ከዓምናው የዓለም ሻምፒዮና የ10,000 ሜትር ሁለተኝነቷ በኋላ፣ ለተሰንበት ግደይ በ5,000 ሜትር የመም (ትራክ) ላይ ሩጫ የምንጊዜውም እጅግ ፈጣኗ ሴት ሆናለች። ኢትዮጵያዊቷ ለሰንበት፣ ረቡዕ ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገችው አስደናቂ ሩጫ ለ12 ዓመታት በጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የነበረውን በስፔን ቫሌንሽያ ከተማ፣ በ14:06.62 በመሮጥ ነው የዓለምን ክብረወሰን መስበር የቻለችው። ይህ ድንቅ ክንዋኔዋ ነው በጥሩነሽ ዲባባ በ2008 በ14:11.15 ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን ለመስበር የበቃችው።
ኦሊምፒክ ቻነልና ራነርስ ወርልድ እንደዘገቡት የመጨረሻዎቹን አምስት ዙሮች ብቻዋን የሮጠችው ለተሰንበት፣ ከውድድሩ ፍጻሜ በኋላ “ይህ የረዥም ጊዜ ሕልሜ ነው፤ በውድድሩም በጣም ተደስቻለሁ!” ብላለች። “ይህ በጣም ግሩም ነው፡፡ ከዚህ በፊት ጥሩነሽ ዲባባ ሰበረች፤ አሁን ደግሞ እኔ፡፡” ስትልም አክላለች። የ5,000 ሜትር የዓለም ክብረ ወሰንን በመስበር የኢትዮጵያውያን ሯጮች የፈጣን ሯጭነት ውርስን የ22 ዓመቷ ለተሰንበት አስቀጥላለች።
ሌላው የምሽቱ ተጨማሪ የክብረ ወሰን አስደናቂ ክስተት በቀነኒሳ በቀለ በ26:17.53 ለ15 ዓመታት ተይዞ የነበረው የ10,000 ሜትር ሪከርድን ዑጋንዳዊው ጆሹዋ ቼፕቴጊ በ26:11.02 በመፈጸም መስበሩ ነው። ባለፈው ነሐሴ በተደረገው ዳይመንድ ሊግ በ5000 ሜትርም የቀነኒሳን የዓለም ሪከርድ መስበሩም ይታወሳል፡፡