Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ መመርያ በወር ማውጣት የሚቻለውን የገንዘብ መጠን እንደማይቀንስ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሦስት ወር በፊት በጥሬ ገንዘብ ከባንክ ይወጣ የነበረውን የገንዘብ መጠን ለመገደብ ባወጣው መመርያ ግለሰቦች በቀን ከባንክ ማውጣት የሚችሉት 200 ሺሕ ብር እንዲሁም፣ ኩባንያዎች ደግሞ በቀን ማውጣት የሚችሉት 300 ሺሕ ብር እንዲሆን በመወሰን ይኸው መመርያ ሲተገበር ቆይቷል፡፡

ይሁንና ይህ መመርያ ሥራ ላይ በዋለ በሦስት ወር ልዩነት  ማሻሻያ በማድረግ ግለሰቦች በቀን ማውጣት የሚችሉትን የገንዘብ መጠን 75 በመቶው እንዲቀነስ  በማድረግ ወደ 50 ሺሕ ብር እንዲወርድ የሚደነግግ መመርያ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ከብሔራዊ ባንክ ወጥቷል፡፡ በዚሁ የብሔራዊ ባንክ አዲስ መመርያ ኩባንያዎች በቀን ከባንክ ማውጣት ይችሉ የነበረውን የገንዘብ መጠንም በሦስት አራተኛ ቀንሶ 75 ሺሕ ብር ብቻ እንዲሆን ተወስኖ የአገሪቱ ባንኮች በዚሁ መሠረት እንዲሠሩ ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በአሁኑ ወቅት እየተሠራጨ ያለውን አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ሥርጭት ለማሳለጥና ከዚሁ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቀነስ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ማሻሻያ ተደርጎበት የወጣው መመርያ በቀን ማውጣት የሚችለውን የጥሬ ገንዘብ መጠን ላይ ገደብ ያድርግ እንጂ ከሦስት ወር በፊት ወጥቶ በነበረው መመርያ በወር ውስጥ በድምር መውጣት የሚችለው የገንዘብ መጠን ላይ ግን ማሻሻያ አለመደረጉ ታውቋል፡፡

ቀደም ብሎ በነበረው መመርያ ግለሰቦች በጥሬ ገንዘብ 200 ሺሕ ብር ማውጣት የሚችሉ መሆኑንና በአጠቃላይ በወር ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ሊበልጥ እንደማይችል ያመላክት ነበር፡፡ በተመሳሳይም ኩባንያዎች በቀን ማውጣት የሚችሉት የገንዘብ መጠን 300 ሺሕ ብር እንደሆነ በሚደነግገው የቀደመው መመርያ በአጠቃላይ በወር ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ኩባንያዎች ሊያወጡ እንደማይችሉ የሚደነግግ ነው፡፡

በዚህ ሳምንት አጋማሽ  ላይ የወጣው መመርያ ግን በወር ውስጥ ከባንክ በጥሬ ገንዘብ ማውጣት የሚችሉትን ጣሪያ ያላሻሻለ በመሆኑ የወርኃዊው መጠን ቀድሞ በወጣው መመርያ መሠረት ተፈጻሚ የሚሆን መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህም የሰሞኑ መመርያ በቀን በጥሬ ገንዘብ የሚወጣውን የገንዘብ መጠን ቀድሞ ከነበረው ዝቅ እንዲል ከማድረጉ በስተቀር ግለሰቦችና ኩባንያዎች በድምር በወር ማውጣት የሚችሉት የገንዘብ መጠን በቀደመው መመርያ ላይ ባለው መሠረት የሚቀጥል ይሆናል፡፡

የጥሬ ገንዘብ ግብይት ጎልቶ በሚታይባት ኢትዮጵያ እንዲህ ያለው የገንዘብ መጠን እንቅስቃሴ የግድ ስለመሆኑ ሲጠቀስ የነበረ ሲሆን ብሔራዊ ባንክ ከሦስት ወር በፊት በዕለት ግለሰቦች 200 ሺሕ ብር ኩባንያዎች ደግሞ 300 ሺሕ ብር በጥሬ ገንዘብ  ማውጣት የሚችሉ መሆኑን ሲደነግግ ይህ የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ነው የሚል አሉታዊ አስተያየት ሲሰጥበት የቆየ ነው፡፡

ቀድሞም ቢሆን አንድ ግለሰብ በቀን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በጥሬ ገንዘብ አወጣ መባሉ ተገቢ አልነበረም የሚሉት የማክሮ ኢኮኖሚው ባለሙያ አሁን ይህ መቀነሱ ተገቢ ዕርምጃ ስለመሆኑ ያመለክታሉ፡፡

ይህ ድንጋጌ ግን ኩባንያዎችም ሆ ግለሰቦች አሁን በጥሬ ገንዘብ በቀን ማውጣት የሚችሉት በ75 እና በ50 ሺሕ ብር ቢገደብም ማንኛውንም ግዥና ሌሎች ወጪዎቻቸውን በሌላ የገንዘብ ማንቀሳቀሻ መንገድ መጠቀም የሚችሉ መሆኑ ታውቋል፡፡

ግዥ መፈጸም ቢፈልጉ ከአካውንት ወደ አካውንት በማዘዋወር ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ የሚችሉ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የዚህ መመርያ መተግበር በዋናነት ከባንክ ውጪ ያለን ገንዘብ ወደ ባንክ ሥርዓት ለማስገባትና ከጥሬ ገንዘብ ግብይት ይልቅ በሌሎች ዘመናዊ የባንክ የክፍያ አገልግሎቶች መጠቀምን ለማበረታታት ጭምር ስለመሆኑ መመርያው በወጣበት ወቅት መገለጹ ይታወሳል፡፡ አሁንም ግለሰቦችና ባንኮች በዕለት በጥሬ ገንዘብ ማውጣት የሚችሉት የገንዘብ መጠን ቢገደብም በሌሎች የክፍያ አገልግሎቶች መጠቀም የሚችሉ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ  ብሔራዊ ባንክ በዕለት የሚወጣውን የገንዘብ መጠን በዚህን ያህል ደረጃ ማውረዱ እንደተባለው ዘመናዊ የክፍያ አገልግሎትን ከማስፋፋትም ሆነ በጥሬ ገንዘብ የሚደረገውን ግብይት እንዲቀንስ ከማድረግ አኳያ ጠቃሚ ስለመሆኑ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎች ያመለክታሉ፡፡

ለባንኮችም ቢሆን ጠቃሚ መሆኑን የሚያስረዱት እነዚሁ የባንክ ባለሙያዎች፣ ከባንክ ውጪ የሚንቀሳቀሰውን ገንዘብ በባንክ በኩል እንዲያልፍ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለው ዕርምጃውን ደግፈውታል፡፡ 

የእነዚህኑ የባንክ ባለሙያዎች አመለካከት የሚደግፉ አንድ ማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ በሌሎች አገሮች በዕለት ከባንክ የሚወጣ የገንዘብ መጠን እጅግ አነስተኛ ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ ቀድሞ በተቀመጠው መመርያ 300 ሺሕና 200 ሺሕ ብር ይሁን መባሉ ራሱ ተገቢ እንዳልነበር ይጠቅሳሉ፡፡ አሁን በተሻሻለው መመርያ ግን መጠኑ ማነሱ ተገቢነት ላይ የሚስማሙ ሲሆን፣ ኅብረተሰቡ ግን ጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተውን ግብይት  እንዲቀይር ብዙ መሠራት እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡ 

ሰሞኑን በወጣው ማሻሻያ በተደገበት መመርያ ላይ ያነጋገርናቸው አንድ የባንክ የሥራ ኃላፊ ግን የተለየ ምልከታ አላቸው፡፡ በእርግጥ ዕለታዊ የጥሬ ገንዘብ ገደቡ  መውረዱ ተገቢና ይህም የተደረገበትን ዓላማ የሚደግፉ ቢሆንም፣ ማሻሻያው አሁን ያለውን የግብይት ሥርዓትና አጠቃላይ ወቅታዊ  የሆነውን ኢኮኖሚ ያገናዘበ ነው ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል፡፡

ይህንንም ሲያስረዱ፣ ‹‹50 ሺሕ ብርና 75 ሺሕ ብር ትንሽ ገንዘብ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በዋናነት መታሰብ ያለበት የአገራችን ኢኮኖሚ በምን ላይ የተመሠረተ ነው? የሚለው መመለስ አለበት፤›› ብለዋል፡፡  

በጥሬ ገንዘብ ግብይት በተስፋፋበትና ሌሎች የክፍያ አማራጮች እንደ ልብ በማይገኙበት ሁኔታ ይህ መመርያ የታሰበውን ዓላማ ለመምታት እንደሚያስቸግር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለምሳሌ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ወዳሉ ወደ አንዱ መደብር ሄዶ ዕቃዎችን ለመግዛት በፖዝ ማሽን ልክፈል ወይም በሞባይል ባንኪንግ ልክፈል ብትል ዕቃውን መግዛት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አማራጭ የክፍያ ዘዴዎች ገና ወደ ገበያው በሚፈለገው ደረጃ ስላልገባ ጥሬ ገንዘብ የግድ ይላል፤›› የሚሉት ባለሙያው ነባራዊ ሁኔታዎች መታየት እንደነበረባቸው አመላክተዋል፡፡

ሌላም ምሳሌ ያነሱት እኚሁ ባለሙያ ወደ ገጠር ወርደው የቁም እንስሳትን ለመገበያየት የሚጠይቀው የጥሬ ገንዘብ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር እንዲህ ያሉ ግብይቶች እንዴት ሊከናወኑ እንደሚችሉ የታሰበበት እንዳልመሰላቸው ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን ሲታይ መመርያውን መተግበር አስቸጋሪ ይሆናል ሲሉም ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደተባለው የገንዘብ ለውጡ እስኪጠናቀቅ ከሆነ መመርያው የግድ መሆኑን  ነገር ግን መመርያው ከዚያም በኋላ የሚቀጥል ከሆነ ይህንን መመርያ በመተግበር ኢኮኖሚውና ኅብረተሰብ ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ መታየት አለበት ሲሉ ምክረ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች