Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ሁለት መርከቦች ሊያስገነባ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ ሁለት ግዙፍ የብትን ጭነት መርከቦች  ለማስገንባት በዝግጅት ላይ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አዲስ የሚገነቡት ሁለት መርከቦች እያንዳንዳቸው እስከ 60,000 ቶን ጭነት የመጫን አቅም ይኖራቸዋል፡፡ ድርጅቱ በቅርቡ መርከቦቹን የሚገነባ ኩባንያ ለመምረጥ ዓለም አቀፍ ጨረታ እንደሚያወጣ የገለጹት አቶ ሮባ፣ መርከቦቹ በመርከብ ግንባታ ከሚታወቁት ከቻይና፣ ከኮሪያ ወይም ከኢንዶኔዥያ ሊገዙ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ለመርከቦቹ ግዥ በጀት መያዙን የገለጹት አቶ ሮባ፣ በአነስተኛ መጠን ወለድ የሚከፈልበት ብድር ከተገኘ ሊወሰድ እንደሚችል አክለዋል፡፡

ለመርከቦቹ ግዥ የተያዘውን በጀት መጠን የጨረታ ሒደቱን ይጎዳል በማለት ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡ የመርከቦቹን ግንባታ ሒደት ለመምራት ስድስት አባላት ያሉት የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢና የማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራና ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሮባ መገርሳ፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱን ሥራ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. አስጀምረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ጽሕፈት ቤት አባላት በመርከብ ማኔጅመንት የካባተ ልምድ ያላቸው፣ ከዚህ ቀደም በተካሄደ የመርከቦች ግንባታ ላይ ልምድና ዕውቀት ያላቸው፣ አንጋፋና ወጣት ባለሙያዎች ያካተተ እንደሆነ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ 

ጽሕፈት ቤቱ ከመርከቦቹ ግንባታ በፊትና በግንባታው ሒደት የሚያስፈልጉ የቴክኒክ ቅድመ ዝግጅቶች የሚያከናውን ሲሆን፣ በዋናነት የመርከቦችን ዲዛይን፣ የግንባታ ቦታዎችን መረጣ፣ መርከቦቹ ላይ ስለሚገጠሙ ማሽነሪዎች ጉዳዮች እንደሚከታተል ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት 11 መርከቦች ያሉት ሲሆን፣ በአጠቃላይ 400,000 ቶን ጭነት የማንሳት አቅም አላቸው፡፡ ድርጅቱ በ2012 በጀት ዓመት 11 ሚሊዮን ቶን ካርጎ ሲያጓጉዝ፣ 25.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱ ታውቋል፡፡ ከታክስ በፊት 2.5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን፣ የኩባንያው ካፒታል 20 ቢሊዮን ብር መድረሱንና ወደ 80 ሚሊዮን ብር  እንደሚያድግ አቶ ሮባ ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በባህር ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ያሳደረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ተቋቁሞ አመርቂ ውጤት እንዳስመዘገበ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች