Saturday, April 20, 2024

‹‹ወይ ሁላችንም በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንሄዳለን ወይም ማናችንም አንሄድም›› ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

2012 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት ጠቅላላ ምርጫ በኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ሊካሄድ ባለመቻሉ የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው እንዲራዘም ከተደረገው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ተጨማሪ፣ የሥራ ዘመናቸውን በጋራ ስብሰባ በጀመሩበት ወቅት የተገኙት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር የሕግ የበላይነትን ማስከበር መንግሥት ዘንድሮ ትኩረት የሚያደርግበት ዓብይ አጀንዳ መሆኑን አስታወቁ።

በአገሪቱ ሕገ መንግሥትና በሁለቱ ምክር ቤቶች የአሠራር ሥነ ሥርዓት መሠረት፣ የነባር ምክር ቤቶች ወይም አዲስ የተመረጡ የፌዴራል መንግሥት ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን የሚጀምረው በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ዕለት ነው። 

የተራዘመው ምርጫ 2013 ዓ.ም. ተካሂዶ አዲስ ለሚመረጥ ምክር ቤት ሥልጣን እስኪያስሰክቡ ድረስ በሥልጣን ላይ እንዲቆዩ በሕገ መንግሥት ትርጉም የተወሰነላቸው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችም በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት አዲሱን የሥራ ዘመናቸውን በጋራ ስብሰባ በይፋ ለመጀመር፣ የዘንድሮው ዓመት መስከረም ወር የመጨረሻ ሰኞ በነበረው መስከረም 25 ቀን በጠቅላይ ሚኒስትር ሕፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው አዳራሽ ተገኝተው የሥራ ዘመን መክፈቻ የጋራ ስብሰባቸውን አካሂደዋል። 

ሁለቱ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመናቸውን በጋራ ስብሰባ የሚከፍቱት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር በጋራ መድረኩ ላይ ተገኝተው፣መንግሥት አካላት በዓመቱ ትኩረት ሰጥተው ሊንቀሳቀሱባቸው የሚገቡ ዓበይት ጉዳዮችን የሚያመላክት ንግግር በማድረግ ነው። 

ይህም ሁሉም የመንግሥት አካላት በዓመት ውስጥ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሯቸውን ተግባራት አመላካች በመሆኑሕዝብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ቀድመው እንዲገነዘቡት የሚያስችል አሠራር ሆኖ ይታመናል። 

ነገር ግን የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር በሚያደርጉት የመክፈቻ ንግግር መንግሥት ትኩረት የሚያደርጉባቸው እንደሚሆኑ በማንሳት የሚገልጿቸው ዓበይት ተግባራት ከራሳቸው የሚያመነጩት ሳይሆንሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ስለሥራ ዘመኑ ዓበይት ዕቅዶቹ ምንነት ለርዕሰ ብሔሩ ከሚያቀርበው ሪፖርት በመነሳት የሚዘጋጅ መሆኑን ሪፖርተር ያገኛቸው ሥነ ሥርዓቱን የሚገልጹ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

በዚህ ሥነ ሥርዓት መሠረት ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር፣ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት ንግግር መንግሥት ትኩረት ያደርግባቸዋል ብለው ካመላከቷቸው ጉዳዮች መካከል ስለሕግ የበላይነት መከበር፣ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ልምምድና ስለብሔራዊ መግባባት አስፈላጊነት ያነሷቸው ሰፊ ሽፋን ይዘዋል። 

የአገርና የሕዝብ ዕጣ ፈንታ የሚቃናው ውጤታማ በሆነና በጥንቃቄ በሚታነፅ የዴሞክራሲ ግንባታ ስለመሆኑ መንግሥት በፅኑ እንደሚያምን የገለጹት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ ነገር ግን ዴሞክራሲ በፍላጎት ብቻ የሚገነባ አንዳልሆነ በአጽንኦት በመግለጽ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

‹‹ዴሞክራሲ ሆደ ሰፊነትን፣ አስተዋይነትንና ምክንያታዊነትን ይጠይቃል፡፡ እንደ አስፈላጊነቱም ዋጋ በመክፈል ጭምር የሚገነባ ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ‹‹ዴሞክራሲ ከፍተኛ ፅናትንና ቁርጠኝነትን የሚፈልግ፣ የመብት ብቻ ሳይሆን የግዴታና የኃላፊነት ጉዳይ ጭምር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መብትና ግዴታ የዴሞክራሲ ሁለት ክንፎች ናቸው፡፡ አንዱን ብቻ ከፍ በማድረግ መብረር አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

በተጠናቀቀው 2012 ዓ.ም. በአገሪቱ የተከሰቱት የሕግ ጥሰቶች፣ የሕዝብን ሕይወትና ንብረት የቀጠፉ አስነዋሪ ተግባራት፣ ‹‹ዴሞክራሲን የተረዳንበት መንገድ ምን ያህል በስህተቶች የተሞላ እንደሆነ በቂ ማሳያዎች ናቸው፤›› ብለዋል።

ዴሞክራሲ የሁሉንም አስተዋጽኦና መስዋዕትነት እንደሚሻ በመረዳት ሁሉም በኃላፊነትና በሠለጠነ መንገድ ለመጓዝ ካልቻለ በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚ ረገድም እንደ አገር ስኬት ለመጎናፀፍ የማያስችል መሆኑን በአጽንኦት አመላክተዋል።

ይህንንም ሲገልጹ፣ ‹‹ወይ ሁላችንም በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንሄዳለን ወይም ማናችንም አንሄድም፤›› ብለዋል።

ዴሞክራሲን ከሕግ የበላይነትና ከዜጎች ዲሲፕሊን ነጥሎ ማየት እንደማይቻል ያወሱት ፕሬዚዳንቷእነዚህን አጣምሮ መተግበር ሲቻል ሁሉም በዴሞክራሲ መንገድ ለመሄድ እንደሚቻለው ገልጸዋል።

‹‹የሕግ የበላይነት ለሁሉም ዜጎች እኩል፣ ሰላማዊና ምቹ የሆነ የዴሞክራሲ ምኅዳር እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ዲሲፕሊን ደግሞ ዜጎች በተፈጠረው ምኅዳር በሠለጠነ መንገድ እንዲሳተፉ ዕድል ይፈጥራል፤›› ሲሉም አብራርተዋል።

በመሆኑም ፖለቲከኞችም ይህንኑ ዜጎች ዴሞክራሲን በባዶ ከመሻት ባለፈ፣ ዴሞክራሲ የሚጠይቀውን ሥርዓትና ዲሲፕሊን እንዲላበሱ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራዎች ዘንድሮ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

‹‹ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው፡፡ ሕዝባችን በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ ሠርቶ ራሱንም ሆነ አገሩን እንዲጠብቅ፣ ብሎም አገራችን ወደ ብልፅግና ለጀመረችው ጉዞ ስኬት ሰላም በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ በመሆኑም በሚቀጥለው ዓመት የአገራችንን ሰላም አስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስ ምልዓተ ሕዝቡን ያሳተፉ ሥራዎች በልዩ ትኩረት የሚሠሩ ይሆናል፤›› ሲሉ ከሚከናወኑት ውስጥ መሠረታዊ ናቸው ያሏቸውን ጠቃቅሰዋል።

ከእነዚህም መካከል ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ተግዳሮት የሆኑ አደረጃጀቶችና የታጠቁ ኃይሎች፣ በመላው አገሪቱ ምንም ዓይነት ሕገወጥ ተግባር ላይ እንዳይሰማሩ ማድረግ አንዱ ነው። 

የዚህ ተልዕኮ ግብም ከመንግሥት ውጪ ማንኛውም ኢመደበኛ አደረጃጀት ሆነ ሸማቂ ኃይል ትጥቅ ይዞ እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ እንደሆነ፣ ይህንንም ዕውን ለማድረግ ከፍተኛ ሥራዎች በመንግሥት የሚፈጸሙበት ዓመት እንደሚሆን አመልክተዋል።

የዜጎች ደኅንነት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ አደጋ ላይ የማይወድቅባት አገር ለመፍጠርና የሕግ የበላይነትን በሚታይና በሚጨበጥ ደረጃ ለማረጋገጥ፣ የተጀመሩ ሰፋፊ ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት ዓመት እንደሚሆን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቷዜጎች የደኅንነት ስሜታቸው እንዲጎለብት ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የተጀመሩ ተቋማትን የማደራጀትና የማብቃት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚከናወኑም ገልጸዋል።

ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የሕግ የበላይነትን በቁርጠኝነት ማስከበር የግድ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅከዚህ አኳያም መንግሥት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ዜጎች ከመንግሥት ጎን ተሠልፈው ለሕግ የበላይነት ዘብ እንዲቆሙ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሒደት ሥር እንዲሰድና ዜጎችም ከትሩፋቱ መጠቀም እንዲችሉ፣ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ሰላማዊ መንገድና አቅጣጫን የተከተለ እንቅስቃሴን በቃልም በግብርም መርጠው መጓዝ እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል። 

የሕዝቦች የሰብዓዊ መብት መከበር ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ እንማይሆን በመግለጽምየሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋማትን አቅም ይበልጥ ለማጠናከር ወሳኝ ተግባራት የሚከናወኑበት ዓመት እንደሚሆን አመልክተዋል። የዳኝነት ሥርዓቱና ሁሉም የሕግ አስከባሪ ተቋማት ይበልጥ አሠራራቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ፣ በሕግ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ብቻ መፈጸም የሚያስችላቸውን አቅም እንዲገነቡ እንደሚደረግም ጠቅሰዋል።

በዓመቱ ይከናወናል ብለው ከጠቀሷቸው ዓበይት ጉዳዮች መካከል ብሔራዊ መግባባት አንዱ ሲሆንከዚህ አኳያ በመንግሥት የተጀመሩ በጎ ጅምሮች እንዲቀጥሉና ለአንድ አገር ሰላምና ብልፅግና መሠረታዊ ከሆኑ እሴቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የሆነው የወንድማማችነት እሴት እንዲጠናከር እንደሚሠራ ገልጸው፣ ለዚህም ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዘንድሮ የሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በንግግራቸው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል።  ‹‹መጪውን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አድርጎ ለማጠናቀቅ የዴሞክራሲ ልምምዳችን በሥርዓት የሚካሄድና በሕግ የበላይነት የሚመራ መሆን ይኖርበታል፤›› ሲሉ አሳስበዋል። ለዴሞክራሲ ሥርዓተ በቂ መደላድል ለማበጀትና የፖለቲካ መበልፀግን ለማረጋገጥ ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ምርጫ መሆኑን በማመልከትዘንድሮ የሚካሄደው ምርጫ ላለፉት አሥርት ዓመታት በአገሪቱ በተካሄዱት ምርጫዎች ላይ የታየውን ጉልህ የሆነ የፉክክር ጉድለት በማረም፣ የሕዝቦችን የዴሞክራሲ ጥማት የሚያረካና ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን የሚያሟላ መሆን እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ 

በመሆኑም የአገሪቱ ፓርላማ የተለያዩ የፖለቲካ ድምፆች የሚሰሙበትና ፓርቲዎች አንፃራዊ ውክልና የሚያገኙበት እንዲሆን፣ ለቀጣዩ ምርጫ ፍትሐዊ የፉክክር ሜዳ ለመፍጠርና የፖለቲካ ምኅዳሩ ምቹ ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ዘንድሮ በህዳሴ ግድብ ሳቢያ የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ ባለፈው ዓመት የተደረጉ ሙከራዎች በማክሸፍ ረገድ የተከናወኑ ስኬታማ ተግባራትን በማጎልበት፣ ጠንካራ እንቅስቃሴ የሚደረግበት መሆኑን አመልክተዋል።

‹‹ትልቁ ቁምነገር ከአገራችን ክብርና ጥቅም የሚቀድም ምንም ጉዳይ አለመኖሩን ማስታወስ ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ‹‹በዚህ ዓመት የምንሠራቸው የዲፕሎማሲ ሥራዎች ይበልጥ አቋማችንን ለዓለም የሚያሳውቁና ሰፊ ተደራሽነት ያላቸው እንዲሆኑ ለማድረግ፣ እንዲሁም የሚደርስብንን ማንኛውንም ጫና ለመመከት ትኩረት ተደርጎ ይሠራል፤›› ብለዋል።

ዘንድሮ የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -