የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት በማሰብና የግል ተበዳይ የሆኑትን ኮስሞ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ሥራ አስኪያጅ የገንዘብ ችግር መሠረት በማድረግ፣ አራጣ በማበደር፣ ከባድ እምነት በማጉደል፣ የባንክ ሥራ በመሥራት፣ በሕገወጥ የተገኘን ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብና የፍትሕ ሥራን በማሳሳት ወንጀሎች የተጠረጠሩ ሰባት ግለሰቦችና ሦስት ድርጅቶች ላይ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ መሠረተ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ወ/ሮ ሐረገወይን ተድላ (በሌሉበት)፣ ወ/ሮ አዜብ ምኅረተአብ (በሌሉበት) እና አቶ ኤፍሬም ሙላቱ (በሌሉበት) የተባሉት ተከሳሾች ኮስሞ ትሬዲንግና ሥራ አስኪያጁ አቶ ኃይለየሱስ ኃይሌ ያለባቸውን የገንዘብ ችግር መሠረት በማድረግ 50 ሚሊዮን ብር በየወሩ ዘጠኝ በመቶ ወለድ ታሳቢ እየተደረገበት በስድስት ወራት ውስጥ የሚከፈል ብድር እንዳበደሯቸው ክሱ ያስረዳል፡፡
ለብድሩ ማካካሻ ወይም መያዣ በኮስሞ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም የተመዘገበና በወቅቱ ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሆቴል አገልግሎት ሕንፃ ማስያዛቸውንና ባዘጋጁት ውል ላይ እንዲፈርሙ ማስደረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡ ውሉ ሙሉ የብድር ገንዘቡን እንደተቀበሉ ተደርጎ ቢፈረምም፣ በወቅቱ በአቶ ኃይለየሱስ የባንክ አካውንት ገቢ የተደረገው ገንዘብ ግን 3,200,000 ብር ብቻ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ ተከሳሾቹ ቀሪውን ብር ለተጎጂው ሳይሰጡ በየወሩ ዘጠኝ በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ ሲጠይቋቸው አቶ ኃይለየሱስ ባለመስማማታቸው፣ ክስ መሥርተውባቸው የ50 ሚሊዮን ብር የፍርድ ባለዕዳ በማድረግ ያስያዙትን ሕንፃ ስመ ሀብት ወደ ግላቸው ማዞራቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡ ብድሩ አራጣ መሆኑ እንዳይታወቅ ለብድሩ ተመጣጣኝ ያልሆነ ማስያዣ፣ ጄጄ ፕሮፐርቲ ማኔጅመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚል ድርጅት በመፍጠር (ድርጅቱ በሕግ ያልተቋቋመ ነው) ለ50 ሚሊዮን ብር ብድር ያስያዙትን ሕንፃ በ60 ሚሊዮን ብር እንደገዙት በማስመሰል፣ የረቂቅ ሽያጭ ውል በማዘጋጀትና ወ/ሮ አዜብ የተባሉት ተከሳሽ የተበዳይ ወኪል መስለው በመፈረም፣ ለተበዳይ 19,800,000 ብር እንደሰጡ በማስመሰል ተበዳይን መክሰሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡
ተከሳሹ አቶ ኃይለየሱስ ኃይሌ ከታሰሩ በኋላ ያልተገባ ጫና ውስጥ በመክተት ወደ ድርድር ስምምነት በማስገባትና በማስገደድ፣ የኮስሞ ትሬዲንግ ባለአክሲዮኖችን ድርሻ ሙሉ በሙሉ እንዲተላለፍ በማስፈረም፣ ሰባት ወለል ሕንፃ፣ የድርጅቱን አንድ አስካቫተር፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪና ሦስት ተሽከርካሪዎችን እንዲያስረክቡ ቃል በማስገባታቸው በፈጸሙት አራጣ ማበደር ወንጀል እንደከሰሳቸው በማብራራት ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት የክስ መዝገብ ከፍቷል፡፡
ሌሎቹም ተከሳሾች ወ/ሮ አዜብና አቶ ተመስገን የተባሉት ተከሳሾች ደግሞ ኮስሞ ትሬዲንግን እንዲያስተዳድሩ የተሾሙ በማስመሰል ከኅብረት ባንክ 40 ሚሊዮን ብር በኮስሞ ትሬዲንግ ስም በመበደርና ሁለቱ ተከሳሾች በጋራ በሚያስተዳድሩት ጄጄ ፕሮፐርቲ ማኔጅመንት አካውንት 32,500,000 ብር ማስተላለፋቸውን ዓቃቤ ሕግ ጠቁሟል፡፡ ወ/ሮ አዜብ በሚያስተዳድሩትና ከተበዳይ ጋር ምንም ግንኙነት ለሌለው ቦስተን ሪል ስቴት ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበር 7,000,000 ብር ማስተላለፉን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡ ተከሳሾቹ በተበዳይ ድርጅት ስም ከኅብረት ባንክ የተበደሩትን ገንዘብ ለአቶ አደፍርስ ሀብቴ ለተባሉት ተከሳሽ በተለያየ ጊዜያት የተለያ መጠን ያለው ገንዘብ በግል አካውንታቸው ገቢ ማድረጋቸውን፣ እንዲሁም አቶ ተመስገን በግል ባቋቋሙትና ሥራ አስኪያጅ በሆኑበት ቲቲኤች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ለተበደሩት ብድር ክፍያ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ፣ በተለያየ ጊዜያት በማስተላለፍ ከባድ የእምነት ማጉደል ወንጀል መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡
ወ/ሮ አዜብ፣ አቶ ተመስገንና ቦስተን ሪል ስቴት የተባሉት ተከሳሾችም፣ ምንም ዓይነት የገንዘብ አስተላላፊነት ሥራ ፈቃድ ሳይኖራቸው፣ የባንክን ሥራ ለመሥራት በማሰብ፣ በተለይ ወ/ሮ አዜብ በትውልድ ኢትዮጵያዊ፣ በዜግነት አሜሪካዊ ሆነው ሳለ፣ በኢትዮጵያ ባንኮች መላክ የነበረባቸውን የውጭ ምንዛሪ በግል በመሰብሰብና ወደ ኢትየጵያ ገንዘብ መንዝረው ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ግለሰቦች በማስተላለፍ ሥራ ላይ ተሰማርተው እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ይህንን የወንጀል ድርጊት ለመሥራት እንዲያመቻቸው ወ/ሮ አዜብ ቦስተን ሪል ስቴት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚል ድርጅት ማቋቋማቸውንና ከኅብረት ባንክ በኮስሞ ትሬዲንግ ስም የተበደሩትን 40 ሚሊዮን ብር፣ በቦስተን ሪል ስቴት አካውንት በማስገባትና አቶ ተመስገንና አቶ አደፍርስ የተባሉት ተከሳሾች በኢትዮጵያ ብር ምንዛሪ መክፈላቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡ በአጠቃላይ 383,484 የአሜሪካ ዶላር ለግል ጥቅማቸው በማዋልና የባንክ ሥራን ተክተው በመሥራት ወንጀል እንደከሰሳቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ሌሎቹንም ተከሳሾችም ላይ በተያያዥ ወንጀሎች ስምንት ክሶችን የመሠረተ ሲሆን፣ ወ/ሮ አዜብ የተባሉት ተከሳሽ የኮስሞ ትሬዲንግ ሥራ አስኪያጅ 1,800,000 ብር ተቀብለው እንዳልተቀበሉ በማስመሰል ለፖሊስ በሐሰት በማመልከትና ምርመራ እንዲደረግባቸው በማድረግ በፈጸሙት የፍትሕ ሥራ በማሳሳት ወንጀል እንደከሰሳቸው ክሱ ያብራራል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ክሱ እውነት መሆኑን ያስረዱልኛ ያላቸውን 35 የሰው፣ 62 የሰነድ ማስረጃዎችንም አያይዞ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡