Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከልብ ሕመም ለመታደግ

ከልብ ሕመም ለመታደግ

ቀን:

በተመስገን ተጋፋው

የልጅነት ዕድሜያቸውን በቅጡ ቦርቀው ሳይጨርሱ በልብ ሕመም የሚሰቃዩትን ለመታደግ የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ ተቋቁሞ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ከክልልና ከከተማ አስተዳደሮች የመጡ ሕፃናት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፣ እየሆኑም ነው፡፡ ነገር ግን ማዕከሉ በተለይ የግብዓትና የገንዘብ ችግር አለበት፡፡  

በማዕከሉ ውስጥ ክትትል እያደረጉ ከሚገኙት መካከል የአቶ ታደሰ ጀጎ ልጅ ናትናኤል ታደሰ አንዱ ነው፡፡ ልጃቸውም ገና በጨቅላ ዕድሜው ለልብ ሕመም በሽታ እንደተጋለጠና ክትትል ለማድረግ ከይርጋ ጨፌ አዲስ አበባ እየተመላለሱ ሕክምና እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡

- Advertisement -

በሚኖሩበት አካባቢም የልብ በሽታን የሚያክም ተቋማት አለመኖሩ ከፍተኛ ችግር ፈጥሮባቸዋል፡፡ ልጃቸውንም ለማሳከም በዓመት አንድ ጊዜ በሚመጡበት ወቅት ለትራንስፖርትና ለአልጋ የሚያወጡት ወጪ እንደሚከብዳቸው፣ በዚህም የተነሳ በኑሯቸው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ እንዳስከተለባቸው ገልጸዋል፡፡

በስድስት ዓመቱ የልብ ቀዶ ሕክምና እንዳደረገና በዚያ ጊዜ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ሁኔታ ላይ እንደነበረ፣ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ልጃቸው ተገቢውን ሕክምና እያደረገ በመሆኑ በፊት ከነበረው የጤና ችግር አሁን ላይ በጥሩ ጤና ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

መንግሥት እንደዚህ ዓይነት የሕክምና ተቋም በየአካባቢው ማቋቋም ይገባዋል የሚሉት የታካሚ ዮዲት ገብረ ሕይወት እናት ወ/ሮ ጥሩ ታደሰ ናቸው፡፡

ዮዲት ሕመሙ እንዳለባት የታወቀው የስድስት ወር ልጅ እያለች ሲሆን፣ ከሕመሙ ጋር 14 ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ ከዚህ ቀደምም በከፍተኛ ሁኔታ ታማ እንደነበር፣ በወቅቱም ድንጋጤ እንደፈጠረባቸው ወ/ሮ ጥሩ ተናግረው፣ በቤት ውስጥም እንደ ዓይን ብሌን የምትታይ መሆኗን፣ ሳቅና ጨዋታዋም ሕመሙ ሲነሳባት እንደሚጠፋ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊትም የተለያዩ ሆስፒታሎች ላይ ክትትል የምታደርግ መሆኑን፣ በዚህም የተነሳ ለብዙ ወጪ መዳረጋቸውን ገልጸው፣ በማዕከሉ ክትትል ማድረግ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ለሕክምናው ምንም ዓይነት ወጪ አለማውጣታቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ በሽታውም በትምህርቷ ላይ ትልቅ ጫና ፈጥሮባት እንደነበርና አሁን ላይ በአግባቡ እየተከታተለች መሆኑን አክለዋል፡፡

በማዕከሉ የልብ ሰመመን ሐኪም ሳምሶን አደሩ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ በልብ ሕመም በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰቃዩ የሚገኙ ሕፃናትን ክትትል በማድረግና ሕክምና በመስጠት ማዕከሉ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ያብራራሉ፡፡

ከመስከረም 19 እስከ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ነፃ ምርመራ ማድረጋቸውንና በቀን ለ50 ሰዎች ያህል አገልግሎት መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ማዕከሉን በጎበኙበት ጊዜ ያሉትን ችግሮች በመረዳት ከዚህ በኋላ በየወሩ ነፃ የምርመራ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀመር መወሰናቸውን ዶ/ር ሳምሶን ጠቁመዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገዳይ የሆነውን የልብ ሕመም ለመቀነስ ማኅበረሰቡ በቂ የሆነ የሕክምና ክትትል ማድረግ እንደሚገባም አክለዋል፡፡

የሕክምና አገልግሎቱን ለመስጠትም በቂ የሕክምና ቁሳቁስ አለመኖሩና ያለው የበሽተኛ ብዛት አለመመጣጠን በሥራቸው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

ሲጋራ ማጨስ፣ ከፍተኛ የሆነ ውፍረት፣ ኮሌስትሮልና እንቅስቃሴ አለማድረግ ለልብ ሕመምን አጋላጭ በመሆናቸው እነዚህን አስቀድሞ በመጠንቀቅ መከላከል ይገባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሕሩይ አሊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማዕከሉ ከተመሠረተ ጀምሮ ከ5,800 በላይ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት እንዳገኙና በአሁን ወቅትም ከ4,600 በላይ ታማሚዎች ወረፋ ይዘዋል፡፡ በኢትዮጵያም በአብዛኛውን ቦታ ላይ የሕክምና አገልግሎቱ የማይሰጥ በመሆኑ የታካሚዎች ቁጥር ቀን በቀን እየጨመረ መምጣቱን አቶ ሕሩይ ተናግረዋል፡፡

የልብ ሕመም እየተባባሰ የመጣበት ዋና ምክንያት ማኅበረሰቡ ስለበሽታው ግንዛቤ ባለማግኘቱና የሕክምና ባለሙያዎችም አድርጉ የሚሉትን ነገር ባለመተግበራቸው ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በቀጣይም የልብ ሕክምና ማዕከሎችን በመክፈት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የዓለም የልብ ቀንን ምክንያት በማድረግ ‹‹የተሰበሩ ልቦችን እንጠግን›› በሚል መሪ ቃል መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ዶ/ር ሊያ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በማዕከሉ ተከብሮ ውሏል፡፡

በአከባበሩ አጋጣሚ የነፃ የልብ ቅድመ ምርመራ መደረጉም ታውቋል፡፡ የልብ ሕመምን ለመከላከል ጤናማ አመጋገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ከሲጋራና ከመጠጥ ሱስ ራስን መቆጠብ ተቀዳሚ የመከላከያ መንገዶች መሆናቸውን የሚያንፀባርቁ መልዕክቶችም ተላልፈዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...