Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢዜማ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውይይት እንዳላደርግ አደናቀፈኝ አለ

ኢዜማ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውይይት እንዳላደርግ አደናቀፈኝ አለ

ቀን:

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) በጥናት አስደግፎ ባዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ ከመሬት ወረራና ኢፍትሐዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ ጋር በተያያዘ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደጋጋሚ ሊያደርጋቸው ያቀዳቸው ውይይቶች እንዳይከናወኑ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮና በከተማ አስተዳደሩ እንቅፋት እየተፈጠረበት እንደሆነ አስታወቀ፡፡

በኢዜማ ጽሕፈት ቤት የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ፣ የፓርቲው የዓለም አቀፍ አባላት ተጠሪ አቶ ኢዮብ መሳፍንት፣ እንዲሁም የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ዓርብ መስከረም 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ወረራና ኢፍትሐዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ ጋር በተያያዘ፣ መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ለማድረግ ዕቅድ ይዞ እንደነበር በማስታወስ፣ በውይይቱ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመሬት ወረራው ተጎጂ ሆነናል የሚሉ አካላትን፣ የከተማውን ፖሊስና የደኅንነት አካላት፣ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ያለበቂ ካሳ ተነስተን በስማችን ለሌሎች አካላት ቤቶች ተሰጥተዋል የሚሉ አርሶ አደሮች ነበሩ ብሏል።

‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ከመስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ከነበሩ ተደራራቢ በዓላት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሥራ ጫና ውስጥ እንደሚገኝ ባደረሰን ጥቆማ መሠረት፣ ተነጋግረን ውይይቱን ለመስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም. አስተላልፈናል፡፡ የውይይት ቀን መቀየራችንን ለፀጥታ አካላት፣ ለከተማ አስተዳደሩና ለሌሎች የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች ደብዳቤ አሳውቀናል፤›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ይሁን እንጂ በታቀደው ቀንና ሰዓት ውይይቱን እንደምናደርግ መረጃው የነበረው የከተማው አስተዳደር ‹የማጥራት ሥራውን አስተዳደሩ ባላጠናቀቀበት ወቅት ውይይት መጥራት ሌላ አተካራና ምናልባትም ወደ ግጭት የሚወስድ በመሆኑ፣ የጠራችሁት ውይይት እንዲሰረዝ እንድታደርጉ እናሳስባለን፤››› እንዳላቸው ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው በከንቲባ ጽሕፈት ቤት በኩል ተላከልን ባለው ደብዳቤ፣ ‹‹መስከረም 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡30 ሰዓት ከመድረሱ በፊት አስቀድመው የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊዎች ውይይቱን እንድንሰርዝ በስልክ ጥሪና በአጭር መልዕክት የተለያየ ሙከራ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፣ ደብዳቤው ሲደርሰን ግን ደብዳቤው ቀድሞ የተጻፈ ለማስመሰል የደብዳቤው ቀን መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በሚል ነበር፤›› ሲልም ወቅሷል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ድርጊት ዓይን ያወጣ ሕገወጥነት ነው ያለው ኢዜማ፣ ‹‹ውይይቱን የማድረግ ሙሉ መብት እንዳለን ብናምንም አላስፈላጊ ፍጥጫ ውስጥ ከመግባትና በዚህም አገራችን አሁን ካለችበት ውጥረት ላይ ሌላ ውጥረት ከመጨመር ይልቅ፣ ያሉትን ሕጋዊ አማራጮች በመጠቀም መብታችንን ማስከበር እንዳለብን፣ የሕግ ተቋማትም ያላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እንዲችሉ ዕድል መስጠት አለብን ብለን በማመን ውይይቱን እንደገና ለማራዘም ወስነናል፤›› ሲል አስታውቋል፡፡

ኢዜማ ነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ባደረገው ጥናት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አምስት ክፍላተ ከተሞች ውስጥ ከ200 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ መሬት በሕገወጥ መንገድ መወረሩን ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁንና ይኼ የጥናት ግኝት መግለጫ ለራሱ ነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ እንዲሁም ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ጠዋት በራስ ሆቴል በጉዳዩ ላይ ሊሰጥ የነበረ ቢሆንም በፖሊስ መከልከሉ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ ኢዜማ አገኘሁት ባለው የጥናት ግኝት፣ ‹‹ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቢሮዎች ሳር ቤት አካባቢ ከሚገኘው ጽሕፈት ቤት ሁሉም የተመዘገቡ ሠራተኞች በሰኔ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. 20,000 ቤቶች የድልደላ ዕጣ የወጣላቸው ሲሆን፣ የድልድል ዕጣ ለደረሳቸው ሰዎች ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ድልድል ተደርጎላቸዋል፡፡ በዚሁ ቀን ሁሉም ሠራተኞች የኮንዶሚኒየም ብሎክ ቁጥርና የቤቱን ቁጥር በስማቸው ተረጋግጦ የተሰጣቸው ሲሆን፣ በተሰጣቸው የቤት ቁጥር የነዋሪነት መታወቂያ የተዘጋጀላቸው መሆኑን ለማወቅ ችለናል፤›› ብሎ ነበር፡፡ የመሬት ወረራ ተፈጸመባቸው የተባሉት አምስት ክፍላተ ከተሞች ደግሞ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ የካ፣ ቦሌ፣ አቃቂ ቃሊቲና ኮልፌ ቀራንዮ እንደሆኑ በወቅቱ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...