Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊነፍስ የዘራው የሐረማያ ሐይቅ

ነፍስ የዘራው የሐረማያ ሐይቅ

ቀን:

በታምራት ጌታቸው

ወዮ ሐረማያ

       ሐረማያ የአወዳይ ልምላሜ 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሐረር ፀባይ ሚስጥር፣ የፍቅር ሁሉ ፍጻሜ፡፡

ሐረማያ የወዳጅነት ልክን ማሳያ

የመስዋዕትነት ጣሪያ፡፡

እስከ መጨረሻው ጠብታ

እስከ ሕይወቱ ዕቅታ፣

      ጠብታ ወዙ ነጥፎ እስኪረታ

ዝም ነው የእሱስ ውለታ፡፡

ሐረርጌ አለቀሰ እንባው ፈሰሰ

የክፉ ቀን ጓዱን ሰርክ እያስታወሰ፡፡

ወዮ ዓለም ማያ የሐረር ሲሳይ ባህርም እንደ ሰው፣

ሞት ይሞታል ወይ፡፡

ማነው የገደለው ብዬ አልጠይቅም

በማን እጅ አለፈ ብዬ

አልልም እኔ፣

የደሙን ሀበላ በሐረርጌ ወዝ ላይ እያየሁ በዓይኔ

የየዋህነቱን የታዳጊነቱን የፍቅርነቱን ልክ መቁጠር ብታክትም፣

እርግማን ሆኖብን በሐበሻ ምድር ላይ ደግ አይበረክትም፡፡

. . . ያለው ከያኒ አበባው መላኩ የሐረማያ ሐይቅ መድረቅን ተከትሎ ነበር፡፡

ከ1990ዎቹ መጀመርያ ጀምሮ የመድረቅ ሥጋት ውስጥ የወደቀውና በመጨረሻም ደርቆ የአካባቢውን ነዋሪዎችና የወንዝና ሐይቅ ባለሙያዎችን ያነጋገረው ሐረማያ ሐይቅ ላለፉት 15 ዓመታት ውኃ ከድቶት ከርሟል፡፡ አቅርቦት እየጨመረ ከመጣው የከተማዋ ነዋሪና ፍላጎት ጋር ማመጣጠንና ተጨማሪ የውኃ ግንባታዎች ካልተከናወኑ ከአካባቢ ጥበቃ ጉድለት ለዓመታት የመከነው ሐይቅ አዲስ አበባ ይገጥማታል ተብሎ በወቅቱ ይነገር ለነበረው ሥጋትም እንደምሳሌ ይነሳ ነበር፡፡ የአዲስ አበባም ቧንቧዎች የሐረማያ ሐይቅ ዕጣ ፈንታ ይደርሳቸዋል ተብሎ በወቅቱም ይነገር ነበር፡፡

ነፍስ የዘራው የሐረማያ ሐይቅ

የሐረማያ ሐይቅ ለዓመታት ያህል ውኃ አልባ ሆኖ ከመቅረቱ አስቀድሞ የተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሐይቁ እየቀነሰ ስለመምጣቱ፣ በደለል ስለመሞላቱ፣ ዕርምጃ ካልተወሰደም እንደሚደርቅ ሥጋታቸውን አካፍለዋል፡፡ ሰሚ አላገኙም ነበርና የሐይቁ ውኃ ለእርሻና ለቤት ፍጆታ በአብዛኛው ሕዝብ በመዋሉና አካባቢው በመራቆቱ ከውኃ ነፃ ሆኖ ከርሟል፡፡

የአካባቢውን ከፍተኛ የውኃ ችግር ይቀርፍ የነበረው ሐይቅ መድረቁ ኢትዮጵያ ካሏት ሐይቆችና የሐይቁ አካላት አንዱን እንድታጣ ያደረገ ብቻ ሳይሆን፣ የአካባቢውን ነዋሪ ውኃ ያስጠማም ነበር፡፡

ቢላል ታጁ ይባላል፡፡ በሐይቁ ዙሪያ ገንደ መሰሬ በሚባለው አካባቢ ነዋሪ ነው፡፡ ውልደቱና ዕድገቱም እዚሁ ነው፡፡ የ18 ዓመት ወጣት ሲሆን ይጠጡት፣ ያርሱበትና ይዋኙበት የነበረው ሐይቁ እንዴት እንደ ዋዛ ከዓይኑ እየራቀ እንደሄደ ያስታውሳል፡፡

‹‹በልጅነቴ ቤተሰቦቼ ከሐይቁ ውኃ ሲቀዱ እኔም የአቅሜን በትንሽ ዕቃ ተሸክሜ እቀዳ ነበር፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ዋኝተን ልብሳችንን አጥበን እንመለስም ነበር፡፡ ዕድሜዬ ከፍ እያለ ሲመጣ ሐይቁም ቀስ በቀስ እየራቀን ነበር፡፡ በኋላም በሐይቁ ከመዋኘት ይልቅ በደረቀው ሥፍራ ኳስ መጫወት ጀመርን፡፡ ቤተሰቦቼ ደግሞ የደረቀውን ሥፍራ ለእርሻ መጠቀም ጀመሩ፡፡ የሽንኩርትና የበቆሎ ማሳ አድርገነው ነበር፡፡›› ቢላልን ከሁለት ሳምንት በፊት በሐረማያ ሐይቅ ተገኝተን ስናናግረው፣ ከውኃ መያዣ ፕላስቲኮች ከሠራው ጀልባ ላይ ሆኖ ነበር፡፡

ዓምና አብዝቶ በጣለው ዝናብ ምክንያት ማገገሙ የተነገረለት ሐይቅ የልጅነቱን ጊዜ እንዲያስታውስ አድርጎታል፡፡ የሐይቁን ውኃ ተሰናብተውና ትዝታውን ብቻ ይዘው በቀረው የብስ ላይ የድሮውን እያወጉ መሬቱን ለእርሻ ያዋሉ የአካባቢው ነዋሪዎችም በክስተቱ አጃይብ ብለዋል፡፡ የሐረማያ ሐይቅ ዛሬ ቀድሞ በነበረበት ቦታ ላይ ውኃ የተንጣለለበት ሲሆን፣ ከዋናው መንገድ በአንድ ገጽታው 50 ሜትር ላይ ይገኛል፡፡ ወደ ሐይቁ ሲጠጉ በአካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች በሐይቁ ዙሪያ ለመዝናናት ተሰብስበው ይታያሉ፡፡ የእጃቸው ክርን ላይ የውኃ መያዣ ፕላስቲክ በማሰር ዋና የሚለማመዱም ይታያሉ፡፡ ሕፃናት እየዘለሉ በመግባት ይቦርቃሉ፡፡ ከከተማ ወደ ሐይቁ የሚያደርሱ ባጃጆች ተሠልፈው ተሳፋሪ ይጠብቃሉ፡፡ ሐይቁ ሊመለስ አይችልም በሚል ግምት መብራት ኃይል የተከለው 4 ሺሕ ኪሎ ቮልት የሚያስተላልፍ ምሰሶም ይታያል፡፡ የአካባቢው ሰዎች እንደሚናገሩትም ከወራት በፊት ዋና ለመለማመድ የገቡ ሦስት ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

በሐይቁ መድረቅ ላይ ተደጋጋሚ ትንታኔ ሲሰጥ የከረመው የሐረማያ ዩኒቨርሲቲም ዳግም ሐይቁ እንዳይነጥፍ ከወዲሁ ሥራዎችን ጀምሯል፡፡

የሐይቁን ውልደትና ሞት በኋላም ትንሳዔ በቅርበት ሆኖ ሲከታተል የከረመው ዩኒቨርሲቲው፣ ዛሬ ላይ ያገገመው ሐይቅ መልሶ እንዳይነጥፍ የግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጁ በተፈጥሮ ሀብት አያያዝና አካባቢ ሳይንስ ክፍል በኩል እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡

‹‹እንደ አጠቃላይ አንድ ሐይቅ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ይወለዳል ያድጋል ይሞታል፡፡ ይህ የተፈጥሮ ሕግ ነው›› የሚሉት የክፍሉ ባለሙያ ክበበው ክብረት (ዶ/ር)፣ የሐረማያ ሐይቅን የሚለየው በሰው ሠራሽ ችግር ያለ ጊዜው መጥፋቱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ሐይቁ መጀመርያ ሲለካ ሰፊ ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚያካልል ጥልቀቱም አሥር ሜትር የነበረ ሲሆን፣ ሊደርቅ የቻለው ለሐረር፣ ለአወዳይ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከዚህ ውኃ በመጠቀማቸው ነበር፡፡

በአካባቢው የነበረው ደን መራቆቱ ከፍተኛ ደለል ወደ ሐይቁ እንዲገባ ማድረጉና በዙሪያው ከፍተኛ እርሻ መካሄዱ ሐይቁ ካለጊዜው እንዲደርቅ ካደረጉ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ሐይቁ ለማኅበረሰቡ ከፍተኛ አበርክቶ የመስጠቱን ያህል ዘላቂ እንዲሆን ምንም ሥራ ባለመሠራቱ ሙሉ በሙሉ በ1997 ዓ.ም. ሊደርቅ ችሏል በማለት ዶ/ር ክበበው ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በ2012 ዓ.ም. የጣለው ከባድ ዝናብ ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች ቤት ሲያፈርስ፣ እርሻ ሲያወድምና ከብት ሲወስድ የከረመ ቢሆንም ለሐረማያ ሐይቅ ትንሳዔ ሆኗል፡፡ የሐረማያ ሐይቅ ከ15 ዓመታት በፊት ወደነበረበት ይዘት መመለስ የጀመረው ዓምና ሰኔ ላይ ነው፡፡ ከባዱ ዝናብ በአካባቢውም የእርሻ መሬትን አጥለቅልቋል፡፡ ሐይቁ ወትሮ ከሚያርፍበት ቦታ በተጨማሪ 400 ሜትር አካባቢ ሰፍቷል፡፡

በሐይቁ ዳርቻ ያገኘነው ወጣት ቢላል ዛሬ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ በኮሮና ምክንያት እቤት መቀመጡ ሰልችቶት እንደነበር ገልጾ፣ ሐይቁ በደንብ ከተመለሰ ሦስት ወራት ማስቆጠሩን ነግሮናል፡፡ ምንም ጊዜ ሳያጠፋ የውኃ ፕላስቲኮችን በመሰብሰብና በማዳበሪያ በመወጠር በባህላዊ መንገድ በተሠራ የእንጨት መቅዘፊያ አንድ ሰው የምትጭን ታንኳ ሠርቷል፡፡ በሠራው ታንኳ ከሐይቁ መነሻ በግምት አሥር ሜትር በመዝለቅ ለደርሶ መልስ አሥር ብር በማስከፈል ሰዎችን ያዝናናል፡፡ ለእሱም ለቤተሰቡም የገቢ ምንጭ እንደፈጠረለት ይናገራል፡፡

በተመሳሳይ የተሠራና ዘጠኝ ሰዎችን ወደ ሐይቁ የሚመጡትን የመጫን አቅም ያለው ጀልባ በሐይቁ ላይ የሚታይ ሲሆን፣ በጀልባ ለመሳፈር የሚታየው ጉጉትና እሽቅድምድም የሐይቁ መመለስ የፈጠረውን ደስታ ያሳያል፡፡ ተንጣሎ የሚታየው ሐይቅ ላይ ዓሳ መምጣቱን የሚያሳዩ ምልክቶች ከሆኑት አንዱ እነሱን የሚመገቡ አዕዋፋትም በሐይቁ ላይ አንዣበው እያረፉ ሲነሱ መታየታቸው ነው፡፡

ሆኖም ሐይቁ ድጋሚ ሊደርቅ እንደሚችል የሚያመላክቱ ሥጋቶች ከወዲሁ ይታያሉ፡፡ ከከተማ፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች ጎርፍ ይገባል፡፡ እነሱ ይዘዋቸው የሚመጡት የውኃ ፕላስቲኮች፣ ፌስታሎችና የተለያዩ ቆሻሻዎች በሐይቁ ዳር ተንሳፈው ይታያሉ፡፡ የሐይቁ አጠቃቀም ሕግ ያልወጣለት በመሆኑ እንስሳት ይጠጡታል፣ ልብስ ይታጠብበታል፡፡ ሊዝናኑ የመጡ ሰዎችም ቆሻሻ ጥለው ይሄዳሉ፡፡ ሌላውና ትልቁ አደጋ በአካባቢው የሚጣለው በየፌስታል የተቋጠረ ቆሻሻ በሐይቁ ላይ መታየቱ ነው፡፡

የሐረማያ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢብሳ ኢብራሂም (ዶ/ር) ችግሮቹን ለመፍታትና ሐይቁን ለመታደግ አስተዳደሩ መሆኑና በቅርቡም የአጠቃቀም ሕግ እንደሚወጣለት ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ሐይቁ እንዲመለስና ተመልሶ እንዳይደርቅ ጥረት ማድረጉን የገለጹት አድማሱ ቦጋለ (ዶ/ር) በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ልማት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ለመመለሱም የአረንጓዴ አሻራ ፖሊሲ ትልቅ አስተዋጽኦ ማምጣቱን፣ እነሱም ቀደም ብለው በሐይቁ ዙሪያ የችግኝ ተከላ በማካሄዳቸው ይመለሳል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ 

ለሐይቁ መድረቅ ዋና ችግር ከሆኑት በዙሪያው የሰፈሩ ሰዎች  አንዱ ሲሆን፣ ለነዋሪዎች መፍትሔ ለማበጀት ከሐረማያ ከተማ አስተዳደር ጋር ውይይት እየተደረገ ነው፡፡ ወደ ሐይቁ የሚገባውን ቆሻሻ ለማስወገድ ሦስት የደረቅ ቆሻሻ መጣያዎች በከተማው እየተዘጋጁ ሲሆን፣ ወደ ሐይቁ የሚገባውን ደለል ለማስቆምም የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ከመንግሥት አካላት ጋር በመሆን ለመተግበር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...