Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የጎርፍ አደጋ ሥጋት እስከ መቼ?

የምሥራቅ አፍሪካ የአየር ንብረት ልህቀት ማዕከል፣ በክረምት ወራት ከ50 እስከ 200 ሚሊ ሜትር በላይ የሚሆን ከባድ ዝናብ በምሥራቅ አፍሪካ አንዳንድ አገሮች እንደሚዘንብ በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል፡፡ በዚህም ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችም በከባድ ዝናብ ከመከሰቱ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ የጎርፍ አደጋ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠር ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያ በክረምት ወራት ከፍተኛ ዝናብ ከተከሰተባቸው የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች አንዷ ናት፡፡ በአምስት ክልሎች ከባድ የጎርፍ አደጋ የተከሰተ ሲሆን፣ ብዙዎች በዚህ ሳቢያ ከመኖሪያ ቦታቸው ተሰደዋል፡፡ ከዚህ የተፈጥሮ አደጋ ጋር ተያይዞ የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ ዜጎችን ከጎርፍ አደጋው ለመታደግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ አቶ ደበበ ዘውዴ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ኮሚሽኑ በአደጋው ጊዜ፣ ከአደጋው በፊትና ከአደጋው በኋላ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች በሚመለከት ከሔለን ተስፋዬና ከተመስገን ተጋፋው ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የጎርፍ አደጋ መከሰቱ ይታወቃል፡፡ ከመከሰቱ በፊት ኅብረተሰቡ ራሱን ከአደጋው አስቀድሞ እንዲጠብቅ በኮሚሽኑ ምን ተሠርቷል?

አቶ ደበበ፡- የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በሰጠን መረጃ መሠረት፣ የጎርፍ አደጋ ሥጋት ያለባቸውን አካባቢዎች የመለየት ሥራ ሠርተናል፡፡ እንዲሁም ከጎርፍ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ለመፍታት ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ከውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣንና ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት፣ ማኅበረሰቡ ራሱን ከአደጋ እንዲጠብቅ ተደርጓል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራውም ቀደም ተብሎ ክረምቱ ሳይገባ ተሠርቷል፡፡ ክልሎች ላይ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፣ ድሬዳዋ ተጠቃሽ ነች፡፡ በድሬዳዋ ማኅበረሰቡ ውስጥ ጠልቆ በመግባት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በመሠራቱ፣ በ2012 ዓ.ም. የተከሰተው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ቢኖርም እንኳን የጎርፍ አደጋ በድሬዳዋ ላይ አለማየታችን እንደ ለውጥ ይታያል፡፡ በዚህም መሠረት በጎርፍና የመሬት መንሸራተት ሥጋት ውስጥ ያሉትን አካባቢዎች በመለየት፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ማሠራጨት፣ የጎርፍ መከላከያ መዋቅሮችን ማጠናከር፣ ማኅበረሰቡ ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ንቁ ሆኖ እንዲጠብቅ ግንዛቤ መፍጠር፣ በደጋማ ቦታዎች የጎርፍ ፍሰት ፍጥነትን ቀድሞ ማወቅ እንዲቻልና ለሚወሰደው ዕርምጃ ዝግጅት በማድረግ አደጋው ከተፈጠረ በኋላም፣ በወቅቱ በአስቸኳይ ድጋፍ የማድረግ ሥራ መሥራት ችለናል፡፡ በዚህም የተነሳ የዜጎችን ሕይወት መታደግ ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ዜጎች በጎርፍ ምክንያት የደረሰው ጉዳት ምንድነው?

አቶ ደበበ፡- በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ በአማራ፣ በጋምቤላና በሶማሌ ላይ ከፍተኛ የሆነ የጎርፍ አደጋ ተከስቷል፡፡ በአጠቃላይ 1,095,350 ዜጎች ላይ የጎርፍ አደጋ የደረሰ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 313,179 ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ለእነዚህም ሰዎች መንግሥታዊ ከሆኑ ድርጅቶችና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ድጋፍ እያደረግን እንገኛለን፡፡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም ድጋፍ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል፡፡ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ ዘይት፣ ዱቄት፣ ብርድ ልብስ፣ ለመጠለያ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን፣ ብስኩት፣ ወተት ድጋፍ ማድረግ ችለናል፡፡ በተለይም በዚህ የጎርፍ አደጋ ሊጎዱ የሚችሉ ሴቶች፣ ሕፃናትና እናቶች ታሳቢ በማድረግ አልሚ ምግብ ተልኳል፡፡ በጎርፍ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋሙ ወደፊት የሚሠራበት ሲሆን፣ ኮሚሽኑ ከተሰጠው ተልዕኮ አንዱ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ከባዱና ፈታኙ ሥራ መልሶ ማቋቋም ነው፡፡ ምክንያቱም ንብረት በጎርፍ ይወሰድባቸዋል፣ የኑሮ ዘይቤ የመሠረቱባቸው ሀብቶች ጎርፉ ጠርጎ ሊወስድባቸው ይችላል፡፡ ይኼን በመከላከልና በማቋቋም ደረጃ መሠራት የሚቻለው በቅንጅት ነው፡፡ ለምሳሌ በምዕራብ ጉጂና ጌዴኦ አካባቢ በጎርፉ ምክንያት 313,179 ለሚሆኑ ተፈናቃዮች በጊዜያዊነት ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው፡፡ ዘላቂ የሆነውን መልሶ ማቋቋም ለመሥራት ሁሉንም በማሳተፍ የሚሠራ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በጎርፍ አደጋ የሚፈናቀሉ ሰዎች በብዛት ወንዞች ዳርቻ የሚኖሩ ናቸው፡፡ አሁን ሥጋቱ ሲቀንስላቸው  ወደ ቦታው መመለሳቸው በተደጋጋሚ የሚታይ ነው፡፡ ሌላ የጎርፍ አደጋ ሥጋት እንዳይኖርና እነዚህን ዜጎች ከጎርፍ አደጋ ቀጣና ውስጥ ለማስወጣት በኮሚሽኑ ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ደበበ፡- በየዓመቱ በእነዚህ አካባቢዎች ነው ችግሩ ያለው፡፡ ምክንያቱም የአደጋ ሥጋት ቀጣናዎች ተለይተዋል፡፡ ነገር ግን እነርሱ ከለመዱት ቀዬ ተለዋጭ ቦታ ለመስጠት ረዘም ያለ ጊዜ ይወስዳል፡፡ በባህልም ከለመዱትና ዕትብታቸው ከተቀበረበት ቀዬ ራቁ ለማለት ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሠራ ነግረውናል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ አደጋውን ማስቀረት ያልተቻለው ለምንድነው?

አቶ ደበበ፡- ኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ውጥረት ውስጥ ናት፡፡ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ዓውድ ውስጥ ችግር የለም ለማለት አያስደፍርም፡፡ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ በድርቅና ከጎርፍ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የመሬት ናዳ፣ የመሬት መሰንጠቅ ያጋጥማል፡፡ አሁን ያለው ሥራ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ጨምሮ የአደጋ ሥጋትን ለመቀነስና ምላሽ ለመስጠት፣ በብሔራዊ ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበርያ ማዕከል (Emergency Coordinating center (-ECC) ተቋቁሟል፡፡ በቨርቹዋል ስብሰባ ሁልጊዜ ምክክር ይደረጋል፡፡ እዚህ ውስጥ ሁሉም ባለድርሻ መሥሪያ ቤቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ኮሮና ቫይረስ ጉዳዩ በዋናነት የሚመለከተው የጤና ሚኒስቴር ቢሆንም፣ ከውጭ አገር ለሚገቡ ዜጎች የጤና ሴክተሩ ብቻ ይሠራል ማለት አይደለም፡፡ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጤናው ሴክተር ጋር ተናበው ይሠራሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ይቀበላል፡፡ ከዚያም ኳራንቲን ገብተው ተገቢው ክትትል ይደረጋል፡፡ ይህን አቀናጅቶ ለመሥራት ኢሲሲ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በጎርፍ አደጋና በሌሎችም ችግሮች በጋራ የሚሠሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ተቀናጅቶ በመሥራት በኩል ጥሩ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በጋራ በመሠራቱ 360,056 የጌዴኦና የምዕራብ ጉጂ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ተችሏል፡፡ አደጋን መከላከል የአንድ ዘርፍ መሥሪያ ቤት ብቻ የሚሠራው አይደለም፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ  ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጎርፍ አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ አካባቢዎች ከተለዩ በኋላ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ደበበ፡- የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ መረጃን መሠረት አድርገን እያንዳንዱ እየተከታተልን እንገኛለን፡፡ ከዚያ በሚወጡ መረጃዎች አማካይነት ቅድመ መከላከል ሥራ ሊሠራ ተችሏል፡፡ አደጋው ቀነሰም አልቀነሰም ግን አደጋውን የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ በድርቅ ምክንያት ለተጎዱ ዜጎችስ ምን እያደረገ ነው?

አቶ ደበበ፡- በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በሚከሰተው ችግር ምክንያት በአሁን ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ 7.5 ሚሊዮን ዜጎች በየስድስት ወሩ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ ድጋፉም የሚደረግላቸው በዓመት ሁለት ጊዜ ሲሆን ይህም ተግባር የሚከናወነው ከጥር እስከ ሰኔ፣ ከሐምሌ እስከ ታኅሣሥ ባሉት ወራት ውስጥ ነው፡፡ ድጋፉ የሚከናወነው በሦስት አካላት ሲሆን 60 በመቶውን የሚይዘው መንግሥት፣ 22 በመቶውን ደግሞ የዓለም ምግብ ፕሮግራምና 18 በመቶውን ደግሞ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች  አማካይነት ነው፡፡ ይህም በየዓመቱ የሚከናወን ሲሆን ዘንድሮ የዕለት ደራሽ ምግብ የሚቀርብላቸው 8.2 ሚሊዮን ዜጎች አሉ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ጦርነቱና ሒደቱ

ሦስት ሳምንታት ያስቆጠረው ሦስተኛው ዙር የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁንም...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ያለው ሦስተኛው ከግል ባንክ ሆነ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን...