- ሃሎ፡፡
- ጤና ይስጥልኝ አለቃ እንደምን አሉ?
- አንተ እያለህ ምን ጤና አለ?
- ምን አጠፋሁ ክቡር ሚኒስትር?
- እንደለመድከው አስጠበስከኝ… ለመሆኑ ምን ዓይነት መግለጫ ነው ያወጣኸው ሰሞኑን?
- ሰሞኑን ያወጣነው መግለጫ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንትን ለማዘመን ያሰብነውን አዲስ አሠራር የሚመለከት ነው።
- አዲስ አሠራር ምናምን የምተለውን ትተህ ምን እንደሆነ ንገረኝ፡፡
- የግል ተሽከርካሪዎች በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓቶች ትራንስፖርት አጥተው ለተቸገሩ ነዋሪዎች ጣምራ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስገድድ አሠራር ነው።
- ጣምራ ማለት?
- ኮድ ሁለት እና ሦስት ቁጥር የሆኑ ተሽከርካሪዎች በሥራ መውጫና መግቢያ ሰዓት መንገደኞችን አሳፍረው እንዲሄዱ የሚያስገድድ በመሆኑ ነው ጣምራ ያልነው። እንደዚያ ካላደረጉ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት እንዳይንቀሳቀሱ ክልከላ ይጣልባቸዋል።
- ወይ ግሩም… ጤንነትህ ነው የሚያሳስበኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በመላው ዓለም የተለመደ አሠራር እኮ ነው፡፡ በእርግጥ መግለጫውን ስናወጣ ትንሽ ስህተት ሠርተናል፣ ለዚያ ነው ትንሽ ጫጫታ የተፈጠረው፡፡
- ምን ዓይነት ስህተት ነው የሠራችሁት?
- የመግለጫው መግቢያ ላይ በጠቅላዩ ሐሳብ አመንጭነት የሚል አላካተትንም…. እሱ ቢኖር ሐሳቡ ይሰምር ነበር፡፡
- ልክ ነው… እኔን ገደል የመክተት ዕቅድህ ይሰምርልህ ነበር፡፡
- ያደጉ አገሮች ጭምር ውጤታማ የሆኑበት ዘመናዊ አሠራር እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የግል ንብረት ላስተዳድር ማለት ነው ዘመናዊ አሠራር? ከዓላማችን እንደሚጣረስ እንኳ አይገባህም?
- እንደዚያ እንኳን አይደለም… በፓርቲ ደረጃ ከያዝነው አቋም የሚጣረስ አልመሰለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ደግሞ ምንድነው በፓርቲ ደረጃ የያዝነው አቋም?
- በብልፅግና ዘመን የእኔ የአንተ የሚባል ነገር የለም አላልንም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- አሃ…. እንደዚያም ብለናል ለካ? ጥሩ ፖለቲከኛ እየወጣህ ነው እባክህ?
- ተጠሪነቴ ለእርስዎ ሆኖ ደካማ ፖለቲከኛ ከሆንኩማ ጥሩ አይመጣም።
- ጥሩ ይዘሃል። እንዲያውም ይህንን ሐሳብ ትንሽ ለወጥ አድርገህ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ችግርን እንዲፈታበት ብታቀርበው ጥሩ ነበር፡፡
- እንዴት? ለቤት እጥረት ይሆናል ብዬ እንኳን አላሰብኩበትም ነበር፡፡
- ትንሽ ለውጥ አድርገህ ግዴታ እንዲጣልባቸው ማድረግ እኮ ነው፡፡
- ማን ላይ?
- ከአንድ መኝታ ክፍል በላይ ቤት ያላቸው ላይ?
- ምን ዓይነት ግዴታ?
- ጣምራ አይደል ያልከው? የጣምራ ኑሮ ግዴታ መጣል ነዋ፡፡
- ያስኬዳል ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የጣምራ ኑሮ የሚለው ተቃውሞ ከተነሳበት ለወጥ አድርገህ ታቀለዋለህ፡፡
- ምን ብዬ?
- ዕለታዊ ጣምራ…. ወይም እንደዚያ ነገር፡፡
- እርስዎ እኮ መለኛ ነዎት፡፡
- መላው እንኳን ነገ በደብዳቤ የሚደርስህ ይሆናል፡፡
- ደብዳቤ… የምን መላ?
- በጣምራ ከምንጠፋ… ራስህን ችለህ ጥፋ የሚል መላ!
[ክቡር ሚኒስትሩ በጠዋት ቢሯቸው ገብተው ማኅበራዊ ገጻቸውን ሲከፍቱ ታችኞቹ ያወጡት መግለጫ መነጋገሪያ ሆኖ ተመለከቱ። ስልካቸውን አንስተው አማካሪያቸው ወደ ቢሮ እንዲመጣ አዘዙ]
- መግለጫቸውን አየኸው?
- አይቼዋለሁ… ምሽት ሆኖብኝ ነው ያልደወልኩልዎት፡፡
- ይኼ ሁሉ ሚኒስትር ዴኤታ እንደነበራቸው አላውቅም ነበር፡፡
- ሃ.ሃ.ሃ.ሃ… እኔም አላውቅም ነበር… ምን አሰደነገጠዎት ግን?
- ምን አስደነገጠዎት?
- ተቆጣጥረውን የለ እንዴ?
- ተቆጣጥረውናል ሳይሆን ረድተውናል ቢሉ ይሻላል፡፡
- እንዴት?
- አልሰሙም እንዴ ክቡር ሚኒስትር አብዛኞቹ እኮ ጥሪውን አልተቀበሉትም?
- ምን?
- በርካቶቹ ለአገራቸውና ለሕዝብ ያላቸውን ወገንተኝነት አሳይተዋል።
- ምን ማለትህ ነው?
- የታገልነው ሕዝብና አገር ለማገልገል እንጂ ፓርቲ ለማገልገል አይደለም ብለው ጥሪውን ውድቅ አድርገውታል፡፡
- እና ይቀጥላሉ ማለት ነው?
- አዎ! ለዚያ እኮ ነው አድነውናል ያልኩት፡፡
- ተው አትቸኩል፡፡
- እኔ ሳልሆን እነሱ ናቸው የቸኮሉት፡፡
- እነ ማን?
- መግለጫ ለማውጣት ተጣድፈው በራሳቸው እሳት ላይ የለኮሱት፡፡
- ምን ተፈጠረ?
- ከኃላፊነት ልቀቁ የተባሉት አመራሮች ጥሪውን ውድቅ በማድረጋቸው በፓርቲው ውስጥ መከፋፈል ተፈጥሯል፡፡
- ተው አትቸኩል፡፡
- የቸኮሉት እነሱ ናቸው፡፡
- እንዴት?
- ፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራልንም ሆነ የክልል መንግሥታትን ሥልጣን አራዝሞ ሳለ እነሱ ግን ቸኩለው አንድ ቦታ ላይ አነጣጠሩ።
- የት ላይ?
- አራት ኪሎ ላይ፡፡
- ባይቸኩሉስ ኖሮ?
- ባይቸኩሉ ኖሮማ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ተቃውመው መንግሥት የለም ማለት ሌላውንም እንደሚመለከት ይገባቸው ነበር።
- ሌላ የሚመለከተው ማን አለ?
- ሁሉም የክልል መንግሥታት፡፡
- እንዴት?
- የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሰጠውን የሕገ መንግሥት ትርጉም ተቃውሞ ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም ማለት የክልል መንግሥታትም የሉም ማለት ነው።
- የክልል መንግሥታትን የሉም ማለት ደግሞ እነሱንም ይጨምራል?
- እነሱንም ይጨምራል ብቻ ሳይሆን ዓላማቸው አገር ማፍረስ ሆኖ ይቆጠራል፣ ይህ ደግሞ ይነጥላቸዋል።
- ከምን ይነጥላቸዋል?
- ከሕዝብ!