Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየወንጀል ክስ በባህላዊ ሥርዓት ውሳኔ የሚያገኝበትን አማራጭ የያዘ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ...

የወንጀል ክስ በባህላዊ ሥርዓት ውሳኔ የሚያገኝበትን አማራጭ የያዘ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ለፓርላማ ቀረበ

ቀን:

የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች አዲስ አበባ በሚገኙ የክልሉ ተቋማት ላይ የዳኝነት ሥልጣን ይሰጣቸዋል

በሁለት ዓመት ውስጥ ያልተፈጸመ የሞት ፍርድ ወደ ዕድሜ ልክ እስራት ይለወጣል

ማንኛውም በምርመራ፣ በክስ ወይም በፍርድ ሒደት ላይ የሚገኝ የወንጀል ጉዳይ በባህላዊ ሥርዓት ታይቶ ውሳኔ ወይም መፍትሔ እንዲሰጥበት የሚያስችል የፍትሕ አማራጭን የያዘ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ። 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ረቂቅ ሕጉ ለስድስት አሥርት ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ የሚተካና የማስረጃ ሕግ ሥርዓትንም እንደ አዲስ የሚያበጅ ነው።

‹‹የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ረቂቅ አዋጅ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ሐሙስ መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው።

ረቂቁ ማንኛውም የወንጀል ጉዳይ በባህላዊ ሥርዓት የሚታይበትን አማራጭ የፍትሕ ሥርዓት ቢያስቀምጥም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን፣ በሰው ልጅ ክብርና በአገር ደኅንነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ግን ባህላዊ ሥርዓት ተፈጻሚ እንደማይሆን ያመለክታል።

በባህላዊ ሥርዓት የሚታይ የወንጀል ጉዳይ በዓቃቤ ሕግ አነሳሽነት ወይም በግል ተበዳይ ወይም በባህላዊ ሥርዓት ሥልጣን ባለው ሰው፣ እንዲሁም አግባብነት ባለው የመንግሥት አካል፣ ወይም ጉዳዩን በሚያየው ፍርድ ቤት ጠያቂነት ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ ፈጸመ የተባለው የወንጀል ድርጊት በባህላዊ መንገድ እንዲታይ ሊቀርብ እንደሚችል የረቂቁ ድንጋጌ ያመለክታል።

ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሽ ፈጽሟቸዋል የተባሉ ተያያዥ ወይም ተደራራቢ ወንጀሎች ከፊሎቹ በባህላዊ መንገድ፣ ቀሪዎቹ በመደበኛው ሥርዓት ሊታዩ የሚችሉ በሚሆኑበት ጊዜ ሁሉም ወንጀሎች በመደበኛው ሥርዓት እንዲታዩ እንደሚደረግ ረቂቁ ይደነግጋል። 

በባህላዊ ሥርዓት እንዲታይ የተወሰነው ጉደይ ሳይታይ ከቀረ ወይም መፍትሔው በሙሉ ወይም በከፊል ሳይፈጸም ከቀረና ሊፈጸም የሚችልበት ሁኔታ የለም ብሎ ዓቃቤ ሕግ በበቂ ሁኔታ ካመነ፣ ጉዳዩ በመደበኛው ሥርዓት እንዲታይ ሊወሰን እንደሚችልም ያመለክታል። 

ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ከተወሰነም ፍርድ ቤት የዘጋውን መዝገብ፣ በዓቃቤ ሕግ ጠያቂነት ዳግም እንዲከፈትና መደበኛው የፍርድ ሥርዓት እንዲቀጥል እንደሚያደርግ በረቂቅ ሕጉ ድንጋጌ ተመልክቷል።

በቅድመ ሁኔታነትም ዓቃቤ ሕግ ጉዳዩ በባህላዊ ሥርዓት መፍትሔ እንዲያገኝ ሲወስን፣ የተጠርጣሪውን ወይም የተከሳሹን ፈቃደኝነትና ጥፋተኛ ለማሰኘት የሚያስችል ማስረጃ መኖሩን ማረጋገጥ እንደሚገባው፣ ዓቃቤ ሕግ ወይም ፍርድ ቤት እንደነገሩ ሁኔታ ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ ተደጋጋሚ ወንጀለኛ ሆኖ ካገኙት ጉዳዩ በባህላዊ ሥርዓት እንዳይታይ ሊወስኑ እንደሚችሉ ረቂቁ ይደነግጋል።

በባህላዊ የፍትሕ አማራጭ ሥርዓት ውስጥ ክልከላ የተጣለባቸው ተግባራትም በረቂቁ ተካተዋል።  በዚህም መሠረት ተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ በፈጸመው አንድ የወንጀል ጉዳይ ላይ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ባህላዊ ሥርዓቶችን ተፈጻሚ ማድረግ፣ ወይም ተከሳሹ ያልተቀበለውን ባህላዊ ሥርዓት ተፈጻሚ ማድረግ፣ ወይም ባህላዊ ሥርዓቱን ከሌላ መፍትሔ ጋር መቀላቀል የተከለከለ መሆኑን ረቂቁ ያመለክታል። 

ረቂቅ ሕጉ አጠቃላይ የአገሪቱን ፍርድ ቤቶች የዳኝነት የሥልጣን ወሰን፣ ከነባራዊው የፌዴራል ሥርዓት ጋር የተጣጣመ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ይዟል። 

በዚህም መሠረት የክልል ፍርድ ቤቶች የወንጀል ክስን በተመለከተ የሚኖራቸው የዳኝነነት ሥልጣን በክልል መንግሥት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ፣ የወንጀሉ አፈጻጸም ከአንድ የአስተዳደር ክልል በላይ ያልወጣ ወይም ያልተፈጸመ ከሆነእንዲሁም አንድ ክልል ከሚያስተዳድረው የአስተዳደር ክልል በላይ በሆኑ ቀላል የወንጀል ጉዳይ ላይና ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ባልተሰጡ ጉዳዮች ላይ የመዳኘት ሥልጣን እንደሚኖራቸው የረቂቁ ድንጋጌዎች ያለመለክታሉ።

ከላይ የተቀመጡት እንዳሉ ሆነውየኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች በተለየ ሁኔታ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ተቋማት ውስጥ በተቋማት፣ንብረቶች፣ በገንዘብናሰነዶች ላይ በሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ላይ የመዳኘት ሥልጣን እንደሚኖራቸው ይደነግጋል። 

በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ ፍርድ ቤቶች በወንጀል ጉዳይ ላይ የሚሰጡት የቅጣት ውሳኔን አፈጻጸምን የተመለከቱ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ድንጋጌዎችን አካቷል። ከእነዚህም መካከል አንዱ ፍርድ ቤቶች የሚወስኑት የሞት ቅጣት በቀጥታ ሊፈጸም እንደማይችል የረቂቁ ድንጋጌዎች ይመለክታሉ። 

በዚህም መሠረት ማንኛውም የሞት ቅጣት ውሳኔ ይግባኝ ቢቀርብበትም ባይቀርብበትም፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚሰየሙ አምስት ዳኞች የቅጣት ውሳኔው ዳግም እንደሚታይ ተደንግጓል።

ለዚህም ሲባል ማንኛውም ፍርድ ቤት የሞት ቅጣት ሲወስን ውሳኔውንና የመዝገቡን ግልባጭ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የማስተላለፍ ግዴታ የተጣለበት ሲሆንጠቅላይ ፍርድ ቤቱም አምስት ዳኞች በመሰየም የቀረበለትን የሞት ቅጣት ውሳኔ በመመርመር ተገቢነቱን አረጋግጦ ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን ረቂቁ ያመለክታል።

ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሚያሳውቅ እንደሚሆን፣ የሞት ቅጣቱን ተፈጻሚ ለማድረግም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሞት ቅጣቱ ላይ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑን፣ በይቅርታ ወይምምሕረት ያልተሻረ ወይም ያልተለወጠ መሆኑን አረጋገጦ ለአገሪቱ ርዕሰ ብሔር በማቅረብ ሲያፀድቅ እንደሚሆን ረቂቁ ይደነግጋል። 

በተጨማሪም የሞት ፍርድ በማንኛውም ምክንያት ሳይፈጸም ከሁለት ዓመት በላይ የቆየ እንደሆነ፣ ወደ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንደሚቀየር ረቂቁ ይደነግጋል።

ከላይ በተቀመጡት ድንጋጌዎች ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች፣ መንግሥት የሞት ቅጣትን በሕግ ለማስቀረት ባይፈልግም የተቀመጡት ድንጋጌዎች በአመዛኙ የሞት ቅጣት ተፈጻሚነትን ሊያስቀሩ እንደሚችሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

በማከልም የሞት ቅጣት ተፈርዶባቸው ቅጣቱ ያልተፈጸመባቸው ከአገር ውጭ የሚገኙ ፍርደኞች ወደ አገር ተመልሰው የእስር ቅጣት እንዲፈጸምባቸው ፈቃደኛ ከሆኑ ድንጋጌው የሞት ቅጣቱን ተፈጻሚነት ሊያስቀርላቸው እንደሚችል ገልጸዋል። 

የእስራት ቅጣቱን መቀበል ከጀመሩ በኋላ ደግሞ በምሕረት ወይም በይቅርታ አማራጮች ቅጣቱ ቀሪ ሊሆንላቸው እንደሚችል አስረድተዋል።  የሞት ቅጣት ተፈርዶባቸው በእስር ላይ ወይም በአገር ውስጥ የማይገኙ የደርግ ባለሥልጣናት ይህ ረቂቅ አዋጅ ከፀደቀ በኋላ ተጠቃሚ ለመሆን የሚችሉት፣ እጃቸውን ሰጥተው የዕድሜ ልክ የእስራት ቅጣት አፈጻጸም ከተጀመረ በኋላ ሊሆን እንደሚችል አክለዋል። 

በረቂቅ ሕጉ ከተካተቱ ቅጣትን የተመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች መካከልበፍርድ ቤት የእስር ቅጣት የተወሰነበት ጥፋተኛ የቅጣቱ ተፈጻሚነት ለተወሰነ ጊዜ እንዲራዘምለት ለማድረግ የሚችልባቸው ሥነ ሥርዓቶች ተጠቃሽ ናቸው።

በዚህም መሠረት በፍርድ ቤት የእስራት ቅጣት የተወሰነበት ፍርደኛ በጠና በመታመሙ የተነሳ በማረሚያ ቤት ቅጣቱን ለመፈጸም የማይችል መሆኑ በሐኪም ሲረጋገጥ፣ ፍርድ ቤቱ ከሕመሙ እስኪድን አስፈላጊ ነው ብሎ ሲወስን ለተወሰነው ጊዜ ያህል ቅጣቱ ሊተላለፍለት ይችላል። 

አሥራ ስምንት ወር ያልሞላው ሕፃን ያላት እናት ስትሆን ሕፃኑ ሰላሳ ወር እስኪሞላው ድረስ፣ ነፍሰ ጡር ከሆነች የእርግዝና ጊዜው እስከሚያበቃና ከወለደች በኋላ ሰላሳ ወር እስኪሆነው፣ ፍርዱ ከተሰጠበት ቀን በፊት ባሉ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ወላጁ፣ ልጁ ወይም የትዳር ጓደኛው የሞተ ወይም በጠና የታመመ እንደሆነ ከአሥራ አምስት ቀናት ላልበለጠ ጊዜ ሊተላለፍ ይችላል። 

ፍርዱ ከተሰጠበት ቀን ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ የትዳር ጓደኛው የወለደች፣ ወይም ፍርድ ከተሰጠ በሚቀጥለው አንድ ወር ውስጥ የምትወልድ እንደሆነና ከተፈረደበት ሰው ሌላ ረዳት የሌላት እንደሆነ ከአንድ ወር ላልበለጠ ጊዜ፣ ቤተሰቡን የሚንከባከብ ሌላ ሰው ከሌለና ባልና ሚስት በተመሳሳይ ጊዜ የተፈረደባቸው እንደሆነ፣ ሚስት ወይም ከሁለቱ አንዱ ቀደም ብሎ የታሰረ እንደሆነ የተፈረደበት ሰው ለሦስት ወር ላልበለጠ ጊዜ፣ የቅጣቱ አፈጻጸም እንዲተላለፍለት የተጠየቀለት ምክንያት አጣዳፊ ወይም ወቅታዊ ለሆነ የግብርና ሥራ ወይም ባልታሰበ ምክንያት የተፈጠረ በአስቸኳይ ሊከናወን የሚገባው ሥራ እንደሆነ፣ ከሦስት ወራት ላልበለጠ ጊዜ ሊተላለፍ እንደሚችል ረቂቁ ይደነግጋል። 

አንድ የምክር ቤቱ አባል ረቂቅ አዋጁ አጠቃላይ ማኅበረሰቡን የሚነካ በመሆኑ፣ እንዲሁም ለረዥም ዓመታት ማገልገል እንዲችል ሰፊ ሕዝባዊ ምክክር ሊደረግ ይገባል ሲሉ በወቅቱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ረቂቅ አዋጁ በጥልቀት እንዲመረመርም ምክር ቤቱ ለሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...