በዕለት ተዕለት ኑሯችን እንደ ክፉ ልማድ ተጣብተውናል ከምንላቸው አጉል ልምዶቻችን መካከል ዛሬ መከወን የምንችላቸውን ጉዳዮች ለነገ በይደር ማቆየት አንዱ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አጉል ልምድ በብዙዎቻችን ዘንድ ተደጋግሞ የሚስተዋል ነው፡፡ ይህ ባህሪያችንም ዋጋ እያስከፈለን እንኳን ከስህተቱ ሳንታረም ለከርሞም እዚያው ስህተታችን ላይ እንገኛለን፡፡ በቸልተኝነት ወይም ነገ ይደርሳል በሚል እሳቤ በወቅቱ ጉዳያችንን ያለመፈጸማችን ለአላስፈላጊ ወጪ ሲዳርገን ወይም የቅጣት ሰላባ የሆንባቸው አጋጣሚዎችም የበረከቱ ናቸው፡፡
እንዲህ ላለው አጉል ልምዳችን እንደ ጥሩ ምሳሌ ሊሆነን የሚችለው በየዓመቱ በየግብር መክፈያ ሥፍራዎች የምናስተውለው የመጨረሻ ሰዓት ሩጫና ትርምስን ነው፡፡ ግብር ለመክፈል የተሰጠውን ጊዜ በአግባቡ ባለመጠቀም በመጨረሻው ሰዓት ላይ የሚፈጠረው ትርምስ መጨናነቅና ያላግባብ የሚወጣው ወጪ እንዲህ በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ የግብር መክፈያ ጊዜ በሕግ ቀነ ገደብ የተቀመጠለት ሲሆን፣ ብዙዎች ግን ማድረግ እየቻሉና ቀድሞ ጣጣቸውን ጨርሰው ዕፎይ ማለት ይቸግራቸዋል፡፡ ነገ ይደርሳል፣ ወይም መጨረሻ ላይ እከፍላለሁ በሚል እሳቤ የሚፈጠሩ መዘናጋቶች መጨረሻ ላይ የግብር መክፍያ ቢሮዎችን ሲያጨናንቁ መመልከት ያልተሻሻለና አብሮን የቆየ ክፉ አመል ሆኖ ዛሬም ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ሁሌም እባካችሁ በተሰጣችሁ የጊዜ ገደብ ቀድማችሁ ኃላፊነታችሁን ተወጡ የሚለው መልዕክት ደጋግሞ ካልተሰማ ወይም ቅጣት የሚጣል መሆኑ ካልተነገረ ያለ ውጣ ውረድ ጉዳይን ለመፈጸም ለምን እንደሚከብደን ግራ ያጋባል፡፡
በመጨረሻ ሰዓት የሚፈጠረው መጨናነቅና እንግልት ብቻ ሳይሆን የመጨረሻዎቹን ቀነ ገደብ አሥልተው የመጡ ግብር ከፋዮች ወረፋ አልደርስ ብሏቸው ጭንቅ ውስጥ ሲገቡ ግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችን ሥራ ሲያበዙ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡ አንዳንዴም በመጨረሻዎቹ ቀናት እስከ እኩለ ሌሊት እንዲሠሩ ሲፈረድባቸው ሁሉ ተመልክተናል፡፡ ይህም ሆኖ በሰዓት እጥረት የመጨረሻ የተባለችው ቀን ስትጠናቀቅ ለቅጣት ሲዳረጉ በራስ ጥፋት ጣትን ሌላ ላይ እስከመቀሰር ይደርሳል፡፡ በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎችም በቀነ ገደብ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ማግኘት ተመሳሳይ ችግሮች ይታያሉ፡፡ ቀነ ገደቡን የመጨረሻ ቀናት በመጠበቅ በራስም ላይ በአገልግሎት አሰጣጡም ላይ የሚፈጥሯቸው ችግሮች ብዙ ዋጋ እያስከፈሉ መሆኑ እየታወቀ እንኳን ለከርሞ ለመታረም አለመቻሉ የአገልግሎት አሰጣጦችን ሳይቀር ሰንካላ እስከ ማድረግ ይደርሳሉ፡፡
ከሰሞኑም የብር ኖት ለውጥ ጋር ተያይዞ ይኼው የቆየ ከአጉል ልምዳችን እየተስተዋለ፣ በታየው ነገ ይደርሳል በሚል እሳቤ በእጅ ያለን ጥሬ ገንዘብን በወቅቱ ወደ ባንክ ሄዶ ለመቀየር ያለ ዳተኝነት ይስተዋላል፡፡ የመጨረሻዎቹ ቀናት እየተጠባበቁ ያሉ ጥቂቶች ስላለመሆናቸውም እየታዘብን ነው፡፡
በተለይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት ከአንድ መቶ ሺሕ ብር እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች የብር ኖቱን እንዲቀይሩ ያስቀመጠው ጊዜ 30 ቀናት ሆኖ ሳለ በተፈለገው መጠን በተሰጠው ጊዜ የገንዘብ ለውጡ እየተደረገ ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ ከ100 ሺሕ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር በታች የያዙ ሰዎችም እስከ 90 ቀን የተሰጣቸው ቢሆንም፣ እነዚህም ነገ ከነገ ወዲያ አደርገዋለሁ እያሉ ቀኑ እየገፉባቸው ነው፡፡ ለማንኛውም አንድ ወር የተሰጣቸውም ሦስት ወር የተሰጣቸውም የቀነ ገደቡን የመጨረሻ ሳምንታት መጠበቅ የሌለባቸው ቢሆንም፣ ክፉ ልማዳቸው አሁንም የመጨረሻ የሚባለውን ቀን እያስጠበቃቸው ነው፡፡ የብር ኖቶቹ ለውጥ ከተጀመረ ከ20 ቀናት በላይ የተቆጠሩ በመሆኑና በመጀመርያዎቹ 30 ቀናት ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መቀየር የሚጠበቅባቸው ሰዎች የተሰጣቸውን ጊዜ እየተጠቀሙ ያለመሆኑ የመጀመርያ ተጎጂ እነርሱ መሆናቸውን ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል፡፡
ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ያላቸው ሰዎች የተሰጣቸው ጊዜ ሊጠናቀቅ የቀራቸው ከአንድ ሳምንት ያልዘለለ በመሆኑ ይህንኑ ጊዜ በአግባቡ መጠቀም ካልቻሉ በቀጣዩ ሳምንት ባንክ ቤቶቻችን ደጃፍ የምናየው ትርምስ ቀላል እንደማይሆን መገመት አይከብድም፡፡ ይህ ደግሞ ባንኮች ሌሎች ሥራዎቻቸው ላይ ጫና ከማሳደሩም በላይ በመጨረሻው ሰዓት የሚመጡ ተገልጋዮችም ከእንግልትም በላይ የሌባ ሲሳይ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡
ሌላው እዚህ ላይ መታሰብ ያለበት ጉዳይ የብር ኖት ለመቀየር በመጨረሻው ሰዓት የሚፈጠር መጨናነቅ ባንኮች ላይ ጫና ማሳደሩ ነው፡፡ ይህም ገንዘቡን በአግባቡ ፈትሾ መረከብ ግድ የሚላቸውና ሐሰተኛ ብር እንዳይቀላቀልባቸው የሚያደርጉት ጥንቃቄ ጊዜ የሚወስድባቸው በመሆኑ በመጨረሻ ሰዓት ተስተናጋጆች በጊዜ ሳይስተናገዱ ቀነ ገደቡ ሊያልፍባቸው የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ከቀነ ገደቡ በኋላ በእጅ ያለ ኦሮጌ የብር ኖት ዋጋ ስለሚያጣ መክሰርም ያጋጥማል፡፡
ስለዚህ መታሰብ ያለበት ከ30ኛው ቀን በኋላ ከ100 ሺሕ ብር በላይ ገንዘብ ይዞ ለውጡልኝ ማለት በሌሎች ጉዳዮች እንደለመድነው በቅጣት የሚታለፍ ያለመሆኑና ቀኑ ካለፈ የተያዘው ነባር የብር ኖት ዋጋ የሚያጣ ስለሆነ ያለውን ጊዜ በአግባቡ መጠቀሙ ተገቢ ነው፡፡ ለሁሉም ነገር የመጨረሻ ቀንን ከመጠበቅ አጉል ባህል መላቀቅ አለብን ሲባል ለራስም ጥቅም ነውና እንንቃ ማለት ተገቢ ይሆናል፡፡
መቼም በእጅ የሚገኝ ገንዘብ ምንጭ ሕገወጥ እስካልሆነ ድረስ በቶሎ ወደ ባንክ ወስዶ መቀየር የሚከብድ አይደለምና አሁንም ነገ ከመቆጨት ያለውን ጊዜ መጠቀም ያሻል፡፡ ነገሩ ‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ያለዚያ ..›› እንደሚባለው ተረት እንዳይሆን አጉል ልምዳችንን ተወት አድርገን የተሰጠንን ጊዜ በአግባቡ እንጠቀም፡፡ አንዳንድ ባንኮች አሁን የብር ኖቱን ለመለወጥ እሑድንም ጭምር እየተጠቀሙ ሲሆን፣ ሌሎችም ባንኮች ተጨማሪ ሰዓትን ጨምረው በማስተናገድ ሊፈጠር የሚችለውን መጨናነቅ የመታደግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡