Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሐሳብ አፍላቂዎች ይበርክቱ!

ከአራት ኪሎ ወደ ሽሮሜዳ ጉዞ ሊጀመር ነው። የኅብረተሰቡ የኑሮ ወግ በኅብረት ጉዞ የሚደምቅበት ጎዳና። ጎዳናው ከዚህ በፊት ብዙ ትውልዶችን አይቷል። ለሥርዓት ለውጥ የታገሉ የያኔው ትውልድ አካላት ሳይቀሩ በዚህ ጎዳና ላይ ደምቀው ታይተዋል። ዛሬ ደግሞ የዛሬዎቹ ናት። ማንም ጊዜን ወደ ፊትም ሆነ ወደ ኋላ መጠምዘዝ አይችልም። ያለፉትም ቢሆኑ ወደ አሁኑ መጠጋት አይችሉም። ከታሰበልን እንዳናልፍ ተፈጥሮ ነቅታ ትቆጣጠረናለች። ሞት ከየትም አይመጣም፣ መድከም ይቀድመዋል። ከመድከም በፊት መሮጥ፣ ከመሮጥ በፊት መራመድ፣ ከመራመድ በፊት መዳህ ተፈጥሯዊ ግዴታ ነው። ደረጃና ፈርጅ የሌለው ነገር የለም። ሁሉም ሒደት አለው፣ ጉዞ አለው። መንገድ አለው። ይኼኛው የእኛ መንገድ ብዙ ቢታይበትም ዛሬም አዲስ ነው። አዕላፍ ትውልድ እንዳልተፈጠረ ሁሉ ከንፋሱ ኅብረ ዝማሬ ጋር ተመሳጥሮ ተረጋግቶ ይታያል። እኛ ደግሞ በፊናችን በኑሮ ትግል ተወጣጥረን ያሰብነውን ለማሳካት፣ የፈራነውን ለማስቀረት፣ ያቀድነውን ዕውን ሆኖ ለማየት እንጓዝበታለን። አሁን ደግሞ ታክሲዎቹ የሚሠለፉበት የመንገድ ክፍል በፍጥረተ አዳም ትርምስ የሚሆነውን ያጣ ይመስላል። ሕይወት እንደ ወትሮው መቀጠሏን በእኛ በኩል ታስተጋባለች። መንገዱን ለተረኛ መንገደኛ እያስለቀቀች!

 የታክሲያችን ወያላ በስሜት እየጮኸ ተሳፋሪ ይጭናልል። ከሥራው ጋር በአዲስ ፍቅር የተለከፈ ይመስላል። ያለ ምንም ትንፋሽ መቆራረጥ ይጣራል። ድንገት ስሜቱ ሲወዘውዘው ታክሲዋን ሥራ በፈታ እጁ ሲነርታት ክፉኛ ያስደነግጠናል። በተለይ ታክሲዋ በተነረተችበት በኩል የተቀመጠችው አንዲት ተሳፋሪ፣ ‹‹ውይ? ምነው አንተ?›› አለችው ልቧ ትርክክ ብሎ። ‹‹ቀልቤን ገፈፈው እኮ! ምናምን ይግፈፈውና!›› ስትል ሳንወድ ፈገግ አልን። የምሯን ደንግጣለች። ‹‹አይዞሽ! አይዞሽ!›› አልናት ሁላችንም። ‹‹ኧረ ዛሬ ቀኑ የእኔ አይደለም፤›› አለችን የልቧን ልታወራን ፈልጋ። አጠገቧ የተቀመጠው ጎልማሳ፣ ‹‹ምነው ምን አገኘሽ?›› አላት። አተኩረን ስናያት ከገጠሪቷ ኢትዮጵያ የመጣች መሆኗን አረጋገጥን። ‹‹አንዱ ወያላ መገናኛ አካባቢ የአራት ኪሎ ታክሲ የት ነው የሚያዘው?›› ብለው፣ ‹‹ያውልሽ እሱ ብሎ የራሱ ታክሲ ውስጥ አስገብቶኝ ይዞኝ ጭልጥ፤›› አለች አፏን በእጇ መዳፍ እየሸፈነች መገረሟን ለማሳየት። ‹‹የት?›› ሲላት ጐልማሳው፣ ‹‹ምን አውቅለታለሁ? ይዞኝ ሄዶ ሄዶ አንተ አልደረስኩም? ብለው፣ ውይ ገብተሻል እንዴ? እኔኮ ቀልዴን ነበር። በይ እስከዚህ የመጣሽበትን አምጪ ብሎ ተቀብሎ አወረደኝ። ተንገላትቼ እዚህ ብደርስ ይኼ ደግሞ ቀልቤን ገፈፈው፤›› ስትለን በሐዘኔታና በመገረም አዳመጥናት። ‹‹አይ ከተሜ! አሁን በሰው ገንዘብና ድካም መቀለድ ምን ይረባዋል? ደግነቱ ኑሮ ሲጫወትበት ስላየሁ ተቃጥዬ አልቀረሁም፤›› ስትለን ትዝብቷን እንድታብራራልን ፈልገን፣ ‹‹እንዴት?›› አልናት ማለቂያ የሌለው የጥያቄ ዘመን!

‹‹ምን እንዴት አለው? የመጓጓዣው፣ የሚበላው፣ የሚለበሰው ሁሉ ጭንቅ መሆኑ ነዋ! ጭው ያለው ሜዳ እየሰለቸን ኧረ እኛ ዘንድ ማን መጥቶ ባጣበበን እንላለን እዚህ ሌላ ነው። ታዲያ ፈጣሪዬን አመሠገንኩት አሁን፤›› አለች ‹‹ወይ ጉድ!›› እያለች። ‹‹እኛን እኮ እንዲህ ያጨናነቀን የሚንቀሳቀሰው ሰው መብዛት ነው። ባለፉት ዓመታት ሰው ብዙም አይሯሯጥም ነበር። አሁን ግን ጊዜ ተለዋውጦ የተገኘውን ሳይንቅ ሠርቶ መኖር እንደ ትልቅ ነገር የሚቆጥርበት ዘመን መጣ። ለነገሩ መንግሥት ይኼንን ቀደም ብሎ መገመቱ ላይ ስለዘገየ እንዳልሽው መጓጓዣው ጭንቅ ሆነ፤›› አላት ጎልማሳው። ‹‹ኧረ ተወኝ። የሚገርመኝ ደግሞ የእኔው አገር ታዳጊና ወጣት ከተማ ካልገባን፣ አዲስ አበባ ሄደን ጫማ ካልጠረግን እያሉ እረኝነቱንና ግብርናውን ትተው ቀዬ መልቀቃቸው ነው፤›› ብላ ስለአገር ውስጥ ስደት ስታነሳሳ የበሰለ ዕይታዋ አስገረመን። ‹‹አንቺ ለመሆኑ ምን ልታደርጊ መጥተሽ ነው?›› አላት ጎልማሳው። ‹‹እኔማ እህቴ ታማብኝ ነው የመጣሁት፡፡ በአካባቢያችን ደህና ሆስፒታል ጠፍቶ እግሯ ላይ የወጣ ቁስል እያመረቀዘ ስላስፈራን ይዘሻት ሂጂ ተባልኩና መጣሁ እንጂ፣ እኔስ ከከብቶቹ ግሳትና ከኩበት ጢስ የሚበልጥብኝ የለም፡፡ እዚህ ከሚንጋጋው መኪና የሚወጣው ጋዝማ ለጤናዬም ጥሩ አይደለም፤›› ስትለን ይህች የገጠር ኮረዳ አስደመመችን። ‹‹ጎበዝ! አያድርስ እኮ ነው ግን የአካባቢ ጥበቃ የመንገዱን ያህል ትኩረት የተሰጠው ይመስላችኋል?›› ሲል ሌላ አንድ ጎልማሳ ዝም እንዳልን ቀረን። ብዙ ሥራና ብዙ መታየት ያለባቸው ክፍተቶች ቁልጭ ብለው ይስተዋሉን ጀመር። ‹‹ጆሮ ያለው ይስማ ልብ ያለው ልብ ይበል›› እንዲሉ!

ወያላው ከጥሪው ገርገብ ብሎ የታክሲዋን ተንሸራታች በር እየዘጋ ‹‹ሳበው!›› አለው ሾፌሩን። ታክሲዋ መሙላቷን ደጋግሞ እየዞረ ይቃኛል። ጉዟችን ተጀመረ። ታክሲዋ ዋናው አስፋልት ውስጥ ገብታ ይዛን ልትነጉድ ስትንደረደር ግን አሁንም አንዴ በሰፊ መዳፍ ተነረተች።ምንድን ነው ነገሩ?› ብለን ሁላችንም ዞረን ስናይ አንዲት ትልቅ ሴት እየሮጡ ደርሰው፣ ‹‹እዚህ ታክሲ ውስጥ ዕቃ ጥያለሁ እባካችሁ ተባበሩኝ፤›› አሉ አንዴ ወያላውንና ሾፌሩን፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እኛን እያዩ። ‹‹የት ነው ተቀምጠው የነበረው?› ሲላቸው ወያላው ሁለት ወጣቶች የተቀመጡበትን ከሾፌሩ ኋላ ያለውን ሥፍራ ጠቆሙ። በእርግጥም ሲታይ ትንሽ ቦርሳ ተገኘ። ሲሰጣቸው ከፍተው ካዩት በኋላ፣ ‹‹ንብረቴ በሙሉ አለ እግዜር ይስጥልኝ። ፓስፖርቴንም፣ የባንክ ደብተሬንም ነበር እኮ ጥዬው የነበረው? አይ ልብ ማጣት እግዜር ይስጥልኝ፤›› እያሉ ሲሄዱ ጉዟችንን ቀጠልን። ‹‹ግን ሰውን እንዲህ ከቀልቡ የነጠለው ነገር ምንድነው?›› ሲል አንዱ ጠየቀ። ‹‹ምኑን እናውቀዋለን ብለህ ነው?›› ይለዋል አጠገቡ የተቀመጠው ተሳፋሪ። ‹‹ሰው ምን ልበ ቢስ ቢሆን ፓስፖርቱንና የባንክ ደብተሩን ይረሳል?›› ሲል ሌላው ወጣት አጠገቡ ያለችው ጓደኛው፣ ‹‹አንተ ደግሞ ስደትና ብድር ቀላል እየሆነ በመጣበት ጊዜ ምን ችግር አለው?›› ስትለው ፈገግ አለ። ‹‹ወይ አንቺ በራስሽ ቢሆን መቼ እንዲህ ትይ ነበር?›› አላት። በራስ ሲመጣማ ብዙ የማንለውና የማንመኘው እኮ አለ። ‹‹ያልተነካ ግልግል ያውቃል›› እየሆነ ነው እንጂ! የቀልብ ነገር ሲነሳ የብዙዎቻችን ችግር መሆኑ ለምን ይዘነጋል? እንኳን ፓስፖርትና የባንክ ደብተር አይደለም የት መሆናችንን እየዘነጋን አውራ ጎዳናው ውስጥ ዘው እያልን ለስንት አደጋ እንዳረግ የለ? ይልቁንስ ዋናው ጉዳይ መረጋጋት ነው!

ወያላው ሒሳቡን እየተቀበለ ነው። ‹‹ለመሆኑ…›› ይላል አንዱ። ‹‹ሰሞኑን የሚወራውን ነገር እየሰማህ ነው?›› ብሎ ወዳጁን ይጠይቀዋል። ‹‹እሺ እዚህ ሒሳብ?›› ብሎ ወያላው ያቋርጠዋል። ይኼኔ ስለሰሞነኛው ወሬ የተነሳለት ተሳፋሪ፣ ‹‹ምን የማንሰማው አለ? አንዳንዶቻችንን ይኼ ወያላ አፍንጫችንን ይዞ እንደሚቀበለን አፍጫችን ላይ ቆመው አለቀላችሁ ይሉናል። አንዳንዶች ግን አሉ ከራሳቸው ሥልጣንና ጥቅም ውጪ የአገር ጉዳይ ምንም የማይታያቸው፤›› ብሎት ወደ መስኮት ዞሮ ጥርሱን ማፋጨት ጀመረ። ‹‹እውነት እኮ ነው፤›› ብለው አንድ አዛውንት ሁላችንንም በየተራ ቃኙን። ‹‹ሥርዓተ መንግሥቱ መቀጠል እንዳለበትና እንደሌለበት በድምፃችን መወሰን ያለብን እኛ ሕዝብ የምንባለው መሆኑ ተረስቶ፣ እንደ ጦር አበጋዝ የሚንጎማለሉ ቀኑን ላያችን ላይ ካላጨለምን እያሉ እኮ ነው፡፡ እንዴ ኢትዮጵያ እኮ የሁላችንም ናት። አይደለም ወይ?›› ብለው ሲጠይቁንእውነት ነው….› አባት እያልን በየተራ ተቅለስልሰን መለስንላቸው። አንዱ ነገረኛ ታዲያ፣ ‹‹አንተ ሰማህ?›› ይለዋል ቀስ ብሎ ጓደኛውን፣ ‹‹እኛ እኮ አይደለንም ከመስከረም ምንትሶ በኋላ መንግሥት አይኖርም ያልነው፤›› ከማለቱ ጓደኛው እየሳቀ፣ ‹‹እኛ ደግሞ እያልን ያለው አጉል ወሬ ይቁም ነው፤›› ቢለው አንጀታችንን ውኃ አጠጣው።  ቅቤ መጠጣትማ ድሮ ቀርቷል!

ዓይናችን ውስጥ ወዲያው ዘሎ በገባ ጉዳይ አንድ ጨዋታ ተነሳ። ወያላው ሱሪውን የታጠቀበት መንገድ በዘመኑ ወጣቶች አጠራር ‹‹ፍሪክ›› በመሆኑ ሱሪው ያለ መጠን ዝቅ ብሎ መቀመጫው እየታየ አሳቀቀን። አዛውንቱ መቼም የአባት ነገር ሆኖባቸው አባታዊ ግሳፄያቸው በለመደ አንደበታቸው፣ ‹‹ኧረ እባክህ ሱሪህን ከፍ አድርገው አንተ ልጅ!? እንዴ! የዛሬ ልጆች እኮ የሚያደርጋችሁን አሳጥቷችኋል። ቀበቶን ጠበቅ አድርጎ ሱሪ መታጠቅ እኮ ትልቅ ትርጉም አለው፣ ክብርም ነው፡፡ የጠንካራ ማንነት መገለጫም ነው። ምነው ለውርደትና ለጥፋት ቸኮላችሁ?›› እያሉ ብዙ ሲናገሩ ወያላው በኃፍረት ሱሪውን ከፍ ማድረግ ጀመረ። ‹‹አይ አባት ማን የሚሰማዎት አለና? ነገሩ እኮ ማጣፊያ ያጠረው ደረጃ ላይ ደርሷል፤›› ሲላቸው አጠገባቸው የተቀመጠ ተሳፋሪ፣ ‹‹ኧረ ተወኝ። ቅጥ አንባሩ የጠፋው ነገር ነው። ሥራ አጦች ተሰብስበው በፈጠሩት ነገር ሥራ ፈቶ መዋል እስኪ ምን ይባላል? አሁን አንተ ይኼን ጊዜ ሱሪህን ከፍ ለማድረግ እያልክ ስንት ሳንቲም ጥለሃል?›› ሲሉት ሾፌሩ ዞር ብሎ አይቶት፣ ‹‹እስቲ ተናገራ!›› አለው። ምኑን ይናገረው!

‹‹የዘመኑ ልጆች ብልጥ ነን የሚሉትን ያህል እጥፍ ሞኝ፣ አዋቂ ነን ከሚሉት በላይ አላዋቂ እየሆኑ መጥተዋል። ወደፊት እናድጋለን ስንል እኮ በልቶ ለመሞት አይደለም። ፅኑ የሆነ የማይነቃነቅ አገር ለመመሥረትም ነው። ለዚህ ደግሞ ባህል፣ ቋንቋና ማንነት አብረው ነው የሚሄዱት፤›› እያሉ አዛውንቱ ሲናገሩ፣ ‹‹.. ኧረ ጉድ ነው!›› እያለች ያቺ የገጠር ሴት ከት ብላ ትስቅ ጀመር። ‹‹ምን ነው ምን የሚያስቅ ነገር ሰማሽ?›› ቢላት አንዱ፣ ‹‹ወይ ከተሜና ሥልጣኔው? አያ ሱሪ ስለመታጠቅ አውርታችሁ ሳትጨርሱ ነው ከተሜ ሥልጡን ነው ብላችሁ የእኛን ልብ የምታሸፍቱት?›› ብትለን ሳንወድ በግዳችን የኃፍረት ሳቅ ሳቅን። ‹‹ከቶም መሠልጠን እቴ!›› እያለች እሷ ከኋላችን ስትሳለቅብን እኛ ደግሞ በኃፍረት አቀረቀርን፡፡ ‹‹በተማረውና ባልተማረው መካከል ያለው ልዩነት አልታይህ አለኝ፤›› ያሉት ኢትዮጵያዊ ማን ነበሩ? እሳቸውማ በሰላም አርፈዋል!

ሳቃችን ያልተመቸው አንድ ወጣት ልጅቷን ማነጋገር ፈልጎ፣ ‹‹ምንም ሥልጣኔ አላያሁም እያልሽን ነው ታዲያ? ይኼ ሁሉ ሕንፃ፣ መንገድ፣ መኪና፣ ወዘተ ስታይ ልብሽ እውነቱን አይቀበልም?›› አላት ሙሉ ለሙሉ ወደ እሷ ለመዞር በሻተ ሁኔታ እየተቀመጠ። ‹‹ኧረ! እሱማ ደግ ነው እንጂ። ግን ምን ዋጋ አለው ከሰው ውጪ። ወያላ እኔን እንደዚያ ለገንዘብ የተጫወተብኝ እኮ እዚህ እናንተ የሠለጠነ ከተማ ከምትሉት እንጂ በገጠር መንደሬ እኮ አይደለም። በአገራችን መንገድ መምራትን እንደ መታደል ነው የምናየው። እንዲህ ያለ ምግባረ ብልሹነት ፈጽሞ ዓይተንም አናውቅም። ሥልጣኔ የሰውን አዕምሮ ካልገራ ምንድነው ፋይዳው? መንገዱ፣ ሕንፃው፣ መኪናው ለማን ነው? ለሕዝብ እኮ ነው፤›› አለችና ትንሽ ትንፋሽዋን ሰብስባ፣ ‹‹እዚህ ያየሁት በርካታ ጎደሎ ነገሮችን እንጂ የተሟላ ሥልጣኔን አይደለም። መጀመሪያ ሁሉም ራሱን አውቆ ራሱን ይመራ ዘንድ አዕምሮውን መሞረድ ነው ያለበት። በእኛ አገር ዘመዶቼ በርስት መሬትጣልተው በመተላለቃቸው ነው ዛሬ ያለ ወገን ያስቀሩኝ፤›› ስትል አዛውንቱ አቋርጠው፣ ‹‹ምን ተፈጠረ?›› አሉዋት። ‹‹ደም ተቃብተው ነዋ! ደም ሲመላለሱ ተላለቁ። ታዲያ የእኛ ኑሮ በዕውቀት ዕጦት የተነሳ ብዙ ችግሮች አሉበት። እዚህም ሱሪን ማንዘላዘል፣ ታክሲው በድብድብ እሱም ከተገኘ፣ ሐኪም በስለት፣ ምግባረ ብልሹነት፣ የገዛ ወገንን መግደልና ማፈናቀል ምን ይባላል?›› ስትለን እንደ ታላቅ አስተማሪ በአንክሮ ሰማናት። ወይ ዘንድሮ! ለካ አንዳንዱ ያለ ቦታው ነው የሚኖረው!

መድረሻችን እየተቃረበ መጥቷል። ወያላው የሱሪው መንዘላዘል ነገር ከተነሳበት ወዲህ ኩምሽሽ ብሎ ነው የተቀመጠው። ‹‹መውረጃዬን አደራ…›› ብላ የተናገረችው አስገራሚዋ የገጠር ወጣት፣ ‹‹ደህና ሰንብቱ›› ብላን ለብዙ ዘመን እንደምታውቀን ሁሉ ተሰናብታን ወርዳለች። ትዝብቷን ተመርኩዛ በሰጠችን አስተያየት ከልባቸው የተነኩት አዛውንቱ፣ ‹‹ግሩም እኮ ነው የሰው ልጅ ነገር። ብዙ ልንለወጥባቸው የሚገቡ ዋና ዋና መስኮች አሉ። አሁን ይኼን እያሰብኩ በአንድ ወቅት መንግሥት ከኃላፊነት አንስቶ ያሰራቸው ሰዎች ትዝ አሉኝ። ለውጥና ዕርምጃ ከራስ ካልጀመረና ካልተረባረብንበት ምን ትርጉም አለው? ሌላውን ከመገምገም በፊት ራስን መገምገም እንዴት ጥሩ ነበር? ታዲያ የዕድገታችን ዋና ማጠንጠኛ አስተሳሰባችን ቢሆን ጥሩ አልነበር?›› ብለው ፈገግ አሉ። የብዙዎቻችን ችግር አዛውንቱ እንዳሉት ከራስ አለመጀመር ነው፡፡ መጀመርያ ሐሳብ መለዋወጥ፣ ከዚያ ባልንጀራን ወይም የቅርብ ሰውን በጠራ መንገድ መረዳት፡፡ ሐሳብ ያላቸው በሰከነ ሁኔታ ሲነጋገሩ ችግሮች ይቀረፋሉ፡፡ መደማመጥ ጠፍቶ ጉልበተኛው ሐሳብ አፍላቂውን ሲያፋጥጠው ውጤቱ ጥሩ አይሆንም፡፡ ወያላው ባኮረፈ ፊቱ ቀና ብሎ ሁላችንንም ገላምጦን ‹‹መጨረሻ!›› ሲለን ወርደን ተበታተንን። ሐሳብ ማፍለቅን ምን የመሰለ ነገር ምን ይኖር? ሐሳብ አፍላቂዎች ይበርክቱ፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት