብለው እርስ በርስ ከተፋጁት የዘመነ ቀይነጭ ሽብር የፖለቲካ ፓርቲዎች ጀምሮ፣ የብዙዎቹ መሠረታዊ ችግር የዴሞክራሲን መሠረታዊ መርሆዎች ጠንቅቆ አለመረዳት ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎች እኮ የፖሊሲ አማራጮች ማመንጫ መሆን ነበረባቸው፡፡ የሕዝብ አስተያየትና ፍላጎት የሚንፀባረቅባቸውና አገር የሚመሩ ሰዎች የሚገኙባቸው ተቋማት ሊሆኑ ይገባ ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩባቸው ነፃ መድረኮችም መሆን አለባቸው፡፡ የተለያዩ ዓላማዎችን የሚያራምዱ ግለሰቦችም ሆኑ ስብስቦች በነፃነት የሚደራጁባቸው ከመሆን አልፈው፣ በአገር ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ዋነኛ ተዋናይ መሆን  ነበረባቸው፡፡ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት የሚባሉት ጽንሰ ሐሳቦች በስፋት የሚስተጋቡባቸውም ሊሆኑ ይገባል፡፡ በውስጣቸው ዴሞክራሲ የሰረፀ እንደሆኑ ስለሚታሰቡ፣ የተለያዩ ሐሳቦች ሊስተናገዱባቸው የግድ ይላል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በንድፈ ሐሳብም ሆነ በተግባር አንድ ለመሆን ከፍተኛ ፍጭት የሚደረግባቸው፣ ጠንካራና በዲሲፕሊን የተገሩ አባላትና ደጋፊዎች የሚያፈሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ዓይነቱ ቁመና ላይ ለመገኘት ዝግጁ ናቸው? ዘመኑን ከማይመጥን የቅጥፈት ፖለቲካ በመላቀቅ አገር ለመምራት ብቃት አላቸው? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ቢነሱ መልስ የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ የተሳሳተና አጥፊ መንገድ ላይ ናቸው፡፡

የአገሪቱ አብዛኞቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ የፖሊሲ ማመንጫ የክርክር መድረኮች፣ የነጠሩ ሐሳቦች መፍለቂያና የሥልጡን ፖለቲካ ማራመጃ መሆን ሲገባቸው፣ በአገሪቱ ምንም እንዳልተፈጠረ እንቅልፋቸውን ከሚለጥጡት ጀምሮ የሴረኞች መጠለያ ሆነዋል፡፡ በውስጣቸው ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ማስፈን ያልቻሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንኳን የተሻለ አጀንዳ ሊያመነጩ፣ አባሎቻቸውን የአሉባልታና የሴራ ፖለቲካ ትንተና ሰለባ አድርገዋቸዋል፡፡ በዚህ ዓመት ይደረጋል ተብሎ ለሚታሰበው ምርጫ ምን ያህሎቹ እየተዘጋጁ ነው ቢባል፣ ምላሹ እንዲያው ዝም ነው ከማለት የዘለለ አይሆንም፡፡ አክቲቪስት የሚባሉ ግለሰቦችን ሩብ ያህል ተደማጭነት የሌላቸው 100 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ ተብሎ ሲነገር ቀልድ ይመስላል፡፡ ለመጪው ምርጫ በሚገባ እየተዘጋጁ ያሉ በጣም ጥቂት ፓርቲዎች መኖራቸው መዘንጋት ባይኖርበትም፣ የብዙዎቹ ጉዳይ ግን ያንገሸግሻል፡፡ ወይ አይጣመሩ፣ ወይ አይዋሀዱ፣ ወይ በየራሳቸው ጠንካራ ሆነው አይወጡ በሕዝብና በአገር ላይ ይቀልዳሉ፡፡ ለውይይትና ለድርድር የሚመጥን አጀንዳ ሳይኖራቸው በባዶ ሜዳ ከሚንጎማለሉት ጀምሮ፣ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳላቸው ማረጋገጫ ማቅረብ የማይችሉ ጭምር አገር ለማጥፋት ሲተራመሱ ማየት ያስገርማል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው በቃችሁ መባል ያለበት፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብና የአገራቸው ጉዳይ የሚያሳስባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን በማነቃነቅ ይህ የሽግግር ጊዜ በሰላም ተጠናቆ ለነፃ፣ ለዴሞክራሲያዊ፣ ለፍትሐዊና ለእውነተኛ ምርጫ ለመብቃት በቁርጠኝነት መሥራት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሰላም እንድትሸጋገር፣ የሕግ የበላይነት የሁሉም ነገር ምሰሶ እንዲሆን፣ ፍትሕ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ተደራሽ እንዲሆን፣ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሴረኝነትና በቀልተኝነት እንዲወገዱና መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን በጋራ ይሥሩ፡፡ ስህተት ሲፈጸም እያረሙ፣ አድልኦ እንዳይኖር እየታገሉ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲመሠረት አርዓያ እየሆኑ፣ ጥቅም የሌላቸው ሥራ አስፈቺ ወሬዎችና አሉባልታዎች ተወግደው የውይይትና የክርክር ባህል እንዲጎለብት ምሳሌ በመሆን፣ ወዘተ. ኃላፊነታቸውን ይወጡ፡፡ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር የሚያስፈልገው ጠመንጃ ሳይሆን፣ የነጠረ የሐሳብ የበላይነት መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡ ሰላማዊው ፖለቲካ የሕገወጦችና የሥርዓተ አልበኞች መጫወቻ እንዳይሆን መተባበር የግድ መሆን አለበት፡፡ ወገን የገዛ ወገኑን እየገደለ የሚኩራራበት፣ ወይም ጠመንጃ ታጣቂ የሚመለክበት ሥርዓት ከኢትዮጵያ መወገድ ይኖርበታል፡፡ አምባገነንነት የሕዝብና የአገር ፀር ነው፡፡ አገር ቁምስቅሏን ስታይ የኖረችው በዚህ አጥፊ ድርጊት ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ በጣም ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው የብዙዎች መነጋገሪያ ነው፡፡ ብዛታቸው በአንድ ወቅት በተጀመረው ቢጤ ለቢጤ የመሰባሰብ ሒደት በተወሰነ ደረጃ ሊቀንስ ይችላል ተብሎ ቢታሰብም፣ አሁንም በተናጠል ተደራጅተው አለን የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡ አለን ማለታቸው የማያስከፋና መደራጀት መብት ቢሆንም፣ ፋይዳ ቢስ ሆነው መቀጠላቸው ግን ለማንም አይጠቅምም፡፡ ዴሞክራሲን ሳይኖሩት ዴሞክራት ነኝ ብሎ መደስኮር ዋጋ ቢስ መሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ‹የሕዝብ ድጋፍ አለንእየተባለ በሕዝብ ስም መቆመር በዚህ ዘመን አያዋጣም፡፡ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሥራቾቻቸው ወይ የአደራጆቻቸው የግል ንብረት መሆናቸው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አደገኛ ነገር ውስጥ በመውጣት ፓርቲዎችን ሕዝባዊ ማድረግ ይቅደም፡፡ ስያሜዎቻቸውም ሆነ ይዘታቸው የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ያማከለ ይሁን፡፡ ኅብረ ብሔራዊነትን የሚፃረሩ ድርጊቶችን እየፈጸሙ ኢትዮጵያውያንን በመከፋፈል አገር ለማፍረስ ማሴር ወንጀል ነው፡፡ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጉዞ ማድረግ የሚቻለው አገራዊ ባህርይን ተላብሶ ዴሞክራሲያዊነትን በመደረብ እንጂ፣ ዘመኑን በማይመጥን ቅጥፈት አይደለም፡፡ ከሥልጣን በስተቀር ምንም የማይታያቸውና ለአገር ፈጽሞ ደንታ የሌላቸው የፖለቲካ ኃይሎች፣ አገር በማተራመስ ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ ለማፋጀት ከመሞከር ቆም ብለው ያስቡ፡፡ ለፀፀት ከሚዳርግና በታሪክ ተጠያቂ ከሚያደርግ የአጥፍቶ ጠፊ ፖለቲካ ራሳቸውን ያላቅቁ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...

በኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት አንድ ድንጋይ ደጋግሞ እንዳይመታን

ከጣሊያን ቅኝ ተገዥነት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በኮንፌዴሬሽን፣ ቆየት ብሎም እንደ አንድ የኢትዮያ ግዛት አካል የነበረችው ኤርትራ ከደርግ ሥርዓት መውደቅ በኋላ ነፃ አገር ሆናለች፡፡ ነፃ አገር መሆንና ከኢትዮጽያ ጋር መቀጠል በወቅቱ ብዙ ሲባልለት የነበረ ጉዳይ ነበር፡፡
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አገር አጥፊ ድርጊቶች በአገር ገንቢ ተግባራት ይተኩ!

ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በመንስዔዎች ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መግባባት ሊኖር የሚችለው ደግሞ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር የሚያስችል ዓውድ ሲፈጠር ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ዕውን...

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...