Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበሽሙጥ ብዛት ሕግ አይከበርም አገርም አይመራም

በሽሙጥ ብዛት ሕግ አይከበርም አገርም አይመራም

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መስተሀቅር የጨረባም ተሰኘ የጨረቃ፣ ወያኔ ምርጫዬ ነው ያለውን ድንቅ ተውኔት አስቀድሞ ሲዝት እንደ ከረመው በዘመን መለወጫው ዋዜማ፣ ማለትም ባለፈው ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዳሻው የሚያንገላታውን ምስኪን ብዝኃ ተጋሩ በግዳጅ ጭምር እያስወጣ ከማካሄድ ያገደው አንዳች ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ያለ ጥርጥር አሳይቶናል፡፡

አሁንማ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ፈቃዱን የነፈገውና የፌዴራሉ መንግሥት አብዝቶ የተሳለቀበት ያ ድራማ ተጠናቆ፣ የመራጮች ድምፅ ተቆጥሮና ውጤቱ በይፋ ታውጆ ከራሱ ጋር ለመወዳደር ይህ ነው የሚባል ይሉኝታና ኃፍረት ያልተሰማው ግብዙ ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጥቂት አጫዋቾቹን ብቻ ከጎኑ አሠልፎ እነ ማንን በዝረራ እንዳሸነፈ እንኳ በውል ሳይረጋገጥ፣ አዲሱን መስተዳድር እንደሰየመና የቀድሞውን ምክትል ፕሬዚዳንት ወዲ ገብረ ሚካኤልን የክልሉ ሙሉ ፕሬዚዳንት አድርጎ እንደ መረጠ ጭምር ሰማን አይደል?

እርግጥ ነው በትግራይ ክልል የተካሄደው የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ ሕገ መንግሥታዊ ስላልሆነ ከመነሻው እንዳልተደረገ የሚቆጠር ነው ተብለናል፡፡ ውጤቱም ተቀባይነት የሌለውና ሊፈጸም የማይችል ነው ሲል ምርጫው ከመካሄዱ አራት ቀናት ያህል አስቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የመጀመርያው የሆነውን አስቸኳይ ጉባዔ በመጥራት፣ በሰፊው ከመከረና ከተከራከረበት በኋላ አለኝ የሚለውን አቋም በአብላጫ ድምፅ አስተጋብቷል፡፡ ሆኖም የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት የመጨረሻ ባለአደራ የሆነው ይህ አካል በመገናኛ ብዙኃን ቅብብሎሽ ከተደመጠ አስደማሚ ውግዘት ባለፈ፣ ያንኑ ውሳኔውን እንዴትና በምን ዓይነት መንገድ ገቢራዊ ሊያደርገው እንደሚችል በዕለቱ የሰጠው ፍንጭ አልነበረም፡፡

በሌላ አነጋገር የተነጣዩን ቡድን አጓጉል ዝንባሌና ሕገወጥ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ የላይኛው ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ (9) እና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 13 ድንጋጌዎች ሥር በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በሚጠበቅበት ልክ፣ ለፌዴራሉ ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆነ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ጨምሮ ያስተላለፈው የማስፈጸሚያ ትዕዛዝ ወይም መመርያ የለም፡፡

ከዚህ በኋላ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምን ሊያደርግ እንዳሰበ መጠበቅ፣ መጠባበቅ በጅጉ ያጓጓል፡፡ በሕገወጥ መንገድ የተመረጠውን የክልል ምክር ቤትና እርሱ ሰየምኩት ያለውን አስፈጻሚ አካል ያፈርሳቸዋል? ወይስ ባይፈርሱም እንደ ፈረሱ እቆጥራቸዋለሁ በማለት ተጨማሪ ቀልድ ያሰማን ይሆን?

በመሠረቱ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ (9) ድንጋጌ ሥር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሰጣቸው ዓበይት ሥልጣንና ተግባራት መካከል፣ ‹‹የትኛውም ክልል በራሱ ጊዜ ሕገ መንግሥቱን በአመፅ ወይም በፍፁም ደንታ ቢስነት ጥሶ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥልበት ጊዜ፣ የፌዴራሉ መንግሥት አስፈጻሚ አካል ጣልቃ ገብቶ የተባለውን ጥሰት ኃይል በመጠቀም ጭምር እንዲያስቆም›› የሚያዘው ይገኝበታል፡፡

የላይኛው ምክር ቤት በሕገ መንግሥት ደረጃ የተጎናፀፈው ይህ ግዙፍ ሥልጣን ዘግይቶ በአዋጅ ቁጥር 359/1995 ዓ.ም. አማካይነት ይበልጥ ተጠናክሮ የተደነገገ ሲሆን፣ ዝርዝር አሠራርም ተበጅቶለታል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎች ጣልቃ እንዲገባ ሲታዘዝ ሊፈጸም የሚገባውን ሥነ ሥርዓት ለመወሰን በወጣውና ቅርጫት ውስጥ ተጥሎ በከራረመው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ መሠረት፣ ‹‹የትኛውም ክልል ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ ስለመሆኑ በራሱ አነሳሽነት ሲያውቅም ሆነ ከሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ወይም ከሌላ ከማናቸውም መንግሥታዊ አካል በኩል መረጃ ሲደርሰው፣ ተፈላጊውን ቅድመ ምርመራ ካካሄደ በኋላ የተባለው አደጋ መኖርና አለመኖሩን ለመወሰን እንዲያመቸው ጉዳዩን በዝርዝር አጣርቶ ውጤቱን ያቀርብለት ዘንድ፣ ለአገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም አግባብ ላለው ለሌላ የመንግሥት አካል›› መመርያ ሊሰጥ ይችላል፡፡

‹‹የደረሰውን ሪፖርት ወዲያውኑ ተቀብሎ ካጣራ በኋላም ከሚያገኘው መረጃ በመነሳት አስፈላጊ መስሎ የተሰማው እንደሆነ፣ ምርመራው እንዲካሄድ በተወሰነበት ክልል ውስጥ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባና የእርምት ዕርምጃዎችን እንዲወስድ ያደርግ ዘንድ›› ከፍ ብሎ የተጠቀሰው አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ (4) ድንጋጌ፣ ለዚሁ ምክር ቤት በማያሻማ ኃይለ ቃል ተጨማሪ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡

የዚሁ አዋጅ አንቀጽ 14 ንዑስ አንቀጽ (2) ፊደል ተራ ቁጥሮች ሀ እና ለ ድንጋጌዎች ደግሞ፣ በክልሎች ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚታዘዘው አስፈጻሚ የመንግሥት አካል የሚወስዳቸውን ዕርምጃዎች ምንነት የሚያብራሩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህም መሠረት ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁኔታውን አሳሳቢነት ተመልክቶ የተደቀነውን አደጋ ሊቀለብስ ወይም በቁጥጥር ሥር ሊያውል የሚችል የፌዴራል ፖሊስ ኃይል ወይም የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ (ካስፈለገም ሁለቱን) በክልሉ ውስጥ በጊዜያዊነት ሊያሰማራ›› ይችላል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ጥሰቱ ቀጥሎ የአመፁ ደረጃ የሚስፋፋ መስሎ ከታየ የዚያ ክልል ሕግ አውጪ ምክር ቤትም ሆነ ከፍተኛው አስፈጻሚና አስተዳደራዊ አካል ሳይቀሩ ከሥራ እንዲታገዱና ለፌዴራሉ መንግሥት በቀጥታ ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር እስከ ማቋቋም›› የሚደርስ መሬት አንቀጥቅጥ ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚችልም ከወዲሁ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ይህ በሚገባ እየታወቀ የአገሪቱ ሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በበኩሉ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደው አራተኛ ዙር አስቸኳይ ስብሰባ፣ ሕገ መንግሥቱ እንዲተረጎም ተደርጎ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሞ የነበረው ስድስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ተገቢው ጥንቃቄ እየተደረገ በአገር አቀፍም ሆነ በክልል አቀፍ ደረጃ በ2013 ዓ.ም. እንዲካሄድ መወሰኑን ተከታትለናል፡፡

በእርግጥ ወያኔ በትግራይ ምድረ ግዛት የተናጠል ምርጫውን ካካሄደበት ቀን ጀምሮ ሲሠላ ሁለት ሳምንት እንኳ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይህንን የመሰለ የፈራ ተባ ውሳኔ ለማሳለፍ በከፍተኛ መርበትበት ያን ያህል የተጣደፈበት ፍጥነት፣ በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን መጫሩ አልቀረም፡፡ የዳር አገር ልምድ ተቀስሞ የተወሰደ ዕርምጃ ነው ብለው የተቹም አልጠፉም፡፡

ቀድሞ ነገር የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች አለቅጥ ተንጠራርቶ እስከ ማስተርጎም በዘለቀ አሠራር ያለ የሌለው ቀዳዳ ተፈልጎ በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. ምርጫው እንዲራዘም የተወሰነው በኮቪድ 19 ምክንያት ከነበረ፣ ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ አሁን ቀንሷልን? ብለው የምፀት ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች መኖራቸውም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

ዱብ ዕዳ በሚመስል መንገድ በፓርላማው በኩል የተላለፈውን የዚህን ውሳኔ የተፈጻሚነት ሽፋን በተመለከተ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አያይዘው ለፕሬስ ግልጽ እንዳደረጉት ከሆነ ደግሞ፣ ስድስተኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ ትግራይን ጨምሮ በመላ አገሪቱ ነው የሚካሄደው፡፡

እብሪተኛው ወያኔ ግን በወኪሎቹ አማካይነት ለፌዴራሉ ምክር ቤት የሚወከሉትን እንደራሴዎች አስመልክቶ እንነጋገር ይሆናል እንጂ፣ ድጋሚ የክልል ምክር ቤት አባላት ምርጫ ብሎ ነገር በትግራይ ክፍለ ግዛት ጨርሶ የሚታሰብ ጉዳይ አይደለም ሲል የመልስ ምት ሲሰጥ አድምጠነዋል፡፡

እንግዲህ በያዝነው 2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ በእርግጥ እንደታቀደው የሚካሄድ ከሆነ፣ ትግራይ የሁለቱ ተፎካካሪ ዝሆኖች መፋለሚያ ሜዳ መሆኗ ነው፡፡ የእኛ ኃላፊነት በዚያ የፉክክር ፍላፃ ምልዓተ ሕዝቡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እንዳይጎዳ በፍልሚያው ወሳኝ ድርሻ ያላቸውን ኃይሎች ከወዲሁ መምከርና ማሳሰብ ብቻ ይሆናል፡፡

በዚህ ጸሐፊ አስተያየት የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት በየትኛውም የአስተዳደር ዕርከን ቢሆን አንድ ሺሕ አንድ ጊዜ ተጥሷል፣ ተደምስሷልም፡፡ ከዚህ አንፃር ጉዳዩን የተመለከትነው እንደሆነ ወያኔ እባክህን ተው በመባል እየተለመነ ይህንኑ የልምምጥ ጥሪ ከቁብ ባለመቁጠር የተናጠል ምርጫ በማካሄዱ፣ እንደ ሌላው ጊዜ ሁሉ ሕገ መንግሥቱን የተዳፈረ ያህል ሊያስቆጥረው እንደሚችል አንድና ሁለት የለውም፡፡

ሆኖም በዚህ ረገድ የራሱ የሕገ መንግሥቱ ቁንጮ ባለአደራ የሆነው የአገሪቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተባለው ምርጫ ሊካሄድ አራት ቀናት ብቻ ሲቀሩት ሁኔታው አባነነውና ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በአስቸኳይ ተሰብስቦ ያሳለፈው የምንተዳዬ ውሳኔ በፀባዩ ሊፈጸም የማይችልና ሒደቱን ጨክኖ ያላቋረጠ ሆኖ በመገኘቱ፣ ማዕከላዊ መንግሥቱ በክልሉ ላይ ያለውንና ሊኖረው የሚገባውን ሕገ መንግሥታዊ መብትና ሥልጣን አጠያያቂና የመከነ አድርጎታል፡፡

ስለሆነም ወያኔ ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ያካሄደው ምርጫ የጨረባ ነው ተብሎ እንደተቃለለው ሁሉ በድጋሚ ይካሄዳል ተብሎ በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የተነገረለት ምርጫም፣ በባሰ ምክንያት ከእነ ጭራሹ ቧልት ሆኖ እንዳይቀር ያሳስባል፡፡

ለመሆኑ ወያኔ ካልፈቀደ በፌዴራሉ መንግሥት ውሳኔ ይካሄዳል የተባለው ምርጫ እንደምን ሊሳካ ይችላል? እስከዚያው ድረስ ትግራይን በሕጋዊ መንገድ የሚመራትና የሚያስተዳድራት ማን ሊሆን ነው?

በሕገወጥ መንገድ ለአምስት ዓመት እንደገና ተመረጥኩ ያለው አላጋጭ ቡድን በአገር አቀፍ ደረጃ የተላለፈውን የምርጫ ማራዘሚያ ውሳኔ በራሱ ጊዜ ውድቅ አድርጎ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን የተቃውሞ መግለጫ ወደ ጎን በመተው ያካሄደውን የይስሙላ ምርጫ ተከትሎ፣ ባገኘው ሥልጣን ላይ የሚቀጥል ከሆነስ ቢያንስ በመሬት ላይ ቅቡልነቱ ተረጋገጠ ማለት አይደለምን?

እንዲያ ከሆነስ ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ›› እንዲሉ በ2013 ዓ.ም. ሌላ ምርጫ ለማካሄድ መነሳሳቱ ሕዝቡን የሚያደናግር ጉንጭ አልፋ ውሳኔ ከመሆን ይዘል ይሆን? ለማናቸውም የሁላችንም መሰባሰቢያ የሆነችው ውድ አገራችን ኢትዮጵያ የራቀው ሰላሟ ተመልሶና ደኅንነቷ ተጠብቆ ቆይቶ የሚሆነውን ለመታዘብ ያብቃን፡፡

ከአዘጋጁጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን 1981 .. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 .. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...