Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትተምዘግዛጊዋ ኮከብ ለተሰንበት ግደይ

ተምዘግዛጊዋ ኮከብ ለተሰንበት ግደይ

ቀን:

“አትሌት የሆነችው በአጋጣሚ ነው፣ ተማሪ እያለች ስፖርት የሚባለውን ክፍለ ጊዜ አትወደውም፣ በተለይ ሩጫ ሲባል ያስጠላታል፡፡ የስፖርት መምህሯ በእልህ ብዙ እንድትሮጥ ያደርጓታል፣ ግን ደግሞ መሸነፍን ስለማትወድ የስፖርት መምህሯን፣ የክፍል ጓደኞቿን አሸንፋ አሳየቻቸው፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሩጫ እንጀራዋ ሆነ፤” የሚለው የተምዘግዛጊዋ ኮከብ ለተሰንበት ግደይ የግል አሠልጣኝ ኃይሌ ኢያሱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ለተሰንበት ግደይና ሩጫ እንዴት እንደተዋወቁ ያስረዳል፡፡

ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከትግራይ የፈለቀችው የ22 ዓመቷ ለተሰንበት ግደይ፣ ረቡዕ መስከረም 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በስፔን ቫሌንሺያ በተደረገው 5,000 ሜትር የሩጫ ውድድር ላይ ተሳትፋ ርቀቱን 14፡06. 65 በመግባት ከ12 ዓመት በፊት በጥሩነሽ ዲባባ በ2008 ኦስሎ ላይ ተመዝግቦና ተይዞ የቆየው 14፡11.05 የርቀቱን ክብረ ወሰን ከአራት ደቂቃ በላይ በማሻሻል አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግባለች፡፡

ዓምና በኳታር ዶሃ በተካሄደው 10,000 ሜትር የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ሁለተኛ የወጣችው ለተሰንበት፣ ቫሌንሺያ ያስመዘገበችው ውጤት በርቀቱ የመም (ትራክ) ላይ ሩጫ የምንጊዜውም ፈጣኗ እንስት አድርጓታል፡፡

ሌላው በወንዶች በተካሄደው 10,000 ሜትር ውድድር ቀነኒሳ በቀለ በ2005 ቤልጂየም ብራስልስ ላይ 26፡17.53 ያስመዘገበው ክብረ ወሰን ዑጋንዳዊ ጆሹዋ ችፕቴጌ 26፡11.02 በመግባት አሻሽሎታል፡፡ ጆሹዋ ባለፈው ነሐሴ በሞናኮ በተደረገው የ5,000 ሜትር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይም በቀነኒሳ በቀለ ተይዞ የቆየውን የርቀቱን ክብረ ወሰን ማሻሻሉ አይዘነጋም፡፡

በሌላ በኩል ለተሰንበት ግደይና የግል አሠልጣኟ ኃይሌ ኢያሱ ለቫሌንሺያው ውድድር መስከረም 24 ቀን ወደ ስፔን ለማምራት በቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ በቦርዲንግ ፓስፖርት ሴክሬታሪት አስተዳደር ከጉዞ ጋር በተገናኘ ችግር ገጥሟቸው የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ክስተቱ እንዴትና ለምን እንደተፈጠረ ብዙዎችን ማነጋገሩ አልቀረም፡፡

ሁኔታውን አስመልክቶ አሠልጣኟ ኃይሌ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው ከሆነ፣ “ለተሰንበት ግደይ ከነ አሠልጣኟ ወደ ስፔን ቫሌንሺያ በምንሄድበት ጊዜ ሁሉም ማስረጃ (ዶክሜንት) ተሟልቶ በነበረበት ሁኔታ (በስም የተጠቀሱ ኃላፊ) የቦርዲንግ ፓስፖርት ሴክሬታሪያት አስተዳደር የሚከለክል ምንም ነገር ሳይኖር እንዳንሄድ ከልክለውን ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ ወደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሪፖርት አድርገን፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ደራርቱ ቱሉ ከምሽት አምስት ሰዓት ላይ ቦታው መጥተው ተነጋግረው እንድንሄድ ሆነ፤” በማለት ሁኔታውን ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ደራርቱ ቱሉ ስለጉዳዩ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ባይሳካም፣ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ፣ ለተሰንበትና አሠልጣኟ ችግሩ እንደተፈጠረ በሞባይል ስልካቸው እንዳናገሯቸው፣ በዛኑ ሰዓት ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ወደ ቦሌ ኤርፖርት ደርሰው ለጉዞ የሚያስፈልጉ ማስረጃዎችን (ዶክመንቶችን) በመያዝ ጉዳዩ ከሚመለከተው ሰው ጋር ተነጋግረው ሊጓዙ መቻላቸውን እንዲሁም ለተሰንበት ግደይ ባስመዘገበችው ውጤት መደሰታቸውን ጭምር ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሕዝብ ግንኙነትና ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሔኖክ ሲራክ በበኩላቸው፣ “ለአትሌት ለተሰንበትና አሠልጣኟ የቀረበላቸው ጥያቄ ከሜዲካል ጋር የተያያዘ ማስረጃ አሳዩ የሚል ነው፣” በማለት ሪፖርተር በእጅ ስልካቸው ላቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል፡፡

በተጨማሪም በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ፣ አንድ አየር መንገድ አንድን መንገደኛ ተገቢውን የጉዞ ሰነድ ሳያሟላ ቢያጓጉዝ የመንገደኛው መዳረሻ የሆነው አገር አየር መንገዱ ላይ ከባድ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጥልበት የመስኩ ባለሙያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...