Tuesday, February 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በሁለት ቢሊዮን ብር የብረት ፋብሪካ ገነቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአራት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የተመሠረተው ታዳሽ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በዱከም ከተማ በሁለት ቢሊዮን ብር የብረታ ብረት ፋብሪካ ገነባ፡፡

በዱከም ኢንዱስትሪ ዞን በ50,000 ካሬ ሜትር ላይ የተገነባው ግዙፍ የብረታ ብረት ፋብሪካ ቁርጥራጭ ብረቶችን (ስክራፕ) በማቅለጥ ፌሮና ስታፋ ብረት የሚያመርት ዘመናዊ ፋብሪካ እንደሆነ፣ ታዳሽ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ አስታውቋል፡፡

የኩባንያው መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ክብርይስፋ ተክሌ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ያለውን የብረት ችግር በመመልከት ከሦስት ጓደኞቻቸው ጋር ታዳሽ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪን በመመሥረት የዚህን ግዙፍና ዘመናዊ የብረት ፋብሪካ ግንባታ በጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም. ጀምረዋል፡፡ የፋብሪካው ግንባታ 98 በመቶ መጠናቀቁን፣ የተለያዩ ማሽኖችና ክሬኖች ከአውሮፓ፣ ከዱባይና ከህንድ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝተው እንደተገጠሙ ተናግረዋል፡፡ ክሬኖቹ ከኦስትሪያ፣ ስቲል ስትራክቸሩ ደግሞ ከዱባይ፣ የብረት ማቅለጫዎችና ማሽኖቹ ታዋቂ ከሆኑ የህንድ ኩባንያዎች እንደተገዙ አስታውቀዋል፡፡

የብረታ ብረት ፋብሪካው አራት ማቅለጫዎች ያሉት ሲሆን፣ የተለያየ መጠን ያላቸው ፌሮና ስታፋ ብረቶች የሚያመርቱ በርካታ ማሽኖች ተገጥመውለታል፡፡ ፋብሪካው በቀን 600 ቶን የብረታ ብረት ውጤቶች የማምረት አቅም እንዳለው የገለጹት አቶ ክብርይስፋ፣ የፋብሪካው የምርት ሒደት አካባቢ እንዳይበክል የተገጠሙለት ዘመናዊ መሣሪያዎች አማካይነት ከብክለት ነፃ እንዲሆን መደረጉን አስረድተዋል፡፡ በፋብሪካው ግንባታ ወቅት ለ400 በአብዛኛው ከአካባቢው ለተውጣጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የገለጹት አቶ ክብርይስፋ፣ ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ምርት ሲጀምር ለ800 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ተናግረዋል፡፡

የፋብሪካው ግንባታ ሥራ ከሞላ ጎደል መጠናቀቁን ጠቁመው የማሽን ተከላ ሥራ ያለቀ ቢሆንም ፋብሪካውን ሞክሮ ወደ ሥራ ለማስገባት የተዋዋለው ማሽን አምራች ኩባንያ ባለሙያዎች፣ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ከህንድ መምጣት ባለመቻላቸው ሥራው መጓተቱን ገልጸዋል፡፡

‹‹በበሽታው ምክንያት ከህንድ መግባትና መውጣት ስለማይቻል ማሽኖቹን የተከሉት ባለሙያዎች ለጊዜው ሊመጡ አልቻሉም፡፡ ሁኔታዎች ተስተካክለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ህንድ በረራ ከጀመረ ባለሙያዎቹ ወዲያውኑ መጥተው ፋብሪካውን የሙከራ ሥራ አጠናቀው ወደ ምርት ያስገቡታል፡፡ በእኛ እምነት ከእግዚአብሔር ጋር በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ማምረት እንጀምራለን፤›› ያሉት አቶ ክብርይስፋ፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ለኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክና ለዱከም ከተማ አስተዳደር ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ ለቢሮ አገልግሎትና ለሠራተኞች መመገቢያና ማረፊያ የሚያገለግል ባለሦስት ፎቅ ሕንፃ ተገንብቷል፡፡ የብረታ ብረት ፋብሪካው 20 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚፈልግ በመሆኑ ከ11 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ (Substation) ስቦ ለማምጣት የሚያስችል የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ለመዘርጋት፣ ታዳሽ ብረታ ብረት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንዳወጣ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በቁርጥራጭ ብረቶች ንግድ ሥራ ከ20 ዓመት በላይ ያሳለፉት አቶ ክብርይስፋ ወደ ብረታ ብረት ፋብሪካ ግንባታ ለመግባት የወሰኑት በአገሪቱ ኮንስትራክሽን ዘርፍ ያለውን የብረት እጥረት፣ የብረት ምርት ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን ከፍተኛ የወጭ ምንዛሪ በመመልከት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ለትርፍና ገንዘብ ለመሰብሰብ ከሆነ ብረት አስመጥቶ በመሸጥ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ማግኘት ይቻላል፡፡ እኔ በአገሬ ሠርቼ ገንዘብ ካገኘኸሁ የዘውትር ህልሜ የሆነውን የብረት ፋብሪካ ከጓደኞቼ ጋር ተባብሬ ብገነባ ለአገሬ ኢኮኖሚ ዕድገት አንድ አስተዋጽኦ እንዳደረኩ እየተሰማኝ የአዕምሮ እርካታ አገኛለሁ ብዬ ነው እንጂ፣ ይህን የሚያክል ግዙፋ ፋብሪካ ለመገንባት ብዙ እልህ አስጨራሽ ፈተና ገጥሞናል፡፡ እንዲህ ከምሰቃይ ብረት ነግጄ ባድርስ የሚያስብሉ ብዙ ችግሮች ገጥመውናል፤›› ብለዋል፡፡

ለግንባታ የሚሆን መሬት በማቅረብ የዱከም ከተማ አስተዳደር ቀና ትብብር እንዳደረገላቸው የሚናገሩት አቶ ክብርይስፋ፣ የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ አስመጪዎችን እንጂ አምራቾችን ብዙም እንደማይደግፍ ገልጸዋል፡፡

‹‹ብረት ለማምጣት አበዳሪህ ብዙ ነው፡፡ ብረት ለማምረት ፋብሪካ ልገንባ ስትል ባንኮቹ ብዙም አይሰሙህም፡፡ ምክንያቱም ባንኮቻችን ፈጣን ገንዘብ ስለሚፈልጉ ነው፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ስትሄድ በአብዛኛው ለአገሩ ራዕይ ያለው ኃላፊ አይገጥምህም፡፡ አብዛኛው ሰው የዛሬን ጥቅም ብቻ ፈላጊ ነው፡፡ ነገን አሻግረው የሚመለከቱ ጥቂት ናቸው፤›› ሲሉ ምሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡  

ለፕሮጀክቱ ብድር ያቀረበውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክንና ለውጭ መሣሪያዎች ግዥ የውጭ ምንዛሪ ለፈቀደላቸው የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ምሥጋናቸውን ያቀረቡት አቶ ክብርይስፋ፣ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚገቡ ባለሀብቶች የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ባንኮች አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

‹‹አገር የምትገነባውና የምትለወጠው በአምራቾች እንጂ በአስመጪዎች አይደለም፡፡ የአገር ኢኮኖሚ በፍጥነት እንዲያድግ ከተፈለገ ለአምራች ኢንዱስትሪው ልዩ ክትትልና ድጋፍ ሊደረግ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ታዳሽ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ በቀጣይ የሚስማርና የኦክስጅን ፋብሪካ በዱከም ለመገንባት ማቀዱን አስታውቋል፡፡

አገሪቱ በየዓመቱ ለብረት ግዥ ከፍተኛ ወጪ በውጭ ምንዛሪ የምታወጣ ሲሆን፣ በ2012 ዓ.ም. 11 ወራት 55.2 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 1.08 ሚሊዮን ቶን ቢሌትን ጨምሮ የተለያዩ የብረት ምርቶች ወደ አገር እንደገቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች