Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር‹‹መካር የሌለው ንጉሥ ያለ አንድ ዓመት አይነግሥ››

‹‹መካር የሌለው ንጉሥ ያለ አንድ ዓመት አይነግሥ››

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ

መቼም አገራችን በምሳሌ፣ በታሪክና በወግ የበለፀገች በመሆኗ እጅግ ደስ ስለሚለኝ በምሳሌ አስደግፌ መክተብን ስለማዘወትር ማንም ይከፋል ብዬ አላምንም። የጋራ ታሪካችን ነውና። ታላቁ ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ የዘመኑን ሳይንስም ሆነ የቴክኖሎጂ ዕውቀት ባልጀመርንበት፣ ከጊዜያቸው የቀደሙና ዛሬ ለደረስንበት የዓለም ሁኔታ እንድንደርስ፣ የዓለም ጭራ ሆነንም እንዳንቀር ፈር ቀዳጅና የትምህርትን ብልጭታ ጥለውልን ያለፉ ንጉሠ ነገሥት መሆናቸውን እኛ ብቻ ሳንሆን፣ የዓለም ታላላቅ መሪዎች የመሰከሩላቸው አዋቂና ብልህ መሪ ነበሩ።                                                   

ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ዛሬ ስማቸውን ለማጉደፍ ለምንሯሯጠውም ወገኖች መንገድ ከፍተው ከባርነት ነፃነትን ያጎናፀፉን የሁላችንም እኩል መሪም ነበሩ።  አፄ ምኒልክ ታላቅ ሰው ከመሆናቸውና አስተዋይ ከመሆናቸው የተነሳ ምንም ነገር ቢያስቡና ለመወሰን ችሎታ ቢኖራቸውም፣ ያለ አማካሪ አይወስኑም ነበር ይባላል፡፡ ከዚህም ሌላ ማንንም ስላወቁ፣ ስለወዱና ስለተማመኑበት ብቻ በፈለጋቸው ጊዜ ጠርተው አይሾሙም፣ አይሽሩም ነበር ይባላል። ለመሾምም ሲፈልጉ ወሬው በከተማው ሕዝብ ዘንድ እንዲሠራጭ አድርገው የሰውን ስሜት ካዳመጡ በኋላ፣ ያ ሰው ምን ያህል ተቀባይነት አለው? ምን ያህል ተወዳጅ ነው? የሚል ግምገማ በማድረግ ነበር የሚሾመው ወይም በወሬ ብቻ ከስሞ የሚቀረው።                                                                     

አፄ ምኒልክ ከአማካሪዎቻቸው ውጪ ምንም እንደማያደርጉ በዘመኑ የነበሩ ታላላቅ ሰዎች ይናገሩላቸው ነበር፡፡ ሩህሩህ፣ አዛኝና ለውሳኔያቸው ወደ ኋላ የማይሉ ታላቅ ንጉሥ ነበሩ። በአንድ ወቅት የጎንደር ሕዝብ አስቸገራቸውና ጦር ሊልኩ ወስነው ከባለቤታቸው ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ሲወያዩ፣ አንድ ወጣት ጭንጫ የቤት ልጅ ይሰማቸዋል፡፡ ይህ ወጣት እጅግ በጣም አዋቂና አስተዋይ ነበርና ይህ ጉዳይ ትንሽ ቅር ያሰኘዋል፡፡ እቴጌይቱ ፊት እንዳይናገር ፈራ፡፡ እንዳይተው ነገሩ ውጤት አልባ እንደሚሆን ይረዳና አፄን ለብቻቸው አግኝቶ ሊያነጋግራቸው መፈለጉን እቴጌ ይሰማሉ። ይህ ወስላታ እንዴት ቢዳፈር ነው ንጉሡን ለብቻው ሊያናግራቸው የፈለገው ብለው በጣም ተቆጥተው ከቤተ መንግሥቱ ያባርሩታል።

ይህ ወጣት ተስፋ ሳይይቆርጥ በየመንገዱ አፄ ምኒልክን ሲጠባበቅ ያገኛቸዋል። ኩታውን መሬት ላይ አንጥፎ ጃንሆይ ላናግርዎት ብሎ ቢጠይቅ እምዬ ምኒልክም አቅርበው ቢያነጋግሩት፣ ‹ጃንሆይ አንድ ነገር ልንገረዎት ይፍቀዱልኝ› ብሎ ጠየቃቸው። ፈቀዱለትም። ‹ጃንሆይ ግማሽ ጎን ታቅፈው እያደሩ እንዴት ግማሽ ጎንን ለመውጋት አሰቡ?› ብሎ ቢጠይቃቸው፣ ንጉሡም በነገሩ ተደንቀውና ሐሳባቸውን ለውጠው ለእቴጌ ጉዳዩን ቢነግሯቸው እቴጌም እጅግ ተደንቀው ወጣቱን ጭንጫ ወደ ቤተ መንግሥት መልሰው በልጅ አዋቂነት ተደንቆ እስከ መጨረሻው የንጉሠ ነገሥቱ አማካሪና የጦር መሪ ለመሆን በቅቶ ሁሉንም በማሸነፍ ዘለቀ። ማን ነበር ብላችሁ አልጠየቃችሁኝም፡፡ ታላቁ ብልኃተኛና የጦር መሪ የነበሩት (አባ መላ) ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ነበሩ።                                          

መንግሥታት እንደ አማካሪያቸው ሁኔታ ይገመገማሉ፡፡ በጣም ጥሩ መሪዎች በጥሩ አማካሪዎች ይመራሉ፡፡ ሌሎች ያልታደሉ ደግሞ የሚያምኗቸው አማካሪዎቻቸው እያሳሳቷቸው ወዳልተፈለገ አዘቅት ገብተው ይቀራሉ፡፡ መጨረሻቸውም የከፋ ይሆናል።                                                                              አፄ ኃይለ ሥላሴ በወጣትነት ዘመናቸው ጥሩ-ጥሩ ታላላቅ አማካሪዎች ነበሯቸው፡፡ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስም አንዱ ነበሩ፡፡ እነ ራስ ካሣ፣ እነ ራስ ዳርጌ ነበሩ። በዕድሜም ቀደም ያሉ፣ ክፉውንና ደጉን ያሳለፉ፣ የተመለከቱ፣ ከአፄ ምኒልክ ወደ ንግሥት ዘውዲቱ ከዚያም ወደ ራስ ተፈሪ የተሸጋገሩ ነበሩና በአክብሮትም በችሎታም ይቀድሟቸው ስለነበረ፣ ወግ ማዕረጉ ሳይፋለስ ዘለቁ። አዘላለቁም ለትንግርት የሚነገር ነበር።                                                             

እነኛ ታላላቅ ሰዎች ካለፉ በኋላ የመጡት በዕድሜም ታናናሾች፣ በልምምድም ገና ያልበለፀጉ በመሆናቸው ወጣቱ ንጉሥ በፈለጋቸው መንገድ መራመድን ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ ንጉሡ ወጣትም ቢሆኑ የመጀመርያውን ዘመናዊ ትምህርት ከመማራቸውም በላይ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በአስተዳደር ያደጉና የመጀመርያው የውጭ አገር የጎበኙ፣ ለዘመናዊነት ራዕይ ሰንቀው የተነሱ በመሆናቸው ብዙዎቹም አማካሪዎች የውጭ ሰዎች ስለነበሩ በተቻላቸው መጠን አገሪቱን ለመለወጥ፣ ወጣቱን ለማስተማር፣ ለመጀመርያ ጊዜ ዘመናዊ የጦር ትምህርት ቤቶችን በመክፈት የነበረውን የጠላት ምኞት ለመግታት ተዘጋጅተውና በየመስኩ ወጣቱን በማሠለፋቸው አገሪቱ በአፍሪካ ታላቅነትንና በመሪነት ደረጃ ቀድማ ተገኘች።

ይህ ልክ አይደለም የሚል ካለ በይፋ ይውጣና እንነጋገርበት። ለማንኛውም ሲሳሳቱ ተው ተመለስ የሚሉ አማካሪዎች ነበሩና ነው። እንደነ ራስ አደፍርሰው፣ እንደ እነ ራስ ብሩ፣ እንደ እነ ደጃዝማች ታዬ ጉልላቴ (ምንም እንኳ የአልጋው ተቀናቃኝ ናቸው ተብለው በነበረው ባህል እንደ ልብ ባይወጡና ባይወርዱም በአገር ጉዳይ ይመክሩ ነበር)፣ በኋላ ደግሞ እንደ እነ ጸሐፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ፣ አቶ መኮንን ሀብተ ወልድና እነ ራስ አበበን የመሳሰሉ ነበሩ። ማንም አዋቂ ቢሆን የበሰለና ለራሴ ባይ ያልሆነ፣ ለሹመት የሚሽቀዳደም የግል ጥቅመኛ ያልሆነ አማካሪ ከሌለ አንድ መሪ የመሪነቱ ዘለቄታው አጠራጣሪ ነው። በዓለም ላይ ብዙ መሪዎች ታይተው ጠፍተዋል፡፡                                       

በአሜሪካን ታሪክ የመጀመርያው ወጣት መሪ ቴዎዶር ሩዝቬልት ሲሆን፣ ሁለተኛ ወጣት የመጀመርያ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይና የአይሪሽ ተወላጅ የነበረው ጆን ኤፍ ኬኔዲ ነው፡፡ ለታሪክ የተፈጠረ ሰው ነው ይሉታል፡፡ ለምን ቢባል አንደኛ ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ የዘር አድልኦ በነበረበትና ጥቁር፣ አይሪሽና ጁይሽ እንኳንስ ለአገር መሪነት ለስቴት ገዥነት በማይታሰቡባት አሜሪካ ወጣቱ ኬኔዲ በመሪነት መመረጡ ተዓምር የተባለለት ቢሆንም፣ ሕዝብ የመረጠው ነውና መቼስ ምን ይደረግ? ግን የአሜሪካ መሪዎች እንደ ልባቸው ያውሩ እንጂ ከአማካሪያቸው ሐሳብ ውልፍት ማለት ስለማይችሉ ነገሩ ሁሉ የሚመራው በአማካሪዎቹ፣ ከዚያም ሲያልፍ በኮንግረስና በሴኔት የአገሪቱ ሁኔታ ሁሌም በሰላም ይካሄዳል። መሪው ምክሩን የማይቀበል ከሆነ አማካሪው ይህ ሥልጣን ይቀርብኛል፣ ነገ ምን እሆናለሁ ሳይል ሥራውን በፈቃዱ (ዌክ አፕ ኮል ይሉታል) ይለቅቃል (ይህ ደግሞ ለመሪው የማብቂያ ጥሪ እንደሚሉት በመሪው ላይ እምነት ያሳጣል)፡፡

አንድ ምሳሌ ላንሳ፡፡ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር በኢራን የአሜሪካኖች ጠለፋ ጉዳይ እ.ኤ.አ. በ1977 ከምክር ውጪ በወሰደው ዕርምጃ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው ቫንስ ምክሬን ሳትቀበል በራስህ መንገድ ስለሄድክ ከሥራዬ ተሰናብቼያለሁ በማለቱ፣ ጂሚ ካርተር መቅኖ አጥቶ ሁለተኛውን ምርጭ ሳያሸንፍ ቀረ፡፡ የፊልም አክተር የነበረው ሮናልድ ሬጋን በአሜሪካ ታሪክ የመጀመርያው ሽማግሌ አክተር ለመመረጥ በቃ። የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ኦውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ ሲሾም ወጣት በመሆኑ፣ የ79 ዓመት አዛውንት በቅርብ እንዲያማክረው ተብሎ ዳቪድ ሎይድስ አጠገቡ ሆኖ እያማከረው ከጊዜ በኋላ ራሱን ችሎ ሌሎች አማካሪዎች ተደርገዋል።

በአፍሪካ የሚመጡት መሪዎች ከእኔ በላይ ላሳር እያሉ ሁሉንም ወሳኝ በመሆን መሥራት ስለሚፈልጉ፣ አማካሪዎቻቸው ከእነርሱ በታች እንጂ ከላይ እንዲሆኑ አይሹም፡፡ ‹አቤት ጌታዬ ምን ልሁንልህ? ምን ላድርግልህ?› የሚሉ አቤት ባይ አማካሪዎች ስለሚፈልጉ፣ ከሥራውና ከአገሩ ፍላጎት ጋር የተመጣጠነ ጠቃሚና ዘለቄታ ሊያመጣ የሚችሉ አማካሪዎች ስለሌሉ፣ ሁሉም ታጥቦ ጭቃ ከመሆን አያልፍም፡፡ የአፍሪካ መሪዎች በጥንቃቄ ከእኔ በላይ ላሳር ማለትን ትተው የአገራቸውንና የወገናቸውን የልብ ትርታ ቢያዳምጡ መልካም ይሆናል።

አንዳንድ በተፈጥሮዋቸው አዋቂና ሊቅ የመሆን አዝማሚያ ያላቸውና ከዕድሜያቸው የቀደሙ ከሺሕ ውስጥ አንድ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን ወጣቱ ሁሉ እንደ እነሱ ነው ማለት አይደለም። ዶክትሬት ዲግሪ ያለው ሁሉ ታላቅ አዋቂ ነው ማለት አይደለም። አንድ ሐኪም የሜዲካል ዲግሪ ስላገኘ ብቻ ከነባሯ ነርስ የተሻለ አይሆንም፡፡ ልምድና ተመክሮ ያሻልና፡፡ ከሁሉ መቅደም የሚገባው አስተውሎትና ልምድ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።  ተመክሮ፣ ፈሪኃ እግዚአብሔር የሚባሉ የተፈጥሮ ሕጎች አሉ፣ ይኖራሉም።

ነገር ግን በአፍሪካ በ1960ዎቹ ብዙ አገሮች ገና ከቅኝ አገዛዝ ነፃ በመውጣት ላይ ስለነበሩና የተማሩ ስላልነበሯቸው፣ የተገኙትን ሁሉ ወደ መሪነት አመጧቸው። ይህም የሆነበት እነዚያው ገዥዎቹ ባዕዳን እንዳይቀጥሉበት ስለተፈለገ ነበር። ይህ እንግዲህ የአንድ ትውልድ ጊዜ ነውና እያደር እየተሻሻለ ይሄዳል የሚል ተስፋ አለ። ለምሳሌ በናሚቢያ ያየሁት አንድ ነገር ሹመቱን ሁሉ የያዘው የአገሬው ተወላጅ ሲሆን፣ ሀብትና ንብረት ግን በእነዚያው በቀድሞዎቹ የውጭ ሰዎች ነበር። ይህ እንግዲህ የተማረም ሆነ በልምድ የዳበረ የአገሬው ተወላጅ ባለመኖሩ ነው። ይህም ቢሆን ከሌሎች በማየት መንገድ መንገዱን እየያዙ ይመስላል።

የሩዋንዳን አጀማመርና የደረሰውን ዕልቂት፣ እንዲሁም ተመልሳ እንዴት ያንን መከራ እንዳሳለፈች መመልከት ይበጃል። ለቴክኖሎጂና ለኢንዱስትሪ ከመሽቀዳደም ይልቅ ለፖለቲካ ሩጫ ትናንትን አለማወቅ፣ ሊያጠፉን አድፍጠው ለሚጠባብበቁን አውራ ጎዳና መክፈት እንዳይሆን ይታሰብበት። ፊደላቸውን አስቀድመው አስገብተዋል፣ በአካል ለመግባትም የወጣቶቻችንን ልብ እንዳይሰልቡ እንጠንቀቅ፡፡ አንፈራራ ተቀራርበን እንወያይ።                                                                                  

ብታምኑም ባታምኑም አንድ የሚደንቅ ነገር ልንገራችሁ፡፡ የኢራንና የአሜሪካ ፍጥጫ በነበረበት ዘመን የታየኝን ምክር ለፕሬዚዳንት ካርተር ጽፌ ብልክ፣ እንደ አፍሪካ መሪዎች በንቀት ሳይመለከቱት በቁምነገር ተቀብለው ምክሬን ሥራ ላይ በማዋላቸው እኔም በጣም ተገረምኩ፣ ተደሰትኩም። ሆዲንግ ካርተር በተባለ ረዳታቸው በኩል የተላከልኝን የምሥጋና ደብዳቤ ‹‹ከባቹማ እስክ ቨርጂኒያ›› በሚለው የሕይወት ጉዞዬ ገጽ 319 ላይ ማንበብ ይቻላል፡፡ የምዕራባዊያንን ቀልጣፋነትንና ለሰው ሐሳብ ምን ያህል ዋጋ እንደሚሰጡም ተረዳሁ። ይህ በአፍሪካ መሪዎች ቀርቶ በቀበሌ ሹማምንት ዘንድ እንኳ ዋጋ የሚሰጠው አይደለም። ‹‹መካር የሌለው ንጉሥ ያለ አንድ ዓመት አይነግሥ›› የሚለውን እስኪ ለማመዛዘንና ለመተርጎም ሞክሩ።                                      

አገር የሁሉም እንጂ የአንድ ገዥ ብቻ አይደለችምና በምክር፣ በማስተዋልና በመግባባት ለማስተዳደር መሞከሩ መልካም ሲሆን በቀናነት ትናትንም ማስታወስ መልካም ይሆናል። ልጅ ያለ አባት እንደማይወለድ ሁሉ፣ ትናንት ምን ነበር ብለው ነባሩን የሚያስታውስን ጭራሽ ማራቁ በሠለጡኑት አገሮች እንደ ነውር የሚቆጠር ነው፡፡ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ከ55 ዓመት በላይ ያሉትን ለአዛውንትነት እንኳ ያልደረሱትን ሲያርቋቸውና የቁንጅና ውድድር ይመስል 50 ዓመታት ያልሞላቸውን አግበስብሰው ሲደናቆሩ ማየት እያስገረመኝ ነው።

ተው ልብ በሉ! ያለ አባት በሬ ምንም ጉልበት ቢኖረው ወይፈን ፈር ከመልቀቅ ስለማይመለስ፣ ግድ የለም ማቀላቀሉ የበለጠ ተመክሮን ስለሚሰጥ እምብዛም አትናናቁ። አለባበስንና ጥራዝ ነጠቅ ቋንቋን ከአሜሪካ ከመቀላወጥ ይልቅ የአስተዳደርና የእኩልነት መብት እንዴት እንደሚጠቀሙ የቋንቋቸውን ያህል ብንሻማ ምን ያህል በጠቀመን ነበር? ለአገር አንድነት፣ ብልፅግናና ለወጣት ዕድገት ሁሉም ተባብሮ ቢሠራ ይባጃል፡፡ ያለፈውን ለመናቅ በልጦ መገኘት እንጂ የቃላት ውዥንብር ፋይዳ ስለማይሰጥ ይታሰብበት ነው አቤቱታዬ።

ግለሰቦች አገር ለመምራት ከመራወጣቸው በፊት ያደረጉትን አስተዋፅኦ ያስመዝግቡ፡፡ መማር ብቻ የአገር መሪ አያደርግምና የድርሻቸውን አስተዋፅኦ ያሳዩ፡፡ ወገን ከወገን ማበጣበጥ፣ ጥሩ ቋንቋ መነጋገር፣ አገሮችን መጎብኘት የሃይማኖት ሊቅ መሆን የመሪነት የምስክር ወረቀት አለመሆኑንም መገንዘብ ያሻል። ‹‹ሁሉ ቃልቻ ማን ይሸከም ስልቻ›› ሆነና ሁሉ መሪ መሆን ሲሻ ተመሪ እየጠፋ እኮ ነው። አገርን በኢንዱስትሪና በቴክኖሎጂ ማራመድና ያለችውን የተፈጥሮ ሀብት ከመጠቀም ይልቅ፣ አገርን በትኖ ቀውስ ውስጥ ለመዶል የሚፈልጉ የፖለቲካ መሪ ነን ባዮች ቆም ብለው ቢያስቡ መልካም ይሆናል፡፡ አንዴ የተሾመን ሰው በይፋ የሚታይና በፍርድ የተወሰነበት ታላቅ ወንጄል እስካልሠራ ድረስ፣ ጊዜውን ጨርሶ ተወዳድሮ እስኪወድቅ ድረስ ጊዜ መስጠት፣ የአዋቂዎች ተግባር መሆኑን በመገንዘብ በትዕግሥት መጠበቅ ተገቢ አይሆንምን? የአፍሪካ ነገር የሚገርም እየሆነ ነው፡፡

ለም መሬትና ወራጅ ወንዞች እያሉ ሠርቶ ያልደከመ ወጣት ሥራ አጥቶ ሲንገላወድ፣ የደላቸውና የሚሠሩትን ያጡ ሥልጣን ቢሰጣቸው የባሰውን አገር የሚያጠፉ ‹‹ከበሮ በሰው እጅ ያምር ሲይዙት ያደናግር›› ዓይነት ወገኞች፣ የሕዝባቸውን ቅሬታና ጭንቀት ቢያዳምጡ መልካም በሆነ ነበር። ወጣቱ ሥራ በማጣት በየዓረብ አገሮች እየተሰደደና ሳይደርስም ቀርቶ የዓሳ እራት እየሆነ እያዩ ምነው ለልማት ታጥቀው አይነሱ? የመሪነት ወንበር አንድ ብቻ ነች፡፡ እርሷንም የመሪነት ችሎታ አለን የሚሉ በየጊዜው ከማወናበድ ጊዜው ሲደርስ በምርጫ ተወዳድረው ቢይዙ ሁሉም ባከበራቸው ነበር።

ለሁላችን ልቦና ይስጠን – አሜን!                        

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ የሕይወት ጉዞአቸውን የተረኩበት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...