በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ተጠቃሽ ከነበሩት የግል የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ የሆነው አኪር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ንብረት የነበረው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ በነበረበት የባንክ ዕዳ ምክንያት ከ203 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ዋጋ በጨረታ ተሸጠ፡፡
ምንጮች እንደገለጹት የአኪር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ንብረት የነበረው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ሊሸጥ የቻለው፣ በአኪር ስም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወጣ ብድር በወቅቱ ሊከፈል ባለመቻሉ ነው፡፡ አኪር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ከሁለት ዓመት በፊት ለሰይፉ አምባዬ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሙሉ የአኪር ሀብትና ዕዳ የተላለፈ ቢሆንም፣ አኪርን የተረከበው ኩባንያ የባንኩን ዕዳ ባለመክፈሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃውን ሸጦታል፡፡ ሰይፉ አምባዬ ኮንስትራክሽን የባንኩን ዕዳ ጨምሮ ሌሎች ግዴታዎችን ለመፈጸም ውል ገብቶ እንደነበር የሚጠቅሰው መረጃው፣ በገባው ግዴታ መሠረት ዕዳው ባለመከፈሉና ባንኩ እንዲከፍለው ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያደርግም ባለመሳካቱ በጨረታ ሊሸጠው ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት በዕዳ የተያዘው ሕንፃ በጨረታ ከ203 ሚሊዮን ብር በላይ መሸጡ ታውቋል፡፡
እንደ ምንጮች ገለጻ ባንኩ ይህንን ሕንፃ የሸጠው አኪር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ለተለያዩ የማሽነሪዎች ግዥ የተበደረውን 60 ሚሊዮን ብር በወቅቱ ባለመከፈሉ ወለዱ ዕዳውን ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡
አኪር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ለሰይፉ አምባዬ ሀብትና ዕዳው በሽያጭ እስከተላለፈበት ጊዜ ድረስ የባንኩ ብድርና ወለድ እየተከፈለ የቆየ ቢሆንም፣ ከዚያ በኋላ ክፍያው ሊፈጸም ባለመቻሉና ባንኩ በተደጋጋሚ ዕዳውን እንዲከፍለው ያቀረበውን ጥያቄ ባለመፈጸሙ የተወሰደው ዕርምጃ ስለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡
አኪር በሽያጭ ሲተላለፍ በወቅቱ ያለበትን ዕዳ ሙሉ ለሙሉ በመክፈል፣ በአኪር ኮንስትራክሽንም ሥራቸው የተጀመሩ ወደ አራት የሚሆኑ የግንባታ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለማስረከብ ጭምር ነበር፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደጠቆሙትም በአኪር ስም የነበሩ ፕሮጀክቶች የሥራ ሒደት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅ ባይቻልም፣ የሕንፃው መሸጥ በአኪር ሥር የነበሩ ከሦስት ሺሕ በላይ ሠራተኞችም ሥጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡
የተክለብርሃን አምባዬ ሥራ አስኪያጅና የሰይፉ ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ሰይፉ አምባዬ አኪር ኮንስትራክሽንን ሲረከቡ ከገቡት ግዴታ ውስጥ፣ በአኪር ስም የነበሩ ፕሮጀክቶችንና ለ30 ዓመታት የቆዩትን ሠራተኞች ይዘው እንደሚቀጥሉ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ሠራተኞችን እያሰናበቱ መሆኑም እየተገለጸ ነው፡፡
አኪር ኮንስትራክሽን ኩባንያ በሽያጭ ከመተላለፉ ቀደም ብሎ ባለፉት 30 ዓመታት በተለይ የደረጃ አንድ ኮንትራክተር ሆኖ በቆየባቸው ጊዜያት የተለያዩ ኤርፖርቶችን፣ መንገዶችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችንና የመሳሰሉ ትልልቅ ግንባታዎችን በማካሄድ ይታወቅ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ የቀድሞ ሥራውን ለማስቀጠል የሚያስችሉትን ሥራዎችን ባለማግኘቱ፣ ኩባንያውን ለሌላ ኩባንያ ለማስተላለፍ መገደዱ ይነገራል፡፡
አኪር ወደ ሰይፉ አምባዬ ኮንስትራክሽን የተላለፈውም በሽያጭ ሲሆን፣ ዋጋው ግን አልተጠቀሰም፡፡