ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የቆየውንና በሥራ ላይ የሚገኘውን የንግድ ሕግ የሚተካ ረቂቅ የንግድ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡ በአክሲዮን የተደራጁ የንግድ ማኅበራት የዕዳ ሰነድ መሸጥ የሚችሉበትን አሠራር የሚፈቅድና ሌሎች አዳዲስ ድንጋጌዎችን የያዘው የንግድ አዋጅ ነው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው።
ረቂቅ አዋጁ ሐሙስ መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲቀርብ፣ በምክር ቤቱ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት መስፍን ቸርነት (አምባሳደር)፣ ነባሩን የንግድ አዋጅ በአዲስ መተካት አስፈላጊ ያደረጉ ምክንያቶችን በመግለጽ የረቂቅ አዋጁን ይዘቶች አስተዋውቀዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት፣ በሥራ ላይ የሚገኘው የንግድ ሕግ በ1952 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ለረዥም ዘመናት ቢያገለግልም፣ አሁን ላይ የንግድ ሒደቱ እየዘመነ በመምጣቱና ዓለም አቀፋዊነት እንዲላበስ ማድረግ ማሻሻል እንዳስፈለገ አብራርተዋል፡፡
ረቂቅ ሕጉ በሥራ ላይ የሚገኘውን የንግድ መጽሐፍ አንድ፣ ሁለትና አምስት ብቻ የሚሽር ሲሆን፣ በሥራ ላይ ያለው የንግድ ሕግ መጽሐፍ ሦስትና አራት የፋይናንስ አገልግሎቶች መድበል (ኮድ) እስኪወጣ ድረስ ተፈጻሚ ሆነው እንደሚቀጥሉ ረቂቁ ያመለክታል።
ረቂቅ የንግድ አዋጁ ከያዛቸው አዳዲስ ድንጋጌዎች መካከልም የአክሲዮን ማኅበራት የዕዳ ሰነድ (ቦንድ) መሸጥ እንዲችሉ የሚፈቅደው ድንጋጌ ይገኝበታል። በዚህም መሠረት አክሲዮን ማኅበራት እንዲሸጡ የተፈቀደላቸው የዕዳ ሰነድን የተመለከቱ የሕግ ትርጓሜዎችንና አሠራሮችን ረቂቁ አካቶ ይዟል።
በመሆኑም የዕዳ ሰነድ ማለት በአክሲዮን ማኅበር የሚወጣ የዕዳ ዋስትና ሲሆን፣ ለዕዳ ሰነድ ያዥ የተወሰነ ወለድ በተወሰነ ጊዜ ለመክፈልና የውሉ ጊዜ ሲጠናቀቅ የተበደረውን ገንዘብ ለመመለስ ግዴታ የሚገባበትና የሚተላለፍ የዕዳ ማረጋገጫ ሰነድ ነው የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶታል።
አንድ የአክሲዮን ማኅበር የዕዳ ሰነዶችን በማውጣት መበደር የሚችለው፣ የአክሲዮን ማኅበሩ ማቋቋሚያ አክሲዮኖች ዋና ገንዘቡ በሙሉ የተከፈሉ ከሆነና አክሲዮን ማኅበሩ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ሥራ ላይ ቆይቶ፣ በማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ የፀደቀ የሒሳብ ሚዛን ካለው እንደሆነ የረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ ያመለክታል።
አንድ የአክሲዮን ኩባንያ የዕዳ ሰነዶችን በማውጣት መበደር የሚችለው የገንዘብ መጠን፣ በፀደቀው የመጨረሻ የሀብትና ዕዳ ሒሳብ መግለጫ ውስጥ ከተመለከተው የተከፈለ የማኅበሩ ዋና ገንዘብ ሊበልጥ እንደማይችል በረቂቅ አዋጁ ተመልክቷል።
አንድ የአክሲዮን ኩባንያ የሚያወጣው የዕዳ ሰነድ ለአክሲዮን ከተከፈለበት ዋጋ በላይ ከፍ አድርጎ ማውጣት የሚችል ሲሆን፣ ለአክሲዮኑ ከተከፈለው ዋጋ በታች ዋጋ የሚሰጥ የዕዳ ሰነድ ግን ማውጣት እንደማይችል በረቂቁ ተደንግጓል።
አንድ የንግድ ሠራተኛ ስለራሱም ሆነ ሦስተኛ ወገን ሆኖ እሱን የቀጠረው ነጋዴ ከሚሠራው የንግድ ሥራ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሌላ የንግድ ሥራ መሥራት እንደማይችል በረቂቁ ተደንጓል።
ረቂቅ አዋጁ ከያዛቸው ሌሎች ድንጋጌዎች መካከል ሌላው የሚጠቀሰው፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማኅበር ወይም የግል ሽርክና ማኅበር መመሥረት የሚቻል መሆኑን ያመለክታል። ረቂቅ አዋጁ በዝርዝር እንዲታይ ለንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።