Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየዘንድሮው የመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ

የዘንድሮው የመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የያዝነው የ2013 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን መጀመርያ፣ ማለትም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 58(9) የደነገገው የመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ የኋሊት መቆጠር የጀመረው፣ ገና የምርጫው መራዘም ውሳኔ ሳይሰጥ በፊት አንስቶ ነው፡፡ ከአምስት ወር በላይም የሆነው ይመስለኛል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንግሥትም የመንግሥት የሥልጣን አካላትም፣ ገዥው ፓርቲም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ በኋላ ሥልጣን የላቸውም፣ በፓርቲዎች መሪዎች መካከል ልዩነት የለም፣ ሁሉም ‹‹በሕግ ፊት እኩል ነው››፣ የገዥው ፓርቲ መሪም እንደሌላው ፓርቲ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አይደለም ተባለ፡፡

የተባለው ቀን እየደረሰ፣ የኋሊት እየተቆጠረና እያለቀ ሲመጣ እየተጨማመረ በሄደ ‹‹ማብራሪያ›› እንደሰማነው ከሆነ ደግሞ ሁልሽም በምርጫ 2007 የሕዝብ ሥልጣን የተሰጠሽ ተወካዮች ምክር ቤት ነሽ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሆንሽ ጠቅላይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሁላ የውክልና ዘመናችሁ ያበቃል፣ ሕዝብ የተነፈሰባችሁ ነፍስ ከሥጋው ይላቀቃል፣ ሥጋና አጥንታችሁ ውስጥ ያለው ደምና መቅኒ ከሥሩና ከምንጩ ይቋረጣል፣ ይደርቃል ተባለ፡፡ በዕለተ ቀኑ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን የጋራ ስብሰባ በንግግር ሲከፍቱ፣ ለእኔም ለራሴ ትዝ ያሉኝ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንትን ከመስከረም 25 በኋላ ዕጣ ፈንታ ግን ሰዎቹ ሲናገሩ አልሰማሁም፡፡ ለስድስት ዓመት የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡትና እንደገና ከተመረጡም በኋላ የስድስት ዓመት የሥራ ዘመን የሚቀራቸው (በሚገርምና በማይገባ ሎጂክ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 70(4) የተደነገገው የሁለት የሥራ ዘመን ገደብ ያለባቸው) ፕሬዚዳንት ያው ነፍስና ሥጋው ከተለየው መንግሥት፣ የሕዝብ ውክልናው ድንገት ከሸሸው ምክር ቤት ጋር አብሮ ያበቃል? ወይስ መንግሥት የሌለው አገር ምልክት ሆኖ ይኖራል? የዚህ ‹‹ሴራ›› ደራሲዎች የዚህ መከራከሪያ ባለቤቶች በየጊዜው እንደታያቸውና እንደሚመልሱት ዓይነት ነው፡፡

ቀደም ብዬ እንደ ጠቀስኩት መስከረም 25 የኋሊት በመቆጠር ላይ እያለ እኔ እንደ አጋጣሚ መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ያየሁት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተዘጋጀ መጠይቅ 24 ጥያቄዎችን ይዞ ሙላኝ ብሎ በተለመደው የመጠይቆች ዘዴና መላ፣ ባሳየሁት አድራሻ የኦንላይን በሬን አንኳኳ፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተዘጋጀው መጠይቅ አሁን ከምንነጋገርበት ጉዳይ ጋር በጭራሽ የተያያዘ አይደለም፡፡ ‹‹የውክልና ሥራን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግና ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ የተዘጋጀ›› ነው፡፡ ከጥያቄዎች መካከል ትኩረቴን የማረከውና እዚህ ድረስ ዘልቆ መሄድና ሐሳቤን መርታት የቻለ አጀንዳ አዕምሮዬ ውስጥ የወበራው አካባቢህን ማን እንደሚወክል ታውቃለህ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ የቀረበልኝ በሁለት ጥያቄዎች አማካይነት ነው፡፡ አንደኛው እርስዎ የሚኖሩበትን አካባቢ በክልል (ወይም በከተማ) ምክር ቤት ማን እንደሚወክለው ያውቃሉ? ይላል፡፡ ሁለተኛው በተመሳሳይ ቋንቋ አካባቢዬን በተወካዮች ምክር ቤት ማን እንደሚወክለው አውቅ እንደሆነ ይጠይቃል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በአዎንታ ከመለስኩ ከዚህ ምላሽ ተፈልቅቆ የሚወጡ ሌሎች ጥያቄዎች አሉ፡፡ እንደራሴዎችን አውቃቸው ከሆነ ስም ዝርዝራቸውን እንድጽፍ፣ የአካባቢዬ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካይ በምን ያህል ጊዜ የሥራ ጉብኝነትና ከሕዝብ ጋር ውይይት እንደሚያካሂዱ እንድገልጽ፣ እኚህን ሰው/ሰዎች ለማግኘት ፍላጎት አድሮብኝ ያውቅ እንደሆነ እንድገልጽ ይጠይቃል፡፡

የገረመኝ ‹‹የውክልና ሥራን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ›› ተፈልጎ የቀረበውን መጠይቅ ለግብር ይውጣ ያህል እንኳን ለመወጣት ገና የመጀመርያው ጥያቄ (ጥያቄ ቁጥር 9) የት ታውቂና!›› ብሎ ከለከለኝ፡፡ የምኖርበትን አካባቢ በክልሌ (በአዲስ አበባ) እና በክፍለ ከተማዬ ማን እንደሆነ አላውቅም፡፡ እንኳንስ አዲስ አበባ ምክር ቤት፣ በክፍለ ከተማዬና ከዚያ በታች ባለ ደረጃ የሚወክለኝን ሰው እያገኘሁ የቀበሌዬ/የወረዳዬ ወይም የክፍለ ከተማዬ ወይም የከተማዬ እንደራሴ (ውጭ ያሉ ሰዎቻችን “My Congress man, my alderman” እያሉ እንደሚዘንጡብን) ማነጋገር፣ ችግሬን ማወያየት ይቅርና እነ ማን እንደሆኑ ማወቅ ይቅርና አዲስ አበባ ላይ ራሱ መቼ ምርጫ እንደተደረገ ጠፋብኝ፡፡ ረሳሁት፡፡ እውነት መቼ ነው አዲስ አበባ የመጨረሻውን ምርጫ ያደረገችው ብዬ ብችል እመራመራለሁ፣ አለዚያም አጠያየቃለሁ ያልኩት ከዚህ በመነሳት ነው፡፡

የአዲስ አበባ የመጨረሻው የምክር ቤት ምርጫ ከክፍላተ ከተሞችና ከዚያም ሥር ባሉ የሥልጣን ቦታዎች ጋር የተካሄደው በ2005 ዓ.ም. ነው፡፡ የምርጫ 97 ውጤት ጣጣና መዘዝ የአዲስ አበባን የከተማ ምክር ቤት ምርጫ በሕግ ከሚታወቀው አጠቃላይ ምርጫ ውጪ አባረረው፡፡ ከአዲስ አበባ ምርጫ ከሁለት ዓመት በኋላ በ2000 ዓ.ም. ከአካባቢ ማለትም የአዲስ አበባ የክፍለ ከተማ የቀበሌ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ጋር ተዳበለ፡፡ ይህ የመጨረሻው የአዲስ አበባ ምርጫ የተካሄደው ከምርጫ 97 በኋላና በእሱ ምክንያት የሕዝቦችን ‹‹ቀጥተኛ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ›› ለማስፋት የቀበሌ/የወረዳ ምክር ቤቶች አባላትን ቁጥር ከ15 ወደ 300 ከፍ በማድረግ ስለነበር በአዲስ አበባ የክፍል ከተማ ምክር ቤቶች 3,480 መቀመጫ፣ ለወረዳ ምክር ቤቶች 34,781 መቀመጫ የተመደበላቸውንና ሁሉንም ኢሕአዴግ ያሸነፈባቸውን እንደራሴዎችን ቀርቶ የከተማውን ምክር ቤት 138 ሰዎችም ማወቅ፣ ቢያንስ ቢያንስ ዛሬ በ2013 ዓ.ም. መባቻ ላይ ማስታወስ ቀላል ‹‹ግዳጅ›› አይደለም፡፡ የረሳነው አዲስ አበባ ይህን ያህል ‹‹የሕዝብ ውክልናዎች›› እንዳሏት ብቻ ሳይሆን፣ የ2010 ዓ.ም. ምርጫ ከድሬዳዋ ምርጫ ጋር አለመካሄዱን፣ መራዘሙን ከ‹‹ዋናው›› አጠቃላይ ምርጫ ጋር ይካሄድ ተብሎ መወሰኑን፣ እናም በዚያ ምክንያት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የ2011 ዓ.ም. መደበኛ የሥራ ዘመን 6ኛው ዓመት፣ የ2012 ዓ.ም. ሰባተኛው፣ የዘንድሮው ደግሞ ስምንተኛው እየባለ እንደተጠራ ረስተናል፡፡ እስከሚገባኝ ድረስ የትም ቦታ ከ2005 ዓ.ም. ወዲህ በየትኛውም ክልል የአካባቢ ምርጫ (የብሔረሰብ ዞን፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ፣ የክፍለ ከተማ ወይም የቀበሌ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ) ስላልተካሄደ፣ በ2010 ዓ.ም. ይህ ምርጫ ስላልነበር ያልኩት ነገር በመላው ኢትዮጵያ እውነት ነው፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተዘጋጀው መጠይቅ እርስዎ የሚኖሩበትን አካባቢ በክልል (ወይም በከተማ) ምክር ቤት ማን እንደሚወክለው ያውቃሉ? ብሎ ሲጠይቀኝ በዚህ ሰበብ አንድ የታወቁ ሰው ትዝ አሉኝ፡፡ በዓለም ዙሪያ በጣም የታወቁ ሰው ናቸው፡፡ ከሰኔ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ስምንተኛው የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ይሠራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የዓለም ዋነኛ ጠላት የሆነውን የኮቪድ 19 ጦርነት በግንባር ይመራሉ፡፡ እንዲያውም በዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት ዕጩዎች መካከል አንዱ እሳቸው ወይም ድርጅታቸው ወይም ሁለቱም ናቸው ሲባል እንሰማለን፡፡ እኚህ ታላቅ ሰው ከትግራይ ክልል ከምሥራቃዊ ዞን፣ ከብዘት ምርጫ ክልል የ2007 የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ አሸናፊ ሆነው የተመረጡ ነበሩ፡፡ ከአረና/መድረክ አቶ ኪዳነ አመነ ይርጉ ጋር ተወዳድረው በሕወሓት/ኢሕአዴግ ቲኬት ያሸነፉት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ ቢያንስ ቢያንስ ከሰኔ 24 ቀን 2009 ጀምሮ ማለትም ላለፉት ሦስት አምስተኛ የምርጫ ዘመናቸው በተመረጡበት የተወካዮች ምክር ቤት ቦታ አልነበሩም፡፡ እንዲህ ያለ የአባላት መጓደል ሲያጋጥም በወቅቱም ዛሬም ባለው ሕግ መሠረት የማሟያ ምርጫ ይደረጋል፡፡ ጥያቄው ለቦርዱ በቀረበ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ መካሄድ ያለበት የማሟያ ምርጫ አልተካሄደም፡፡ ስለምርጫ ስንናገርና ስንንገበገብም ይህ ሁሉ ሊቆረቁረንና ሊሰማን ይገባል፡፡

የዚህ ዓይነት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛም ሆነ የትኛውም ስብሰባ (በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሠረት) ምልዓተ ጉባዔ መሟላቱ ሲረጋገጥ በሕገ መንግሥቱ (አንቀጽ 58/1) እንደ ተደነገገው ከ547 የምክር ቤቱ አባላት መካከል ከግማሽ በላይ ከተገኙ ዋናውና ትልቁ ምናልባትም ብቸኛው ሥራና አደራ የስብሰባው መቀጠል ነው፡፡ ከ274 እንደራሴዎች በላይ ስለመገኘታቸው ከሚጨነቅ የፎርማሊቲ ትጋት በስተቀር የተቀሩት የት እንዳሉ፣ ምን ያህሉ በቋሚነት እንደማይኖሩ የሕዝብ ግንዛቤና ንቃት ቀርቶ ብዙ ጊዜ ተራ ወሬ እንኳን ሆኖ አያውቅም፡፡ አሁንም መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የጋራ ስብሰባ ላይ እንዳየነው (ለዚያውም ሆን ብሎ መቅረት ማስፊራሪያና መታገያ በሆነበት ስብሰባ) በአካል የተገኙ የሕዝብ ተወካዮችም ሆኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቁጥር አልተነገረንም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች (በሞት ጨምሮ) በቋሚነት አባል መሆናቸውን እርግፍ አድርገው የተውት ሰዎችም ሕጉ እንደሚያዘው፣ የማሟያ ምርጫ ይደረግባቸው ሲባል ሰምተን አያውቅም፡፡ ምርጫ ግን የማሟያ ምርጫንም ይጨምራል፡፡

እዚህ ሁሉ ብዙም ትርጉም በሌለው ‹‹የወግ›› ጉዳይ የገባሁት ‹‹ምርጫ›› አምላኪዎች፣ ለምርጫና ለቀነ ገደቡ እንሞታለን ለሱም እንጋደላለን ባዮች በዚህ ረገድም ቢሆን ብዙ የሳቱት፣ እንዳሻቸው የተውት፣ የረገጡትና አሸቀንጥረው የጣሉት ነገር መኖሩን ለማሳየት ነው እንጂ ይህ ሁሉ ራሱ፣ በባዶ ሜዳ ምርጫ ምርጫ የሚለው ጩኸትና የመስከረም 25 የጊዜ ገደብ ዋናው የዴሞክራሲ ጥያቄ ተጭበርብሮ እንዲዘነጋ የማድረግ አገልግሎት የሰጠ መሣሪያ ነው፡፡

ዋናው ጥያቄ፣ ዋናው የፖለቲካ ጥያቄ ደግሞ ከፈላጭ ቆራጭነት ወደ ዴሞክራሲ የማለፍ ጉዳይ ነው፡፡ ሽግግር የሚባለውም ይኸው ነው፡፡ ወደ ምርጫ ለመሄድ፣ ምክር ቤቶችን በምርጫ ለማደራጀት፣ በየትኛውም ደረጃ ያሉ ምክር ቤቶች የሕዝቦች የተለያዩ ልቦች፣ የጠያቂነት ድፍረቶችና ነፃነቶች የሚለወሱባቸውና የሚፍለቀለቅባቸው ለማድረግ ሕዝብን የሚፈሩና የሚያከብሩ እንደራሴዎች ለመላክና መጀመርያ ዴሞክራሲን ለማደላደል፣ ዴሞክራሲን ለማደላደል ደግሞ ለለውጡና ለሽግግሩ ሰላም መስጠት ሕግን ማክበር የተለያየ አቋምና ሐሳብ ያላቸው ሁሉ የጋራ ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ እኔ እሻላለሁ፣ እኔ የሚሉ እውነተኛ የድምፅ ብልጫ አግኝቶ ፍላጎትን ውሳኔ ማድረግ የሚያስችል የጨዋታ ሜዳ ሳያደላድሉና የጨዋታ ሕግ ላይ ሳይስማሙ (ይህንን ቀዳሚ የዴሞክራሲ መደላደል ሳያበጁ) ባልተለወጠው ሁኔታ፣ በድሮው በሬ ወደ ምርጫ እንሂድ ማለት ዕብደትን ማወጅ ነው፡፡ በዚያ መንገድ ሄደንበታል፡፡ የት እንደደረስን ዓይተናል፡፡ የደረስንበት ቦታ የመታነው ግብ የፈለግነውና የታገልንበት አለመሆኑን የፕሮፓጋንዳ ሥጋጃ ለብሶ ሕዝብ ውስጥ ሲንተከተክ የነበረው ብሶትና ቅሬታ ቁጣ ሆኖ ፈንድቶ፣ ይህን ለውጥና ሽግግር አምጥቷል፡፡ የለውጡ የሥር የመሠረት ተጠናዋቾችና በለውጡ ሒደት ውስጥ ‹‹ሥልጣንና ትክክለኛነት የእኔ ብቻ ነው››፣ ይህ ካልሆነ ለውጡና ሽግግሩ ተጠልፏል የሚሉ ጽንፈኞች አሁንም ከአዲስ ተነስተን የድሮውን መንገድ ተከትለን እንሩጥ ባዮች ናቸው፡፡ ከዚህ የበለጠ ዕብደት የለም፡፡ የዕብደት ትርጉሙም ይኸው ነው፡፡

ኢሕአዴግ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ዴሞክራሲን መገንባትና ሙስናን የመዋጋት ሚና መጫወት ያልቻለው፣ ይልቁንም የወረሰውንና በራሱም መልክ ያደላደለውን መንግሥታዊ ዙፋንና ቢሮክራሲውን በራሱ በፍላጎቱ ልክ ቀርፆ ከመንፈላሰስ፣ በልሽቀትና በንቅዘት ከመበከል ነፃ መውጣት አልችል ያለው ሥልጣንና ትክክለኛነት የእኔ ብቻ ነው ከሚል አመለካከት ሊገላገል ባለመቻሉ፣ መሰሪ መንገዶችንና በሥልጣን መማገጥን የትግል መሣሪያ በማድረጉ፣ ይህንንም እንዳያደርግ የሚከለክሉ እርስ በርስ የሚናበቡና የሚጠባበቁ ሕግን ብቻ መሠረት አድርገው የሚሠሩ ቋሚ መንግሥታዊ አውታራትን አስቀድሞ መገንባት ባለመቻላችን ነው፡፡

ነፃ ምርጫ ማካሄድ የውሸት የውሸት የሆነው፣ በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶችን በምርጫ ማደራጀት ሳይቻል የቀረው፣ መራጩ ሕዝብ ወደ ምክር ቤት የላካቸውን ወኪሎችን፣ የሕዝብ ወኪሎች የሚያቋቁሙትንና የሚያደራጁትን አስፈጻሚ፣ የሚያወጡትን ሕግ ተፈጻሚነት መቆጣጠር ያልቻሉት በአጭሩ የዴሞክራሲያዊነትና የሪፐብሊካዊነት ሽታ የሕዝብ ተሳትፎና ምርጫ፣ የመንግሥት አሠራርና ቁጥጥር ውስጥ ድራሹ የጠፋው የእኛ ዴሞክራሲ በአንድ ድርጅት በጎ ፈቃድና ቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ኢሕአዴግ ራሱ በፓርቲነቱም በመንግሥትነቱም ወደ ለየለትና ወደ ባሰበት ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ተወለጠ፡፡ ወደ ፍፁማዊ አገዛዝ (አውቶክራሲ) ወረደ፡፡ ይህም ህልውናችን ከኢሕአዴግ ጋር ስለተጣበቀ፣ ከኢሕአዴግ በጎ ፈቃድ የወጣ ሥርዓት ማደራጀት ስላልተቻለ፣ ለራሱ ለድርጅቱ ለኢሕአዴግም ለአገራችንም በእሳት ተበልቶ የመጥፋት አደጋ ሆነ፡፡

የለውጡና የሽግግሩ ግብ ሲጀመርም የትግሉ ዓላማ ገዥው ቡድን/ፓርቲ አይደለም፡፡ ሥልጣንም፣ እውነትም ትክክለኛነትም የእኔ ብቻ ብሎ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ፣ በአኗኗር፣ በአደረጃጀት፣ በአስተሳሰብና በሥራ ባህል ላይ ያደረሰው ብልሽት ነው፡፡ ይህን ብልሽት ለማስወገድ የቡድኖች ወይም የፓርቲዎች መንግሥታዊ ገዥነት ከነፃና ከትክክለኛ ምርጫ የሚመነጭበት ምዕራፍ ለመክፈት፣ ራሱ ነፃና ትክክለኛ ምርጫ መኖሩን ለማረጋገጥ፣ የብዙ ፓርቲዎችን ነፃ ውድድር ለማንተርከክ፣ ወዘተ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተደነገጉት መብቶችና ነፃነቶች መኗኗሪያ መሆናቸውን ቢያንስ ቢያንስ የሚያስጀምር ሁኔታ መፍጠር አለብን፡፡ ተወዳዳሪና የምንመርጣቸው ፓርቲዎች ሁሉ የተወሰነ የዴሞክራሲያዊ አመለካከትና ዴሞክራሲያዊ የድርጀት አኗኗር መለኪያ ያለፉ እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡ የተቃዋሚ፣ የተፎካካሪም ሆነ የተቀናቃኞች (ፓርቲዎች፣ ቡድኖች) ትግል በሰላማዊ ክልል ውስጥ መቆየትና እዚያው ውስጥ መገታት አለበት፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ነባሮቹም፣ አዲስ የተቋቋሙትም፣ ከስደት፣ ከበረሃና ከጫካ የመጡትም፣ ከትጥቅ ትግል የተነሱትም፣ ከሥልጣን የተፈነገሉትም፣ ከሥልጣን የተገፈተሩትም፣ አዲስ ተቃዋሚ የሆኑትም ሁሉ ሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ ተፎካካሪ መሆን አለባቸው፡፡ ወደዚህ መለወጥ አለባቸው፡፡ ከተለመደው የጦርነት ሥልት መውጣት ይህም፣ ሰላማዊና ሕጋዊ ተፎካካሪነት የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር መያዝ ይገባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ የአገሪቱ የፖለቲካ አየር እየጠራ ወደ ሰከነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊ ግብግብ መሸጋገር ይኖርበታል፡፡

ዴሞክራሲን ለማቋቋም የሚያስችሉ ለውጦች ውስጥ መግባት ፀጥታና ሰላም፣ ሕግና ሥርዓት ማስከበርን ይፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲን የማደላደልና ከዚያም በላይ የሥርዓት ግንባታ ትግሉ፣ የመንግሥት የሥልጣን መዋቅሮች ከአንድ ፓርቲ ወገናዊነት ተላቀው እንዲደራጁ ማድረግ፣ ከቡድን ይዞታነት ነፃ የሆነ አገዛዝ የመገንባት ተቀዳሚ ተግባር መጀመርያ ለውጡን ከክሽፈት ለማዳን ከመረባረብ መነሳት አለበት፡፡

ምርጫ የግድ መካሄድ አለበት የሚባለው ግን ይህን ሁሉ ቅድሚያ የሚሰጠውን የሽግግር ሥራ ትቶና ረስቶ ነው፡፡ ምርጫን ራሱንና ብቻውን ለውጥና ግብ አድርጎ ነው፡፡ ለራሱ ለኢሕአዴግ እንኳን ማፈሪያ ከሆነው ከ2007 ምርጫ ተነስቶ ቀን ከመቁጠር የተሰጠ ግዳጅ ነው፡፡ ከ2007 ምርጫ፣ ከ2008 የ‹‹አዲስ›› መንግሥት መቋቋም በኋላ ግን የአምስት ዓመቱን ጊዜ መቆጠር ያቋረጠና ያሰናከለ የኢትዮጵያን መደበኛ የምርጫ ካላንደርና ሰዓት እንደገና ያስተካከለ (Reset) ያደረገ ታሪክና ፖለቲካ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ከ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ምርጫ በኋላ፣ በዚያ ምርጫ መሠረት የተቋቋመውን የባለ መቶ በመቶ የኢሕአዴግ መንግሥት ባራደና ባንቀጠቀጠ፣ ለአገርም አደጋ ሆኖ አስፈራርቶ በተመለሰ ርዕደ መሬት (ከኅዳር 2008) ጀምሮ ተመታለች፡፡

በዚህ ርዕደ መሬት ገዥውን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን አገርንም ጭምር ሊበላ ካስፈራራ እሳትና እሳተ ገሞራ የዳንነው በገዥው ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል መጨረሻ ላይ በዓብይ አህመድ የግንባሩ ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥ ከተቋጨ በኋላ ነው፡፡ ለውጡን የወለደውና ሽግግሩን ያስጀመረው ይህ ሁነት ደግሞ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 60 ከተዘረዘሩት (ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ በራሱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ጠይቆ ሲወስን፣ የመንግሥት ሥልጣን የያዙ ከአንድ በላይ የሆኑ ፓርቲዎች ጣምራነት ሲፈርስ) ሁኔታዎች የበለጠ የምክር ቤቶችን የአምስት ዓመት የሥራ ዘመንም ሆነ የምርጫውን የጊዜ ቀጠሮና ቅደም ተከተል ሥራ (Timing and Sequencing) የሚያናጋ ፖለቲከኞችና የለውጥ ኃይሎች ሁሉ ሊያውቁትና ሊያስተናግዱት የሚገባ፣ የፖለቲከኛነትና የአመራር የጥበብና የዕውቀት መጀመርያ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመን አለቀ አላለቀም፣ ‹‹የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት››፣ ‹‹የመስከረም ወር የመጨረሻ ሰኞ›› ምንትስ ብሎ ነገር የለም፡፡ ምክር ቤቱ ከተበተነ በኋላ ምርጫው በስድስት ወራት ውስጥ ይደረጋል፡፡ ምርጫው በተጠናቀቀ በአንድ ወር ውስጥ (30 ቀን) አዲሱ ምክር ቤት ሥራ ይጀምራል፡፡ ለውጥ የሚበትነው ምክር ቤት ወይም ምርጫነቱ ላይ ለውጥ ፉርሽ ብሎ የሚበይንበት አዲስ አሠራር ደግሞ፣ ከዋናው ሁነት ጀምሮ በሚቆጠር ጊዜ ውስጥ (በኢትዮጵያ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ) በአዲስ ሕግ በአዲስ ስምምነት ይወሰናል፡፡

አገርን እንደ እንቅብ ባርቀበቀበ በአንፃራዊነት በሰላማዊና በሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ በተወሰነ ተቃውሞ ውስጥ የመጣው ለውጥ አገር ሳይተራመስ፣ መንግሥት ሳይገረሰስ ታይቶ የማይታወቅ ያልተመደ ዓይነት የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ አምጥቷል፡፡ የተለመደ ዓይነት የ‹‹መተካካት›› ወይም ከሞት በኋላ የመጣ የመንግሥት መሪ ቅያሪ/ለውጥ አይደለም፡፡ ይህ የሆነው ከኮቪድ-19 በፊት ነው፡፡ ኮቪድ መጣ ብለን ከመዘጋጀታችን ልክ ከሁለት ዓመት በፊት ነው፡፡ በወቅቱ እኮ በርካታ የሚባረሩ፣ የሚሸኙ የምክር ቤት አባላት ነበሩ፡፡ በመደበኛው አሠራርም የሚተኩ በርካታ ክፍት ቦታዎች ነበሩ፡፡ ወዲያውኑ ያልተባረሩት፣ ያልተሰናበቱት ወይም አጠቃላይ በየደረጃው የሚገኙትን ምክር ቤቶች በከፊልም ሆነ በጅምላ ብተና ውስጥ ያልገባነው ገና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቁና ዝግጁ ስላልሆንና ዴሞክራሲን ስላላደላደልን፣ በምርጫ መብትና ነፃነት በሌሎችም የምርጫን መብትና ነፃነት በሚያጅቡና ለእሱም ቅድመ ሁኔታ በሆኑ ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻችን ውስጥ መኗኗርን ገና ስላላወቅንበት፣ ገና ምርጫ ማካሄድ ስለማንችል ነው፡፡ ይህ ቅድመ ኮቪድ ነው፡፡ ኮቪድ 19 ተጨማሪ ችግራችን ነው፡፡ ምርጫ በማካሄድ የማንታማ፣ በተቋማችን ስመ ጥር ብንሆን፣ ‹‹ለሁሉ አቀፍ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት ለሚካሄድ ምርጫ›› ባዕድ ባንሆን፣ ሁሌም ንቁና ዝግጁ ብንሆን ኖሮ እኮ ኮቪድን እየተከላከልን ምርጫ ማካሄድ አንችልም? የሚለውን ጭብጥ ቀጥታ መጋፈጥ አያቅተንም ነበር፡፡

ነፃ ምርጫ ዓይቶም ሰምቶም፣ ነፃ ምርጫ ገብቶት በማያውቅ፣ በነፃ ምርጫ ሲቀልድ በኖረ እንደ ገና መዋቀር በሚገባው ሥርዓት ውስጥ ነው ኮቪድ 19 የመጣብን፡፡ ኮቪድ እንቅፋት የሆነው፡፡ ከዚያም በተጨማሪ በለውጡ አዲስ ሁኔታ ውስጥ ፀጥታና ሰላም ማስከበር አበሳ በሆነበት፣ የለውጡ አዳዲስ ኃይሎች ሕግና ሰላም ማስከበርን በማያግዙበት፣ ለውጡ የነባርና የአዲስ ገብ ፓርቲዎችን የርብርብ ድጋፍ ባልተጎናፀፈበት እንዲያው ወንጀልና ሕገወጥነት የትግል መሣሪያ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡

ዛሬም ኮቪድ 19ን እየተዋጋን፣ በሽታውን ለመከላከል የወጡትን አዲስ ሕጎችን እያከበርን ምርጫ ማድረግ እንችላለን ማለት፣ ከምርጫ በፊት መደረግ የሚገባቸው መሰናዶዎች፣ ቅድመ ሁኔታዎች አያስፈልጉንም ማለት አይደለም፡፡ በድሮው ‹‹በሬ›› ስናርስ የያዝነው የ2012 የምርጫ ካሌንደር፣ የተለመደው የመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ቀጠሮም አልተናጋም ማለት አይደለም፡፡ የዘንድሮው የመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ከአዲስ ምርጫ በኋላ አዲስ መንግሥት የሚቋቋምበት ቀን ያልሆነበትም ምክንያት ይኸው ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...