Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምኮቪድ-19 በዋይት ሃውስ

ኮቪድ-19 በዋይት ሃውስ

ቀን:

በኮቪድ-19 ከተጠቁት 7.4 ሚሊዮን አሜሪካውያን አንዱ የሆኑት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከቫይረሱ ሙሉ ለሙሉ ነፃ ባይሆኑም ሲታከሙበት ከነበረው ዋልተር ሪድ የመከላከያ ሆስፒታል ወደ ዋይትሃውስ ተመልሰዋል፡፡

ከሦስት ቀናት የሆስፒታል ቆይታ በኋላ ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ ዋይት ሃውስ የተመለሱት ትራምፕ፣ ኮቪድ-19 ከ210 ሺሕ በላይ አሜሪካውያን ሕይወት ቢነጥቅም ለሕዝባቸው ‹‹ኮቪድን አትፍሩ›› ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ትራምፕ በሙከራ ላይ ያለ መድኃኒት እንደወሰዱ የተነገረ ቢሆንም፣ ዋይት ሃውስ የገቡት ከቫይረሱ ሳያገግሙና የመተላለፍ ዕድሉም ባለበት ሁኔታ ነው፡፡ በኮቪድ-19 ቫይረስ ተያዙ ተብሎ ከተነገረበት ካፈው ሳምንት ጀምሮ ለኮቪድ-19 በነበራቸው የተናናቀ ምልከታ በየዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙኃን ሲተቹ ቢከርሙም፣ በዋይት ሃውስ በረንዳ ላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛቸውን አውልቀው ተስተውለዋል፡፡

ኮቪድ-19 በዋይት ሃውስ

 

አልጀዚራ እንደሚለው፣ በዋይት ሃውስ ትራምፕ ብቻ ሳይሆኑ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎችም በቫይረሱ ተጠቅተዋል፡፡ ባለቤታቸው ሚላኒያ እና የቅርብ አማካሪያቸው ሆፕ ሂክስ፣ የፕሬስ ሴክሬታሪ ኬይሊ ማክኢናኒ እና ሁለት ረዳቶቻቸው እንዲሁም ሦስት የዋይት ሃውስ ጋዜጠኞችን ጨምሮ 11 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡

ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሁለተኛ ዙር ፕሬዚዳንትነት ከዴሞክራቱ ጆ ባይደን ጋር የሚወዳደሩት ትራምፕ፣ በኮቪድ-19 መያዛቸው በምረጡኝ ዘመቻቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ቢባልም፣ እሳቸው ለዚህ ሥፍራ አልሰጡም፡፡

‹‹ኮሮና እንዲያሸንፋችሁ ዕድል አትስጡ፣ አትፍሩት እናሸንፈዋለን፣ ሕይወታችሁን እንዲነጥቅ አትፍቀዱለት፣ እኔ ደህና እሆን ይሆናል ግን አላውቅም፤›› ብለው በቪዲዮ መልዕክት በትዊተር ገጻቸው ላይ ማስፈራቸውንም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ዶክተሮች የኮቪድ-19 ቫይረስ በትራምፕ ሳምባ ላይ ጉዳት ስለማድረሱም ሆነ ከዚህ ቀደም ምርመራ አድርገው ለመጨረሻ ጊዜ ኔጌቲቭ የተባሉበትን ጊዜ ከማብራራት ተቆጥበዋል፡፡

የ74 ዓመቱ ትራምፕ ለ72 ሰዓታት ያህል ትኩሳት ያላሳዩና የኦክስጅን መጠናቸውም መደበኛ ቢሆንም፣ ቫይረሱ ከሰውነታቸው ለመጥፋትና ተላላፊነቱን ለማቆም ሁለት ሳምንት እንደሚወስድ በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ የምርምር ፕሮፌሰር አሊ ፋቶም ተናግረዋል፡፡

ትራምፕ በተደጋጋሚ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ሲያናንቁ ተሰምተዋል፡፡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግንም አሻፈረኝ ካሉት አንዱ ናቸው፡፡ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ከተቀመጡ መሥፈርቶች ርቀትን መጠበቅ የሚለውን መመርያ ባለማክበርም ይታወቃሉ፡፡

ሮይተርስ እንደሚለውም፣ ባለፈው ሳምንት ሲታመሙ ሆስፒታል ለመሄድ ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ ከሆስፒታል ለመውጣትም በጣም ጓጉተው ነበር፡፡ የአሜሪካ ተወካዮች  ምክር ቤት አፈ ጉባዔ  ናንሲ ፒሎሲ፣ የትራምፕ ወደ ዋይት ሃውስ መመለስ ከፖለቲካ የመነጨ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ትራምፕ ከሆስፒታል ቢወጡም ፀረ ቫይረስ መድኃኒታቸውን በዋይት ሃውስ ሆነው እንደሚወስዱና ራሳቸውን ለተወሰነ ጊዜ አግልለው እንደሚቀመጡም ታውቋል፡፡

‹‹ማስክስ ማተር›› የአፍና አፍ መሸፈኛ ዋጋ አለው

ሮይተርስ ትራምፕ በኮቪድ መያዛቸውን ተከትሎ ባደረገው ፑል 65 በመቶ ተሳታፊዎች ትራምፕ የቫይረሱን አደገኛነት ተቀብለውት ቢሆን ኖሮ በቫይረሱ አይያዙም ነበር የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

ዕጩ ፕሬዚዳንት ባይደንም፣ አሜሪካውያን ትራምፕ ‹‹ኮቪድን አትፍሩ›› ብለው የተናገሩትን ነቅፈዋል፡፡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለማድረግ ያላቸውን ዳተኝነትም እንዲሁ፡፡

‹‹ፕሬዚዳንቱ ያልፈዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ተሽሎት ለአሜሪካውያን ትክክለኛውን መልዕክት ቢያስተላልፍ፣ ማስክስ ማተር ቢል ደስተኛ ነኝ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እነዚህ ማስኮች ሕይወት ያድናሉ፣ የቫይረሱን ሥርጭት ይቆጣጠራሉ›› የሚሉት ባይደን፣ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ክርክር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ የኮቪድ-19 ምርመራ አድርገው ነፃ መሆናቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

በጥቅምት 5 ቀን 2013 ዓ.ም. በማያሚ ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ክርክር የሕክምና ባለሙያዎች ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ካሉም ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የትራምፕ የቅስቀሳ ዘመቻ አቀናባሪዎችም ትራምፕ በክርክሩ ለመገኘት እንደሚፈልጉ አሳውቀዋል፡፡

ትራምፕ ከመታመማቸው አስቀድሞ በክርክሩ ‹‹የአሜሪካ ኢኮኖሚ ማገገም›› አንዱ አጀንዳ እንደሚያደርጉ ተነግሮ ነበር፡፡ ነገር ግን የቫይረሱ በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ መገኘት፣ የትራምፕ አስተዳደር ለወረርሽኙ ምላሽ መስጠት ላይ እንዲያተኩር አድርጎታል፡፡

የኮቪድ ወረርሽኝ በዓለም አገሮች በሚባል ደረጃ ቢከሰትም፣ ትልቁን የተጠቂ ቁጥር የያዘችው አሜሪካ ናት፡፡ በአሜሪካ በቫይረሱ የተጠቁ ቁጥር 7.4 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ የሞቱት ደግሞ ከ210 ሺሕ በላይ ናቸው፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...