የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በመኖሪያ ቤታቸው፣ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ሰኞ ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲሰጡት የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በታጠቁ ኃይሎች መቋረጡን፣ የፓርቲው ጊዜያዊ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በቴ ኡርጌሳ ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡
ከዚህ ቀደም ባሉት ሳምንታት በአገሪቱ አጠቃላይ ‹‹የሽግግር መንግሥት ይመሥረት›› የሚል ጥያቄ ፓርቲው ማቅርቡን ያስታወሱት አቶ በቴ፣ የሰኞ ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ዓላማም ይህን አቋም ለማብራራት ያለመ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡
ሰኞ ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. 8፡30 ሰዓት ገደማ መግለጫው ተጀምሮ እንደነበር ያስታወሱት አቶ በቴ፣ ነገር ግን መግለጫው ለ30 ደቂቃዎች ያህል እንደተከናወነ የፀጥታ ኃይሎች ወደ አቶ ዳውድ መኖሪያ ቤት በመግባት፣ መግለጫው እንዲስተጓጎል ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
ከመግለጫው መስተጓጎል በኋላ ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ የመግለጫው ታዳሚዎችን ለመውሰድ መሞከሩን የገለጹት አቶ በቴ፣ ነገር ግን አቶ ዳውድ ‹‹የታጠቀ ኃይል ያለ ፈቃድ ወደ መኖሪያ ቤቴ አይገባም፣ ችግር ካለም እኔን ጠይቁኝ፣ ካስፈለጋችሁ እኔን እሰሩኝ እንጂ እንግዶቼን አታስሩም፤›› በማለታቸው በርካቶች በእሳቸው መኖሪያ ቤት እንደሚገኙ አቶ በቴ ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ‹‹ስድስት ያህል የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለጥያቄ እንፈልጋችኋለን›› ተብለው ወደ ጣቢያ መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በመግለጫው ላይ የነበሩ ከ20 እስከ 30 የሚሆኑ ግለሰቦች እዚያው ማደራቸውንና ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስም እዚያው እንደሚገኙ የገለጹት አቶ በቴ፣ ይሁን እንጂ ማክሰኞ ዕለት ከአቶ ዳውድ መኖሪያ ቤት የወጡ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አክለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት መግለጫ ወይም ማብራሪያ አለማግኘታቸውን የሚገልጹት አቶ በቴ፣ ‹‹ከመግለጫው መስተጓጎል ጀምሮ አቶ ዳውድ ቤት ውስጥ ናቸው፡፡ ከቤት የሚወጡ እንግዶች በር ላይ ተጠብቀው የሚታሰሩ ከሆነ የእሳቸው ሁኔታም አሳሳቢ ነው፤›› ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኦነግ ከቅርብ ወራት ወዲህ በመሪዎቹ መከፋፈል ምክንያት የመገናኛ ብዙኃን የፊት ገጽ ማሟሻ የነበረ ሲሆን፣ በሊቀመንበሩ አቶ ዳውድና በምክትል ሊቀመንበሩ አቶ አራርሶ ቢቂላ መካከል የተከሰተው የማገድና የመልሶ ማገድ ኩነት ፓርቲውን ለሁለት ከፍሎታል፡፡
በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም. የተደረገው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ‹‹ያለ እኔ ዕውቅና የተካሄደ ነው›› በሚሉት ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድና ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ አራርሶ በሚመሩት ቡድን መካከል በተፈጠረ ውዝግብ፣ በፓርቲው ስብሰባ ላይ ውሳኔ መተላለፉን በመጥቀስ አቶ ዳውድ መታገዳቸው የተገለጸ ሲሆን፣ አቶ ዳውድ በበኩላቸው ደግሞ የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ ከቤት እንዳይወጡ ተደርገው እያለ የተካሄደው ስብሰባ ሕገወጥ ነው በማለት፣ ስድስት የሚሆኑ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ማገዳቸው የሚታወስ ነው፡፡
በዚህ ውዝግብ መካከል ከሊቀመንበሩ ቡድን ተከፍሎ የወጣው በምክትል ሊቀመንበሩ የሚመራውና የፓርቲውን የሕዝብ ግንኙነት አቶ ቀጄላ መርዳሳና አቶ ቶሌራ አዶባን በአባልነት የያዘው ቡድን፣ ‹‹በአቶ ዳውድ ምክንያት በፓርቲው ውስጥ የጋራ አመራር ጠፍቶ ወደ ግለሰባዊ አመራር ማዘንበል ተይዟል፤›› በማለት ሊቀመንበሩን ከሷል፡፡
ከዚህ በተቃራኒው አቶ ዳውድ፣ ‹‹ውሳኔው ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዕውቅና ውጪ በሆነ መንገድ መተዳደርያ ደንቡን የጣሰ፣ ምልዓተ ጉባዔው በሁለት ሦስተኛ ተሳታፊዎች ሳይሟላ የተደረገ ስብሰባ በመሆኑ፣ እንዲሁም ውሳኔውን ያስተላለፉት አባላት የታገዱ በመሆናቸው ውሳኔው ተቀባይነት የለውም፤›› በማለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቤት ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኦነግ አመራሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት የሚያስረዱትን አቤቱታዎችና ደብዳቤዎች መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም. መመርመሩን ያስታወቀ ሲሆን፣ ከሁለቱም ወገኖች አንድ አንድ ተወካይ የሚካተትበት ጊዜያዊ ጉባዔ እንዲቋቋም ወስኗል፡፡
በዚህም መሠረት በሁለቱ አካላትና በቦርዱ የተመረጡ ባለሙያዎች ጉዳዩን አጣርተው በሚያቀርቡት የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተመርኩዞ፣ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥም መስከረም 29 ቀን 2013 ማስታወቁ ይታወሳል፡፡